የመረጃ ሥርዓቱ የሥራ እድል፤ ፍላጎት እና አቅርቦትን ማጣጣም የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት አካል የሆነው ብሔራዊ የሥራ መረጃ ሥርዓት የሥራ ዕድል ፍላጎትንና አቅርቦትን ማጣጣም የሚያስችል መሆኑን በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አለቃ ገለፁ።

አቶ ብርሃኑ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት ፤ብሔራዊ የሥራ መረጃ ሥርዓቱ በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር የትኛው የሥራ ዘርፍ ተፈላጊ ነው የሚለውን በመለየት የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ ወዴት መሆን እንዳለበት የሚጠቁም ነው።

ብሔራዊ የሥራ መረጃ ብሔራዊ የሥራ መገበያያ ቦታ መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊው፤ ሥርዓቱ የትኛው የሥራ መስክ ላይ ተፈላጊ ነው ፤ ሥልጠናዎቻችንስ በምን ላይ ያተኩሩ ፣ የሚለውን ለመለየት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

ሥርዓቱ በሰው ሠራሽ አስተውሎ ተደግፎ ፤ የወራትን ጨምሮ ከዓመታት በኋላ የሚኖረውን ፍላጎት መገመት እንደሚችል አመልክተው ፤ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሀገር ያሉ የሥራ ዕድሎች ላይ ምን ያህል ሰው ፤ በምን ዘርፍ እንደሚፈለግ በመለየት ፖሊሲዎች እንዲስተካከሉ እንደሚረዳም ገልፀዋል።

በተለይም የሰው ሀብት ልማት ላይ የሚሠሩ ተቋማትን መስመር የማስያዝ ጠቀሜታ እንዳለው የገለፁት ኃላፊው፤ ውጤታማ የአቅርቦትና የፍላጎት መጣጣም እንዲኖር የተዘረጋ ሥርዓት መሆኑን አስረድተዋል። ሥርዓት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ክፍት ነው ፤ ኢትዮጵያዊ ሆኖ እድሜው ከ 15 እስከ 64 አመት የሆነ ሁሉ ሊጠቀምበት እንደሚችል አስታውቀዋል።

ሥርዓቱ ከ15 ዓመት ዕድሜ የተነሳበት ምክንያትም በዚህ የዕድሜ ክልል ያሉ ተማሪዎች ያሉበት የትምህርት ደረጃ ላይ ሆነው በምን ሙያ ብማር እና ብመረቅ የሥራ ዕድል አገኛለሁ የሚለውን እንዲያስተካክሉ ይረዳቸዋል በሚል እንደሆነ አመልክተዋል። ተመርቀው ወደ ሥራ ገበያው ለተቀላቀሉ ሥራ ፈላጊዎች ደግሞ ሶስት የሥራ ገበያ አማራጮች አሏቸው ብለዋል።

አንደኛው የሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል ነው ያሉት ኃላፊው፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት የወጡትን ጨምሮ በየቀኑ የሚወጡትን የሥራ ማስታወቂያዎች በዚህ ሥርዓት ማየት እንደሚቻል የጠቆሙት ሃላፊው ፤ ሁለተኛው የውጪ ሀገር የሥራ ስምሪት መሆኑን ገልጸዋል።

በውጪ ሀገር ያሉ ድርጅቶች የሚያስፈልገውን ሂደት ሁሉ ጨርሰው ሠራተኛውን የሚወስዱበት መንገድ ነው። በዚህ የሥራ አማራጭ ከሶስት ሚሊዮን በላይ የሥራ ዕድሎች አምጥተናል ፤ በዚህ ዓመት ብቻ ከመቶ ስልሳ አምስት ሺህ በላይ ዜጎች በእድሉ ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል።

ሶስተኛው የሥራ አማራጭ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው ኢንተርኔት በመጠቀም ለውጪ ድርጅቶች የሚሠራበት ዕድል እንደሆነ ገልጸው ፤ በዚህ ሥርዓት ተጠቃሚ የሆነ ሰው በትንሹ ሁለት ሺህ አርባ ስምንት ዶላር ይከፈለዋል። በዚህ የሥራ አማራጭ ሰማንያ ስድስት ሺህ ሥራዎች አምጥተናል ፤ ወደ ሰላሳ አምስት ሺህ የሚጠጉ ዜጎች የእድሉ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ብሔራዊ የሥራ መረጃ ሥርዓት የኢትዮጵያ ሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ውስጥ ካሉ ሃያ ሶስት አገልግሎቶች አንዱ መሆኑን አስታውሰው፤ የሥራ ማስታወቂያዎችን በሙሉ ወደ አንድ ቋት የሚሰበስብ ብሔራዊ የሥራ መገበያያ መሆኑን ገልፀዋል። አስካሁን በነበረው ሁኔታ ሥራ ፈላጊዎች ሥራ አግኝተው እስከሚቀጠሩ ድረስ ያለው ምህዳር ምቹ እንዳልነበር አመልክተዋል።

ሂደቱን በማዘመንና ዲጂታላይዝ በማድረግ ከሃያ በላይ ድረገፆች ወደ አንድ ማዕከል እንዲመጡ አድርገናል። ባለፉት ሁለት ዓመታትም በሀገር ውስጥ ብቻ ወደ አራት መቶ ሃምሳ ሺህ የሥራ ማስታወቂያዎች በሥርዓቱ መካተታቸውን አስታውሰዋል። በዚህ ሥርዓት የተመዘገበ፣ አሻራ የሰጠ፣ የሠራተኛ መለያ ቁጥር ያለው ሁሉ የሥርዓቱ ባለቤት በመሆኑ መረጃውን እንደፍላጎቱ መጠቀም እንደሚችል አብራርተዋል።

አገልግሎቱን በተለያዩ ቋንቋዎች በ17 የማህበረሰብ ሬዲዮኖች፣ በመገናኛ ብዙሃንና በማህበራዊ ሚዲያዎች ዜጎች መረጃው እንዲኖራቸውና እንዲጠቀሙ ለማድረግ መሞከሩን ፤ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ከሁለት ሚሊዮን ሰዎች በላይ ወደዚህ ሥርዓት መምጣታቸውን ገልፀዋል።

አብዛኞቹ የሥርዓቱ ተጠቃሚዎች የውጪ ሀገራት የሥራ ስምሪት ፈላጊዎች እንደነበሩ የጠቆሙት ኃላፊው፤ ሥርዓቱ ለሀገር ውስጥ ሥራ ፈላጊዎች ሁኔታዎችን እጅግ በጣም የሚያቀል አማራጮች እንዳሉት አስታውቀዋል።

ሃላፊው ፤ ዜጎች በዚህ ሥርዓት ተመዝግበው፣ ዐሻራ ሰጥተውና መለያ ቁጥር አውጥተው እያንዳንዱን አገልግሎቶች ምን ፋይዳ እንዳላቸው በመለየት ለሚፈልጉት ዓላማ እንዲጠቀሙበት ጥሪያቸውንም አስተላልፈዋል።

ነፃነት አለሙ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You