የካፒታል ገበያ ሥርዓት ለስታርትአፕ ንግዶች አዲሱ በረከት

የካፒታል ገበያ በኢትዮጵያ ውስጥ በሕግ ተደግፎ ወደ ተግባር ለመግባት ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ይገኛል። በመጪው ጥር 2017ዓ.ም በይፋ ሥራውን እንደሚጀምር ተገልጿል።በጅምር ላይ ያሉ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራ ንግዶች ምርትና አገልግሎታቸውን እንዲያሳድጉ ጉልህ

ድርሻ እንደሚኖረውም ይጠበቃል። የዝግጅት ክፍላችን ‹‹ለችግር ፈቺ ቴክኖሎጂ ነክ ፈጠራ ንግዶች የፈንድ አማራጭ ከማስፋት አኳያ ምን ድርሻ ይኖረዋል›› ሲል ባለሙያዎችን አነጋግሯል።

በጅምር ላይ ያሉ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራ ንግዶች የተለያዩ የፈንድና የመዋዕለ ንዋይ ማሰባሰብ ደረጃዎችን ያልፋሉ የሚሉት የኢንቬሽንና ስታርትአፕ ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሰላምይሁን አደፍርስ፤ ከመንግሥት አሊያም ከተለያዩ ድርጅቶች የሚደረግ ነፃ ድጋፍ አንደኛው የፈንድ አማራጭ ሲሆን በዚህኛው ደረጃ የፈጠራ ሃሳቦቹን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚደረግ ትርፍ የማይጠበቅበት ሂደት መሆኑን ያስረዳሉ።

በሁለተኛነት የፈጠራ ሥራ ንግዶች (startups) ፍሬያማ የሚሆኑበት የኢንቨስትመንት ደረጃ መሆኑን ያነሳሉ። የካፒታል ገበያ ሚና ከፍተኛ የሚሆነው እዚህ ጋር መሆኑን ይገልፃሉ። የቴክኖሎጂና አዳዲስ የንግድ ሥራ ፈጠራ ንግዶች ውጤታማ ሲሆኑ ንግዳቸውን ለማስፋፋት በካፒታል ገበያ አማካኝነት ለማህበረሰቡ፣ ለኢንቨስተሮችና ልዩ ልዩ ኩባንያዎች የድርጅቶቻቸውን ድርሻ የማከፋፈል መብት ይኖራቸዋል ነው ያሉት።

አቶ ሰላምይሁን፤ ይህም ንግዳቸውን ለማሳደግ የሚያስችል መዋዕለ ንዋይ ያለ ችግር እንዲያገኙ እድል እንደሚሰጣቸው ይገልጻሉ። ከዚህ ቀደም በኢንቨስተሮች እና በፈንድ እጦት በአጭሩ የሚቀጩና የሚጠፉ የፈጠራ ሃሳቦችና ጅምር ንግዶች በዚህ የካፒታል ገበያ ሥርዓት ውስጥ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ያስረዳሉ።

‹‹በጅምር ላይ ያሉ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራ ንግዶች ትርፋማነትና አቅም የሚለካው ለወደፊት ይኖራቸዋል ተብሎ በሚቀመጥ ግምታዊ ስሌት ነው›› የሚሉት አቶ ሰላምይሁን፤ ይህንን ግምታዊ ስሌት የሚቆጣጠር አካል (security exchange body) እንደሚኖር ይገልጻሉ።

የካፒታል ገበያ ሥርዓት መዘርጋቱ ከዚህ ቀደም ችግር ፈቺ የፈጠራ ሃሳቦች በገበያው ላይ ይገጥማቸው የነበረውን የገንዘብ ችግር በዘላቂነት የሚቀርፍና አዳዲስ ንግዶች እንዲያድጉ የሚያበረታታ መሆኑን ያነሳሉ። ንግዶቹን ለማስፋፋት ከባንኮች ብድር ማግኘት ውስብስብ ሂደት የሚጠይቅ መሆኑ በካፒታል ገበያ ሥርዓቱ ተጠቃሚ መሆናቸው ተመራጭ መሆኑንም ያነሳሉ።

አቶ ዳንኤል በቀለ የአሸዋ ቴክኖሎጂ አክሲዮን ማህበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። የካፒታል ገበያ በኢትዮጵያ ውስጥ መጀመር በጅምር ላይ የሚገኙ ችግር ፈቺ የንግድ ፈጠራ የፋይናንስ አቅም በማጎልበት ወደ ፍሬያማነት እንዲቀየሩ ትልቅ እድል ይዞ መምጣቱን ይናገራሉ።

የስታርትአፖቹ ማደግ ለኢንቨስተሮችም ሆነ ለሀገር ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸው፤ ለዚህ የካፒታል ገበያ በኢትዮጵያ ውስጥ መተዋወቅ ቅድሚያ ተጠቃሚ ከሚያደርጋቸው ውስጥ ቀዳሚ እንደሆኑ ያስረዳሉ።

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ሃሳብ፤ የስታርትአፖች ትልቁ ማነቆ አቅማቸውን የሚያጎለብቱበት የፋይናንስ ድጋፍ እጦት ነው። የካፒታል ገበያ ሥርዓት መጀመሩ ይህንን ማነቆ በመፍታት ከማህበረሰቡ በቦንድና በአክሲዮን ድርሻ ሽያጭ በማከናወን ወደ ቀጣዩ የእድገት ደረጃ እንዲሸጋገሩ ያግዛል።

‹‹አብዛኛዎቹ በአዳዲስ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂ ነክ የሥራ ፈጠራ ላይ የተሰማሩት ወጣቶች ናቸው›› የሚሉት የአሸዋ ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስፈፃሚ፤ እነዚህ ፈጣሪዎች ከእውቀት በዘለለ የመሰረቱትን ሰታርትአፕ ወደ ከፍተኛ እድገት ለማሸጋገር የፋይናንስ አቅም እንደሌላቸው ይናገራሉ። በዚህ ምክንያት ስታርትአፖች ወደ ትላልቅ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የንግድ ድርጅትነት እንዳይሸጋገሩ የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት ዋናው ማነቆ መሆኑን ያስረዳሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ የሥራ ፈጠራ ሃሳብ የያዙ ስታርትአፖች እየተፈጠሩ ነው። በመሆኑም ከምንጊዜውም በተለየ የፋይናንስ አማራጭ መፈለግ የግድ ይላል። ለዚህም የካፒታል ገበያ ሥርዓት መጀመሩ እንደ አንድ መፍትሔ ሊወሰድ ይችላል ይላሉ።

የካፒታል የገበያ ሥርዓት በኢትዮጵያ ውስጥ በይፋ ሥራ ሲጀምር ስታርትአፖች የፋይናንስ ማነቋቸውን የሚፈቱበትን አማራጭ እንደሚፈጥር ተረድተው በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚኖርባቸው ሁለቱም የዘርፉ ባለሙያዎች ምክረ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር የስታርትአፕ ፈንድ ማሕቀፍ ማዘጋጀቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You