እአአ 1960 በፊት የዓለም አትሌቲክስ ገጽታ አሁን ከምናውቀው የተለየ ነበረ:: በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች የሚካሄዱ ውድድሮች አፍሪካውያን አትሌቶች የድል ቦታ አልነበራቸውም። ተሳትፏቸውም እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም።
እኤአ የ1960ው ሮም ኦሊምፒክ ግን ይህን ታሪክ እስከወዲያኛው የቀየረ ክስተት ይዞ መጣ። ጀግናው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ የዓለም አትሌቲክስን ገፅታ የለወጠውን ታሪክ በሮም ኦሊምፒያድ የማራቶን የባዶ እግር ድል የማይፋቅ ዐሻራ አኖረ። ይህም የዓለማችን ጥቁር አትሌቶች ተወዳድረው ማሸነፍ እንደሚችሉ ያሳየና ተነሳሽነትን የፈጠረ ነበር። ከዚያ ጊዜ አንስቶ የአበበን ዱካ ተከትለው ጥቁር አትሌቶች በተለይም በረጅም ርቀትና በማራቶን ውድድሮች የበላይነቱን ተቆጣጥረው ዛሬም ድረስ ዘልቀዋል።
የአበበ ቢቂላ ዘመን አይሽሬ የአትሌቲክስ ጀብዶች በታሪክ ማህደር የተፃፉት በወቅቱ ስፖርቱን በብቃትና በእውቀት በሚመሩ ሰዎች አስተዋፅኦም ጭምር ነው። አትሌቲክስ ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ ኩራት እንዲሆን ልክ እንደ እንቁ አትሌቶቻችን ታሪክ የሚዘክራቸው ብዙ አርቆ አሳቢ የስፖርቱ አመራሮች የጣሉት መሠረት ትልቅ ነው። እነዚህ ጉምቱ የስፖርቱ አመራሮች ኢትዮጵያውያን ሮጠው ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ዘርፉን ከሀገር ተሻግሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ መምራትና ማስተዳደር እንደሚችሉ አስመስክረዋል። ለዚህም ይድነቃቸው ተሰማ እና ፍቅሩ ኪዳኔን የመሳሰሉ ታላላቅ ሰዎች ከአፍሪካ ተሻግረው እስከ ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ድረስ የነበራቸው ተፅዕኖና ተሰሚነት ህያው ምስክር ነው።
ስፖርት በባህሪው ከዘመን ጋር እየተራመደ የሚዘምን ነውና በዚያው ልክ አብሮ መራመድ የሚችል ወቅቱን የዋጀ አመራር ግድ ይላል። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም የስፖርት አይነቶች አልታደለችም። ዛሬም ድረስ የዓለም ከዋክብት አትሌቶች መፍለቂያ ብትሆንም ይህን ፀጋዋን በሚገባው ደረጃ የሚያስተዳድርና የሚመራ ሰው ከፊት ማምጣትና ይበልጥ ውጤታማ እንድትሆን ማድረግ አልተቻለም። ይህም ስፖርቱን እጅከወርች አስሮ አላራምድ ሲለው በየጊዜው እየታዘብን እንገኛለን።
ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ያላት ተጽእኖ ፈጣሪነት በአትሌቶቿ ድል ብቻ የተወሰ ነው ቢባል ትክክል ነው። እንኳን በዓለም አትሌቲክስ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ተፅዕኖ የሚፈጥር የሀገሩ ውስጥ የስፖርቱን ችግሮች ማስተካከል የሚችል ሰው አጥታለች። በእርግጥ ሰው አጥታ አይደለም፣ ትክክለኛውን ሰው ማን ከፊት ያምጣው ነው ጉዳዩ።
ሌላው ዓለም በቴክኖሎጂ ተራቆ ስፖርቱን ሳይንስ አድርጎታል። ትናንት በአትሌቲክስ የማይታወቁ ሀገራት ዛሬ ላይ ችግሮቻቸውን በሳይንስና ምርምር እየቀረፉ የእኛ የምንላቸውን ድሎች ወደ መሻማት ተሸጋግረዋል። እኛ ደግሞ አትሌቲክስን አንድ ብሎ እንደሚጀምር ዓለም አቀፍ ውድድር በደረሰ ቁጥር በአትሌቶች መምረጫ መስፈርት ውዝግብ ውስጥ እንዳክራለን። አሁንም መነሻችንን ዞር ብለን ከማየት ይልቅ በቆምንበት መቅረታችን ከሌላው ዓለም ምን ያህል ወደ ኋላ እየጎተተን እንደሚገኝ መረዳት ካልቻልን ከገባንበት አዙሪት ልንወጣ አንችልም::
በርካታ ሀገራት በተለይም ምዕራባውያኑ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በረጅም ርቀትና ማራቶን ውድድሮች የተወሰደባቸውን የበላይነት መልሰው ለማግኘት የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ባለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት ታዝበናል። በእኛው አስተዳደራዊ ስንክሳሮች የተማረሩና ቅር የተሰኙ ብርቅዬ አትሌቶችን አስኮብልለው ዜግነት በመስጠት ባንዲራቸውን በታላላቅ ዓለም አቀፍ መድረኮች ማውለብለብ ችለውበታል። የእኛን የአትሌቲክስ ስኬት ሚስጥር አጥንተውና ተመራምረው አትሌቶቻቸውን በእኛው የአየር ንብረት አሰልጥነው ጭምር ወደ ውጤት እየተመለሱ እንደሚገኙም የተደበቀ አይደለም። ለዚህም ኢትዮጵያና ኬንያ ለረጅም ዓመታት እየተፎካከሩ ውጤታማ የሆኑባቸውን ርቀቶች ባለፉት ዓመታት እያሸነፉ መገኘታቸው ማሳያ ነው።
ስኬታማ ባልሆኑባቸው የመም ረጅም ርቀት ውድድሮችን ቁጥር በመቀነስ ወይም በማጥፋት በኦሊምፒክ እና የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ብቻ እንዲወሰን የሚያደርጉትም ጥረት ይታወቃል። የአስርና አምስት ሺ ሜትር ውድድሮችን ከኦሊምፒክና ከዓለም ቻምፒዮና የመሰረዝ እንቅስቃሴ የጀመሩበትም ወቅት የሩቅ ታሪክ አይደለም።
የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ለመምራት ኃላፊነቱን የሚረከቡ ሰዎች በሀገር ውስጥ የሚታየውን አስተዳደራዊ ችግሮች የማራገፍ ብቻ ሳይሆን ከዚያ የገዘፈ ዓለም አቀፍ የቤት ሥራ የሚወጡ መሆን ይገባቸዋል። ለራሳቸው እንደሚመቻቸው አካሄዳቸውን የሚቀያይሩትን የዓለም አትሌቲክስ መሪዎችን በመሞገት መሰል ውሳኔዎችን የማስቀልበስ ተገዳዳሪ አቅም መፍጠር የሚችሉ መሆን አለባቸው።
በእርግጥ ይህ የቤት ሥራ የኢትዮጵያን አትሌቲክስ የሚመሩ ሰዎች ብቻ አይደለም። ኬንያና ዩጋንዳን ከመሳሰሉ በዓለም አትሌቲክስ ተፅዕኖ ያላቸው ሀገራት አትሌቲክስ መሪዎች ጋር መታገል አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ የዓለምን አትሌቲክስ ገፅታ በመቀየር ፈር ቀዳጅ እንደሆነችው ሁሉ በዚህም ጉዳይ ከፊት መሰለፍ ይጠበቅባታል። ይህ ካልሆነ ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ በእነዚህ ርቀቶች ስኬታማ የሆኑት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በትብብር አለመሥራታቸው እንዲሁም ማሳመንና ተጽእኖ መፍጠር የሚችል የአትሌቲክስ ባለሙያ አለማግኘታቸው ዋጋ እያስከፈላቸው መጓዙን ይቀጥላል።
ከስልሳና ሰባ ዓመታት በፊት እስከመኖሯም የተዘነጋችውን አህጉረ አፍሪካ በአትሌቲክስ ውጤት በማስመዝገብ ይቻላልን ያስተዋወቀችው ኢትዮጵያ መሆኗን ደግሞ ማስታወስ ተገቢ ነው። ወትሮውንም የስፖርቱ ፊት አውራሪ አብዮተኛ ናትና አሁንም የአትሌቲክሱን ዓለም የፖለቲካ ጎዳና በመጥረግ አርዓያነቷን ማስቀጠል ይጠበቅባታል:: ስለዚህም በዓለም አትሌቲክስ ተሰሚ ለመሆንና በስራ አስፈጻሚው አፍሪካን ወክሎ ወንበር ለማግኘት የሚችሉ ግለሰቦችን ማፍራት የግድ ይለናል::
ኢትዮጵያ የይድነቃቸው ተሰማ እና የፍቅሩ ኪዳኔ ሀገር መሆኗን ዛሬም የሚያስመሰክሩ በዕውቀትና በዲፕሎማሲ ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች የሏትም ለማለት አይቻልም:: ነገር ግን ከሀገር ውስጥ አንስቶ ወደ አመራርነት እንዲመጡና ሃሳባቸውንም እንዲያንጸባርቁ ለስፖርቱ ስብራትም መፍትሄዎችን እንዲያመነጩ በማድረግ ረገድ የሚታየውን ክፍተት መጠገን ላይ ነው ችግሩ።
ከዚህ ቀደም በአህጉር አቀፍና በቀጣናዊ የስፖርት ማህበራት ውስጥ በአባልነትና በኃላፊነት የመመረጥ ዕድልን ያገኙ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ አመራሮች አንዳችም አበርክቶ ሳይኖራቸው የሥራ ዘመናቸውን ጨርሰው ከስፖርቱ ይገለላሉ። ይህ ከዚህ በኋላ መደገም የለበትም።
በመሆኑም አዲሱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ያገኘውን ዕድል እንዲሁ ከማባከን ይልቅ ከሀገራዊ ሥራው ጎን ለጎን ኢትዮጵያ የሚገባትን እንድታገኝ ሩቅ ዓላሚ ሊሆን ይገባል:: አሁን ላይ እየተነሱ ያሉትን መሠረታዊ የአትሌቲክስ ችግሮች ዘመናዊ አካሄዶችን በመቀየስ፣ አደረጃጀትን በማስተካከል እንዲሁም ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር እጅና ጓንት ሆነው በመሥራት ሊቀርፉ ይችላሉ:: ጠንካራ ጽህፈት ቤት፣ የቴክኒክ ኮሚቴ፣ የራሳቸውን መብት የሚጠይቁና ለስፖርቱ እድገት የሚታትሩ የሙያ ማህበራትን በማደራጀትና የየራሳቸውን ድርሻ አውቀው እንዲሠሩ ማድረግምን ማስታወስ ተገቢ ይሆናል።
ከምንም በላይ ሕግን ማስከበርና ዘመኑን የዋጀ አስተዳደርን ሥራ ላይ ማዋል የኢትዮጵያን አትሌቲክስ መጻኢ እድል ለመወሰን ቁልፍ ጉዳይ ነው:: ራዕይ ያለውና የኢትዮጵያን አትሌቲክስ እንደጀግናው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ ከፍ አርገው ባስቀመጡት የክብር ማማ የማስቀመጥ ፍላጎት ያለው መሪ እይታው ዓለም አቀፋዊ ሊሆን ይገባል::
ሥራ አስፈጻሚው ከመመረጡ አስቀድሞ በነበረው የምረጡኝ ቅስቀሳ የተናገሯቸውና ያቀረቧቸው እቅዶች ወደመሬት ለማውረድ የሚጠበቅባቸው ቅንነት ብቻ ነው:: የኢትዮጵያውያን ክብር ምክንያትና መገለጫችን ለሆነው አትሌቲክስ ከመሥራት የሚቦዝን ባለሙያ ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም:: በተለያዩ ምክንያቶችና መልካም አስተዳደር ችግሮች ያኮረፉትም ቢሆኑ በሀገር ጉዳይ አይጨክኑምና በአንድነት ለተነሳ መሪ ተገዢ መሆናቸው አያጠራጥርም::
ስለዚህም የሀገር ውስጡን የአትሌቲክስ ችግር ለመፍታት ከመሥራት እኩል ዓለም አቀፋዊነትን ማሰብና በተገኘው አጋጣሚ መጠቀም ያስፈልጋል:: በዓለም ላይ ተጠቃሽ ከሆኑ ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ እንደመሆኗ በገነባችው ስም ልክ ተጠቃሚ እንድትሆን ለማድረግ ከባለሙያዎች ጋር በምክክር መሥራትም የግድ ነው:: በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመጥርና ለሌሎችም ምሳሌ ሊሆን የሚችል ፌዴሬሽን መገንባት የአዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዓላማ ሊሆንም ይገባል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 16 ቀን 2017 ዓ.ም