የቀድሞ መንግሥታት የውጭ ግንኙነት እና የብሔራዊ ደህንነት ፖሊሲያቸውን ከጎረቤት ሀገር ጋር በፅኑ ሰላማዊ እና የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ከመመሥረት ይልቅ፤ በጠላትነት መፈረጅ እና በጥርጣሬ ዓይን መመልከት ላይ ያተኮረ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። በተቃራኒው የአሁኑ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ላይ እንደተመላከተው፤ በብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት ላይ የሚሰነዘሩ አደጋዎችን መከላከል አስፈላጊ መሆኑ ቢታመነም፤ ወደ ውጭ ከመመልከት ይልቅ ውስጥን በማየት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ላይ የትብብር እድሎችን ማስፋት ቅድሚያ ይሰጠዋል። በዚህ ውስጥ ደግሞ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚኖር ሰላማዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ልዩ ትኩረት አግኝቷል።
ፖሊሲው ከምን አንፃር ለጎረቤት ሀገራት ልዩ ትኩረት ሰጠ? የሚያስገኘው ጥቅምስ ምን ያህል ነው? ስንል የተለያዩ ምሁራንን አነጋግረናል። የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአውሮፓና የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተንታኝ ዳር እስከዳር ታዬ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ በአብዛኛው በውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከሀገራት ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት በግልፅ ማስቀመጥ የተለመደ ነው። ግንኙነቱ የቅርብና የሩቅ ጎረቤት በሚል መከፋፈል ይቻላል።
በአመዛኙ ሀገራት በፖሊሲያቸው ለጎረቤት ሀገራት በተለያዩ ምክንያቶች ቅድሚያ ይሰጣሉ። አንደኛው ጂኦግራፊው ስለሚያስገድዳቸው ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከቅርብ ጎረቤት ጋር የሚኖረው የግንኙነት አድማስ በጣም ሰፊ መሆን ይችላል። ማለትም ከቅርብ ጎረቤት ጋር በሆነ ጥቂት ጉዳይ ብቻ እንገናኝ ማለት አይቻልም።
ለአብነት ኢትዮጵያ ከኤርትራ እና ከሶማሊያ ጋር የሚኖራት ግንኙነት እንደ ሌሎች ሀገራት በተመረጠ ጉዳይ ላይ ብቻ አይሆንም። ምክንያቱም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አለ። የማንነት ተመሳሳይነት ይኖራል። ጎረቤት በመሆን ብቻ ሕጋዊና ሕገ ወጥ የንግድ ግንኙነት ይፈጠራል። ድንበር በጋራ ማስተዳደርም አለ። እንደ ዳርእስከዳር (ዶ/ር) ገለፃ፤ እነዚህ ሁሉ ጉዳዮች ሲታዩ ተወደደም ተጠላ ከጎረቤት ሀገር ጋር የሚኖረው ግንኙነት ጥብቅ እንደሚሆን አያጠራጥርም።
ሌላው ዳርእስከዳር (ዶ/ር) የተብራራው፤ ከጎረቤት ሀገር ጋር ግንኙነት የሚመሠረተው በመምረጥ አይደለም። ጂኦግራፊው ራሱ አስገዳጅ ሁኔታን ይፈጥራል። ነገር ግን ከሌሎች ሀገራት ጋር ግንኙነት የሚመሠረተው በምርጫ ነው። ለአብነት ኢትዮጵያ እና ኢምሬት በጂኦግራፊያዊ አቀማመጣቸው ጎረቤት አይደሉም። ስለዚህ ግንኙነት ሊመሠርቱ የሚችሉት በተመረጡ ጉዳዮች ላይ ብቻ ነው። ኢትዮጵያ ከመካከለኛው አፍሪካ ሀገራት ከየትኞቹ ጋር መጠቃቀም እችላለሁ? ብላ መምረጥ ትችላለች። ያልፈለገችውን ሀገርም መተው መብቷ ነው።
ጎረቤት ሀገር ጋር ሲመጣ ግን፤ በዚህ መንገድ መምረጥ አይቻልም። በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ፖሊሲ ከ2010 ወዲህ ለጎረቤት ሀገራት ትኩረት የሰጠ ሆኗል። ይህንን ተከትሎም በብዙ ሥራዎች ቅድሚያ ለጎረቤት ከመስጠት በተጨማሪ፤ ከሁሉም ጎረቤት ሀገራት ጋር መልካም ግንኙነት ለመመሥረት ጥረት ይደረጋል።
‹‹ከለውጡ አስቀድሞ በነበሩ ዓመታት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ኤርትራን በጠላትነት የማቆየት ስትራቴጂ ነበር። ከሶማሊያና ከኬንያ ጋር የነበረው ግንኙነትም ሁልጊዜ ይህን ታሳቢ ያደረገ ነበር›› ያሉት የፖለቲካ ተንታኝ ዳርእስከዳር ታዬ (ዶ/ር)፤ አሁን ላይ ጎረቤት ተኮር እናድርገው ሲባል ግን፤ ሁሉንም ጎረቤት ሀገራት በተቻለ መጠን ወደ አንድ ማምጣት የሚያስችል ፖሊሲ ታስቦበት መዘጋጀቱን ተናግረዋል። በዋናነትም ከሁሉም ጋር በሰላም መኖርን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
ላለፉት ሃምሳ እና ስልሳ ዓመታት በአፍሪካ ቀንድ ላይ አንዱ በሌላ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ይገባ ነበር። አንዱ የሌላ ሀገርን ተቃዋሚ ኃይል ከማሰልጠን በተጨማሪ የማስታጠቅና መሰል ልምዶች ነበሩ። ከዚህ የተነሳ ከ1960ዎቹ ጀምሮ በኢትዮጵያና በጎረቤት ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት አንድ ጊዜ ሲሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀዝቀዝ እያለ እንደየወቅቱ ሁኔታ የሚቀያየር ነበር። ለዚህ ዋነኛው ምክንያት አንዱ በአንዱ ጉዳይ ጣልቃ ይገባ ስለነበረ መሆኑን አስረድተዋል።
ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ለሁሉም የሚጠቅም ጎረቤት ተኮር ፖሊሲን ብታዘጋጅም፤ አንዳንድ ጎረቤቶች አሁንም ከኖሩበት ልማድ አለመላቀቃቸውን በመጠቆም፤ ቀላል ምሳሌ ብለው በቅርቡ የኤርትራው ፕሬዚዳንት በሰጡት ቃለ ምልልስ ብዙ ሰዓት ስለኢትዮጵያ ሲያወሩ ተደምጠዋል ብለዋል። እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ነበሩ፤ አሁንም አሉ። አሁን ላይ የተለወጠው ነገር ኢትዮጵያ በመፈቃቀድና በመተባበር ካልሆነ በስቀተር በጎረቤት ሀገር ጉዳይ እጇን አታስገባም። በዚህም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሰላማዊ ግንኙነት መፍጠር እና በኢኮኖሚ መተሳሰርን ዋነኛ ግቧ ሆኖ በመንቀሳቀስ ላይ እንደምትገኝ አመላክተዋል።
ጨምረውም ከዚህ በፊት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለ ግንኙነት የሚቃኘው ከኃያላን ሀገራት ጋር ያለን ግንኙነት መሠረት በማድረግ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ግን ይህ ተቀይሯል ብለዋል። ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለው ጥቅም የሚሰላው በራስ ውሳኔ መሆኑን አስታውቀው፤ ኃያላን ሀገራት ምን ይፈልጋሉ? ምን ይላሉ? የሚለውን መሠረት በማድረግ የቆመ መሆኑንም ተናግረዋል። ከዚህ አንጻር ለውጥ መኖሩንም አብራርተዋል።
በኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ለሶስት ዓመት ፕሬዚዳንት ሆነው ያገለገሉት እና በአሁኑ ወቅት በጨፌ ኦሮሚያ የምክር ቤት አባል እና የመንግሥት በጀት እና ሀብት አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ገመቹ አራርሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው ዳርእስከዳር (ዶ/ር) ጋር ተመሳሳይ የሆነ ምልከታ አላቸው። እሳቸው እንደሚሉት ከዚህ በፊት የነበረው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አንዱን ሀገር ወዳጅ ሌላኛውን ደግሞ ጠላት ብሎ የሚፈርጅ ነበር።
ለአብነት ኤርትራን እንደ ጠላት የሚፈርጅ እንደነበር የገለፁት ገመቹ (ዶ/ር)፤ ከሶማሊያ ጋርም የነበረው ግንኙነት ጠንካራ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ላይ የተመሠረተ ትብብር እንዳልነበር ያስረዳሉ። የተወሰነ ከሌሎች የምዕራብ ሀገሮች ጋር በመሆን ሽብርተኝነትን የመዋጋት ሥራ ይሠራ እንደነበር አስታውሰው፤ ያም ቢሆን የነበረው ፖሊሲም ሆነ በተግባር ከጎረቤት ሀገራት ጋር የነበረው ግንኙነት ጤናማ አልነበረም ማለት ይቻላል ብለዋል።
ገመቹ (ዶ/ር)፤ መገለጫውም ብለው ያነሱት ከፖሊሲው ባሻገር በተግባርም ከኤርትራ ጋር በነበረው ግንኙነት ለሃያ ዓመታት ሰላምም ጦርነትም ውስጥ አልነበረም። ሁለቱ ሀገሮች አንዱ የአንዱን ስም ለማጠልሸት፤ አንዱ ሌላኛው ላይ የዓለም አቀፍ ጫና እንዲደረግበት ይሠራ ነበር። በጊዜው የነበረው ሥርዓትም ኤርትራ ላይ ጫና ለመፍጠር፤ ጤናማ ባልሆነ መልኩ ይንቀሳቀስ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ባለው በውጭ ጉዳይ ፖሊሲም ሆነ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ባለው ግንኙነት የቆየውን የፖለቲካ ዕሳቤ በመቀየር፤ ጠላት ብሎ መፈረጅ ቀርቷል ብለዋል። ከሀገሮች ጋር የሚኖረው ግንኙነት በተለይም ከጎረቤት ሀገሮች ጋር፤ በዋናነት የጎረቤት ሀገሮች ሲባል ኤርትራን ጨምሮ የሚኖረው ግንኙነት ትልልቆቹ ጉዳዮች ብሔራዊ ጥቅም እና የዜጎች ክብር መሠረት ባደረገ መልኩ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ገመቹ (ዶ/ር) ገለፃ፤ ከለውጡ ወዲህ በተግባርም በመካከላቸው ጦርነትም ሰላምም ያልነበረባቸው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ እርስ በእርስ እንዲቀራረቡ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ናቸው። በዚህም የኖቬል ሽልማት እስከ ማግኘት ደርሰዋል። አሁን በተግባርም እየተሠራ ያለው ይኸው ነው። አሁንም የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራ ጠላቴ ናት ብሎ አልፈረጀም። አሁንም የሚታመነው የኤርትራ ሕዝብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወንድም እንደሆነ ነው።
የኢትዮጵያ አዝማሚያ አብሮ የመልማት እና የማደግ፤ በጋራ የቀጣናውን ሰላም የማስከበር ነው። ይህ ከየትኛውም ጎረቤት ሀገር ጋር በሚኖረው ግንኙነት የሚታይ መሆኑን ጠቁመው፤ በተቃራኒው ግን በሕዝብ ደረጃ ሳይሆን መንግሥታት ወይም ሥልጣን ላይ ያሉ አመራሮች አልያም በዛ ሀገር ያለው ሥርዓት ቀና የሆነ ግንኙነት ላይኖረው እንደሚችል ጠቁመዋል። ይህ ሲሆን ግንኙነቱ በተመሳሳይ መልኩ ትርጉም ላይሰጠው ይችላል ብለዋል።
ለዚህ የራሱ ምክንያት ሊኖረው ይችላል ያሉት ገመቹ (ዶ/ር)፤ ምናልባትም አንዳንዴ የኃይል ግፊያ ግንኙነትን እንደሚያሻክር አብራርተዋል። ይህች ሀገር በኢኮኖሚ ከተጠናከረች ተፅዕኖ ልትፈጥር ትችላለች የሚል ግፊያ ይኖራል። በግለሰብ ደረጃ ሸፍጥ ሊኖር ይችላል። ስለዚህ ከጎረቤት ሀገር ተመሳሳይ ምላሽ ላይኖር እንደሚችል አመላክተዋል።
በኢትዮጵያ በኩል የጎረቤት ሀገር ምላሽ ምንም ሆነ ምን ኢትዮጵያ ግንኙነቷ ሰላማዊ እንዲሆን ፍላጎቷን በመግለጽ ላይ እንደምትገኝ ጠቁመው፤ ይህ ደግሞ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አብራርተዋል። ያልተረጋጋች ሶማሊያ፣ ኤርትራ ወይም ኬንያ ቢኖሩ ኢትዮጵያ ምንም ልታተርፍ አትችልም። እንደውም እነርሱ ሰላም ካልሆኑ ኢትዮጵያም ሰላም መሆን አትችልም። ሰላም ካልሆነች ደግሞ ትኩረቷን ልማት ላይ ለማድረግ እንደምትቸገር አስረድተዋል።
ሌላው የቀጣናውን ኢኮኖሚ ማስተሳሰር ቢቻል ቀጣናው በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ይሆናል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የምታንቀሳቅሰው ትልቅ ኢኮኖሚ ነው። ኬንያም የምታንቀሳቅሰው ኢኮኖሚ ትልቅ ነው። ሁሉም ሀገሮች የራሳቸው ፀጋ አላቸው። ይህንን ፀጋቸውን ማቀናጀት ቢቻሉ፤ እያንዳንዱ ሀገር በተለያየ መልኩ ተጠቃሚ ይሆናል። በቀጣናውም በጣም ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት ይቻላል ብለዋል።
ለሁሉም ነገር መሠረቱ ኢኮኖሚ ነው። ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት ከተቻለ፤ ጠንካራ ደህንነት ይኖራል። የቀጣናው ተሰሚነት ይጨምራል። ያሉት ገመቹ (ዶ/ር)፤ ይህ ሲሆን ማንም እንደፈለገው እጅ መጠምዘዝ የሚችልበት ዕድል ይዘጋል። በደህንነት ጉዳይ ላይ መተሳሰርም ከባድ እንደማይሆን አስረድተዋል።
ሌላው በገመቹ (ዶ/ር) የተነሳው፤ ቀይ ባህር የአፍሪካ፣ የአውሮፓ እና የኤዢያ አህጉራት በንግድ የሚተሳሰሩበት ነው። ቀጣናው በጣም ስትራቴጂክ ነው። በጣም ትልቅ የዓለም ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀስበት ቀጣና በመሆኑ፤ በርካታ ሀገራት ምስራቅ አውሮፓዎች ሳይቀሩ የጦር ሠፈር (ሚሊተሪ ቤዝ) ይዘዋል የሚለው ነው።
ይህ ማለት ቀጣናው ላይ በጣም ስትራቴጂክ ጥቅም አለ። ስለዚህ የቀጣናው ሀገራት በጋራ በመሆን፤ ከዚህ አካባቢ የሚገባቸውን ድርሻ ማግኘት አለባቸው ብለዋል። የሩቅ ሀገር መጥቶ ፍላጎት እያሳየ ኢትዮጵያ ችላ ብላ ልትቀመጥ አትችልም። ስለሆነም በቅርብ ያሉ ሀገራት እርስ በእርስ ከመገፋፋት ይልቅ ተባብረው በአንድነት ከተንቀሳቀሱ በቀጣናው ላይ ማሳደር የሚገባቸውን ጫና ማሳደር ይችላሉ የሚል እምነት እንደላቸውም ተናግረዋል።
እንደ ገመቹ (ዶ/ር) ገለፃ፤ ተባብረው በአንድነት መቆማቸው ተፅዕኖ መፍጠር ባይችሉ እንኳ ቢያንስ የሚመጣባቸውን አሉታዊ ጫና መመለስ የሚችሉትን ዕድል መፍጠር ይችላሉ። ለዚህም እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ የጎረቤት ሀገራትም ፖሊሲያቸውን ጎረቤት ተኮር አድርገው ሰላማዊ ግንኙነት ላይ እና የጋራ ጥቅምን በማስከበር ዙሪያ መረባረብ ይገባቸዋል።
የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ግን ከሶሻሊስት እና ከካፒታሊስት ሀገራት ጋር፣ ከምዕራባውያን እና ከምስራቅ ሀገራት ጋር እያለ ይከፋፍል ነበር። ለቀጣናው ሀገራት ለአብዛኞቹ ትኩረት የሚሰጥ ፖሊሲ አልነበረም። አሁን ግን ኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የጎረቤት ሀገር ላይ ትኩረት አድርጎ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን፤ የደህንነት እና የማህበራዊ ትስስርን እንዲሁም የሕዝቦችን ታሪካዊ ትስስር ላይ ተመስርቶ እየተሠራበት ይገኛል። ይህም በፅኑ የሚደገፍ መሆኑን አመላክተዋል።
እንደ ምሁራኑ ገለፃ፤ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ላይ እንደተቀመጠው ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚኖሩት ግንኙነቶች የሀገሪቷን ብሔራዊ ጥቅም መሠረት ባደረገ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ነው። የሀገራትን ሉዓላዊነት እና ፍላጎታቸውን በማይነካ መልኩ የዜጎቻችንን ክብርም በጠበቀ ሁኔታ የተቀረጸ በመሆኑ አዋጭነቱ አጠራጣሪ አይደለም።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 15 ቀን 2017 ዓ.ም