«የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዶሎ ከተማ ለተፈጠረው ክስተት የኢትዮጵያን ኃይሎች ተጠያቂ ማድረጉ መሠረተ ቢስ ክስ ነው´ – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፡- የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዶሎ ከተማ ለተፈጠረው ክስተት የኢትዮጵያን ኃይሎች ተጠያቂ ማድረጉ መሠረተ ቢስ ክስ ነው ሲል የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ እንዳለው፤ ኢትዮጵያ የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ታህሳስ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አዝናለች። የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዶሎ ከተማ ለተፈጠረው ክስተት የኢትዮጵያን ኃይሎች ተጠያቂ ማድረጉ መሠረተ ቢስ ክስ ነው ብሏል ።

እንደ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ፥ ክስተቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረውን ሰላም ለማደፍረስ በሚሹ አካላት የተጠነሰሰ ነው። እነዚህ ሶስተኛ ወገኖች የአፍሪካ ቀንድን የማተራመስ ዓላማ ያላቸውና በየጊዜው የቀጣናውን ሰላም ለማወክ የሚሠሩ ልማደኞች ናቸው ብሏል መግለጫው።

እነዚህ ኃይሎች በአንካራው ስምምነት የተንፀባረቀውን የሁለቱን ሀገራት የሰላም ቁርጠኝነት እንዲገዳደሩት ሊፈቀድላቸው አይገባም ብሏል።

ተመሳሳይ ክስተቶች እንዳይፈጠሩ ለመከላከል የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚመለከታቸው የሶማሊያ መንግሥት ተቋማት ጋር በትብብር መሥራቱን ይቀጥላል ሲል ገልጿል።

በአንካራው ስምምነት መንፈስ በሁለቱ እህትማማች ሀገራት መካከል የቆየውን ወዳጅነት ለማደስና ለማጠናከር ለሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ ትልቅ ግምት ትሰጣለች ብሏል የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው።

የሀገራቱ መሪዎች የሁለትዮሽ አጋርነትን ብሎም ቀጣናዊ ትብብርን ለማጠናከር የወሰዱት ቁርጠኝነት የተመላበት ርምጃም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያለው።

በተያያዘ ዜናም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከሶማሊያ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር አብዱላሂ መሐመድ አሊ ጋር በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል ስላለው ግንኙነትና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አድርገዋል።

ሁለቱ ሀገራት ከአንካራው ስምምነት በኋላ ያሉ አደናቃፊዎችን ለመታገልና ወደ ፊት ለመጓዝ ቁርጠኛ መሆናቸውን በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You