ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የፈረንሳይ አበርክቶ

ከሰሞኑ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በባሕር በር ጉዳይ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ከፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የሚጨበጥ ውጤት እንደሚጠብቅ ገልጸውላቸው ነበር፤ ፕሬዚዳንቱም ለጥያቄው አዎንታዊ ምላሽ እንደሰጧቸው ይታወሳል።

ለመሆኑ ፈረንሳይ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታገኝ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ ምን ያህል ነው? ሚናዋንስ እንዴት ልትወጣ ትችላለች? በሚሉት ጥያቄዎች ላይ ምሁራን አስተያየት እንዲሰጡባቸው አድርገናል።

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር ዓለምሰገድ ደበሌ (ዶ/ር) እና በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህርና የትምርት ክፍሉ ሃላፊ አቶ ሙሉዓለም ኃይለማርያም እንደሚያስረዱት፤ የኢትዮጵያና የፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተለይም ከ18ኛው ክፍለዘመን መጨረሻ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ተጠናክሮ የዘለቀ ነው።

ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ ነባር፣ ጥብቅና ተጨባጭ ውጤቶች የታዩበት ነው፤ ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ የተዘረጋው የባቡር ሃዲድም የተሠራው በፈንሳይ ነው። ዛሬም ድረስ አብዛኛው የሀገሪቱ የወጪ ገቢ ንግድ የሚካሄደው በዚሁ ኮሪደር ነው። ይህ በኢትዮጵያና በጅቡቲ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ወዳጅነት ቀደምትና ጠንካራ መሆኑን የሚያሳይ ነው ይላሉ ምሁራኑ።

አቶ ሙሉዓለም ከዓድዋ ድል በኋላ ኤምባሲያቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ ከከፈቱ ሀገራት የመጀመሪያዋ ፈረንሳይ እንደሆነች ጠቅሰው፤ በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ ድጋፍ ስታደርግ እንደቆየች ያመለክታሉ።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዓለምሰገድ (ዶ/ር) በባንክ፣ በቴሌፎን፣ በትምህርት፣ በጤና ፣ በሆቴሎች ግንባታ ፣ በንግድ (በጦር መሣሪያ ንግድ) ኢትዮጵያን ከማዘመን አንጻር ፈረንሳይ ውለታ እንደሠራችና ዛሬም ደረስ ድጋፏ እንዳልተለየ ይገልጻሉ።

አቶ ሙሉዓለም በዚሁ ላይ ተጨማሪ ሲያደርጉ፤ ፈረንሳይ ከዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ለምታቋቁመው የባሕር ኃይል ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብታለች፤ አሁንም ቅርሶችን በማደስ ረገድ የፋይናንስና የሙያ ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች። የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት ዘመናትን ተሻግሮ የመጣና ዛሬም ድረስ ያልደበዘዘ ነው ይላሉ።

ፕሬዚዳንት ማክሮን ከባለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ ሁለት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል፤ በሰሞኑ ጉብኝታቸው ከጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ባደረጉት ንግግር የአንካራውን ስምምነት አድንቀዋል። ለስምምነቱ እውቅና መስጠታቸው ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄዋ በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ ጎልቶ እንዲታይ ያደርጋል ሲሉ ያብራራሉ።

ስምምነቱ ከወረቀት አልፎ መሬት ላይ እንዲያርፍም ጫና ያሳድራል፤ ፈረንሳይ በቀጣናው ካላት የረዥም ጊዜ ቆይታዋ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፍላጎቷ አንጻር በጅቡቲ ላይ ብቻ ሳይሆን በቀጣናው ካሉ የቀይ ባሕርም ይሁን የሕንድ ውቅያኖስ ወሰንተኛ ሀገራት ላይ የዲፕሎማሲ ጫና በማሳደር ኢትዮጵያ በሊዝ ወይም በኮንትራት የባሕር በር አማራጮችን እንድታሰፋ ልታደርግ ትችላለች ይላሉ።

ፈረንሳይ በቀጣናው ላይ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነት አላት የሚሉት አቶ ሙሉዓለም ተጽዕኖዋም በዚያው ልክ ስለሆነ የሚያዳምጧት ሀገራት ይኖራሉ። ሌሎች ዓለም አቀፍ ሀገራትም ጭምር የዲፕሎማሲ፣ የፋይናንስና የሎጂስቲክ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጫና ማሳደር እንደምትችልም ይናገራሉ።

ዓለምሰገድ (ዶ/ር)፤ ይህንኑ ሃሳብ ሲያጠናክሩ፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የሚመለሰው ከጎረቤት ሀገራት ጋር ትብብር እና መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ሲፈጠር ነው፤ ይሁንና እንደፈረንሳይ አይነቶቹና በቀጣናው ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉ ሀገራትን መያዝ ደግሞ የበለጠ ውጤታማ ያደርጋል።

ሁለቱም ምሁራን እንደሚያስረዱት ፈረንሳይ በቅኝ ግዛት የያዘቻቸውን የምእራብ አፍሪካ ሀገራት ከለቀቀች በኋላ በቀይ ባሕር አካባቢ ጦሯን በማስፈር ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ አልማ እየሠራች ነው። ፈረንሳይ ከራሷ ተጠቃሚነት አንጻር በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖርም ትፈልገዋለች፤ ተጽዕኖም መፍጠር ትችላለች። በቀጣናው ያላትን የረዥም ጊዜ ቆይታና ልምድ በመጠቀም የአፍሪካ ቀንድ የተረጋጋና ሰላማዊ መስተጋብር ያለው እንዲሆን ማድረግ ትችላለች።

ኢትዮጵያም ትልቅ አቅም ያላት ሀገር ስለሆነች ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መሥራት ትፈልጋለች። ፈረንሳይ ከሶማሊያ፣ ከጅቡቲ ፣ ከኤርትራና ከሌሎችም የአፍሪካው ቀንድ ሀገራት ጋር ጥሩ ግንኙነት ስላላት ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታገኝ የማግባባት ሚና ልትጫወት ትችላለች ይላሉ ምሁራኑ።

ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳይኖራት በሚመስል መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሀገራት እጃቸውን ሰብስበው እንዲቀመጡ ከማድረግ አንጻር ፈረንሳይ የነቃ ተሳትፎ ታደርጋለች ተብሎ ይታመናል ይላሉ። የፈረንሳይን ተጽዕኖ ፈጣሪነት አጥብቆ በመያዝና ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚኖረውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት አጠናክሮ በመቀጠል በወደብ ጉዳይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ምሁራኑ ይስማማሉ ።

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You