የዋልያዎቹን የቻን ተሳትፎ የሚወስነው ፍልሚያ

በሀገር ውስጥ ሊጎች በሚሳተፉ ተጫዋቾች ብቻ የሚካሄደው የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) ከሁለት ወራት በኋላ በምስራቅ አፍሪካውያኑ ሀገራት አዘጋጅነት ይካሄዳል። ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ እና ኬንያ በጥምረት ለ8ኛ ጊዜ በሚያደርጉት በዚህ ውድድር ላይም 19 ሀገራት ተሳታፊ ናቸው። ከእነዚህ ሀገራት መካከል ለመሆንም ሀገራት የማጣሪያ ጨዋታዎቻቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ።

በማጣያው ተሳታፊ ከሆኑት ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ዛሬ ከሱዳን አቻቸው ጋር ወሳኙን የመልስ ጨዋታቸው ያከናውናሉ። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሱዳን አቻው ጋር የሚያደርገው ጨዋታ በሊቢያ ቤንጋዚ መካሄዱ የሚታወስ ነው። ሁለቱ ጎረቤት ሀገራት በተገናኙበት ጨዋታም የሱዳን ብሄራዊ ቡድን ሁለት ለምንም በሆነ ውጤት የኢትዮጵያ አቻውን ማሸነፉ የሚታወቅ ነው። ሱዳኖች ከፍተኛ የማለፍ ተስፋ ይዘው በወጡበት ጨዋታም ያሲር ሞዛሚል እና ሙሳ ካንቲ በ7ኛው እና በጭማሪ ሰዓት ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ኢትዮጵያ የምትገኝበት የመካከለኛው ምስራቅ ዞን 10 ሀገራት በማጣሪያው ይሳተፋሉ ተብሎ ቢጠበቅም ኤርትራ እና ሶማሊያ ተሳታፊነታቸውን በመሰረዛቸው ምክንያት ተጋጣሚዎቻቸው ብሩንዲ እና ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር ሊቀላቀሉ ችለዋል። በመጀመሪያው ዙር ከታንዛኒያ ጋር የደረሰው የሱዳን ብሄራዊ ቡድን በበኩሉ በደርሶ መልስ ጨዋታ አንድ እኩል በመለያየቱ በፔናሊቲ 6ለ5 በሆነ ጠባብ ውጤት ነበር ሁለተኛውንና የመጨረሻውን የማጣሪያ ዙር ሊቀላቀል የቻለው።

ሁለቱም የደርሶ መልስ ጨዋታ በገለልተኛ ሜዳ በሊቢያ ቤንጋዚ የሚካሄድ ሲሆን፣ በመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ባለሜዳ እንደመሆና በዝግ ስቴድየም ማድረጓ የሚታወስ ነው። በዛሬው ጨዋም በዚያው በቤኒና ማርቲየርስ ስታዲየም የሚደረግ ይሆናል። የዋልያዎቹ ጊዜያዊ ዋና አሠልጣኝ መሳይ ተፈሪ ተደጋግሞ የሚነሳውን የዋልያዎቹ የአጥቂ መስመር ተጫዋቾች ችግር ለመቅረፍ በዝግጅት ወቅት መሥራታቸውን ቢገልጹም በመጀመሪያው ጨዋታ የታየው ግን በተቃራኒ ነበር። ዛሬ በሚኖረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሶስትና ከዚያ በላይ ግቦችን በተጋጣሚው ላይ በማስቆጠር ውጤቱን መቀልበስ ካልቻለ የቻን ተሳትፎ ያከትማል።

ኢትዮጵያ ሱዳንን የምትገጥመው በመድረኩ ለአራተኛ ጊዜ ለመሳተፍ መሆኑ ይታወቃል። በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ስር የሚገኙ ስድስት ዞኖች የማጣሪያ ውድድራቸውን እያደረጉ ያሉ ሲሆን፤ ከታህሳስ 11-13/2017ዓ/ም እንዲሁም ከታህሳስ 18-20/2017 ዓ/ም ጨዋታዎቻቸውን ያከናውናሉ። ከየዞኑም ሶስት ሶስት ሀገራት የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫን (ቻን) የሚቀላቀሉ ሲሆን፤ በመካከለኛው ምስራቅ አፍሪካ ዞን የውድድሩ አዘጋጅ የሆኑት ሶስቱ ሀገራት (ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ እና ኬንያ) በቀጥታ ማለፋቸውን ተከትሎ በማጣሪያው አንድ ሀገር ብቻ ለማለፍ ፍልሚያውን ያደርጋል።

ኢትዮጵያ በመጀመርያው የመድረኩ ተሳትፎ የምድብ ማጣርያ ሶስት ጨዋታዎችን አድርጋ ያለምንም ነጥብ በአራት የጎል እዳዎች ነበር የተሰናበተችው። በ2016 ርዋንዳ አስተናጋጅ በነበረችበት ውድድር ዴሞክራቲክ ኮንጎ ለሁለተኛ ጊዜ ቻምፒዮን ስትሆን፣ የኢትዮጵያ ተሳትፎ በአንድ ነጥብ ከምድቧ በመሰናበት ነበር ያጠናቀቀችው።

ከሁለት ዓመት በፊት በአልጄሪያ በተስተናገደው የቻን ውድድር ሶስተኛ ተሳትፎዋን ያደረገችው ኢትዮጵያ በተመሳሳይ አንድ ነጥብ ይዛ ከምድቡ ተሰናብታለች። ከምድብ ማጣሪያ ያልዘለለው የኢትዮጵያ የመድረኩ ተሳትፎ፣ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ ለመሳተፍ በሚደረገው የማጣርያ ጨዋታ ከዞኑ ጠንካራ ሀገራት መካከል አንዷ በሆነችውና ለቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ማለፋን ባረጋገጠችው ሱዳን ይፈተናል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You