– ክትባቱ ከታህሳስ 21 ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ይሰጣል
አዲስ አበባ፦ የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ከዘጠኝ እስከ 14 ዓመት ከ 177 ሺህ በላይ ለሆኑ ታዳጊ ሴት ልጆች በትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማት እና በጊዜያዊ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች እንደሚሰጥ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ እንዳስታወቁት፤ ክትባቱ በዘመቻ ከታህሳስ 21 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ይሰጣል ፤ በክትባት ዘመቻውም 177 ሺህ 933 ለሆኑ ታዳጊ ሴት ልጆች ክትባቱን እንዲወስዱ ይደረጋል።
የክትባት ግብዓቶች በየክፍለ ከተማውና ጤና ጣቢያዎች በበቂ መጠን መድረሳቸውን የጠቆሙት ኃላፊው፤ 381 የክትባት ቡድኖችን በማዋቀርና የሚመለከታቸው ሁሉ በትምህርት ቤቶችና ከትምህርት ቤት ውጭ የሚገኙ ሴት ልጆችን ተደራሽ ለማድረግ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልፀዋል።
ክትባቱ አንድ ጊዜ ከተወሰደ በቂ እንደሆነ እና ድጋሚ መከተብ እንደማያስፈልግ ገልፀው፤ የኤች አይ ቪ ቫይረስ ተጠቂዎች ግን ክትባቱን ከወሰዱ ከስድስት ወር በኋላ ድጋሚ ሊሰጣቸው እንደሚችል ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ በዓመት ሰባት ሺህ ሴቶች የበሽታው ተጠቂ መሆናቸውን፤ ከዚህ ውስጥ አምስት ሺህ የሚሆኑት እንደሚሞቱ ያመለከቱት ሃላፊው ፤ በሽታው በኢትዮጵያ ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በገዳይነቱ በ2ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በሽታው በዋናነት የሚከሰተው በግብረ ስጋ ግንኙነት በሚተላለፍ ቫይረስ መሆኑንጠቁመው ፣ ከ15 ዓመት በላይ ከሆኑ ሴቶች ከአምስቱ ፣ አራቱ ለቫይረሱ ተጋላጭ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ክትባቱ በሁሉም 737 ትምህርት ቤቶች ስለሚካሄድ የትምህርት ዘርፉ አመራሮች፤ መምህራን፤ ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች፤ የሚዲያ ተቋማት እና ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የክትባት ዘመቻ የሚካሄደው ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን እንደሚሆን ገልጸው፣ አብዛኞቹ ከዘጠኝ እስከ 14 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴት እህቶች በትምህርት ቤቶች ይገኛሉ፣ ይህንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በተሻለ መልኩ ተማሪዎች ጤናቸው እንዲጠበቅ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ክትባቱ በትምህርት ቤት የሚሰጥበት ዓላማም ጤናቸው የተጠበቀ ተተኪ ትውልድ ለማፍራት እንደሆነም የቢሮው ኃላፊ ተናግረዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 17 ቀን 2017 ዓ.ም