ትራምፕ ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት ለመውጣት እቅድ እያዘጋጁ እንደሆነ ተገለጸ

የተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሽግግር ቡድን አባላት አሜሪካን ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት ለማስወጣት እቅድ እያዘጋጁ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በመጀመርያ ቀን የሥልጣን ቆይታቸው ከሚያስተላልፏቸው ቁልፍ የፖሊሲ ውሳኔዎች መካከል ከድርጅቱ አባልነት መውጣት አንዱ ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግዙፉ የጤና ኤጄንሲ ወረርሽኞችን እና ሌሎች ዓለምአቀፋዊ የጤና ቀውሶችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ዋሽንግተንን በማግለል ተወቅሷል፡፡ በተጨማሪም በመሰል ዓለም አቀፋዊ የጤና ጉዳዮች ከአሜሪካ ይልቅ ወደ ቻይና አድልቷል በሚልም በትራምፕ የሽግግር ቡድን ውንጀላ ቀርቦበታል፡፡

በመጀመርያ የሥልጣን ዘመናቸው ትራምፕ ከድርጅቱ አባልነት ለመውጣት ለአንድ አመት ያህል በሂደት ውስጥ ከዘለቁ በኋላ በአዲሱ የጆ ባይደን አስተዳደር ውሳኔው መሻሩ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመከሰቱ ድርጅቱ ቻይናን ተጠያቂ ለማድረግ ወደ ኋላ ብሏል። “ድርጅቱ የቻይና አሻንጉሊት ነው” በሚል በትራምፕ ተደጋጋሚ ወቀሳ ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡

ከሳምንታት በፊት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሀኖም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ትራምፕ ከድርጅቱ አባልነት ለመውጣት ባሰሙት ዛቻ ዙርያ ተጠይቀው፤ አሜሪካ በአስተዳደር ሽግግር ውስጥ ስለምትገኝ ጊዜ ያስፈልጋታል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ዳይሬክተሩ “የትራምፕ አስተዳደር በድርጅቱ አሠራር ዙሪያ በሚያነሳቸው ቅሬታዎች ላይ ተቀምጦ ለመነጋገር እድል ይሠጠናል ብለን እናምናለን” ብለዋል፡፡ የተለያዩ የጤና ባለሙያዎች የአሜሪካ መውጣት የድርጅቱን አቅም እንደሚያዳክመው ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን የዓለም ጤና ድርጅት የአሜሪካን ክፍተት ለመሙላት በክትባት እና በዓለም አቀፍ የወረርሽኝ ቁጥጥር ጉዳዮች ዙርያ ወደ ቻይና የሚያዘነብል ከሆነ በጤናው ጉዳይ የዋሽንግተንን ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ሊጎዳው እንደሚችል መግለጻቸውን አል ዐይን ዘግቧል፡፡

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You