የአያቴ «ሰጥተህ´ ታዘበኝ ነገር

ተወልጄ ያደኩት አንድ ትንሽ ከተማ ነው:: እናቴ እኔን ስትወልድ ልጅ ስለነበረች የማሳደግ እና የመንከባከብ አቅምም፤ ጊዜም አልነበራትም:: በመሆኑም አያቴ እና ቅድመ አያቴ በስስት እና በወግ ልጅ ከሚያገኘው በላይ ሰው እንድሆን አድርገው አሳደጉኝ:: ያ የልጅነት ጊዜ በሕይወቴ ትልቅ ዋጋ ነበረው እና ሰዎች እስኪገረሙ ብዙ ነገሮችን በደንብ አስታውስበታለሁ:: በደማቁ በልቤ ከተፃፉ እልፍ ጉዳዮች ውስጥ የአያቴ ፀሎት እና ልመና ከነቅደም ተከተሉ ከነፍሰቱ ዛሬም በጆሮዬ ያቃጭልብኛል:: አቤት አያቴ::

ራት በልተን ዕቃውን አሰናድተን ከጨረስን በኋላ ወደ መደባችን እንወጣና የእመዬን ፀሎት ማጣጣም ልምድ ሳይሆን ግዴታ ነበር:: መቁጠሪያዋን እያቃጨለች ኤሎሄ… ኤሎሄ… የአቡነ ዘበሰማያት… ቋሚ ፀሎት ከተጠናቀቀ በኋላ በየቀኑ ከሚገጥሟት ጉዳዮች ላይ መሠረታቸውን ያደረጉ ተማፅኖዎች ይቀርባሉ:: አንድ ቀን ግን ከተለመደው የተለየ ፀሎት ይሁን ትዕዛዝ አሁንም ያልገባኝን ጉዳይ ለፈጣሪዋ አቀረበች:: አምላኬ «ሰጥተህ´ ታዘበኝ፤ እባክህ… በቃ «ሰጥተህ´ ታዘበኝ:: ዓይኗን ጣሪያው ላይ ሰክታ ወዲያው እንደሚመልስላት ጠየቀችው:: ግን «ሰጥተህ´ ታዘበኝ ምን ማለት ነው…

«ሰጥተህ´ ታዘበኝ የጎረበጠችኝ ሀረግ ስለነበረች ብዙ ቀን ስጠይቃት እንደነበር አስታውሳለሁ:: አያቴ በጣም አዛኝ ከመሆኗ የተነሳ የተቸገረ ሰው ስታይ ያላትን ሁሉ ትሰጥ ነበር:: አምላክም የእውነት ሊታዘባት ፈልጎ ወይም ልቧ ውስጥ የተሞላው እምነት እና ርግጠኝነት አስደስቶት ባላውቅም ያሻችውን በረከት ሰጣት:: አባቷ ብዙ ሀብት አወረሷት:: አያቴ በማያልቀው ምስጋናዋ ደምቃ የቻለችውን ሁሉ አድርጋ በዙሪያችን የነበሩ ምስኪኖችን ትጋብዝ ነበር:: የተሰጣትን ለትዝብት ሳታስቀር በተግባር አውላ አሳየችኝ::

በነገራችን ላይ አያቴ ሰው እያያት ለሰው በፍፁም ስትሰጥ አይቻት አላውቅም:: የጓሮ በር ከፈት አድርጋ ስጦታ ካስቀመጠች በኋላ በፊት ለፊት በር ገብታ እንደ አዲስ እንግዳ ሰላም ስትላቸው አይቻለሁ:: በዘመኔ ግን ካሜራ ካልተደቀነ ታዛቢ ካልተሰበሰበ ስጦታ አይሰጥም፤ ሲሰጥም ሂደቱ ፍጥነቱን ቀነስ አድርጎ እየተሸኮረመመ ነው ወደ ተቀባዩ የሚሄደው:: እናም አያቴ «ሰጥተህ´ ታዘበኝ የምትለው አምላኳ የሚያያት በድብቅ ብቻ ከሆነ ይመስለኝ ነበር:: ግን እኮ ሊሆንም ይችላል:: በአደባባይ እየሰጠን እና እየተቀበልን ይሆን የተሰጠን የማይበረክተው፤ የምንሰጠውስ የምናጣው…።

ዛሬ ላይ «ሰጥተህ´ ታዘበኝ ለማለት ብቃቱ፣ ዝግጅቱ፣ ቀናነቱ፣ ቻይነቱ ብዙ ብዙ አስፈላጊ ጉዳዮችን በበኩሌ ስላላሟላሁ ደፍሬ ስጠኝ አልልም:: በድፍረት ጠይቀው ይሁን ወይ እሱ ፈጣሪ እስኪ ሰጥቼ ልታዘባቸው ብሏቸው ምንም ባላውቅም ብዙዎች ሳይሰጣቸው ተሰጠው ሰጪውን ሲያሳዝኑ አያለሁ:: የሰው ልጅ ሲፈጠር በሳይንሱም ሆነ በሃይማኖት ቢመሳከር የማይካደው ነገር ወደዚች ምድር ሲመጣ ለራሱ ብቻ የተሰጠው ልዩ ማንነትና ችሎታ አለው:: ያን ችሎታ በትምህርት፣ በሥራ ወይም በሰዎች እገዛ ማወቅ እና መለየት ሲችል ስኬታማ ሥራ ሰርቶ ውጤት ያሳያል:: ጥሩ ገበሬ መሆን የሚችል ሰው አስተምራለሁ ብሎ ቢሞግት ራሱም አይደሰት ወይም የሚታይ ውጤት አያመጣ እንዲሁ እድሜውን በንጭንጭ እና በምሬት መፍጀት ብቻ ይሆናል::

ኃላፊነት፣ አደራ፣ ሕዝብ ከሁሉም በላይ ሀገር ሥራልኝ ወይም ሥሪልኝ ብሎ ተዘጋጀህም አልተዘጋጀህም እጅህ ላይ ቁጭ ሊል ይችላል:: እነዚህ ጉዳዮች ከራስ ጥቅም እና ፍላጎት በላይ ናቸው እና ከራስህ እንዳስበለጥካቸው እና እንደረጋገጥካቸው ትዝብት ላይ ሊጥሉህ በተግባር ይፈትኑሃል:: ይሄ ቃላዊ ትውልድ ይላሉ አንዳንድ ሰዎች… በቃል አልፈክ በተግባር ዘጭ ስትል ኃላፊነቱን የሰጠህ ፈጣሪ አደራ ያለህ ሕዝብ ከማፈር ጋር ይታዘብሃል::

በእኔ አረዳድ ኃላፊነት ወይም ወንበር እንደ ትምህርት ዝግጅታችን፣ ብቃታችን እና ብሎም አስተዋጽኦ ማሳደር መቻላችን ከሌሎች ሰዋሰዋዊ እይታዎቻችን ጋር ተዳምረው ወደ አገልግሎት መስጫ ወንበር ሊያመሩን ይችላሉ:: አያቴ በልበሙሉነት «ሰጥተህ´ ታዘበኝ እንዳለችው እኛም ለወንበሩ ብቁ የሚያደርጉንን መስፈርቶች አሟልተን «ሰጥተህ´ ታዘበኝ ካልን ውጤታማነት ከደስተኝነት ጋር እናሳያለን:: አሁን አሁን ላይ ግን በኔ አረዳድ ወንበሩ ከእኛ ብቃት እየበለጠ ባለበት እኳኋን ማስቀጠል አቅቶን ወንበሩን ስንነቀንቅ ከሰው በፊት ወንበሩ እራሱ ስንቴ እንደታዘበን ወንበሩ እራሱ ይታዘበው::

ከላይ ከተጠቀሱት አመክንዮዎች ባንዱ ወይም በሁሉም ምክንያት ወንበር ላይ ተቀምጠው ስንቱን ብልሹ አሠራር እንደ መርህ አፀደቁ አስፀደቁ ብቻ ወንበሩ ይቁጠራቸው:: በኔ አመለካከት መንግሥት የትኛውንም ሥራ እና ኃላፊነት በሕግ ከመደንገግ እና ለክትትል የሚበጅ ፖሊሲ ከማርቀቅ ባሻገር የሚያምንባቸውን ባለወንበሮች አደራ መስጠት እና ማመን ግድ የሚሆንበት ብዙ አጋጣሚ አለ::

ከብዙ የመረጃ ምንጮች እንዳነበብኩት እና በታሪክም በተግባር ከሀገራት ታሪክ እንዳየሁት ብዙ ጊዜ መንግሥት እንደ መርህ የሚያወጣው ሕገ ደንብም ይሁን ፖሊሲ በተቀመጠው ልክ ካልተፈፀመ የሕጉ ወረቀት ላይ መኖር ብቻውን ከመገምገም እና ከመተቸት አያድነውም:: ለዚህም ይመስላል በመንግሥት ሕገ እና ፖሊሲ እምነት እና ቀና አመለካከት የሌላቸው ሰዎች ወደ ወንበሩ የማይጋበዙት:: ችሎታ እና የትምህርት ዝግጅት ከተጠቀሰው ጉዳይ ጋር ተጣምሮ ከተገኘ የተሻለ አሠራር ቢያንስ በሃሳብ ደረጃ ይሳካ ይሆናል::

ሀቅም እና ቀናነት ወይም ሕግን በተገቢው ሁኔታ ለመፈፀም ችሎታ ያነሳቸው አጋጣሚ ወንበሩ የጠራቸው አረሞች መንግሥት እና ሕዝብን ለመነጠል ብሶት እና ጉስቁልናን ለማፋጠን ብቻ በየቢሮው ተሰግስገው ማየት ለእኛ አፍሪካዊያን ብርቅ አይደለም:: በፖለቲካ እና ማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ያሉ ምሁራን በጥናታቸው እንዳስቀመጡት ማህበረሰባዊ ስሪታችን በተለይ የታዳጊ ሀገራት ከኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችን ጋር እጅግ የተሰናሰሉ ስለሆኑ አስተዳደጋችን እና አመለካከታችን ከዚህ የድህነት ችግር የምንወጣበትን የተዛባ አመለካከት በባሕል ቅርፅ ይዞ እናገኘዋለን::

ለምሳሌ «ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል….» የሚል የቆየ አባባል አለ:: በዚህ አባባል ስር ሁለት ነጥቦችን መረዳት ይቻላል:: አንደኛው አንድ ሰው ወደሆነ ኃላፊነት ሲመጣ በታማኝነት ከማገልገል ይልቅ የራሱን ጥቅም እና መደላድል ማስተካከል የሚደገፍ ነው የሚል ብልሹ አሠራርን የሚያበረታታ ሃሳብ አለው:: ይሄ ማለት የተሰጠው ኃላፊነት ላይ ሆኖ ግዴታውን ባይወጣ ያን ያህል ወቀሳም ሆነ ቅጣት አያገኘውም ማለት ይሆን የሚል ነጥብም ያስነሳል::

ለምን ቢባል መጠየቅ ቢኖረውማ ኖሮ ከአባባሉ ጋር ተደራቢ የሆነ ማረሚያ አገላለጽ ይኖር ነበር የሚል መከራከሪያ አለ:: ሁለተኛው ጉዳይ አንድ ሰው ወደ ሥልጣን የሚመጣው በሆነ አመክንዮ እንጂ በመክሊት ባለመሆኑ አንዴ ያን ቦታ ካጣሁ ሌላ መግቢያ አጋጣሚ የለውም የሚል ተርጓሜ ያነገበ አገላለጽ አለው ብለው የሚከራከሩ ወገኖች አሉ:: ምክንያቱም ሲሻር ይቆጨዋል ይላልና:: ያም ሆነ ይህ ግን ማህበረሰባዊ ስሪታችን ትርክታችን መሻሻል ይፈልጋል እላለሁ::

እነዚህ ባለወንበሮች ታምኖባቸው አደራው ከብዷቸው የተጣለባቸውን ግዴታ እና ኃላፊነት ለባለቤቱ ማለትም ለሕዝቡ አድርሰዋል….. ወንበርዬ እስኪ ሹክ በለኝ… መንግሥት ሥርዓት ዘርግቶ በዚህ በኩል አድርጋችሁ ሕዝቤን አገልግሉ ብሏቸው አደራውን በተገቢው ሁኔታ አድርሰው ምስጋን የተቸሩ ወንበሩም በኩራት የሚቀበላቸው እፁብ ድንቅ የሀገሬ ልጆች እንዳሉ አውቃለሁ:: ማመስገን የመሰልጠን ምልክት ነው እና ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ አገልግሎት ሰጭ መሥሪያ ቤቶች በአንፃራዊነት መልካም ሊባል የሚችል አሠራር በመተግበር ላይ እንደሆኑ በግሌ አይቻለሁ:: ጥሩ ሲሠራ በማመስገን ለበለጠ ቀልጣፋ አሠራር በር መክፈት ቢለመድ መልካም ነው::

የኔ ትውልድ ካላየሁ አላምንም የሚል ሆኖ ነው ወይስ ድርጊት ከቃል በላይ ይናገራል ስለሚባል፤ ብቻ ተግባር እልፍ ቃላትን እና ትርጓሜዎችን ይይዛል:: እናም በተለይ እኩይ ትግበራዎች ከመልካሞቹ በበለጠ ትኩረት ይስባሉ:: ያም ብቻ አይደለም ሰዎች በተፈጥሮ ይሁን በልምድ በግልጽ አላውቅም አንድ ሰው ከቦታው ከተነሳ ደግም ይሠራ ጥሩ በጅምላ ከማመስገን ይልቅ መኮነን እና ማጣጣል ሲቀናቸው አያለሁ::

በእኔ አስተሳሰብ ግን ሰዎች ባሉበት ሁኔታ ከመታዘባችንም በፊት የሚቃኑበትን መንገድ በመጠቆም የተሰጠው ጊዜ ሳያልፍ እና ሳንተዛዘብ የተሻለ ሥራ እንዲሠሩ ማድረግ ይቻላል:: እዬዬም ሲድላ ነው እንዲሉ አንዳንድ ሰዎች ግን ለራሳቸው ከሚሰጡት የተሳሳተ ግንዛቤ በሚመዘዝ አመክንዮ ካለ እነሱ አዋቂ ካለ እነሱ ሠራተኛ ካለ እነሱ ወሳኝ የለም ብለው ስለሚያምኑ ለወንበሩም ለሰውም ለፈጣሪውም አስተዛዛቢ ሆነው ይታያሉ:: ከላይ እንደጠቀስኩት ማህበረሰባዊ ሥነ ልቦናችን እና አወቃቀራችን በተለይ በተነሳው ጉዳይ ላይ ትንሽ ማስተካከያ ያስፈልገዋል የሚል እምነት አለኝ:: አንድ ግለሰብ ሕዝብን እንዲያገለግል አደራ ሲቀበል ተጠያቂነቱ ለሚያገለግለው ሕዝብ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ራሱን ማዘጋጀት፤ ለዚህ የሚሆን ዝግጁነት መፍጠር ይጠበቅበታል ባይ ነኝ::

ከዚህ አኳያ በአብዛኛው በታዳጊ ሀገራት እንደሚታየው ወንበር ትርጓሜው የተዛባ በመሆኑ ሥራውም ውጤቱም እንደ እሳቤው የተዛባ ነው:: ከላይ በቀረበው ማህበራዊ ስሪት እና ትርክት ያደገን ዜጋ ከተረቱ ለማሻገር ማገዶ መፍጀቱ ቢታወቅም በሥልጣኑ ከምንተዛዘብ የፈጀውን ማገዶ ይፍጅ ከሚሉት ጎን ብቆም ይሻለኛል:: በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚወጡ ሕጎች፣ አዋጆች፣ ፖሊሲዎች እና የተለያዩ ማሻሻያዎች የማህበረሰቡን ህልውና እና ቀጣይ እጣ ፋንታ የሚያሳልጡ በብዙ ወጪ እና ልፋት የሚዘጋጁ እንደሆነ ይታወቃል::

ነገር ግን እነዚህ የተደከመባቸው ረቂቆች ሕዝቡም በጉገት እየጠበቃቸው መንግሥትም የሚገባወን የማጽደቅ ሥራ ሰርቶባቸው አሻጋሪ በትር ወይም ፈፃሚ አካላት ከሀቅም ወይም ከቀናነት ወይም ደግሞ የተለየ አጀንዳ ከማራገብ አንፃር መሰናክል ሲሆኑ እታዘባለሁ:: እነዚህ አካላት ከሥራ ይልቅ በሴራ የተካኑ በመሆናቸው የሚያስጨንቃቸው የራሳቸው መውጫ መንገድ እንጂ የሥራቸው ውጤታማነት ባለመሆኑ ብዙ ጊዜ ተጠያቂ ሳይሆኑ አበላሽተው እና ዘርፈው ሲሾልኩ እናውቃለን:: ይሄ ከሁሉም የከፋ ምሳሌ በመሆን ትውልዱንም የሚበርዝ እጅግ ጥንቃቄ የሚፈልግ ጉዳይ ነው:: ይሄ ምልክትን የሚሻ ትውልድ ሲዘርፍ፣ ሲበድል፣ ሲያጎድል ያየውን ባለወንበር በነፃነት ሲፈነጭ ካየው በየትኛው አመክንዮ ይሄን ትውልድ አንተ መልካም እና ታማኝ አገልጋይ ሁን ብለን ልንቀርጸው እንችላለን…

ፍየል ወዲያ … የሚለው እሳቤ ብዙ ጊዜ ለባለወንበሮች የሚሠራ ይመስለኛል:: ፍፁም የማይመጥኑ ሕዝብ እና መንግሥትን ሆድ እና ጀርባ እንዲሆን የሚያደርጉ አሉ:: የአገልጋይነት ትርጉም ገብቷችሁ በተግባር ተገልጣችሁ ዋጋ እየከፈላችሁ ያላችሁ ባለወንበሮች ከምሥጋና ባለፈ ትውልዱን በሥራችሁ እየሰበካችሁ ለጠንካራ እና ሀቀኛ አሠራር እያዘጋጃችሁ ስለሆነ በመልካም ታዝቤያለሁ::

«ሰጥተህ´ ታዘበኝ…. የሚሉ እልፍ ችሎታዎች ያሉበት ቦታ ሆነው ሲያንፀባርቁ ውጤት እና መልካም ከባቢ ይፈጠራል:: ይህም ከፍ ሲል የተደሰተ እና ነገን በተስፋ የሚቀርጽ ትውልድ እና ማህበረሰብ እየተገነባ ሀገርም እያደገ ይመጣል:: «ሰጥተህ´ ታዘበኝ ብሎ በድፍረት ለመጠየቅ ግን ራስን መመርመር እና መገምገም ይጠይቃል:: ሲሾምም ሲወርድም ትችቱም ሆነ ምስጋናው ለራሱ ለግለሰቡ ነው እና::

በመቅደስ ታዬ (ፒ ኤች ዲ)

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You