
ኢትዮጵያ በከበሩ ማዕድናት ሀብቷ ትታወቃለች፤ እንደ አፓል ያሉት እነዚህ ማዕድናት ለውጭ ገበያ ሲቀርቡ የቆዩት ግን እሴት ተጨምሮባቸው አለመሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ:: በእዚህ አይነቱ መንገድ የከበሩ ማዕድናትን ለውጭ ገበያ ማቅረብ፣ አምራቾችን፣ ላኪዎችንና ሀገር የሚፈልገውን ያህል ተጠቃሚ ሳያደርጋቸው መቆየቱ ሁሌም ይገለጻል::
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ጥረት የሚያደርጉ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን ማየት ተለምዷል፤ እነዚህ አካላት በከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር ለውጭም ለሀገር ውስጥ ገበያም ምርቶቹን እያቀረቡ ስለመሆናቸው መረጃዎችም ይጠቁማሉ:: በማዕድን ዘርፉ ኢግዚቢሽኖች ላይም እሴት የተጨመረባቸው የከበሩ ማዕድናት ምርቶቻቸውን ይዘው እየቀረቡ ያሉበት ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል::
በእዚህ ስራ ከተሰማሩት መካከል አንዷወይዘሮ ነጃት ሀሰን ናቸው:: ወይዘሮ ነጃት በከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር ምርቶቻቸውን ለውጭም ለሀገር ውስጥ ገበያም ያቀርባሉ::
በማዕድን ዘርፉ እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ በኩል በብዛት ተሰማርተው የሚገኙት ወንዶች መሆናቸውን ወይዘሮ ነጃት ጠቅሰው፤ እሴት ጭመራው እንደ አሁኑ ብዙ እውቅና ባላገኘበት በቀደመው ጊዜ ሴቶች በዚህ ልማት ሲሰማሩ ይስተዋል እንዳልነበርም ይናገራሉ:: አሁንም ድረስ በጣት የሚቆጠሩ ሴቶች ብቻ ናቸው በዚህ ስራ የተሰማሩት ይላሉ::
በዚህ ስራ ደፍረው ከገቡት ከቀዳሚዎቹ መካከል አንዷ በመሆን የከበሩ ማዕድናትን በጌጣጌጥ መልኩ በማስዋብ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ የሚገኙት እኚሁ የለዛ የከበሩ ማዕድናትና ላኪ ድርጅት መስራችና ባለቤት ወይዘሮ ነጃት ሀሰን፣ ትውልድና እድገታቸው በአዲስ አበባ ከተማ ነው::
ወደ ማዕድን ስራ ለመግባታቸው መነሻ የሆናቸው በሰሜን ሸዋ ሸዋ ሮቢት አካባቢ ለሰርግ የሄዱበት አንድ አጋጣሚ ነው፤ በወቅቱ ሰዎች ስለማዕድናት ሲያወሩ ይሰማሉ፤ ይህ ሁኔታም እሳቸውም ስለማዕድናቱ የማወቅ ፍላጎቱና ጉጉት እንዲያድርባቸው ማድረጉን ያስታውሳሉ::
በሂደትም በማዕድናቱ እየተሳቡና እየተማረኩ በመምጣታቸው ወደ ማዕድን ስራ በመግባት ሥራቸው አድርገውት መቀጠላቸውን ይገልጻሉ:: ወደ ስራው ከገቡ በኋላ ማዕድናት የሚሸጡባቸውን ቦታዎች ባለማወቃቸው የማዕድናቱን አይነት ለናሙና አምጥተው ለነጋዴዎቹ ሲያሳዩ ነጋዴዎች ናሙናውን ወስደው ይጠፉ እንደነበር ወይዘሮ ነጃት ያስታወሳሉ::
ወይዘሮ ነጀት ገበያውን በደንብ እያወቁ ሲመጡ የማዕድናትን ባህሪያትም ሆነ ስለሚሸጡበት ሂደት አብጠርጥረው ማወቅ ቻሉ:: በ2008 ዓ.ም ነው በዚህ ላይ የሚሰራ የከበሩ ማዕድናትና ላኪ ድርጅት መስርተው፣ የማዕድናት አዘዋዋሪነት ፈቃድም አውጥተው፣ የከበሩ ማዕድናትን በተለያየ መልኩ በማስዋብና በማስጌጥ ለገበያ ማቅረብ ስራ ውስጥ የገቡት:: በዘርፉ እያካበቱ የመጡትን ልምዳ ተጠቅመው የከበሩ ማዕድናት ላኪነት ፍቃድ በማውጣት ማዕድናትን በተለያዩ መልኩ በማስዋብ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማቅረብ ጀመሩ::
‹‹ብዙ ሰው ማዕድን ሸጦ ወዲያውኑ ባለሀብት የሚሆን ይመስለዋል፤ ወደ ሥራው ሲገባ ግን እንዲህ አይደለም:: የማዕድን ሥራ በጣም ረጅም ጊዜያትን የሚወስድ አድካሚና ትዕግስት የሚጠይቅ ነው›› የሚሉት ወይዘሮ ነጃት፤ ማዕድን ላይ እሴት ለመጨመር ብቻ ሳይሆን አዘዋውሮ ለመሸጥም ሆነ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ልምድ ሊኖር ይገባል›› ሲሉ ያስገነዝባሉ::
‹‹ስራው ጊዜ ተሰጥቶ የሚሰራ እንጂ ወዲያውኑ ውጤት የሚያስገኝ አለመሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል፤ ማዕድን ቀስ ተብሎ የሚሰራ ስራ ነው፤ ወዲያውኑ አምጥተን የምንሸጠው ላይሆን ይችላል፤ በገበያው የመወዳደርና የመደራደር ብቃትን ይፈልጋል:: በከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት የመጨመር ስራ በኛ ሀገር ስላልተለመደ ስራው ትንሽ ይከብዳል ›› ሲሉ ያስረዳሉ::
እሳቸው እንዳሉት፤ ድርጅታቸው ‹‹ለዛ የከበሩ ማዕድናትና ላኪ ድርጅት›› በከበሩና በጌጣጌጥ ማዕድናት በብዛት ኦፓልና ኤመራልድ ላይ ይሰራል፤ ሳፋየር ላይም በመጠኑ ይሰራል:: ሳፋየር ማዕድን አይነቱ ብቻ ሳይሆን ዋጋው ትንሽ ውድ ስለሆነ ለጊዜው ለመድፈር እንዳቃታቸው ተናግረዋል:: ከማዕድናቱ መካከልም በኦፓልና ኤመራልድ ማዕድናት የካበቱትን እውቀትና ልምድ በመጠቀም ማዕድናቱን በማስዋብና በማስጌጥ ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል::
ድርጅታቸው ማዕድናቱን ከአምራቾች ወይም አቅራቢዎች በጥሬው በመረከብ በማስዋብና በማስጌጥ በተወሰኑት ላይ ደግሞ እሴት በመጨመር እሴት የተጨመረባቸው እና ያልተጨመረባቸውን ማዕድናት ለገበያ ያቀርባል:: ኦፓልና ኤመራልድ የተሰኙትን ማዕድናት የተወሰነ እሴት እየጨረባቸው በተለያዩ ጌጣጌጥ መልኩ እያመረተ ለውጭ ገበያ ይልካል:: በተለይ የጌጣጌጥ ማዕድናትን ለእጅ፣ ለጆሮ፣ ለአንገትና ለጣት ቀለበት በሚውል መልኩ በማስዋብና በማሳመር ለሀገር ውስጥ ሆነ ለውጭ ገበያ ያቀርባል::
የገበያ መዳረሻዎቹ በዋናነት ህንድ እና ስሪላንካ ናቸው:: በስሪላንካ የኦፓል ማዕድንን ብዙም አይታወቅም፤ እንዲያም ሆኖ ማዕድኑን ወደ ሀገሪቱ በተደጋጋሚ በመላክ የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ ነው::
እንደ ወይዘሮ ነጃት ማብራሪያ፤የማዕድናቱ ገበያ ማዳረሻ ሲሰፋና ተፈላጊነት ሲጨምር የገበያው ዋጋ በዚያው ልክ እየጨመረ ይሄዳል:: ማዕድናቱን ወደ ተለያዩ ሀገራት ገበያ ሲያቀርቡ የሀገራቱ ዋጋ ይረክሳሉ:: ምክንያታቸው አማራጭ ሲያጡ ይሸጡታል የሚል ነው፤ የእኒዘህ ሀገሮች የማእድን ምርቶቹ ፈላጊዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ግን ያለምንም ማራከስ ገዝተው ይሄዳሉ::
ማዕድናቱ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ኦፓል ከወሎ ደላንታ፤ ከአፋር ይገኛል፤ ኤመራልድ ሸኪሶ፣ ያቤሎ እና አፋር አካባቢዎች ላይ ይገኛል:: ማዕድናቱ በሌሎች ቦታዎችም እየወጡ ስለመሆናቸው ከሚላኩላቸው አንዳንድ ናሙናዎች መረዳታቸውን ወይዘሮ ነጃት አስታውቀዋል:: አካባቢው ድረስ ሄዶ በማየት ማዕድናቱን በማምጣት እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል::
ወይዘሮ ነጃት በማዕድን ማውጣት ሥራ የተሰማሩ ሰዎች እውቀት እና ልምድ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉም ያስገነዝባሉ:: እውቀትና ልምድ ብቻ ሳይሆን የአቅም ማነስ እንዳለም ይገልጻሉ:: በማዕድናት ማውጣቱ ላይ አጠንክሮ መስራት አይስተዋልም፤ ከላይ የተገኘው ብቻ ነው የሚመረተው ሲሉም አመልክተው፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ማዕድናቱ አሉ፤ ማዕድን የሌለበት ቦታ የለም ማለት ይቻላል ብለዋል::
የማዕድናቱ የአቅርቦት ችግር ባይኖርም፣ የሚሰራው በልምድ ተመስርቶ እንደመሆኑ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስራ እንደማይሰራ ይጠቁማሉ:: ምናልባት አቅም ያላቸው ሰዎች ይሰሩ ይሆናል፤ በዚህ ዘርፍ አቅም ያላቸው ሰዎች ብቻ ማሳተፉ ደግሞ ሌላውን ይጎዳዋልና ለሁሉም አመቺ እንዲሆን ድጋፍ ተደርጎ በማሽን እንዲመረት ቢደረግ ማዕድናቱ ሳይሰባበሩ ለሚፈለገው አላማ ማዋል ይቻላል:: በተለይ ማዕድን ማውጣት ላይ ከባድ በመሆኑ ማዕድናት የመሰባበርና የመሰንጠቅ ነገር ሊከሰት ይችላልና ይህ ደግሞ ማዕድኑን ጥቅም ላይ ለማዋል ያዳግታል ሲሉ አስገንዘበዋል::
እሳቸው እንደሚሉት፤ በሌሎች ሀገራት እንደሚስተዋለው ማዕድን ከማውጣት ጀምሮ በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ይሰጣል፤ ስልጠናው በዚህ ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም:: ማዕድናትን የመሸጥና የመግዛት ስልጠናም ጭምር ይሰጣል:: በኢትዮጵያም በዚህ ላይ በስፋት ሊሰራበት ይገባል:: እውቀትና ልምድ ከሌለ ማዕድናት መሸጥም ሆነ መግዛት ለኪሳራ የሚዳርግበት ሁኔታ ይፈጠራል::
‹‹ላኪው ዋጋ ከፍ አድርጎ ይገዛና ራሱን ሊጎዳ ይችላል፤ አልያም ዋጋውን ዝቅ አድርጎ ገዝቶ ሌላውን ሰዎች ይጎዳል፤ ማዕድን በእውቀትና ልምድ ተመስርቶ በሚደረግ ምልከታና ግምት የሚገዛ ነው፤ ከገዛሁት በኋላ በምን ያህል እሸጠዋለሁ የሚለውን በደንብ መገመት ይጠይቃል ›› ይላሉ::
‹‹ማዕድናቱ በቁፋሮ ነው የሚወጡት፤ ይህ ደግሞ የሚሰባበሩበት ሁኔታ እንዲከሰት ያደርጋል፤ በዚህም ለብልሽት ይዳረጋሉ›› የሚሉት ወይዘሮ ነጃት፤ ለዚህ ደግሞ መንግሥት የገበያ ትስስር በመፍጠር የማሽነሪ እና የመሳሰሉ ድጋፎች ቢያደርግ የተሻለ ነው ብለዋል::
በተለይ በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎቱ ላላቸው ሴቶች እሳቸው ልምዳቸውን እንደሚያጋሩ ጠቅሰው፤ አሁን ብዙ ሴቶች በዘርፉ እየተሰማሩ ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውንም ጠቅሰዋል:: እነዚህ ሴቶች ድጋፍ ቢደረግላቸው የተሻለ መስራት እንደሚችሉ አመላክተዋል::
ማዕድናት በኦንላይን ገበያ በብዛት እንደሚሸጡ የሚናገሩት ወይዘሮ ነጃት፤ ደንበኞቹ ምርቶቹን አይተው ከወደዷቸው እንደሚገዙ ይናገራሉ:: የማዕድን ገበያው በእውቀት ላይ የተመሰረተ ማብራሪያ መስጠትንና ታማኝነትን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል:: ‹‹ እኔ ብዙዎቹ ያመኑኛል በትክክል የነገርኳቸው ነገር አምነው ይገዙኛል፤ እስካሁን ቅሬታ ያቀረበብኝና የተቀየመኝ ደንበኛም አልገጠመኝም፤ ደንበኛን በማክበር በታማኝነት እየሰራሁ ነው›› ብለዋል::
ወይዘሮ ነጃት ማዕድናት ላይ እሴት የመጨመር ስራ ብዙ ልፋትና ድካም እንደሚጠይቅ ያመላክታሉ:: በዚህ መልኩ የተለፋበትን ማዕድን በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ገበያ በመላክ ሀገሪቱ ማግኘት ያለባትን የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ ማድረግ እንደሚገባም አስታውቀዋል:: በሕገወጥ መንገድ ማዕድናቱ ወደ ወጭ እየተላኩ ያለበት ሁኔታ ይህን ለማሳካት ደንቀራ መሆኑን ተናግረው፣ ህገወጥነቱ በአጠቃላይ ገበያውን እየጎዳው መሆኑን አስታውቀዋል:: አምራቾቹ ብቻ ሳይሆኑ ሀገርም ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ እያደርገም መሆኑን ያመላክታሉ::
ድርጅቱ የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋት እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን በብዛት ለውጪ ገበያ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን ወይዘሮ ነጃት ያመላክታሉ:: በተለይ ኦፓልን በቀላሉ በመቁረጥ እሴት በመጨመር ለተለያዩ ጌጣጌጥነት እንዲውል በማድረግ ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ይገልጻሉ::
ኤመራልድ ግን ዋጋው ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ማዕድኑን ቆርጦ ለመስራት ያስቸግራል ብለዋል፤ ኤመራልድ ሀገር ውስጥ ተቆርጦ ለውጭ ገበያ ሲቀርብ ትክክለኛው ኤመራልድ ማዕድን ነው ብሎ የአለማመን ሁኔታ እንደሚታይም አስታውቀዋል:: የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ወደ ውጭ ገበያ ለሚቀርቡ ማእድናት በሀገሪቱ ሰርተፊኬት እየተሰራ አለመሆኑ መሆኑን ጠቁመዋል:: ሰርተፊኬት ካለው ግን ሻጩም ሆነ ገዢው በመተማመን መገበያየት እንደሚችሉ ተናግረዋል::
ማዕድናቱን በመለየት ሰርተፊኬት እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል:: በሀገሪቱ ምን እንደሆኑ የማይታወቁ ብዙ አይነት ማዕድናት እንዳሉ ጠቅሰው፤ የማዕድናቱን ምንነትና ባሕሪያት ማወቅ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል:: ማዕድናትን መለየትና መመርመር የሚያስችሉ መሳሪያዎች እንዲኖሩ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ አስገንዘበዋል::
የደንበኞችን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ጥራቱን የጠበቀ ምርት እንደሚያመርቱ የሚናገሩት ወይዘሮ ነጃት፤ ማዕድናት የውጭ ሀገር ዜጎች አክብረው የሚጠቀሙባቸው ውድ ሀብቶች እንደሆኑ ይገልጻሉ:: ‹‹በኛ ሀገር አብዛኛውን ሰው ማዕድናቱን በደንብ ለይቶ አያውቅም፤ እውቀቱ ያለው የተወሰኑ ሰዎች አካባቢ ብቻ ነው ሲሉ ተናግረዋል::
‹‹ማዕድናት ሲያጌጡባቸው ያምራሉ፤ የሀገር ሀብት ስለሆኑ በሀገራችን ምርት ተጠቅመን ማጌጥ ያለብን እኛም ነን:: በተለይ ኦፓል ልክ እንደሰው ልጅ አሻራ ነው፤ አንድ ሰው ቢገዛው የዚያን ቅርጽና ከለር ዓለም ላይ ማግኘት አይቻልም፤ ያ ማዕድን የዚያ ሰው ብቻ ነው›› ይላሉ:: ‹‹ማዕድናትን ለራስ ገዝቶ አጌጦ ፣ለትውልድም ማስተላለፍ ትልቅ ታሪክ ነው:: የሀገራችንን ማዕድን ሁሉም ሰው ሊያጌጥበት ይገባል›› ሲሉ ተናግረዋል::
‹‹ሴቶች ለከበሩ ማዕድናት የተሰጡ ናቸው:: እኔ በተለይ ለማዕድናት ያለኝ ፍቅር ይለያል፤ ቤተሰቦቼ በሙሉ የማዕድን ስራዬን አይደግፉትም ነበር፤ ስጀምረው ፍቅሩ ብቻ ስላለኝ ገባሁበት እንጂ ያስገኘልኝ ትርፍ ባለመኖሩ አይደግፉትም ነበር›› የሚሉት ወይዘሮ ነጃት፤ በሀገራችን የማዕድን ሥራ ገና በሚባል ደረጃ ላይ መሆኑን ያመላክታሉ::
እሳቸው እንደሚሉት፤ የማዕድን ሥራ በጥንቃቄና በታማኝነት የሚሰራ መሆን አለበት:: በውጭ ሀገራት ማዕድናት ሲሸጡ ችግር ካለበት ምንም ሳይደበቁ እንደዚህ አይነት ችግር አለበት ይላሉ፤ በሀገሮቹ ማዕድኑ ላይ ያሉ ችግሮችን በሙሉ ለገዢው ማሳወቅ ያስፈልጋል::
እኛ ሀገር ግን በተለይ አሁን በማዕድናት ላይ የተለያዩ አይነት ባዕድ ነገሮች እስከ መጨመር የሚደርሱ ህገወጥ ድርጊቶች ይስተዋላሉ፤ ለአብነት ሩቢን የተሰኘውን ማዕድን ስኳር አቅልጠው ቀብተው አቅልተው ሊያቀርቡ ይችላሉ:: ይህ አሰራር ግን ሊታረም ይገባዋል፤ ሕገወጥ አሠራር ነው:: ይህን ተግባር ለሚፈጽሙ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠት ያስፈልጋል::
‹‹የሀገራችን ስም በጥሩ መጠራት ስላለበት ጥሩ መስራት ያስፈልጋል›› የሚሉት ወይዘሮ ነጃት፤ የመጥፎ ነገር ትንሸ ትጋነናለች፤ እንደዚህ አይነት ስህተቶች ሲፈጸሙ በማስተካከልና ጥሩ ምርቶች በማቅረብ በዓለም ላይ ስማችን በጥሩ እንዲጠቀስ ማድረግ አለብን›› ሲሉ አስገንዘበዋል::
ለዛ የከበሩ ማዕድናት ላኪ ድርጅት አሁን በአብዛኛው እሴት የተጨመረባቸውንም ሆነ ያልተጨመረባቸውን ምርቶ ለውጭ ገበያ እየላከ ያለው በኦንላይን ገበያ አማካኝነት ነው ሲሉ ጠቅሰው፤ በቀጣይ በአምራችነት ለመሰማራት ፍላጎቱ እንዳለውም ጠቁመዋል:: በዚህም በሰፊው ወደ ምርት ሥራ በመግባት ለብዙ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል::
በማዕድን ስራ መሰማራት የሚፈልጉ ሰዎች ማዕድናቱ ለሚያስገኙት ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ለማዕድናቱም ፍቅር ሊኖራቸው እንደሚገባ አመልክተው፣ የማዕድናት ስራ በፍቅር ሊሰራ እንደሚገባው ይገልጻሉ:: ‹‹በስራው እውቀትና ልምዱ የሌለው ባይገባ ይመረጣል፤ በማዕድን ስራ ስኬታማ ለመሆን ማመንም መታመንም ያስፈልጋል›› ሲሉም ተናግረዋል::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 18 ቀን 2017 ዓ.ም