አንድ ማኅበረሰብ የቴክኖሎጂ እድገትን በየትኛውም ደረጃ ለማምጣት በመጀመሪያ የባሕል ዝግጅት እንደሚያስፈልገው የዘርፉ ታሪክ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። የሀገራት ሥልጣኔም ቴክኖሎጂን በባሕላቸው ለመጠቀም ካላቸው ዝግጁነት እና ፍላጎት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። ስለሆነም ማንኛውም ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራና አዳዲስ አሠራር በማህበራዊና፣ ሥነልቦናዊ ዝግጅት መደገፍ ይኖርበታል። በዚህ መንገድ መጓዝ ካልተቻል የቴክኖሎጂዎች ትግበራዊ ማኅበረሰባዊ ቅቡልነትን እንደሚያጣ ምሁራኑ ይገልፃሉ።
ዓለማችንን የለወጡ እንደ ስልክ፣ ኤሌክትሪክ (ELECTRICITY)፣ ክትባት (VACCINATION)፣ መኪና፣ አውሮፕላን እና መሰል የቴክኖሎጂ ውጤቶች አሁን ያላትን መልክ እንድትጎናጸፍ አድርገዋታል፡፡ በዘመኑ በነበረው ማኅበረሰብ ዘንድ ባሕላዊ ዝግጁነት ባለመኖሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶቹ ማህበረሰባዊ ተቃውሞ አስተናግደዋል። ለአብነት የስልክ ቴክኖሎጂ እንጥቀስ። የስልክ ቴክኖሎጂ በ1868 ዓ.ም. በተፈጠረባት አሜሪካም ስልክን ከጥንቆላና፣ ከአስማት ጋር በማያያዝ ሰፊው ማህበረሰብ እስኪጠቀመው ጊዜ ፈጅቷል። አንዳንዶቹ እንደ ተፈጥሯዊ ያልሆኑ ግዑዝ ነገር ሲቆጥሯቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ የሰይጣን ሥራ በማለት ያጣጥሏቸው ጭምር ነበር።
በኢትዮጵያ የዘመናዊነት ጉዞ አዲስ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ያለው አመለካከትና ፍላጎት አለመኖር ከዚህ የተለየ እንዳልነበር ታሪክ ይናገራል። ሀገሪቷን ለማዘመን የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን በመተለም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስገባት፣ በራስ አቅም የማምረት ራዕይ በመያዝ ጥረት ሲያደርጉ ነበር። ራዕዩን ለማሳካት በሚያደርጉት ጥረት ውጫዊ እና ውስጣዊ ፈተናዎችን ተጋፍጠዋል። በዚህ ረገድ ፈተናውን ተቋቁመው በተሳካ ሁኔታ ኢትዮጵያን ወደ ዘመናዊነት ማሸጋገር የቻሉት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ እንደነበሩ በታሪክ ተጽፏል።
ጳውሎስ ኞኞ “አጼ ምኒልክ” በሚለው መጽሐፉ ንጉሡ ጥንታዊ ሥልጣኔዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ምን ያህል ችግርና ፈተና ደርሶባቸው እንደነበር ገልጾታል። በዘመናዊት ኢትዮጵያ፣ በቴክኖሎጂ ረገድ በተደረገው ግሥጋሴ ፊት አውራሪ መሆናቸውን በመጥቀስ ፤ አጼ ምኒልክም በወቅቱ በዓለም ዙርያ አሉ የተባሉት የጥበብና የፈጠራ መገለጫ አገልግሎቶችና ቁሳቁሶች ወደ ኢትዮጵያ አስገብተዋል። የዘመናዊ ሥልጣኔ ራዕይ ይዘው የተነሱት ንጉሡ በመጀመሪያው ማዕበል ወደ ከተማዋ የመጡት ባቡር፣ ባንክ፣ ጥይት ፋብሪካ የስልክ መስመር፣ ቴሌግራፍ፣ ወፍጮ፣ በእንፋሎት የሚሄድ ሞተር እና ሌሎችም ሲጠቀሱ፤ በሁለተኛው ዙር ከገቡት የፈጠራ ውጤቶች መካከል ደግሞ ቴያትር ቤት፣ መኪና፣ የቧንቧ ውሃ፣ ሆቴል እና በርካታ ትናንሽ ቁሳቁሶች ይገኙበታል። ንጉሡ በዘመኑ ቴክኖሎጂዎቹ ወደ አዲስ አበባ በገቡበት ወቅትም ከማህበረሰቡ ከፍተኛ ተቃውሞ ይገጥማቸው እንደነበር በመጽሐፉ አመላክቷል።
ጳውሎስ ኞኞ ፤ አንዳንዶቹ እንደ ተፈጥሯዊ ያልሆኑ ግዑዝ ነገር ሲቆጥሯቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ የሰይጣን ሥራ በማለት ያጣጥሏቸው ነበር። ስለሆነም አብዛኞቹ ፈጠራዎች በንጉሱ ጥብቅ ክትትልና የበላይ ጠባቂነት በቤተ – መንግሥቱና በአራት ኪሎ አካባቢ ከማህበረሰቡ ጋር የመጀመሪያ ትውውቃቸውን አድርገዋል። በዚህም አጼ ምኒልክ የቴክኖሎጂ ባሕላዊ ቅቡልነት እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ እንደ ልዩ ነገር በጥርጣሬ ይታይ ከነበሩት ቴክኖሎጂዎች መካከል ስልክ ዋነኛው ነበር ይላል።
በወቅቱ የሰውነት አካል የሌለውን ድምጽ መስማት በአካባቢው ቀሳውስቶች ዘንድ ፍርሃትን የፈጠረና እንደክፉ መንፈስ ሥራ የተቆጠረ ነበር። በዚህ ምክንያት ስልክ ከቤተክህነት አካባቢ ከፍተኛና የአደባባይ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። በቤተመንግሥት ውስጥ ያሉ ቢሮዎችን ለማገናኘት የስልክ መስመር መዘርጋት ሲጀምር ከቤተክርስቲያን በተላኩ ቄሶች አማካኝነት የሰይጣን ሥራ ስለሆነ መሳሪያው እንዲወገድ የሚል ቅሬታም ቀረበ።
በዘመናዊት ኢትዮጵያ፣ በቴክኖሎጂ ረገድ በተደረገው ግሥጋሴ ፊት አውራሪ የሆኑት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የሕዝቡን ችግር በማሰብ የእህል ወፍጮ ወደ ሀገራችን እንዲገባ ሲያደርጉ ትልቅ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል እንደነበር መጽሐፉ ያስረዳል። ‘የእህል ወፍጮ የሚፈጨው በጋኔል ነው’ እያለ ሕዝቡ በውኃ መዘውር በሚንቀሳቀስ ወፍጮ እህል አላስፈጭ ቢላቸው ወፍጮው ጋኔል አለመሆኑን ለማሳየት ዱቄት አስፈጪ ሆነው እስከ መሥራት መድረሳቸውን ጳውሎስ ኞኞ ጽፏል። በዘመኑ የዳግማዊ አጼ ምኒልክ የቴክኖሎጂ ጥማት እና ከማህበረሰቡ ንቃት ጋር ባለመጣጣሙ ዘመናዊ ሥልጣኔን የማስፋፋት ርምጃውን ፈታኝ እንዳደረገው መረዳት ይቻላል።
በዚህ ዘመንም በሀገራችን አዳዲስ ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ለማድረግ ሲሞከር ተመሳሳይ እንቅፋቶች ይገጥማሉ። ለዚህ ደግሞ በ2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ መተግበር የጀመረው “ፋይዳ” ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ለአብነት ይጠቀሳል። አሁን ባለንበት የዲጂታል ዓለም አንድ ሰው ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጋር በሚኖረው ግንኙነት ለማንነቱ ማሳወቂያም መተማመኛም ማስፈለግ ከጀመረው ሁለት አስርት ዓመታት ማስቆጠሩ ይታወቃል። በርካታ ሀገራት የዘመናዊ መታወቂያን ፋይዳ በመረዳት በርካታ ሀገራት የዲጂታል መታወቂያን በሚመለከት ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፈው፣ ሕግ አውጥተው ወደ ተግባር ተሸጋግረዋል። እንደ ኢስቶኒያ ያሉት ሀገሮች ደግሞ በአስደማሚ ብቃትና ውጤታማነት ተግባራዊ በማድረግ ለበርካታ ሀገሮች አርዓያ ሆነዋል፡፡ ህንድ ከአጠቃላይ ሕዝቧ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን የሚሆነው ዲጂታል መታወቂያ አለው፡፡ የቀራት 100 ሚሊዮን የሚሆን ብቻ ነው፡፡
ቢዘገይም በኢትዮጵያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የበለፀገ፣ ዘርፍ ተሻጋሪ፣ መሠረታዊ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ለመዘርጋት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል። በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የ’ፋይዳ’ ዲጂታል መታወቂያን ተደራሽ ለማድረግ ከኢትዮ-ቴሌኮም፣ ከጤና፣ ከትምህርት፣ ከፋይናንስ ተቋማትና ከሌሎችም ጋር በጥምረት እየሠራ ይገኛል።
በአሁን ወቅት ለ10 ሚሊዮን ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል። ይሁንና ከታቀደው አንጻር አፈጻጸሙ የሚፈለገውን ያህል እንዳልሆነ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል። ይህም በማኅበረሰቡ ዘንድ በተፈጠረ የተሳሳተ የአመለካከት ችግር ሊከሰት እንደቻለ ይፋ አድርጓል። በኅብረተሰቡ ዘንድ የ’ዲጂታል መታወቂያ ከሃይማኖት አስተምህሮት ጋር የሚጣላ ነው’ የሚል አመለካከት መኖሩን ለመረዳት ተችሏል። ይሁንና የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ከሃይማኖት አስተምሮ ጋር ምንም ዓይነት ተቃርኖ የለውም።
በአንድ መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንዳረጋገጡት፤ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ከሃይማኖት አስተምሮ ጋር ከመቃረን ይልቅ፤ ከሃይማኖታዊ አስተምሮት ጋር የሚጣጣም ሥርዓት ነው። ዲጂታል መታወቂያ በማኅበረሰብ መካከል እርስ በእርስ መተማመን የሚፈጥርና ፍትሐዊነት የሚለውን ሃይማኖታዊ አስተምህሮን የሚከተል፤ ሀገራዊ ልማትን ለማረጋገጥ፣ ወንጀልን ለመከላከል የሚረዳም ጭምር እንደሆነ ገልጸው፤ ይህም የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ከሃይማኖት አስተምሮ ጋር ምንም ዓይነት ተቃርኖ እንደሌለው ነው ቀሲስ ታጋይ ያስታወቁት። ይሁንና ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በአብዛኛው ማኅበረሰብ ዘንድ በግንዛቤ እጥረትና የተሳሳተ አመለካከት የተነሳ ተደራሽነቱ አናሳ እንደሆነ ተነግሯል። በተለይ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ማኅበረሰቡ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዝ፣ እንዲጠራጠር የማድረግ ሥራ ተሠርቷል።
በመግቢያችን እንደገለጽነው፤ የሀገራት ሥልጣኔም ቴክኖሎጂን በባሕላቸው ለመጠቀም ካላቸው ዝግጁነት እና ፍላጎት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው መሆኑን ሊታወቅ ይገባል። ማንኛውም ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራና አዳዲስ አሠራር በማህበራዊና፣ ሥነ ልቦናዊ ዝግጅት መደገፍ እንዳለበት ይታመናል። የብሔራዊ መታወቂያ ሥርዓት ትግበራው ስኬታማ ለማድረግ ማኅበረሰባዊ ቅቡልነትን መፍጠር እንደሚገባ መታወቅ ይኖርበታል። ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ከሃይማኖት አስተምህሮት ጋር ተቃርኖ እንደሌለው በማስተማር ማኅበረሰቡ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህም በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላትን ጠንካራ ተሳትፎ ይጠይቃል።
በዚህም የመንግሥት አካላት ዲጂታል መታወቂያን በመውሰድ ለህብረተሰቡ ሞዴል ሆነው መታየት ይኖርባቸዋል። በዘመናዊት ኢትዮጵያ ጉዞ የአንበሳውን ድርሻ እንደያዙ የጠቀስናቸው ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ሕዝቡ ቴክኖሎጂዎችን እንዲቀበል ለማድረግ ሲሞክሩ የነበሩት በቃላት ሳይሆን በተግባር እንደነበር ይታወቃል። ከ’ሺህ ቃላት፤ አንድ ድርጊት’ እንደሚባለው በዝርዝር የቀረቡትን የፋይዳን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች በተግባር በተደገፈ ማሳያ ሕዝቡ እንዲያይ ማድረግ ያስፈልጋል። ለምሳሌ አገልግሎትን ከማቅለል አኳያ ያለውን ጥቅም በተግባር እንዲመለከት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ከዚህ ባሻገር የህብረተሰቡ ግንዛቤ መጨመር የሚያስችሉ የንቅናቄ ሥራዎችን መሥራት እንዲሁም ዜጎች በተለያዩ ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት ሲፈልጉ “ፋይዳ” ዲጂታል መታወቂያን መያዝ ቅድመ ሁኔታ እንዲሆን መደረግ ይኖርበታል፡፡
ሌላው የሃይማኖት አባቶች ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው። በሁሉም ቤተ እምነት የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓቱ ከሃይማኖት አስተምሮ ጋር ተቃርኖ የሌለው መሆኑን ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እና ተዓማኒነት ባላቸው የሃይማኖት አባቶችን ምሳሌ በማድረግና በሚሰጡት አስተምሕሮ በመጠቀም ተደራሽነቱን ማስፋት ያስችላል። በመሆኑም የእምነት አባቶች በሃይማኖት ተቋማቸው የሚገኘውን ማኅበረሰብ በማስረዳት፣ ምሳሌ በመሆን እና በማስተማር እውነታውን በማሳወቅ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል። ይህ የሃይማኖት አባቶች ተሳትፎ የሚፈጥረውን ተጽእኖ ከሦስት ዓመት በፊት በኮቪድ -19 ወረርሽኝ ወቅት ማሳያ ይሆናል።
ኮቪድ-19 በዓለም አቀፍ ደረጃ መከሰቱን ተከትሎ በርካታ ሰዎች በወረርሽኙ ሳቢያ ለውስብስብ የጤና ጉዳቶችና ለሞት ተዳርገዋል። በወቅቱ የሳይንሱ ጠበብቶች የኮቪድ 19 ክትባትን መፍጠር ቢችሉም፤ ቅቡልነቱ አጥጋቢ እንዳልነበር ይታወሳል። በተመሳሳይ በሀገራችን ክትባቱ ጋር ተያይዞ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ስለክትባቱ የሚጻፉ መረጃዎች በርካቶችን አሳስተዋል፤ ጥርጣሬ እንዲፈጠር ማድረጋቸው ይታወሳል። ይሁንና ህብረተሰቡ ክትባቱን እንዲወስድ የሃይማኖት አባቶች በመከተብ ጭምር ተፈጥሮ የነበረውን ጥርጣሬ ለማጥፋት ጥረዋል። በዚህም የሃይማኖት አባቶች በኮቪድ – 19 የክትባት ዘመቻው ውጤታማነት ትልቅ ሚና እንደነበራቸው ሁሉ በፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት መድገም ይኖርባቸዋል።
በተጨማሪም ታዋቂ ሰዎች ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የሀገር ሽማግሌዎች በማሳተፍ ሀገራዊ ንቅናቄ በማድረግ መታወቂያው ሀገራዊ ልማትን ለማሳደግ፣ ማጭበርበርንና ወንጀልን ለመከላከል እንዲሁም ቀልጣፋ አገልግሎት ለማግኘት የሚረዳ መሆኑን ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል። ኅብረተሰቡ አገልግሎቱን በመጠቀሙ የሚያገኘውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም በሚገባ ማወቅና መረዳት ከቻለ በአጭር ጊዜ የሚፈለገው ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ይታመናል።
በጥቅሉ ዘመናዊ የመታወቂያ ሥርዓት በአንድ ሀገር ውስጥ ተግባራዊ ሲደረግ መሠረታዊ የሚባሉ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ይታመናል። የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በአዋጅ ቁጥር 1284/2015 በኢትዮጵያ ይፋ የሆነ መሠረታዊ ህጋዊ መታወቂያ የዲጂታል መታወቂያ ትግበራው ለሀገሪቱ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ እንዲሁም ለአሥር ዓመቱ የመንግሥት የልማት ዕቅድ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
በአግባቡ የተተገበረ ዲጂታል መታወቂያ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጠቅላላ ምርት (ጂዲፒ) ላይ እስከ ስድስት በመቶ የሚደርስ ጭማሪ ያለው አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚችል ይታመናል፡፡ በዚህም ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብቷንና የዜጎችንም የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ስለዚህ በዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ዝርጋታ የሚገኝን የውጤት ፍሬ መብላት የሚቻለው የማኅበረሰቡን የተሳሳተ አመለካከት አስተካክሎ ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ ሲቻል እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 15 ቀን 2017 ዓ.ም