ኢትዮጵያ ቀደምት ከሚባሉ ሀገራት አንዷናት። ይቺ ሀገር በአፍሪካ ታላቅ እና ተስፋ ያላት ሀገር ነች። ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር የተሸከመች እና ፈጣን ኢኮኖሚ የምታንቀሳቅስም ነች፡፡ የኢትዮጵያ ሰላም መሆን ለቀጣናው ሰላም እና ብልጽግና ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ኢትዮጵያ ባላት ጂኦፖለቲካዊ አቀማመጥና በቀጣናው ባላት ከፍተኛ ተደማጭነት የተለያዩ ሀገራት ለወዳጅነት ይመርጧታል፡፡
ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት መንግሥታት ሲቀያየሩባት የነበረ ቢሆንም በዲፕሎማሲው ረገድ እስካሁን የተሳካላት ሆና ቆይታለች፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር ለ127 ዓመታት የቆየ ወዳጅነቷ ነው፡፡ የበለጠ ተጠናክሮ ለትውልድ እንዲሻገርም እየተሠራበት ይገኛል፡፡
የፈረንሳይ መንግሥት ለኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ቆይቷል፡፡ ከነዚህም ውስጥ በባቡር መሠረተ ልማት፤ በትምህርት፤ በጤና፣ እና በቅርስ ጥበቃ ያደረጋቸው ድጋፎች በአበይትነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ከቅርስ ጥበቃ ጋር ተያይዞ የኢዮቤልዩ ቤተመንግሥት ለማደስና አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ ለማድረግ ፈረንሳይ የአንበሳውን ድርሻ ወስዳለች፡፡ የተሠራው ሥራም የማደስ ብቻ ሳይሆን ቦታው ለጎብኚዎች ክፍት እንዲደረግ የሚያደርግም ነው። ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ ቅርሶች ድጋፍ ያደረገችው ለቤተ-መንግሥቱ ብቻ አልነበረም፡፡ የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና እዚያ አካባቢ ያሉ አጠቃላይ ሥራዎችን ለማደስ እና ወደሚገባው ደረጃ ለማምጣት የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፍ አድርጋለች፡፡
የፈረንሳይ መንግሥት ፕሬዚዳንት ከዚህ ቀደም እ.ኤ.አ በማርች 2019 ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር፡፡ በመጀመሪያው ጉብኝታቸው በጣም ትልልቅ ፕሮግራሞች ከኢትዮጵያ ጋር አብረው እንደሚሠሩ ቃል ገብተው ነበር። በዚያን ወቅት በተደረገው ስምምነት ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እድሳት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ቡድኖች ተመሥርተው ነበር። ይህ በዓለም የመጀመሪያ ልንለው የምንችል የተለየ የትብብር ፕሮግራም ነበር። የእድሳቱ ሥራ አሁን ላይ ሃምሳ ከመቶ ገደማ ላይ ይገኛል ፤ቀሪውን ሥራ በሚቀጥሉት ጊዜያት በማጠናቀቅ ወደ ሥራ እንዲገባ ከመግባባት ላይ ተደርሷል።
እንደሚታወቀው ፈረንሳውያን ለባህል እና ለቅርስ ትልቅ ቦታ የሚሰጡ ሕዝቦች ናቸው፡፡ በቅርቡ የእሳት አደጋ የደረሰበትን የኖተራንዳም ቤተክርስቲያናችንን እንደ አዲስ አድሰው ለሕዝብ ክፍት ማድረግ ችለዋል። ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትም የገንዘብ፣ የቴክኒክ እና የባለሙያዎች ድጋፍ አድርገዋል፡፡ በሥራው ትላልቅ ትውልደ ፈረንሳውያን አርክቴክቶች፤ የተለያዩ እውቀት ባለቤቶች ፣ የሙዚየም እድሳት ባለሙያዎችን ልከው በሥራው ላይ የአቅማቸውን ማበርከት ችለዋል፡፡
ከዚህ ውጪ በቅርቡ ኢትዮጵያ ያካሄደችው የኢኮኖሚ ሪፎርምም በፈረንሳይ እና በቻይና የሚደገፍ ፕሮግራም ነው። ይህ ፕሮግራም እንዲሳካ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በጣም ከፍተኛ ድጋፍ ለኢትዮጵያ እና ለሪፎርሙ አድርገዋል፡፡ ለዚህም ከፍተኛ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል። በአውሮፓ ህብረት እና በአይ ኤም ኤፍ መድረክም የፈረንሳይ ድጋፍ አይተኬ ነበር፡፡
ከዚህ ውጪ የፈረንሳይ መንግሥትና ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ ውስጥ ዋነኛ ኢንቨስተር በመሆን ሌሎች የአውሮፓ ሀገራትን በማስተባበር እንደምትሠራ ከመግባባት ላይ መደረሱ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፕሬዚዳንቱ ጋር በዝርዝር የተወያዩባቸውና የኢትዮጵያ የዘመናት እና የህልውና ጥያቄን ሊያስመልስ የሚችለው በሰላማዊ መንገድ የቀይ ባሕር ተጠቃሚ መሆን የሚለው ነጥብ ለትውልድና ለሀገር መሠረት ነው፡፡
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ 130 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ሀገር ናት፡፡ ኢኮኖሚዋ በፍጥነት እያደገ ያለበት ሁኔታ አለ፡፡ በዚህም ሀገሪቷ የባህር መውጪያ ያስፈልጋታል። በዓለም ሕግ ፣በሰላማዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንደ ፈረንሳይ ያሉ ወዳጅ ሀገራትን ተጠቅመን ይህንን ፍላጎታችንን ማሳካትም ይኖርብናል፡፡
ኢማኑኤል ማክሮን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ባደረጉት ውይይትም የባሕር በር መኖር አስፈላጊነት እና ይህንን ማመቻቸት ተገቢ ጥያቄ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል። ፈረንሳይም ባላት አቅም ማድረግ የምትችለውን ድጋፍ እንደምታደርግ፤ በምን መንገድ? ለሚለው በንግግር እና በውይይት ፤ዓለም አቀፍ ሕጎችን እና ጎረቤት ሀገራትን ባከበረ ፤ ለኢትዮጵያ እና ለክልሉ በሚጠቅም መልኩ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል። የኢትዮጵያም ጥያቄ እሳቸው እንደሚሉት በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ማግኘት ነውና በዚህ ዙሪያ ያሉንን ወዳጅ ሀገራት በየጊዜው እየጠራን ውይይት ማድረግና ዓላማውን ማስረዳት ተገቢ ነው፡፡
ከኢኮኖሚ ምጣኔ ሀብት ጋር በተያያዘ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በተነጋገሩት መሠረት እ.ኤ.አ በማርች 2019 በመጡ ጊዜ በሀገሪቱ ለተጀመረው ታላቅ የኢኮኖሚ ሪፎርም ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡ የተለያዩ የቴክኒክ ድጋፎችን አድርገዋል። በቀጣይም ሌሎች ድጋፎችን እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡ ከኤሌክትሪክ ኔትወርክ ጋር በተያያዘ የፈረንሳይ ድርጅቶች መግባት የሚችሉበት አጋጣሚ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል። ከእዳ ጋር በተያያዘም ከጂ 20 እና ከቻይናም ጋር የሚሠራ ሥራ ይኖራል።
በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የፈረንሳይ ድርጅቶች የበለጠ ተሳታፊ እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ስለመገኘቱም ተጠቅሷል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም ማስፈን ይቻል ዘንድ የፕሪቶሪያ ስምምነት ትልቅ ርምጃ ነው፡፡ ለዚህም ስምምነቱን ለማሳካት ከፈረንሳይ ጋር እየተሠራ ነው። ፈረንሳይም የስምምነቱ ተግባራዊነት እየደገፈች ትገኛለች፡፡
በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በውይይታቸው ወቅት እንደገለጹት እርሻን ማበረታታት፤ የተጎዱ ሆስፒታሎችን መልሶ መገንባት፤ ከዛም በተጨማሪ የሽግግር ፍትህ ተግባራዊ የሚሆንበትን እና የሕግ የበላይነት የሚከበርበትን ሁኔታ ለማረጋገጥ ድጋፍ እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርን በቱርክ ከሶማሊያው ፕሬዚዳንት የሰላም ንግግር ማድረጋቸውን እንደሚደግፉትም ገልጸዋል፡፡ ታዲያ ይህ አይነቱ ትብብርና ትስስር የብሄራዊ ጥቅምን የሚያረጋግጥ ነውና ከሌሎች ወዳጅ ሀገራትም ጋር በተመሳሳይ መንገድ ሊሠራ ይገባል መልዕክቴ ነው፡፡
መክሊተ-ወርቅ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 15 ቀን 2017 ዓ.ም