ታታሪዎቹ የምዕራብ አባያ አርሶ አደሮች

ዜና ሐተታ

በደቡብ ኢትዮጵያ ጋሞ ጎፋ ዞን ምዕራብ አባያ ወረዳ የቆላ ሙላቶ ቀበሌ ነዋሪው አርሶአደር ዳዊት ገሳ እንደወትሮ ሁሉ ማልደው ተነስተዋል። ከዓመታት ልፋት በኋላ ተፈጥሯዊ ልምላሜው በተመለሰለት ሃደቼ ተፋስስ ተራራ ላይ ከሚገኘው የማህበራቸው የንብ መንደርም ሲደርሱ ማንም አልቀደማቸውም። ነጩን ጋዋናቸውን ከራስ ቅላቸው እስከ እግራቸው ድረስ ተላብሰውና ቦት ጫማቸውን ተጫምተው የማነብ ሥራቸውን ጀምረዋል።

ብዙም ሳይቆይ ሌሎችም የማህበሩ አባላት የሊቀመንበራቸውን እግር ተከትለው ከንብ መንደሩ ተሰይመዋል። የተለመደውን አካባቢውን የማፅዳትና የመንከባከብ ሥራቸውን በጋራ አከናወኑ። በኋላም ለቆረጣ የደረሰውን ማር በተሻለ ጥራትና ዋጋ ለገበያ በሚያቀርቡበት፤ የገቢ አቅማቸውን በሚያሳድጉበት ሁኔታ ላይ በአርሶ አደር ዳዊት መሪነት ምክክር ያካሂዳሉ።

አርሶ አደር ዳዊት እንደሚሉት፤ የሃደቼ ተፋሰስ እንዲህ እንደዛሬው ውብና ማራኪ ከመሆኑ በፊት ደኑ በመናመኑና በመራቆቱ ምክንያት ብሎም የአባያ ወንዝ ሙላት እያደገ በመምጣቱ አብዛኛው የቀበሌዋ ነዋሪዎች የጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ነበሩ። እርሳቸውን ጨምሮ የበርካታ አርሶአደሮች ማሳ በተደጋጋሚ በጎርፍ በመጥለቅለቁ የመንግሥትና የሌሎችንም እጅ ለመጠበቅ ተገደው ቆይተዋል። ትንሽ የማይባለው አርሶአደር የቤተሰቡን የእለት ጉርስ መሸፈን ስለተሳነውም የልማታዊ ሴፍትኔት ተጠቃሚ እንዲሆን ተደርጓል።

በአባያ ሃይቅ ላይ ዓሳ በማስገርና አነስተኛ ግብርና ሥራ ላይ ይተዳደሩ እንደነበር የሚያነሱት አርሶ አደሩ፤ አካባቢው ዝናብ አጠርና ጎርፍ በተደጋጋሚ የሚያጋጥም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በቂ ምርት ማምረት ከባድ ፈተና እንደሆነባቸው ያስታውሳሉ። የነበሯቸው ከብቶች ሁሉ በአደጋው በማለቃቸው ለከፋ ችግር በማጋለጣቸው እርሳቸውም ሆነ ባለቤታቸው የቀን ሥራ በመሥራት የምግብ ፍጆታቸውን ለመሸፈን ጥረት ያደርጉ እንደነበርም ይገልፃሉ።

ይህም ቢሆን ሰባት ልጆቻቸውን የምግብ ፍላጎት ማሟላትና ትምህርት ቤት መላክ ስለከበዳቸው በ2013 ዓ.ም መንግሥት ባመቻቸው የልማታዊ ሴፍትኔት መርሃግብር ለመታቀፍ መገደዳቸውን ያብራራሉ።]

በመርሃ-ግብሩ ተካተው ለስድስት ወራት ያህል በየወሩ ሶስት ሺህ ብር ድጋፍ ማግኘት ከመጀመሩ ወዲህ የቤተሰቡን ቀለብ መሸፈን መቻላቸውን ይናገራሉ። ድጋፍ አገኘሁ ብለው ግን እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም፤ ይልቁንም የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት የሚያገኟትን ገንዘብ በመቆጠብና ከመንግሥት የወሰዱትን ብድር ተጠቅመው ጥሪት ለማፍራት ሌት ተቀን እየታተሩ መሆኑን ይገልፃሉ።

‹‹በመጀመሪያው ዓመት ባለችኝ አነስተኛ እርሻ ላይ በማምረትና ዓሳ በማስገር የማገኛትን ገንዝብ በመቆጠብና 16ሺ ብር ተበድሬ ሁለት ላምና ሰባት ፍየል በመግዛት እያረባሁ ነው›› ይላሉ። በአሁኑ ወቅት ሁሉንም ልጆቸውን ትምህርት ቤት መላክ ከመቻላቸውም በተጨማሪም አዲስ ዘመናዊ ቤት ሠርተው የቤተሰባቸውን ኑሮ ማሻሻል ጥረት እያደረጉ ነው።

የከብት እርባታቸውንም ሆነ የእርሻ ሥራቸውን የማስፋት እቅድ እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ ዳዊት፤ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ከተረጂነት ለመላቀቅ እቅድ ይዘው እየሠሩ መሆኑን ያመለክታሉ።

ከግብርና በተጨማሪ በንግድ ሥራ የመሰማራት ሃሳብ ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ከራሳቸው አልፈው ሌሎችም ከርዳታ ጠባቂነት እንዲወጡ እገዛ እያደረጉ ነው። እንደእርሳቸው ሁሉ ሌሎቹም የማህበሩ አባላት ከተረጂነት ለመላቀቅ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ነው የተናገሩት።

‹‹ጥራት ያለው ማርና ሰም ለገበያው ለማቅረብ ፍላጎት ያለን ቢሆንም እንደማር ማጣሪ ያሉ ግብዓቶችን ማግኘት ባለመቻላችን ፍላጎታችንን ማሳካት አልቻልንም›› ሲሉ ያነሳሉ።

የቆላ ሙላቱ ቀበሌው ግብርና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘካሪያስ ሻንካ እንደሚናገሩት፤ በቀበሌው 141 አባወራ አደረጃጀት ውስጥ የሚገኙ 600 ነዋሪዎች የሴፍኔት ተጠቃሚዎች ይገኛሉ። በመርሃ-ግብሩ ምንም አቅም የሌላቸውና መሥራት የማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በቀጥታ ድጋፍ የሚያገኙበት ሥርዓት ቢኖርም አብዛኞቹ በማህበረሰብ ሥራ ማዕቀፍ ተካተው የራሳቸውናን የቤተሰባቸውን ኑሮ እንዲያሻሽሉ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።

‹‹በቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ መርሃ-ግብር 52 ተጠቃሚዎች ብድር እንዲያገኙና ወደ ሥራ እንዲገቡ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል። ከእነዚም ውስጥ አስሩ ነፃ ብድር ያገኙ ሲሆን ቀሪዎች ሠርተው ከሚያገኙት ገንዘብ በረጅም ጊዜ የሚከፍሉበት ሁኔታ ተመቻችቶላቸዋል›› ይላሉ። እያንዳንዳቸው በመረጡት ዘርፍ እንዲሠማሩ የብድር አቅርቦት ከመቻቸቱም ባሻገር የሙያና የቴክሎጂ እገዛ እየተደረገላቸው መሆኑን አቶ ዘካሪያስ ያነሳሉ። አብዛኞቹ በእንስሳት ማድለብ፤ በንብ ማነብና በመሰል የግብር ሥራዎች ላይ ተሠማርተው ጥሪት እያፈሩና የቤተሰባቸውን ኑሮ እያሻሻሉ መሆናቸውን ያስረዳሉ።

በተለይም 42ቱ ተጠቃሚዎች ባለሙት ተፋስስ ላይ በንብ ማነብ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ የቀፎ ድጋፍ የተደረገላቸው መሆኑን ይጠቁማሉ። ከዚህ ጎን ለጎን የምግብነት ይዘት ያላቸውን የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞች እንዲያለሙ መደረጉን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት ፍሬ እያገኙ በመሆናቸው ለቤተሰባቸው የምግብ አቅርቦት እገዛ እያደረተገላቸው መሆኑን ያነሳሉ።

በተጨማሪም በፍየል ድለባ የተሠማሩ የፕሮግራሙ ተጠቃዎችም በየሶስት ወሩ ፍየል እየሸጡ የገቢ አቅማቸውን የሚያሳድጉበት ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው ያስረዳሉ።

በንብ ማነብ የተሠማሩ ተጠቃሚዎች የሚያነሱትን የቴክሎጂና የገበያ ትስስር ጥያቄ በሚመለከትም ‹‹ጥያቄያቸው ተገቢ ነው፤ በአሁኑ ወቅት ምርታማነታቸው እያደገ ቢመጣም ማር የሚያጣሩበት መሣሪያ የሌላቸው በመሆኑ ከሌላ ቀበሌ ከሚመረተው ማር ጋር በገበያ ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን እንቅፋት ሆኖባቸዋል›› ይላሉ።

ይህን የቴክኖሎጂ ጥያቄ ለሚመለከተው አካል የቀበሌው አስተዳደር ያቀረበ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ችግር ከተፈታ ግን የገበያ ትስስሩ አብሮ የሚጠናከር በመሆኑ ስጋት አይሆንም ባይ ናቸው።

የቀበሌዋ አርሶአደሮች በአሁኑ ወቅት ምርታማነታቸውን እያሳደጉ ኑሯቸውን እያሻሻሉ መሆኑን አቶ ዘካሪያስ አመልክተው፤ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ሙሉ ለሙሉ ከመርሃ-ግብሩ እንደሚመረቁ አውቀውና አምነውበት ከተረጂነት ለመላቀቅ እየሠሩ መሆኑን ያነሳሉ። በተያዘው በጀት ዓመት 70 በመቶ የሚሆኑት ሙሉ ለሙሉ ለማስመረቅ እየተሠራ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በጋሞ ዞን የምዕራብ አባያ ወረዳ ፅህፈት ቤት አደጋ ስጋት አመራር ዘርፍ ሃላፊ አቶ መላኩ ደአ እንደሚሉት፤ በወረዳው 21 ቀበሌ ያሉ ሲሆን ሁሉም ወረዳዎች በሴፍትኔት ታቅፈዋል። በማህበረሰብ ልማት ሥራ የተሰማሩ 13 ሺ 961 ተጠቃሚዎች ያሉ ሲሆን 2 ሺህ 44 ሰዎች ደግሞ በቀጥታ ድጋፍ እያገኙ ይገኛሉ። በማህበረሰብ ልማት ሥራ ተጠቃሚ የሆኑና እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ፣ የጤና እና የአቅም ችግር የሌለባቸው ነዋሪዎች በተፋሰስ ልማት ፣ በደንና ችግኝ ልማት፣ መኖ ልማት፣ በመንገድ ሥራ እንዲሠማሩ ተደርጓል።

‹‹አካባቢው በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋ የተፈጥሮ ሀብት መመናመን የደረሰበት ሲሆን፣ በተለይ የአፈር መሸርሸር ችግር በማጋጠሙ ምርታማነት ዝቅተኛ ነበር›› የሚሉት ኃላፊው፤ መርሃ-ግብሩ መተግበር ከጀመረ ወዲህ በ24 ተፋሰሶች ላይ በተሠራው ሥራ ከ3ሺህ ሄክታር በላይ ማልማትና ወደ ቀደሞ ይዞታው መመለስ መቻሉን ያመለክታሉ። በተጓዳኝም ህብረተሰቡ በአካባቢውን ያሉትን ፀጋዎች በመጠቀም ኑሮውን እንዲያሻሽል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያነሳሉ።

በዚህም አንድ ሺህ 300 አባዎራዎችን በመለየት በተለያዩ ገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ እንዲሠማሩ መደረጉን ጠቁመው፤ በተለይም ወረዳው በንብ ማነብ ሰፊ አቅም ያለው በመሆኑ ይህንን በመጠቀም 999 ቀፎችን ለሶስት ቀበሌዎች መሰራጨቱንና ከተፋሰስ ልማት ሥራ ጋር ማስተሳሰር መቻሉን ነው ያስገነዘቡት።

ከግብዓት አኳያ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እስከ ክልል ድረስ ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ በተለይ ለንብ አንቢዎች የማር ማጣሪያና ሰም ማተሚያ መሣሪያ ድጋፍ እንደሚያሻቸው ታምኖበት በእቅድ መያዙን ይጠቁማሉ።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You