– የአረንጓዴ ዐሻራ እና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ሊቋቋም ነው
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ 54 ሚሊዮን ሄክታር የሚገመት የተጎሳቆለ መሬት እንዳለ ጥናቶች ማመላከታቸውን ተገለጸ። የአረንጓዴ ዐሻራ እና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ሊቋቋም መሆኑም ተጠቁሟል።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 12ኛ መደበኛ ስብሰባው የአረንጓዴ ዐሻራ እና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ትናንት በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
በምክር ቤቱ የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ የረቂቅ አዋጁን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ሲያቀርቡ እንዳሉት፤ በሀገሪቱ ውስጥ 54 ሚሊዮን ሄክታር የሚገመት የተጎሳቆለ መሬት እንዳለ ጥናቶች አመላክተዋል። ከዚህ ውስጥ 11 ሚሊዮን ሄክታር መሬቱ በፍጥነት እንዲያገግም ካልተደረገ በዘላቂነት ለጉዳት የሚዳረግ ይሆናል።
አዋጁ የሀገሪቱን የተጎሳቆለ መሬት እንዲያገግም፣ የደን ሽፋንን በማሳደግ ምርታማነት እንዲጨምር በማድረግ በኩል ጉልህ ሚና እንደሚያበረክት ጠቅሰው፤ እየተገበረ ያለውን የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ በወጥነት እና በልዩ ፈንድ ተደግፎ መተግበሩ ሪፎርሙን ትርጉም ባለው መንገድ ለማስቀጠል ያስችላል ብለዋል።
የሀገሪቱ የተጎሳቆለ መሬት እንዲያገግም እና የተሻለ የደን ሽፋን እንዲኖራት በማድረግ በደን ልማቱ በሚገኘው ዘርፈ ብዙ ተግባራት ለኢኮኖሚው አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።
የተራቆተ መሬትን ተቋማዊ በሆነ መንገድ እንዲመለስ መሥራት ይገባል ያሉት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፤ ከሀገሪቱ የፌዴራል በጀት ከዜሮ ነጥብ አምስት እስከ አንድ በመቶ ለአረንጓዴ ዐሻራና የተጎሳቆለ መሬት መልሶ እንዲያገግም ለሚሠራው ሥራ ይመደባል ብለዋል።
አዋጁ ለአረንጓዴ ዐሻራ ሥራዎች ቋሚና ተቋማዊ ሥርዓት ያለው የፋይናንስ አቅም እንዲኖር ማስቻል አስፈላጊ ሆኖ የተዘጋጀ መሆኑን አስታውሰው፤ በዘላቂነት የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም እና ከአየር ንብረት ብክለት የፀዳ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተያዘውን ሀገራዊ ራዕይ እንዲሳካ አስተዋፅኦ ያደርጋል ነው ያሉት።
በተጨማሪም የተቀናጀ ቋሚና ዘላቂነት ያለው የሀገር ውስጥ የፋይናንስ ምንጭ በመመደብና በማሰባሰብ ሁሉም ክልሎች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሠራር መቀየስ ተገቢ እንደሆነ ገልጸው፤ ለዚህም የአረንጓዴ ዐሻራ እና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል።
በሀገራችን የተጎሳቆሉ አካባቢዎችን በደን ልማት እና በጥምር ደን ግብርና መልሰው እንዲያገግሙ ማድረግ ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ-ምህዳራዊ ጠቀሜታ እንዲያድግ ያግዛል ያሉት ሰብሳቢው፤ በአረንጓዴ ዐሻራ የተተከሉና ወደፊት የሚተከሉ ችግኞች ቀጣይነት ባለው መልኩ፣ በቋሚነት እና በተቀናጀ አግባብ የፌዴራል መንግሥት የበጀት ድጋፍ የሚያደርግበት እንደሆነ ጠቁመዋል።
ሀገሪቱ በደን ዘርፍ ከልማት አጋሮችና ከሌሎች ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ሰጪ ምንጮች እና ከካርበን ግብይት ሥርዓቶች የምታገኘውን ድጋፍና ጥቅም ለማሳደግ እንደሚያስችልም ተመላክቷል።
ምክር ቤቱ በቋሚ ኮሚቴው በቀረበው ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ላይ ከተወያየ በኋላ የአረንጓዴ ዐሻራና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1361/ 17 በመሆን በሙሉ ድምጽ ጸድቋል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 16 ቀን 2017 ዓ.ም