እስራኤል የሐማሱ መሪ ኢስማኢል ሀኒዬን መግደሏን አመነች

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር የሐማስ የፖለቲካ ክንፍ መሪ ኢስማኢል ሀኒዬ ባለፈው ሐምሌ ቴህራን ውስጥ በእስራኤል መገደላቸውን አመኑ። ሚኒስትሩ እስራኤል ካትዝ በኢራን የሚደገፉ የሁቲ መሪዎችን ዒላማ እንደሚያደርጉ በሰጡት መግለጫ ወቅት ነው ይህን ያሉት። ሀኒዬ በኢራን መዲና ቴህራን በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ሳሉ ነው የተገደሉት። እስራኤል ግድያውን መፈፀሟን ባታምንም ብዙዎች ግን ከጥቃቱ ጀርባ እጇ አለበት ሲሉ ቆይተዋል።

የሁቲ አማፂያን እስራኤል ላይ የድሮን እና የሚሳዔል ጥቃት እያደረሱ ይገኛሉ። እስራኤል የሁቲ አማፂያን ላይ “ከፍተኛ ርምጃ” ትወስዳለች፤ የቡድኑ መሪዎችን ጭንቅላት “ትቀላለች” ሲሉ ካትዝ ተናግረዋል።”ልክ ሀኒዬን እንዳደረግነው፣ [ያህያ] ሲንዋርን፣ እና [ሐሰን] ናስራላሕን በቴህራን፣ ጋዛ እና ሊባኖስ እንዳደረግነው በተመሳሳይ በሆዴይዳ እና ሰንዓ እናደርጋለን” ብለዋል።

የ62 ዓመቱ ሀኒዬ በሐማስ እንቅስቃሴ ትልቅ ቦታ ያላቸውን በጋዛ ሰርጥ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ብዙ የጣሩ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል። ሀኒዬ ከተገደሉ በኋላ ሐማስ ያህያ ሲንዋርን በጋዛ የቡድኑ መሪ አድርጎ መረጠ። ሲንዋር ሐማስ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7/2023 እስራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃት ካቀነባበሩ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው።

ሲንዋር ባለፈው ጥቅምት 2024 እስራኤል ጋዛ ላይ ባደረሰችው ጥቃት መገደሉ ይታወሳል። ቡድኑ እስካሁን አዲስ መሪ አልመረጠም። በኢራን የሚደገፈው የሊባኖሱ ቡድን ሄዝቦላህ መሪ የሆኑት ሐሰን ናስራላሕ ባለፈው መስከረም ነው ቤይሩት ውስጥ የተገደሉት።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት እስራኤል በጋዛ የከፈተችውን ጦርነት ተከትሎ የየመን ሁቲዎች በቀይ ባሕር የሚመላለሱ የእስራኤል እና ሌሎች ዓለም አቀፍ መርከቦችን ማጥቃት ጀመሩ። ሰሜን-ምዕራብ የመንን የሚቆጣጠሩት የሁቲ አማፂያን እስራኤል በጋዛ ያለውን ጦርነት እስካላቆመች ድረስ ጥቃታቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

ባለፈው ቅዳሜ የየመን አማፂያን የተኮሱት ሚሳኤል በእስራኤል መዲና ቴል-አቪቭ የሚገኝ አንድ ፓርክ ላይ ወድቋል። የሁቲ ቃል-አቀባይ በበኩላቸው በሀይፐርሶኒክ ባለስቲክ ሚሳኤል ወታደራዊ ዒላማ መምታቸውን አስታውቀዋል።

በተያያዘ ዜና በጋዛ የተኩስ አቁም ለማድረግ የሚደረገው ውይይይት ቀና መንገድ እንደያዘ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ተናግረዋል። ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስምምነቱ መች ሊደረስ ይችላል የሚለውን ከመናገር ተቆጥበዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You