የፈረንሳይ መንግሥት ለቅርሶች እድሳት የሚያደርገው ድጋፍ ለታሪክ ያለውን ከበሬታ በተጨባጭ ያሳየ ነው!

ሀገራችን የተለያዩ ሃይማኖቶች እና ብሔር ፣ ብሔረሰቦች መኖሪያ ከመሆኗ ጋር በተያያዘ የብዙ ማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶች እና ቅርሶች ባለቤት ሆናለች። ካሳለፈችው የረጅም ዘመን ሀገረ መንግሥት ታሪክ አንጻርም በየዘመኑ የነበሩ ነገሥታት ጥለዋቸው የሄዷቸው ዐሻራዎች የየዘመኑ አስተሳሰብ እና የሥነ ጥበብ መገለጫ በመሆን ዘመናትን አሻግረው ማየት ያስቻሉ መስታወቶቻችን ናቸው።

እንደ ሀገር እኛ ኢትዮጵያውያን ዓለምን በብዙ መልኩ መገረም እና መደነቅ ውስጥ የሚከቱ፣ የብዙዎችን አፍ በእጅ ያስጫኑ ፣ ዛሬም ድረስ ለዓለም ድንቅ የሆኑ ቅርሶች ባለቤቶች ነን። የአክሱም ሀውልቶች ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ፣ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ቤተመንግሥቶች ፣ ገዳማት እና አድባራት ዘመን ተሻግረው ዛሬ ላይ ያሉ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ባህል እና ባህላዊ እሴቶች ከብዙ በጥቂቱ ተጠቃሾች ናቸው።

አብዛኞቹም በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ እውቅና አግኝተው ዓለም አቀፍ ጥበቃ የሚደረግላቸው ቢሆኑም፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት እነዚህን ሀብቶች ጠብቆ እና አልምቶ ሀገራዊ ተጠቃሚነትን ተጨባጭ ለማድረግ የተደረጉ ጥረቶች እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም። ከታሪክ እና ከማንነት ማድመቂያነት ባለፈ ዘመኑን በሚመጥን መንገድ አስበን እና አቅደን ተገቢውን ጥበቃ አላደረግንላቸውም።

ከዚህም የተነሳ አብዛኞቹ ቅርሶች ከእድሜ እና ከተለያዩ ሰው ሰራሽ ችግሮች ጋር በተያያዘ ለተለያዩ አደጋዎች ተጋልጠው ቆይተዋል። አንዳንዶቹም በሚታይ አደጋ ውስጥ ወድቀው ለህልውናቸው የዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ ድጋፍ ለመጠየቅ የተገደድንበት ሁኔታ መፈጠሩ የአደባባይ ምስጢር ነው።

እንደ ሀገር የመጣንበት መንገድ ለታሪክ እና ታሪክ ለሚፈጥሯቸው ትርክቶች በብዙ መልኩ ቅርብ ብንሆንም፤ ለታሪካዊ ትርክቶቻችን መሰረት ለሆኑት ቅርሶቻችን ተገቢውን ትኩረት መስጠት የሚያስችል የአስተሳሰብ መሠረት አልነበረንም። በዚህም የብሔራዊ ክብራችን መሠረት የሆኑ ቅርሶቻችን ለከፋ አደጋ ተጋልጠው እና ተመልካች አጥተው የብዙዎችን ልብ አድምተው ኖረዋል።

ይህን ሀገራዊ እውነታ ለመቀየር ባለፉት አምስት ዓመታት በመንግሥት በኩል ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል። ቅርሶቹን አውቆ በመጠበቅ እና በማልማት ላይ የተመሰረተ አዲስ አስተሳሰብ በመፍጠር እና በመገንባት ቅርሶቹ በሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖራቸውን ጠቀሜታ በተጨባጭ እንዲያበረክቱ ብዙ ርቀት መጓዝ ተችሏል። በተለይም በቅርሶች እድሳት ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት በሀገሪቱ በዘርፉ አዲስ እሳቤ ስለመምጣቱ ተጨባጭ ማሳያ ሆኗል።

በመንግሥት በራሱ አቅም ሊታደሱ የሚችሉትን ቅርሶች በማደስ፤ ከቅርስነት ባለፈ የተሻለ ኢኮኖሚ ማመንጨት የሚችሉበትን አስቻይ ሁኔታ ለመፍጠር እየሠራ ነው። ለዚህም አሁን ላይ በእድሳት ላይ የሚገኙ የጎንደር እና የአባ ጅፋር ቤተመንግሥት ፣የሶፉመር ዋሻን እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል።

ከመንግሥት አቅም በላይ የሆኑትን ዓለም አቀፍ የትብብር ድጋፎችን በማፈላለግ የእድሳት ሥራቸው እንዲከናወን እያደረገ ነው። ለዚህም በፈረንሳይ መንግሥት የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ እየተከናወኑ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና የኢዮቤልዩ ቤተመንግሥት እድሳት ተጠቃሽ ናቸው። ድጋፉ በሀገራቱ መካከል አዲስ የትብብር ምዕራፍ መክፈት ያስቻሉም ናቸው።

የፈረንሳይ መንግሥት ፣ በፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኩል፤ ቅርሶቹን ለማደስ እና ለማልማት እየተደረገ ያለው ድጋፍ የፈረንሳይ ሕዝብ ለቅርስ በተለይ ደግሞ ለኢትዮጵያውን ትናንቶች ያለውን ከፍ ያለ ከበሬታ በተጨባጭ ያሳየ ነው። በመላው ኢትዮጵያውያን እውቅና የተቸረው አዲስ የትብብር ምዕራፍ ጅማሬም ነው!

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You