በአዳማ ከተማ በበጋ መስኖ ስንዴ ሰላሳ ሺህ ሄክታር እየለማ ነው

አዲስ አበባ፦ በአዳማ ከተማ በበጋ መስኖ ስንዴ ሰላሳ ሺህ ሄክታር ለማልማት እየተሰራ ሲሆን፤ እስካሁን ሃያ ሶስት ሺህ ሄክታሩን በዘር ለመሸፈን መቻሉን የከተማው ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አለሙ ቂልጦ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ ከተማዋ በመስኖ ሊለሙ የሚችሉ ሰፋፊ መሬቶችን ከምሥራቅ ሸዋ ዞን ተቀብላ በማስተዳደር ላይ ትገኛለች።

ከዚህም ውስጥ በተጀመረው በጀት ዓመት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሰላሳ ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፤ እስካሁን ሃያ ሶስት ሺህ ሄክታሩ በዘር መሸፈኑን አስታውቀዋል።

በአዳማ ከተማ የከተማ ግብርና ለማከናወን ከፍተኛ አቅም ያለ ቢሆንም እስከ ቅርብ ጊዜ በቂ ትኩረት አልተሰጠውም ነበር ያሉት ኃላፊው፤ በአሁኑ ወቅት ግን በመንግሥት በኩል በየደረጃው ከፍተኛ ትኩረት በመሰጠቱ አበረታች ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በከተማዋ ሃያ አምስት ሺህ ስድስት መቶ ሃምሳ ሰባት ሄክታር ሊለማ የሚችል መሬት መኖሩን ያመለከቱት ኃላፊው፤ ባለፈው ዓመት መሬቱን ሙሉ በሙሉ በሰብል በመሸፈን ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል በላይ እህል ለመሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።

ዘንድሮም በፍራፍሬ ልማት ረገድ ስልሳ ሦስት ሄክታር ሙዝ፣ አርባ ስምንት ሄክታር ፓፓዬ፣ አስራ ስድስት ሄክታር ብርቱካን፣ አስራ ሁለት ሄክታር ዘይቱን፣ ስድስት ሄክታር አቡካዶ በክላስተር እየለማ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

ሁለት ሺህ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን በማዘጋጀትና ሥር አጥ ወጣቶችን በማደራጀት ከተማዋን በከበበው ተራራ ላይ የንብ ማነብ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ፤ በዶሮ እርባታ ረገድም በመንግሥትና በህብረት ስራ ማህበራት አምስት መቶ አርባ አራት የዶሮ ማርቢያ በማዘጋጀት ለአምራቾች መከፋፈሉን አስታውቀዋል ።

በዚህም ባለፈው ዓመት አስራ ሶስትና አስራ አራት ብር ይሸጥ የነበረውን አንድ እንቁላል ዘጠኝ ብር ማድረስ ተችሏል። በአሳማና በአሳ እርባታም ረገድ የተጀመሩት ስራዎች አበረታች ውጤት እያስመዘገቡ ይገኛሉ ብለዋል።

የከተማ ግብርና በየወቅቱ ቁጥሩ የሚጨምረውን የከተማ ነዋሪ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና ከፍተኛ ቁጥር ላለው የሰው ኃይል የስራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል ነው። ባለፈው አመት የተፈጠረው የስራ እድል ሃያ ሶስት ሺህ ብቻ ነበር። ዘንድሮ ግን በከተማ ግብርና ብቻ ለሰላሳ አምስት ሺህ ሰው የስራ እድል ለመፍጠር በእቅድ ተይዞ እስካሁን ለአስራ ስድስት ሺህ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን አመልክተዋል።

ይህም ሆኖ በከተማዋ ካለው ምቹ ሁኔታና አምራች የሰው ኃይል አኳያ በርካታ ስራዎች የሚቀሩ በመሆኑ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ጠቁመዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You