
ዜና ሀተታ
በኢትዮጵያ ጋብቻ ከወሳኝ ኩነት በተጨማሪ፣ በሃይማኖትና በባህል ስለሚፈጸም ትክክለኛውን የተጋቢዎች ቁጥር ማግኘት አደጋች እንደሆነ ይገለጻል። የአዲስ አበባ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያሳየው በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የተመዘገበ ጋብቻ በ2016 ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ከተፈጸመ ጋብቻ ጋር ሲነጻጸር የ15 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የተፈጸመ የፍቺ ምዝገባ በ2016 በጀት ዓመት ከተመዘገበው የ53 በመቶ ብልጫ እንዳለው ያመለክታል፡፡ ይህ ብቻ ፍቺ ጨምሯል የሚለውን ለመወሰን በቂ ባይሆንም የሀገር መሠረት የሆነው ጋብቻ ዘላቂ እንዲሆን ግን ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት አመላካች ነው፡፡
የሥነ-ልቦና ባለሙያ አቶ ሽመልስ ገበየሁ ጋብቻ ትልቅና ሰፊ የሕይወት ሽግግር ነው፡፡ ሰዎች ወደ ጋብቻ ከመግባታቸው በፊት ለጋብቻ ዝግጁ ነኝ ወይ? የሚለውን መመለስ አለባቸው ይላል፡፡ ዝግጁነቱ ከአካላዊ ዝግጁነት አንስቶ እድሜዬ ለጋብቻ ደርሷል ወይ? የሚለውን መወሰን አለባቸው፡፡
አንዳንድ ጊዜ እድሜያቸው ለጋብቻ ቢደርስም ጋብቻ ሲባል የፍርሃት፣ የድንጋጤ፣ ኃላፊነት መሸከም አልችል ይሆን ብሎ የመጠራጠርና ጋብቻን ተከትሎ የሚመጡ ነገሮችን የመፍራት ሁኔታ እንደሚታይ ጠቁሟል። ለዚህም ትዳር ስሜታዊ ዝግጅት ይፈልጋል ነው ያለው።
ትዳር በቂ ዝግጅት ይፈልጋል የሚሉት የሥነ-ልቦና ባለሙያው፤ ጥንዶች ለሰርጉ ድግስ ከሚደረገው ዝግጅት ቀንሰው ሕይወታችንን እንዴት እንምራው? ላይ ሲያውሉት እንደማይታይ ይናገራሉ፡፡ ከአዳራሽ መረጣና ከአገባብ አንስቶ እስከ ፎቶ አነሳስ ረዥም ጊዜ ወስደው እንደሚዘጋጁት ሁሉ የጋብቻ ሥልጠና ወይም ልምድ ልውውጦችን እንደአንድ የዝግጅታቸው አካል ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የቅድመ ጋብቻ ሥልጠናዎች በሥነ-ልቦና ባለሙያዎች የሚሰጡ ድርጅቶች ጋር ወይም በእምነት ተቋማት ማግኘት ይችላሉ፡፡ ሥልጠናውን ለመጋባት ያሰቡ ጥንዶች የዝግጅታቸው አካል ሊያደርጉት ይገባል ነው ያሉት፡፡
እንደ ሥነ-ልቦና ባለሙያው ማብራሪያ፤ አንድ ሰው ወደ ጋብቻ ሲገባ እኔ ጥሩ ባል ወይም ሚስት መሆን እችላለሁ ብቻ ሳይሆን ጥሩ እናትና ጥሩ አባት መሆን እችላለሁ ወይ የሚለውን ጥያቄ መመለስ ያሻል። ትዳር ከመመሥረቱ በፊት ለጋብቻና ተያይዘው ለሚመጡት ነገሮች የአእምሮ ዝግጁነትና ብስለት ያስፈልጋል። ጥንዶቹ ኑሮን ሲመሩ በኢኮኖሚ ደረጃ ዝግጁ መሆናቸውን ማየት ይገባል፡፡ ለዚህም ከቤተሰብ ጋር ምን አይነት ግንኙነት ይኖረኛል? ችግር ቢያጋጥም እንዴት እፈታለሁና? መሰል ነገሮች በቅድመ ጋብቻ ዝግጅት ውስጥ መታየት ያለባቸው ናቸው፡፡
ጠበቃና የሕግ አማካሪ ብሩክ አያሌው ማሞ፤ በቤተሰብ ሕጉ በሀገራችን ጋብቻ ለመፈጸም መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች መደንገጋቸውን ያስረዳሉ። ጋብቻው በሁለቱም ፈቃደኝነት ላይ ሊመሠረት ይገባል።ጥንዶቹ እድሜያቸው 18ና ከዛ በላይ መሆን አለበት።፡ የቅርብ የሥጋ ዝምድና ሊኖር አይገባም፡፡ ምንም እንኳን የስጋ ዝምድና ባይኖርም እንደ ልጅ ካሳደጉትና ማህበረሰቡም እንደልጅ እውቅና ከሰጠው ሰው ጋር ጋብቻ መፈጸምና በጋብቻ ላይ ጋብቻ እንደማይቻል ያስረዳሉ፡፡
እንደሕግ ባለሙያው ማብራሪያ ጥንዶች ጋብቻን ሲያስቡ የራሳቸውንም ሆነ የጥንዳቸውን እድሜ፣ ፍቃደኝነት፣ የጋብቻ ሁኔታና ዝምድና ሊያውቁ ይገባል፡፡ ሕጉ ተጋቢዎች ከጋብቻ በፊት ያፈሩት ንብረት የግላቸው ሆኖ እንዲቀር መብት ይሰጣል፡፡ ይህ እንዲሆን መጀመሪያ በጋብቻ ውል መታሰር አለበት፡፡ በውሉ ላይ ንብረቱ ተዘርዝሮ በባለቤቱ ስም ይቀመጣል፡፡ ከጋብቻ በኋላ የሚፈራ ንብረት የጋራ ይሆናል፡፡ ጋብቻው ባይቀጥልና ቢፈርስ የንብረት ክፍፍል ላይ ንብረታቸውን መውሰድ ይችላሉ፡፡
የጋብቻ ውል ማሰር የሚፈልጉ ጥንዶች ከመጋባታቸው አስቀድሞ የጋብቻ ውል ማሰር ይችላሉ፡፡ የጋብቻ ውል ሲባል ብዙ ሰዎች ንብረትን ብቻ ታሳቢ ያደርጋሉ የሚሉት አቶ ብሩክ፤ ውሉ ግላዊ ግንኙነቶችንም ማካተት ይችላል ብለዋል፡፡ በውሉ ላይ ልጅን በተመለከተ ምን እንደሚያደርጉ፤ ገቢንና ቤትን ማን እንደሚያስተዳድር በግል ቤት ውስጥ የሚወሰኑ ነገሮችን በውሉ ማካተት እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡
እንደ የሕግ ባለሙያው ማብራሪያ፤ የጋብቻ ውል ሳያስሩ ጋብቻ የፈጸሙ ጥንዶች በፍቺ ወይም አንዱ ወገን በሞት በሚለይበት ወቅት ለረዥም ክርክርና ወጪ ይዳርጋሉ፡፡ አንድ ሰው ከጋብቻ በፊት ያፈራው ንብረት እንደሆነ በበቂ ማስረጃ ማረጋገጥ እስካልቻለና የጋብቻ ውል ከሌላቸው ምንም እንኳን ከትዳር በፊት የፈራ ንብረት ቢሆን፤ ንብረቱ የጋራ እንደሆነ ተቆጥሮ እንዲካፈሉ ሊፈረድበት እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
አቶ ሽመልስ ጥንዶች በእጮኝነት ጊዜ ፍቅርንም ጸብንም አስተናግደው ወደ ጋብቻ ቢገቡ ይመከራል ይላሉ፡፡ በተለይ አንዳንድ ጥንዶች ተጣልተን አናውቅም፤ ተጨቃጭቀን አናውቅም፤ ሲሉ እንደሚያፍሩ ይገልጻሉ፡፡ ትዳር ውስጥ ገብተው ከሚማሩት በእጮኝነት ጊዜያቸው የሃሳብ ልዩነት ሲኖር እንዴት እናስተናግደዋለን የሚለውን አስቀድሞ ማየታቸው ትልቅ ጥቅም አለው ፡፡ ምክንያቱም ሲገቡበት እንግዳ አይሆንባቸውም ነው ያሉት፡፡
የቅድመ ጋብቻን ሥልጠናን የሚወስዱ ጥንዶች ልዩነቶች ሲያጋጥሙ መታረቅ የሚችለውን አስታርቀው መታረቅ የማይችለውን ልዩነታቸውን ተቀብለው ለመኖር ወስነው ስለሚገቡ የመፋታት ዕድላቸው አነስተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የሥነ-ልቦና ባለሙያው ከዚህ ቀደም እናቶች በቡና ዙሪያ ችግሮቻቸውን ይወያዩ ነበር፤ ወንዶቹም ሰብሰብ ብለው የሚተነፍሱበት አማራጭ ነበራቸው፡፡ መደበኛ በሥነ-ልቦና ባለሙያ የተደገፈ መደበኛ የምክክር ክፍለጊዜ ባይኖርም ከልምድ አንዳቸው ለሌላቸው መፍትሄ እያመላከቱና ከጋብቻ በፊትም እየተጠናኑ የሚቆዩበት ጠንከር ያለ ማህበራዊ ግንኙነቶች እንነበር አንሰተዋል፡፡ በሃይማኖት አባቶች፣ በሀገር ሽማግሌዎችና እርስ በእርስ ልምድ ልውውጡም የፍች መጠኑ ዝቅተኛ እንዲሆን ማድረጉን ገልጸው፤ አሁን እነዚህ ግንኙነቶች ላልተዋል ነው ያሉት፡፡
በአሁኑ ጊዜ ዘመኑ ከቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ ጥንዶች የሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች ከበፊቱ እንደሚለይ ጠቁመዋል፡፡ ሰዎች በቀላሉ ስለፍቅር ግንኙነትም ሆነ ስለሌላው ነገር በእጅ ስልካቸው በርካታ አስፈላጊም፤ አላስፈላጊም መረጃ የሚያገኙበት ዘመን ነው የሚሉት አቶ ሽመልስ፤ በዚህ ዘመን ያሉትን ፈተናዎች ያለ እውቀት ልንፈታቸው አንችልም ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
ሰዎች የቅድመ ጋብቻ ሥልጠና መውሰዳቸው የሚገቡበትን የትዳር ሕይወት አውቀውትና ለዛም ዝግጁ ሆነው እንዲገቡ እንደሚያግዛቸው አስረድተዋል፡፡
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15 /2015