ኢትዮጵያ ባለ ነጭ ቆዳ የሆነውን ማህበረሰብ ሁሉ በፈረንሳይ ወክላ የምትጠራ ሀገር ናት፡፡ ይህም የኢትዮጵያና ፈረንሳይን ግንኙነት ለየት የሚያደርገው ዘመናዊው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ብቻ አለመሆኑ ነው። ሕዝባዊ፣ ታሪካዊና ተረካዊ ይመስላል፡፡ በተረክ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ ትስስር ያለው ነው፡፡
እንደሚታወቀው እኛ ኢትዮጵያውያን ነጮችን (በተለይም አውሮፓና አሜሪካውያንን) ‹‹ፈረንጅ›› ብለን እንጠራለን፡፡ ሌሎች የዓለም ሀገራት ‹‹ነጮች›› እያሉ ነው የሚጠሯቸው፡፡ ምንም እንኳን በኢትዮጵያም የተማሩ የሚባሉት እና የውጭ ሀገራት የቆይታ ጊዜ ያላቸው ሰዎች ‹‹ነጮች›› እያሉ ቢጠቀሙም የገጠሩ ክፍል ግን ‹‹ፈረንጅ›› እያለ ይጠራቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ልማድ ሆኖ ‹‹በፈረንጆች አቆጣጠር፣ የፈረንጆች አዲስ ዓመት፣ የፈረንጆች ገና…›› እንላለን፡፡ ለመሆኑ ፈረንጅ ማን ነው?
ፈረንጅ የሚለው ቃል ‹‹ፍራንች›› ከሚለው ቃል የተዋለደ መሆኑን የቋንቋና የታሪክ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ፍራንች የሚባሉት ደግሞ በአሁኑ አጠራር ‹‹ፈረንሳይ›› የሚባሉት ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ለሙሉ ነጮች መጠሪያ ያደረገችው ይህ ቃልነው ፤ እውነታው ኢትዮጵያውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ያዩት ነጭ ፈረንሳዊ ነበር እንዴ? ያሰኛል።
ነጮች ኢትዮጵያ ውስጥ መቼም መጥተው ሊሆን ይችላል፡፡ ስያሜው የወጣው ግን በነበራቸው ቆይታና ቀረቤታ ነው፡፡ ፈረንሳዮች ኢትዮጵያ ውስጥ ሲቆዩ ‹‹ፍራንች›› እየተባሉ ነበር፡፡ ይህ ቃል እየቆየ ሲሄድ በሐበሻ አፍ ‹‹ፈረንጅ›› እየተባለ መጠራት ጀመረ፡፡ በኋላ የሁሉም ነጭ መጠሪያ ሆነ ማለት ነው፡፡
በኢትዮጵያውያን ልማድ ለፈረንጅ ትልቅ ቦታ ይሰጣል፡፡ ለምሳሌ የጓሮ አትክልቶችን ሳይቀር ትልልቅ የሆኑትን ‹‹የፈረንጅ›› የማለት ልማድ አለ፡፡ የፈረንጅ ቲማቲም፣ የፈረንጅ ጎመን፣ የፈረንጅ እንቁላል ይባላል። እነዚህን ነገሮች ያነሳናቸው ስለፈረንጅ (ነጮች) ለማውራት ሳይሆን፤ የሰሞኑን የኢትዮጵያንና የፈረንሳይን ግንኙነት ምክንያት በማድረግ ነገሩ ታሪካዊና ሕዝባዊ መሆኑን ለማስታወስ ነው፡፡
አንድ ቃል በማህበረሰብ ተፈጠረ ማለት፣ ያ ነገር በሕዝቡ ውስጥ ታሪካዊ ቦታ ነበረው ማለት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ነጮችን ሁሉ በፈረንሳይ ወክላ ትጠራለችና ግንኙነታቸው ጥንታዊ፣ ታሪካዊና ሕዝባዊ መሆኑን ያሳያል፡፡
ፈረንሳይ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ቦታ አላት። ለምሳሌ ብዙ ቃላት አማርኛ መስለው የሚያገለግሉ አሉ፡፡ በፈረንሳይኛ ቃላት የተሰየሙ ብዙ የንግድ ቤት ስያሜዎች አሉ፡፡ ፈረንሳዮች አብዝተው የሚወዱትና በፈረንሳይ ውስጥ እንደ ጀግና ወታደር፣ ብዙ ፀሐፊ፣ ምርጥ ፖለቲከኛ… በአጠቃላይ የፈረንሳይ አርክቴክት እያሉ የሚጠሩትን ቻርለስ ዴጎል ኢትዮጵያ አደባባይ (ዴጎል አደባባይ) ሰይማለታለች፡፡ የሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤትም ሌላኛው ዝነኛ ትምህርት ቤት እና የቦታ ስም ጭምር ነው፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ ፈረንሳይ የሚባለው አካባቢ ስመ ጥር ቦታ ነው፡፡ የታክሲ ረዳቶች በየቦታው ይጠሩታል። ብዙ ታዋቂ አርቲስቶችና ፖለቲከኞች የወጡበት ስለሆነ በየመድረኩና በየሚዲያው ስሙን ይጠሩታል፡፡ በአጠቃላይ ፈረንሳይ ኢትዮጵያ ውስጥ ስሟ የሚነሳበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡
ወደ ሀገራዊና የመንግሥታት ግንኙነት ስንመጣ ታሪካዊ ቁርኝት ያለው ነው፡፡ በተለይም የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመር በብዙዎች ዘንድ የሚታወስና የኢትዮጵያና ፈረንሳይን ወዳጅነት ያዘለቀ ነው፡፡ በተለያዩ መንግሥታት ወቅት ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ከፍተኛ ቁርኝት ያላቸው ሀገራት ናቸው፡፡
በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑበት የለውጡ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያና ፈረንሳይ ግንኙነት የበለጠ ተጠናክሯል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሥልጣን በያዙ በ8ኛው ወር በጥቅምት 2011 ዓ.ም ወደ ፈረንሳይ አቅንተዋል፡፡ በቆይታቸውም የኢትዮጵያና ፈረንሳይን የጋራ ትብብር ዙሪያ ተወያይተው ስምምነቶችን ተፈራርመዋል፡፡
ከአራት ወራት በኋላ በመጋቢት 2011 ዓ.ም የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ የነበራቸው ቆይታም በሁለቱ ሀገራት መካከል ቁልፍ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊና የባህል የትብብር መስኮች እንዲጎለብቱ ያደረገ ነበር፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችውን ታሪካዊው የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናትን መጎብኘታቸውና ለማስጠገን ቃል መግባታቸው በወቅቱ ብዙዎችን ያስደሰተ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲም ነበር፡፡ ከመሪዎቹ በተጨማሪም የሁለቱም ሀገራት ሚኒስትሮችና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች የሥራ ጉብኝቶችንና የልምድ ለውውጦችን አድርገዋል፡፡
የዘንድሮውን የፈረንሳዩን ፕሬዚዳንት ጉብኝት ለየት የሚያደርገው ደግሞ ኢትዮጵያ የወደብ ተጠቃሚ ለመሆን በትጋት እየሠራች ባለችበት እና ፈረንሳይ ደግሞ ለዚህ ወሳኝ ሚና ያላት መሆኑ ነው፡፡ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን በጥበብ፣ በብልሃት እና በሰላማዊ መንገድ የመወጣት ልምድ ያላት ኢትዮጵያ በቅርቡ በአንካራ ከሶማሊያ ጋር ስምምነት ማድረጓ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ ከእነዚህ ሀገራት ጋር የምታደርገው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለብዙ ዓመታት ተዳፍኖ የኖረውን የወደብ ጉዳይ መፍትሔ እንዲያገኝ እንደሚሠራ ይታመናል፡፡
ኢትዮጵያ በተለይም ከ1983 ዓ.ም ወዲህ የወደብ ባለቤት አለመሆን ብቻ ሳይሆን ጭራሹንም የወደብ ጥያቄ እንዳታነሳ ስትደረግ የቆየች ነበረች፡፡ በወቅቱ የነበረው መንግሥት ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ የወደብ ጉዳይ ሲያነሱ ‹‹የድሮ ሥርዓት ናፋቂ፣ ወራሪ፣ ጨፍላቂ…›› እያለ የሚሳደብ ነበር፡፡ በየትኛውም መንገድና አማራጭ ወደብን ጉዳዩ አድርጎ አያውቅም ነበር፡፡ የሀገሪቱ ከፍተኛው ወጭም የወደብ ወጪ ሆኖ ነበር፡፡
ከለውጡ ወዲህ በተደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ግን ቢያንስ ወደብን ጉዳይ ማድረግ ተችሏል፡፡ ጉዳይ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ሂደቶች እንዲጀመሩ ማድረግ ተችሏል፡፡ ለዚህ ደግሞ ብልህነት በተሞላው መንገድ ወዳጅነታዊ ግንኙነቶች እየተደረጉ ነው፡፡ ከሶማሊያ ጋር በቱርክ በኩል፣ ከጅቡቲ ጋር በፈረንሳይ በኩል የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነቶች ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ናቸው፡፡
ሀገር ወዳድ ነን የሚሉ፣ ለሀገር እንቆረቆራለን የሚሉ ወገኖች እንዲህ አይነት ግንኙነቶችን ሊያደንቁ እና ሊያበረታቱ ይገባል፡፡ አለበለዚያ በሀገር መሪ ትግል ብቻውን ሊሳካ አይችልም፡፡ ሕዝባዊ ድጋፍ ሊኖረው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሕዝቡን ድጋፍ ካወቀ ድጋፉን ይሰጣል፡፡ እንዲህ አይነት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች መሪ ከመሪ ጋር የሚጨባበጡበት ብቻ ሳይሆን ሀገራት ከሀገራት ጋር፣ ሕዝብ ከሕዝብ ጋር የሚወዳጁባቸው ናቸው፡፡
ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ያላቸውን ታሪካዊና ሕዝባዊ ግንኙነት ከላይ ባየናቸው ነባራዊ ሁኔታዎች ገልጸናል። ፈረንሳይ በኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ የገባች ሀገር ናት፡፡ በብዙ ነገሮቻችን ውስጥ ‹‹የፈረንሳይ….›› ማለት የተለመደ ነው፡፡ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት ላይ የነበሩትን ጨምሮ ብዙ ታዋቂ ሰዎቻችን ፈረንሳይ ውስጥ ኖረዋል፣ ፈረንሳይን ቤተሰብ አድርገዋል፡፡ ይህ ታሪካዊና ሕዝባዊ የፈረንሳይና የኢትዮጵያ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የአሁኑ ትውልድም በትጋት መሥራት አለበት!
ሚሊዮን ሺበሺ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 17 ቀን 2017 ዓ.ም