በመስኖና ቴክኖሎጂ የታገዘ የቡና ልማት

ዜና ትንታኔ

በአሁኑ ጊዜ የቡና ዋጋ በዓለም ገበያ እየጨመረ ነው። ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት 298 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ አንድ ነጥብ 43 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች። ዘንድሮ ደግሞ መጠኑን ወደ 400 ሺህ ቶን በማሳደግ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት ታቅዷል። ዘንድሮም ባለፉት አምስት ወራት 117 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ ለመላክ ታቅዶ ከ178 ሺህ ቶን በላይ በመላክ 797 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደተገኘ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን መረጃ ያሳያል።

በኢትዮጵያ ቡናን በመስኖና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማልማት ምርታማነትን ማሳደግ ቢቻል ተጠቃሚነትን መጨመር እንደሚቻል እየተገለጸ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በተለያዩ አካባቢዎች ያደረጉትን ጉብኝት አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳሉት፤ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ገላን ወረዳ በቀርጫንሼ ትሬዲንግ አማካኝነት በመስኖና ሜካናይዝድ መንገድ ቡና እንዲለማ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በመስኖ እየለማ ያለው የቡና እርሻ በሄክታር 60 ኩንታል ቡና ማግኘት  የሚያስችል ነው፡፡ ይህን ተሞክሮ ወደ ሁሉም ቡና አምራች አካባቢዎች በማስፋት የዘርፉን የወጪ ንግድ ገቢ ማሳደግ እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ማስገንዘባቸው ይታወቃል፡፡

የቡና ምርታማነት ወደ ቡና አምራች አካባቢዎች ለማስፋት ምን ማድረግ ይጠበቃል? በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ቡና ላይ ለረጅም ጊዜ ምርምር ያደረጉት ፕሮፌሰር ዋሱ መሀመድ አሊ በኢትዮጵያ በሄክታር ከ45 እስከ 50 ኩንታል ቡና የማምረት አቅም እንዳለ ጠቅሰው፣ በተያዘው ቴክኖሎጂና መስኖ ልማት ምርታማነቱን በሄክታር 60 ኩንታል ለማድረስ መታሰቡ ሊያስኬድ እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡

በተለምዶ የሚሠራበት ቡናን ዛፍ ውስጥ ማልማት /በሼድ/ አነስተኛ ምርት እየሰጠ እስከ 40 እና 50 ዓመት ቡና ምርት ሲለቀም የነበረበት ሁኔታ መኖሩን ይገልጻሉ። ይህን ቴክኖሎጂ በደንብ ማስፋት ከተቻለ በሄክታር 60 ኩንታል ብቻ ሳይሆን ከዚያ በላይ ማምረት ይቻላል ባይም ናቸው፡፡

እንደ ብራዚልና ቬትናም ያሉ ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየው በሚጠቀሙበት የግብርና ቴክኖሎጂ ልክ አሁን ላሉበት ደረጃ መድረሳቸውን ነው ሲሉ ገልጸው፤ እንደ ሀገር ቴክኖሎጂን በመጠቀም የቡና ምርታማነት በዚህ ልክ ማስፋፋት እንደሚቻል ያመላክታሉ፡፡

ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት፤ ለአብነት ብራዚሎች በጠባብ ቦታ አድርገው ለማሽኑ ብቻ መንገድ ትተው በማሽን ያመርታሉ፡፡ በብዛት የሚያመርቱበት አንድና አንዱ ምክንያትም ይሄው ነው፡፡ ‹‹በዚህም ከእኛ የተሻለ ያመርታሉ፡፡ ከእኛ በኋላ በቅርብ የጀመሩ 40 ዓመት ያልሞላቸው ቬትናሞችም እንዲሁ ቡና በብዛት እያመርቱ ነው›› ብለዋል፡፡

አርሶ አደሩ በቴክኖሎጂው ተጠቅሞ ቡና ወደ ማልማት ሲገባ በበቂ ባለሙያዎች የቴክኒክ ድጋፍ እንዲሁም ክትትል ሊደረግለት እንደሚገባም ይጠቁማሉ። ጅምሩ ጥሩና ለሌሎችም ምሳሌ እንደሚሆን አመልክተው፣ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል። በመንግሥትም፣ በምርምር ረገድም መደገፍ ከተቻለ ማስፋቱ ችግር አይሆንም ይላሉ፡፡

‹‹እኛ እጃችን ላይ ያለውን ወርቅ ሳንጠቀምበት ኖረናል፡፡ ኬንያ በሄክታር ከ30 እስከ 40 ኩንታል ታመርታለች፤ ቁጭት የሚኖረው ካለ እና በመንግሥት በኩል የባለሙያና የቴክኒክ ድጋፍ ካለ ይህንን ለማድረግ የተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው የሚፈጀው ›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ቡና ብዙ ምርታማ ለመሆን ከአራት ዓመት ጊዜ በላይ የሚፈጅ መሆኑን ፕሮፌሰር ዋሱ ጠቅሰው፣ አርሶ አደሩም ቢሆን አንድ ጊዜ ተጠቅሞ ካየ በራሱ ያስፋፋዋል ይላሉ። ብልጭ አድርጎ ከመተው ሥር ይዞ በደንብ እንዲሰፋ ማድረግ ላይ ሊሠራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ ስጋታቸውንም ጠቁመዋል፤ በማስፋቱ ሥራ በርካታ ችግሮች ሊገጥሙ እንደሚችሉ ገልጸው፣ የመጀመሪያው ችግር ከፍተኛ የባለሙያ እጥረት ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ በቡና ዘርፍ ላይ ብቻ የሰለጠነ ባለሙያ የለም፡፡ እንደ ብራዚል ያሉ ሀገራትን ተሞክሮ ስንመለከት የቡና ባለሙያዎች (ከዲግሪ ጀምሮ እስከ ፒኤች ዲ ድረስ) የሚያሠለጥኑበት ራሱን የቻለ ኢንስቲትዩት አላቸው፡፡ በእኛ ሀገር በዲግሪ ደረጃ በቡና ብቻ የሠለጠነ አርሶ አደሩን ሊደግፍ የሚችል ባለሙያ የለንም፡፡ በቴክኒክም ሆነ በእውቀት ከአርሶ አደሩ የተሻለ ባለሙያ ሊኖር ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

ሁለተኛው ሊያጋጥም የሚችለው ችግር ለማምረቱ ሥራ የሚውል ግብዓት በጊዜውና በበቂ ሁኔታ አለማቅረብ መሆኑን ጠቁመው፣ የቡና ተክል መግረዣ ፣ መጎንደያ፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያና የመሳሰሉትን በወቅቱ ማቅረብ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ከዘርፉ የሚወጣው ገንዘብ ይህን ሥራ መልሶ መሥራት እንደሚያስችል ጠቅሰው፣ አቅሙ ስላለ ከወጪ ጋር ተያይዞ መንግሥትን ችግር ውስጥ የሚከት ነገር አይኖርም ይላሉ፡፡ ምርታማነቱ ላይ በመሥራት የተሻለ ምርት ማግኘት እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ምርታማነት የሚያሳደግና ምርምር ሥራውን የሚሠራ የተጠናከረ መሥሪያ ቤት ያስፈልጋል፡፡ እንደ ብራዚሎቹ የጅማን ምርምር ማዕከል ኢንስቲትዩት አድርጎ ባለሙያዎች በማሠልጠን በቡና ማምረት ላይ ተመሥረተው ብቻ ኑሮአቸውን የሚመሩ አርሶ አደሮች በበቂ ባለሙያዎች እንዲረዱ ሊደረግ ይገባል። የቡናና ሻይ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤትንም ማጠናከር ይገባል፡፡

ሥራው በዘርፉ የተሰማሩ ነጋዴዎችን፣ ዩኒየኖችን፣ ላኪዎችን፣ ወዘተ በማናቀናጀት መሥራትን እንደሚጠይቅ ገልጸው፤ ትኩረት ሠጥቶ በመሥራት ከተቻለ ሥራውን ባለሙያው የሚሠራው ዘርፍ ራሱን በራሱ መደገፍ የሚችል ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማህበር ፕሬዚዳንት ሁሴን አምቦ (ዶ/ር)፤ የፕሮፌሰሩን ሃሳብ የሚያጠናክር ሃሳብ አላቸው፡፡ ቴክኖሎጂው የሚበረታታ ነው ይላሉ፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ ቴክኖሎጂው ለአርሶ አደሩ በሁለት መልኩ ይጠቅማል፣ አንደኛው ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ሁለተኛው ጥራቱን የጠበቀ ቡና ማምረት ማስቻል ናቸው፡፡

ቴክኖሎጂውን ለማስፋት ግን ጊዜ እንደሚፈልግ ተናግረው፣ አሁን ባለው የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች አቅም ሊፈጸም የሚችል መሆን አለመሆኑ በቅድሚያ በደንብ መታየት እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል፡፡

ሁሴን (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፤ ቡና በመካናይዜሽን በመጠቀም በሄክታር 60 ኩንታል ለማምረት ሰፊ መሬትና ቦታ ይፈልጋል፡፡ ይህን መጠቀም የሚችሉት አቅም ያላቸው አርሶ አደሮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አነስተኛ ማሳ ባላቸው አርሶ አደሮች ይዞታ ላይ ይህን መተግበር እንደሚያዳግትም ያመላክታሉ፡፡

እንደ ቀርጫሼ እና ሆራይዘን ያሉት ድርጅቶች ሰፊ ቦታ እንዳላቸው ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰው፣ እነዚህ ድርጅቶች ቴክኖሎጂ ተጠቅመው በመስኖ ማምረት ይችላሉ፤ አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች ግን ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም ይቸገራሉ ብለዋል፡፡

ቡና ለውጭ ገበያ እየቀረበ ያለው ከአምስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን አርሶ አደሮች ተሰብስቦ መሆኑን ጠቅሰው፣ የዚህ ቡና እርሻ በተበታተነ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ያመላክታሉ፡፡ ቴክኖሎጂውን ለማስፋት መሬት አሲይዞ መሥራት እንደሚጠይቅ ጠቁመው፤ ለዚህም እቅድ፣ እውቀትና ቴክኖሎጂ ይፈልጋል ነው ያሉት፡፡

እሳቸው እንደተናገሩት፤ እንደ ሀገር ያለን እርሻ የተበጣጠሰ በመሆኑ ለመካናይዜሽን አይመችም። እርሻው በሰፊ ማሳ ላይ እየተካሄደ አይደለም፤ ይህም ቴክኖሎጂ ለማስፋት ተግዳሮት ይሆናል፡፡ ቴክኖሎጂውን ለማስፋት ከችግኝ ጀምሮ የመሬት ዝግጅት እና የመሳሰሉት አስፈላጊ ሥራዎች ታቅደው በደንብ መሠራት አለባቸው፡፡

ያለውን እውቀትና ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ የቡና መሬት ወደዚህ ቴክኖሎጂ እንዲመጣና በመስኖ እንዲለማ በማድረግ የቡናን ምርታማነት ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ሁሴን (ዶ/ር) ጠቁመዋል፡፡ በየቦታው መስኖን መጠቀም ከተቻለ በዓመት ሁለት ጊዜ ማምረት እንደሚቻልና በዚህም የቡና ምርታማነትን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚቻል አመልክተዋል፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ኢትዮጵያ የቡና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየሠራች መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህን ተከትሎም ዓመታዊ ቡና የማምረት አቅም አንድ ሚሊዮን ቶን ደርሷል፡፡

ኢትዮጵያ በቡና ምርት ከብራዚልና ቬትናም ቀጥላ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህን ደረጃዋን ለማሳደግ በመሥራት ላይ ናት፡፡ ሀገሪቱ በርካታ ሀገራት እያለፈች አሁን ላለችበት ደረጃ የደረሰች ሲሆን፣ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት የጀመረችውን ያረጁ የቡና ተክሎች ጉንደላና ችግኝ ተከላ አጠናክራ በመቀጠል ከቡና የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ በእጅጉ ለማሳደግና ተጠቃሚ ለመሆን በትኩረት መሥራት ይጠይቃል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/ 2017 ዓ.ም

Recommended For You