‹‹የባሕር በር ጥያቄ ቀጣናውንም ሊቀይር የሚችል ትልቅ ጥያቄ ነው›› – ዳርእስከዳር ታዬ (ዶ/ር) – በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአውሮፓና የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር

ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ለጎረቤት ሀገራት ልዩ ትኩረት ትሰጣለች። ይኸው ፖሊሲም ኢትዮጵያ በቀጣናው ላይ ያላትን ተሰሚነት የሚያጎለበት እና ቀጣናውንም በማስተሳሰር ያላትን ሚና በአግባቡ እንድትወጣ የሚያስችላት ነው፡፡

ይህንኑ መነሻ በማድረግ የባሕር በርን በተመለከተ ኢትዮጵያ እየሄደች ያለችበትን መንገድ እንዴት ይታያል? የባሕር በር ለማግኘት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ምን መልክ አላቸው? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአውሮፓና የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተንታኝ ዳርእስከዳር ታዬ (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ፡-

 አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ለምን የበለጠ ትኩረት ሰጠች?

ዳርእስከዳር (ዶ/ር)፡– በአብዛኛው ሀገራት በውጭ ግንኙነት ፖሊሲያቸው ለሀገራት በተለያዩ ምክንያቶች ቅድሚያ ይሰጣሉ። ልዩነቱ ምናልባትም የቅርብና የሩቅ ጎረቤት በሚል መከፋፈል ይቻላል። ያም ሆኖ ለጎረቤት ሀገር ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል። ለዚህም ጂኦግራፊው ያስገድዳል።

ከሩቅ ካሉ ሀገራት ጋር ምናልባትም በተወሰኑ ጥቅሞች ጉዳይ መገናኘት ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ከቅርብ ጎረቤት ጋር የሚኖረው የግንኙነት አድማሱ በጣም ሰፊ ነው። ይህም ማለት በሆነ ጉዳይ ላይ ብቻ እንገናኝ ማለት አይቻልም። ለአብነትም ኢትዮጵያ እና ኢምሬት በጂኦግራፊያዊ አቀማመጣቸው ጎረቤት አይደሉም። ስለዚህ ግንኙነት ሊመሠርቱ የሚችሉት በተመረጡ ጉዳዮች ላይ ብቻ ነው።

ኢትዮጵያ ከኤርትራ እና ከሶማሊያ ጋር የሚኖራት ግንኙነት እንደሌሎች ሀገራት አይሆንም። ምክንያቱም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አለ። የማንነት ተመሳሳይነት ይኖራል። ጎረቤት በመሆን ብቻ ሕጋዊና ሕገወጥ የንግድ ግንኙነት ይፈጠራል። ድንበር በጋራ ማስተዳደርም አለ።

ሌላው ከጎረቤት ሀገር ጋር ግንኙነት የሚመሠረተው በመምረጥ አይደለም። ነገር ግን ከሌሎች ሀገራት ጋር ግንኙነት የሚመሠረተው በምርጫ ነው። ለአብነት ከመካከለኛው አፍሪካ ሀገራት ከየትኞቹ ጋር መጠቃቀም እንችላለን ብሎ መምረጥ ይቻላል። ጎረቤት ሀገር ጋር ሲመጣ ግን በዚህ መንገድ መምረጥ አይቻልም። በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ፖሊሲ ከ2010 ወዲህ ለጎረቤት ሀገራት ትኩረት የሰጠ ነው ሲባል፤ በብዙ ሥራዎቻችን ቅድሚያ ለጎረቤት እንሰጣለን ማለት አንደኛው ሲሆን፤ ሁለተኛ ደግሞ ከሁሉም ጎረቤት ሀገራት ጋር መልካም ግንኙነት ለመመሥረት ጥረት ይደረጋል ማለት ነው።

ከለውጡ አስቀድሞ በነበሩ ዓመታት ኤርትራን በጠላትነት የማቆየት ስትራቴጂ ነበር። ከሶማሊያና ከኬንያ ጋር ስንገናኝም ሁልጊዜ ይህን ታሳቢ ያደረገ ግንኙነት ነበር። ጎረቤት ተኮር እናድርገው ሲባል ግን፤ ሁሉንም ጎረቤት ሀገራት በተቻለ መጠን ወደ አንድ ማምጣት የሚችል ፖሊሲ ከሁሉም ጋር በሠላም መኖርን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡

ጎረቤት ተኮር ፖሊሲ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያለው ሌላ ትርጉም አንዱ በሌላ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት፤ አንዱ የሌላ ሀገርን ተቃዋሚ ኃይል ማሠልጠን፤ ማስታጠቅና መሰል ልምዶች ላለፉት 50 እና 60 ዓመታት ነበሩ። ከ1960 ዎቹ ጀምሮ ከዚህ የተነሳ በኢትዮጵያና በጎረቤት ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት አንድ ጊዜ ሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀዝቀዝ እያለ እንደየወቅቱ ሁኔታ የሚቀያየር ነው። ለምን? ቢባል አንዱ በአንዱ ጉዳይ ጣልቃ መግባት የተለመደ ነው።

ቀላል ምሳሌ ብናነሳ በቅርቡ የኤርትራው ፕሬዚዳንት በሰጡት ቃለምልልስ ብዙ ሰዓት ስለኢትዮጵያ ሲያወሩ ተደምጠዋል። እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ነበሩ፤ አሁንም አሉ። አሁን ላይ የተለወጠው ነገር እኛ በጎረቤት ሀገር ጉዳይ እጃችንን አናስገባም። በመፈቃቀድና በመተባበር ካልሆነ በስተቀር በሚል የፖሊሲ እይታ ለውጥ ተከስቷል። ሌላው ጎረቤት ሀገርን በተመለከተ የሠላም ተዋናይ መሆን የሚል አንድምታ አለ። ለአብነትም ገና ‹‹ሀ›› ብሎ ለውጡ ሲመጣ ሱዳን ከአልበሽር መወገድ ጋር ተያይዞ በሲቪሊያኑና በወታደራዊ ኃይል መካከል አለመግባባት ሲፈጠር የማደራደር ሥራዎች ተሠርተዋል።

በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያና በኤርትራ መካከል ወደአንድነት የመምጣት ፍላጎት ሲታይ እና በዚህም ጅቡቲ ስትቀየም የመዳኘት ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል። ይህ የሚያሳየው በመጀመሪያ ደረጃ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለን ችግር መፍታት ነው። ከዚህ ባለፈም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለን ግንኙነት የሚቃኘው ከኃያልን ሀገራት ጋር ያለንን ግንኙነት መሠረት በማድረግ ነበር። አሁን ላይ ግን ይህ ተቀይሯል። ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለው ጥቅም የሚሰላው በራስ ውሳኔ ነው። ያኔ ቢሆን ኃያላን ሀገራት ምን ይፈልጋሉ? ምን ይላሉ? የሚለውን መሠረት በማድረግ ነበር። ከዚህ አንጻር ለውጥ አለ ማለት ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በቀጣናው ሠላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን እያደረገች ያለውን ጥረት እንዴት ይመለከቱታል?

ዳርእስከዳር (ዶ/ር)፡- እኛ ለጎረቤት ሀገራት ሠላም አስተዋፅዖ እናደርጋለን ስንል የሠላም ጥረቱን የምናደርገው በሰው ሀገር ውስጥ ነው። ይህም የመሳካት ዕድሉ የሚወሰነው በአብዛኛው በዛ ሀገር ፍላጎት ነው። ለአብነት ደቡብ ሱዳንን አደራድራለሁ ወይም ሠላም ለማምጣት እጥራለሁ ሲባል፤ የእኛ ጥረት የእኛ የዲፕሎማሲ አቅምና ተፅዕኖ የመፍጠር ሁኔታ የተወሰነ አስተዋፅዖ አለው። ነገር ግን የሠላም ጥረቱን የሚቀበለው ሀገር ወሳኝ ነው።

ባለፉት ስድስት ዓመታት የታዘብነው ነገር ይህንን ነው። የመጠራጠርና በጠላትነት የመተያየት ሁኔታ ነበር። የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በአንድነት እንሥራ ወደ መተባበር እንምጣ በመደመር አስተሳሰብ አንድ ላይ እንቁም እንበርታ የሚለው አመለካከት ሲመጣ ተመሳሳይ ምላሽ ቢገኝ ጥሩ ነበር።

ሌላው ሠላምን ለማምጣት በምናደርገው ጥረት፤ በአንድ በኩል ሠላምን ለማምጣት ጥረት እናደርጋለን። በሌላ በኩል የራሳችን ፍላጎት አለን። ለጎረቤት ሀገር ሠላም እንደምንሠራው ሁሉ ለእኛ ጥቅም እንሠራለን። ለአብነት የባሕር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ መሠረታዊ ፍላጎት ነው። ዓባይ ግድብን መገደብ መሠረታዊ ፍላጎት ነው። ነገር ግን ይህን ስናደርግ ደስ የማይለው ጎረቤት ሀገር አለ። ይህ ደግሞ የሚፈጥረው የራሱ የሆነ ችግር አለ።

በጎረቤት ሀገራት ሠላም ለማምጣት ብዙ ጥረት ተደርጓል። ለአብነት ሱዳን ወደ ጦርነት ከመግባቷ አስቀድሞና ከገባች በኋላም ብዙ ጥረት ተደርጓል። ነገር ግን ሱዳን ላይ ሠላም እናመጣለን የሚሉ ብዙ ተዋናዮች አሉ። ሌሎች በሌላ መንገድ ሲገቡ፤ ከባድ ይሆናል። ደቡብ ሱዳን ላይ ጥሩ ተደማጭነት አለን። በማደራደርም የተሻለ ሠላም እንዲመጣና ግጭቶች እንዲቆሙ በማድረግም ከለውጡ አስቀድሞ የተሠሩ ሥራዎች ስኬታማ ናቸው። ምናልባት ደቡብ ሱዳን ላይ ያለው ችግር ወደ ዲሞክራሲያዊና ወደ ምርጫ ሥርዓት የመምጣት ሂደቱ መጓተት ይታይበታል። ይህ ማለት ሠላም ላይ አልሠራንም ማለት አይደለም፡፡

ሌላው ኤርትራ ላይ የተሠራው ሥራን መጥቀስ ይቻላል። በወቅቱ ቀጣናው ላይ የሠላም ንፋስ እንዲነፍስ አድርጎ ነበር። አዲስ ዓይነት የአፍሪካ ቀንድ እንዲመጣ አድርጎ ነበር። ይሁንና ኋላ ላይ ነገሮች እየተቀየሩ መጥተዋል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሠላም ትልቅ ሚና ተጫውታለች። የሚለው ይወሰዳል። መዘንጋት የሌለበት ግን ሁልጊዜ ለጎረቤት ሀገራት ብቻ ተብሎ አይሠራም፤ የራስ ሥራም ይሠራል። ይህም ምን ዓይነት ለውጥ አምጥቷል የሚለው በቀጣይ አብሮ የሚታይ ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትስስርን ለማምጣት ምን ያህል እየሠራች ነው?

ዳርእስከዳር (ዶ/ር)፡– ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትስስር ለማምጣት የምትሠራቸው በርካታ ሥራዎች አሉ። ሠላም መፍጠር አንድ ነገር ነው። በተፈጠረው ሠላም ላይ ደግሞ ወደ ተሻለ መንገድ መሄድ ሌላ ጉዳይ ነው። በዚህ መንገድ የሚፈጠር ቀጣናዊ ትስስር ወደፊት በጉልህ ሊወሰድ የሚችልና ትልቅ ስኬት ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ምክንያቱም ሠላም ፈጥሮ አብሮ መነገድ ካልተቻለ፤ በጋራ ጉዳዮች ላይ በጋራ መቆም ካልተቻለ፤ ትርጉም የለውም። ለአብነት አሁን ላይ የተጀመሩ ሙከራዎችን ማንሳት ይቻላል።

ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ኢንቨስት ማድረግ ጀምራለች። ይህን የኤሌክትሪክ ኃይል በሠላም ጊዜ ለኬንያ፣ ለሱዳንና ለጅቡቲ ማቅረብ ችላለች። ይህ ማለት ከፖለቲካ ነፃ በሆኑ በእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች በጋራ የሚሠራባቸው ዕድሎች እየሰፉ መጥተዋል። ኢትዮጵያ ከሱዳን ሽንኩርት ሳይቀር ታስመጣለች በጋራ ይነገዳል። ነዳጅም ይመጣል፤ ይህ ትልቅ ዕድል ነው። ይህም ማለት ተቀራርቦና ተነጋግሮ በጋራ የመሥራት ዕድሎች እየጨመሩ ናቸው፡፡

አንዳችን ለአንዳችን ጥገኛ እየሆንን እንሄዳለን ማለት ነው። ስለዚህ የአቅም ግጭት በእነዚህ ሀገራት መካከል ሊመጣ አይችልም። ለአብነትም ከሌሎች ውሃና የኤሌክትሪክ ኃይል ከሚወስዱ ሀገራት ይልቅ ኢትዮጵያና ጅቡቲ የመዋጋት ዕድላቸው ዝቅተኛ ነው። ለምን? እነዚህን ጥቅሞች ላለማጣት ሲባል ችግሮቹን በውይይት የመፍታት ዕድል የሰፋ ይሆናል። ከሱዳንና ከኬንያም ጋር ተመሳሳይ ነው።

ብዙ ችግሮች ከሱዳን ጋር የተፈጠሩ ቢሆንም በመካከል የተፈጠረ የጎላ ችግር አልነበረም። ለምን ቢባል በእነዚህ ጥቅሞች እየተሳሰርን ነው። ከደቡብ ሱዳን ጋር ያለው ግንኙነት እየሰፋ ነው። በመንገድ ሥራ ሁሉ የመሰማራት ፍላጎቶች እየታዩ ናቸው። ያለንን ውስን ሃብት ማካፈል ችለናል። በዚህም እርስ በእርስ መተሳሰር ተችሏል፡፡

ዲፕሎማሲው ቀስ እያለም ቢሆን ሀገርንና ቀጣናውን ሊጠቅም በሚችል መልኩ መስመር እየያዘ መጥቷል። ነገር ግን ከተፅዕኖና ከችግሮች ነፃ ነው ማለት አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም። ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ሱዳን ውስጥ ሠላም ለማምጣት የበዛ እንቅስቃሴ አድርጋለች። ነገር ግን ከዚህም ባለፈ ብዙዎች የተለያየ ፍላጎት እያሳዩ ነው። ስለዚህ ሠላም የመምጣት ዕድሉ ይዘገያል እያለች በተደጋጋሚ ሃሳብ አንስታለች። ይሁንና እንደዚህ አይነት ውስብስብ ጉዳዮች ውስጥ ገብታ ተጨማሪ ራስ ምታት ላለመሆን፤ አሁን ላይ እራሷን ወደኋላ እየጎተተች ነው፡፡

ቀጣናው ትኩረት የሚስብ እንደመሆኑ በተለይም ከእሥራኤል ጋዛ ጦርነት፣ ከሀውቲ ጥቃት ጋር በተያያዘ ወደ አፍሪካ ቀንድ የሚደረገው ትኩረት እየሰፋ ነው። በመሆኑም አንድ ሀገር ብቻዋን ምንም ማድረግ የማትችልበት ሁኔታ እየመጣ ነው። በጋራ መሥራት የሚቻሉትን በጋራ በማጥናት መሥራት ይቻላል። አላስፈላጊ ጫና ውስጥ የሚከቱ ነገሮች ከሆኑ ግን እራስን እያገለሉ መጓዝ ነው። እንዲህ አይነት ሁኔታዎችም እየታዩ ናቸው።

በጋራ መሥራት የሚቻልባቸው ነገሮች ላይ አብሮ በማጥናት እና በመሥራት አላስፈላጊ ነገሮች ሲያጋጥሙ ደግሞ ራስን ማግለል ያስፈልጋል። አሁን የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን እያደረገ ነው። ሶማሊያም ሆነ ሱዳን ላይ ተመሳሳይ ችግሮች አሉ። ደቡብ ሱዳን ላይ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ በጣም ስትሠራ ነበር። አሁን ኬንያ ዋና ተዋናይ ሆና እየመጣች ነው። ኬንያ ከተሳካላት መልካም ዕድል ብሎ መተባበር ነው። በበጎ መንፈስ የሚመጡ ተዋንያን ካሉ አብሮ መሥራት ነው። በአጥፊ መንፈስ እኔ ብቻ ላድርግ ብለው የሚመጡ ካሉ እስከሚቻለው ድረስ ሔዶ ራስን ማግለል ነው። እንደዚህ ዓይነት ነገር ቀጣናው ላይ አለ።

አዲስ ዘመን፡- የባሕር በርን በተመለከተ ኢትዮጵያ እየሄደች ያለችበትን መንገድ እንዴት ያዩታል?

ዳርእስከዳር (ዶ/ር)፡- ኢትዮጵያ የባሕር በር ያስፈልጋታል አያስፈልጋትም፤ ጥያቄው መቅረብ አለበት የለበትም የሚለውን ድልድይ አልፈነዋል። እነዚህ አሁን ተመልሰዋል። ብዙ የዓለም ክፍል ያስፈልጋችኋል። የባሕር በር ጥያቄ መቅረቡም ችግር የለውም የሚባልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ቀጣዩ ነገር እንዴት ታገኙታላችሁ የሚለው ነው። ለእዚህ ደግሞ ብዙ ፖለቲካዊ እና ሕጋዊ አቅጣጫዎች እየታዩ ናቸው።

የባሕር በር ጥያቄ ለኢትዮጵያ የግድ የሕልውና የሆነ ጉዳይ ነው። ይህንን የምንለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ታዳጊ ነው። ታዳጊ ኢኮኖሚ እና ታዳጊ ሕዝብ አለ። ይህንን የሚያህል ሕዝብ ይዞ በትንሽዬ ፖርት ላይ፤ ለዛውም በደካማ መሠረተ ልማት በአንድ የባቡር መስመር፤ እየተበላሸ በሚቋረጥ አንድ የአስፓልት መንገድ ላይ ለዘላለም እኖራለሁ ብሎ የሚያስብ ሀገር የለም።

አንደኛ በጅቡቲ በኩል በቂ መሠረተ ልማት የለም። በሌላ በኩል አንድ ፖርት ላይ መንጠላጠል ደግሞ ለተጋነነ ዋጋ ያጋልጣል። ይኼኛውን ወደብ ከዚህኛው ወደብ አወዳድሬ እጠቀማለሁ የሚባል ነገር የለም። የሚሠራው እንደተፈለገ በባለወደቡ በተወሰነ ሂሳብ ነው። በሌላ በኩል አንድ ሀገር በምንም መልኩ የሌላ ሀገር ጥገኛ መሆን የለበትም። ይህ ከደኅንነትም አንፃር መታየት አለበት።

ደኅንነት ሲባል ከፖለቲካ አንፃር ሳይሆን ከዋስትና አንፃርም መታየት አለበት። ለምሳሌ ድንገት ጅቡቲ ውስጥ ወይም በመስመሩ ላይ የሆነ ነገር ቢፈጠር፤ መርካቶ ላይ የፍጆታ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ያሻቅባል። ሌላው የምናስገባቸውን የፀጥታ መሣሪያዎች የሚለውን እንኳን ትተን የፍጆታ ዕቃ ለማግኘት አዳጋች ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ያጋጥማል። ስለዚህ ለኢትዮጵያ አማራጭ በጣም ያስፈልጋታል።

በሌላ በኩል ከደኅንነት አንፃር ለምሳሌ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ሲጀምር፤ በዛ ጊዜ በአሰብ ወደብም እንጠቀም ነበር። ወዲያውኑ ጦርነቱ ሲጀመር ኤርትራ ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ ሊጫኑ ተራግፈው የነበሩ ንብረቶች በሙሉ እዛው ቀሩ። ንብረቱ ይቅር ግድ የለም። ነገር ግን ድንገት ሳንዘጋጅ በጅቡቲ በኩል ለማስገባት ተገደድን። ጅቡቲ ስንጠቀም በሰው ወደብ ስለምንጠቀም የማዕቀብ ሰለባ ሆነናል። ጅቡቲ ላይ ሌላው ቁጭ ብሎ እኛን ይከታተላል። በቀጣይ ምን ይሆናል? ምን ሊፈጠር ይችላል? የሚለውን አናውቅም።

የትግራይን ጦርነትም እንጥቀስ። እዛ ጦርነት ውስጥ መግባታችን አለመታደል ነው። ነገር ግን ጦርነቱ በተለይ ሁለተኛ እና ሦስተኛው ዙር ላይ አቅጣጫው ያተኩር የነበረው መስመሩን በመያዝ፤ በኢትዮጵያ ላይ ትልቅ ችግር ለመፍጠር ታስቦ ነበር። ስለዚህ ሀገራዊ ደኅንነታችን ራሱ አደጋ ውስጥ ይገባል ማለት ነው። ምናልባት ደግሞ ሌላ ልናየው የምንችለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤት አባላት አጀንዳ አድርገው ሲናገሩ፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆኑ የሚቀራት አንድ ነገር ብቻ ነው። እርሱም በቅርቡ ይሳካል ብለው ስለባሕር በር ሲናገሩ ነበር።

ወደ ፊት ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ወይም በአፍሪካ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን ትችላለች ወይ? ሲባል የመሆን ዕድል አላት አቅሙ አላት፤ ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን አትችልም። ስለዚህ ያለንን አቅም ለመጠቀም የባሕር ኃይል በማቋቋም የወታደር ኃይሉን በመሬት እና በአየር ላይ ብቻ ሳይሆን በውሃ ላይም መኖር አለበት። ለዛ ደግሞ የባሕር ኃይል እናቋቁማለን ተብሎ ከለውጡ ጀምሮ ሲሠራ ነበር። እነዛን መሬት ላይ እናስቀምጣቸውም፤ የውሃ አካል ያስፈልጋቸዋል።

እንደተራ ዜጋ ደግሞ ከተቻለ አሰብን ካልሆነም ሌላ የባሕር በር ብናገኝ ብዬ አስባለሁ። ኢሕአዴግ ከፍተኛ ድጋፍ ያጣበት ትልቅ ምክንያት ይኸው ነው። የባሕር በር ቢገኝ መንግሥት ከፍተኛ ድጋፍ ያገኛል።

በተጨማሪ በተለያየ ምክንያት የባሕር በር ያስፈልጋል። ከታሪክ አንፃር እናንሳም ቢባል አሰብ፣ ታጁራ፣ በርበራ፣ ዘይላ እነዚህ ሁሉም አካባቢዎች የኢትዮጵያ የባሕር መዳረሻ ነበሩ። ነገር ግን ኦቶማንስ ከመጡ በኋላ አንዴ አንዱን ስናጣ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሌላኛውን ስናጣ፤ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ አንዴ ወደ ዘይላ እያልን ቆየን። ከዛ ኮሎኒያሊዝም ሲመጣ ያው የሚታወቀው ሆነ። አንዴ የእኛ የነበረን ነገር መጠየቅም ላያስፈልግ ይችላል። ያው በፊት ስለነበረን አሁንም ይኑረን ሲባል ለጎረቤት ሀገራትን ሊያስቆጣ ይችላል። ነገር ግን ይሄን ጥያቄ የጎረቤት ሀገሮች ችላ ይሉታል ብዬ አላስብም።

ቀንዱ ላይ ያለችው ትልቋ ሀገር፤ በር ተዘግቶባት በሌሎች ሀገሮች እስከ መቼ ጥገኛ መሆን እንደሚቻል አይታወቅም። ከኤርትራ ጋር የተፈጠሩ አንዳንድ ሁኔታዎች፤ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነትም ልናገኝ እየቻልን እንዳጣን ፖለቲካው ያሳየናል። ስለዚህ ይህንን ጉዳይ ማንሳት ወቅታዊ ብቻ ሳይሆን እጅግ አስፈላጊ ነው። አሁን ዋናው ነገር በምን መንገድ እናግኘው የሚለው ነው።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የባሕር በር ልታገኝባቸው የምትችልባቸውን አማራጮች እንዴት ያዩታል?

ዳርእስከዳር (ዶ/ር)፡- ሕጉ በቀጥታ የባሕር በር ማግኘት ይቻላል አይልም። ነገር ግን መውጫ መግቢያ የማግኘት መብት እንዳለን ያስቀምጣል። ይኼም ከዛ ሀገር ጋር በሚኖራቸው መልካም ስምምነት መጠቀም ይችላሉ ይላል። መግቢያ መውጫ የማግኘት ጉዳይ ጅቡቲ ብቻ ሳትሆን ሶማሌ ላንድም ፈቅዳልናለች። ግን ደግሞ ሕጉ ላይ ያለው በሁለቱ ሀገራት መካከል መደራደር ከተቻለ ባሕር በር ማግኘት እንደሚቻል ተቀምጧል። ለምሳሌ ጅቡቲ የሆነች መሬት በሆነ ዓይነት መንገድ ብትሰጠን፤ ኢትዮጵያ በአንድ ጊዜ የባሕር በር ባለቤት ሆነች ማለት ነው።

ለሕግ መገዛት ጥሩ ስለ ሆነ እና ኢትዮጵያም የሠላም አማራጭን የምትከተል ሀገር ስለሆነች እየሄደች ያለችውም ሠላማዊ በሆነ መንገድ ነው። ዋናው ትኩረት ማድረግ ያለብን ፖለቲካውን ነው። ፖለቲካው ላይ ያሉትን ዕድሎች በደንብ ማጤን ያስፈልጋል። ያሉ ጥያቄዎች ምንድን ናቸው? ለማን ምን መስጠት አለብን? ከማን ምን መቀበል አለብን? የሚለውን በደንብ አስልቶ መሥራት ነው። የተገኘውን አማራጭ ሁሉ መጠቀም ያስፈልጋል። አሁን የመግባቢያ ስምምነቱም የእዛው አካል ነው።

ሶማሌላንድ ላለፉት 31 ዓመታት ከሶማሊያ የተገነጠለችው በኢትዮጵያ ምክንያት አይደለም። በራሷ ምክንያት ነው። የሶማሊያ ችግር እና የሶማሌላንድ ችግር የእኛ ችግር አይደለም። እኛ ሀገር እየፈጠርን አይደለም። ቀድሞም ሀገር ተፈጥሯል። ኤርትራ ቢባል በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ ተዋጊዎች መካከል በተፈጠረ ጦርነት ኢትዮጵያ ዕውቅና ሰጥታ የተፈጠረች ሀገር ናት ማለት ይቻላል።

ሶማሌላንዶችን ግን ዚያድባሬ በጦር ጀት ጨፈጨፋቸው፤ ከዛም ከዚህ በኋላ የሶማሊያ አካል አንሆንም ብለው የራሳቸውን መንግሥት መሠረቱ። የራሳቸውን የተሻለ ሥርዓት እና መንግሥት መሥርተዋል። ላለፉት 30 ዓመታት ነክተናቸው አናውቅም። ፖለቲካዊ ንግግር ሲደረግ እዛ ጋር ተደረሰ። ደግሞም ሶማሊያዎች ራሳቸው በሕገመንግሥታቸው ሶማሌላንድ የሶማሊያ ግዛት እንዳልሆነች አስቀምጠዋል። ስለዚህ ባለው ነገር እኛ ልንጠቀም ብናስብ ምንም ክፋት የለውም። ክፍተት ካለ ማንኛውንም አማራጭ ከመጠቀም ወደ ኋላ አንልም።

አብሮ የሚሠራ ካለ አብረን እንሠራለን። ይህ ሁሉም ሀገር የሚያደርገው ነው። ለምሳሌ እኛ በዚህ ሰዓት ይህንን አስልተን አብሮን ከሚሠራው ጋር እንተባበራለን። የእኛ ሐቅ ይህ ነው። ግን ደግሞ በጎን የሚጠበቅም የማይጠበቅም ውጤት እያየን ነው። መቼም ሁሉም ነገሮችን ከራሱ ጥቅም አንፃር ነው። ይሄ ጥያቄ የጎረቤት ሀገራትም መካከል በተለይ በአንዳንዶቹ ያልተገራ የመንግሥት ባሕሪ ያላቸው ላይ አላስፈላጊ ምላሽ ሊመጣ እንደሚችል ይታወቃል።

አንዳንዶቹ ደግሞ ነገሩን በጣም በመለጠጥ ከቀጣናው ውጪ ያሉ ሀገሮች ወደ ቀጣናው እንዲመጡ እያደረጉ ነው። አንድ ዓመት ሳይሞላ ብዙ ነገሮች እየተለወጡ እያየን ነው። ለምሳሌ ኤርትራ ምክንያቷን ግልፅ ሳታደርግ ለምን ከሶማሌላንድ ጋር ተፈራረማችሁ ተደራደራችሁ ብላ እየተቃወመች አይተናታል። የት ድረስ ልትሔድ እንደምትችል አይታወቅም፤ መገመት ግን ይቻላል። ስለዚህ የባሕር በር ጥያቄ ቀጣናውንም ሊቀይር የሚችል ትልቅ ጥያቄ ነው። በዚህም በዚያም የተለያዩ አሰላለፎችን ሊስብ እንደሚችል ይታወቃል። በቀላሉ ሊገኝ እንደማይችል ይታወቃል። ብዙ ጥረት እና ልፋት እንዲሁም ብዙ ዋጋ መክፈል ሊጠይቅ ይችላል። ያንን ለማግኘት ብዙ መስጠትም ሊኖርብን ይችላል።

አዲስ ዘመን፡- ከሶማሊያ ጋር ያለንን ግንኙነት በተመለከተስ ምን ይላሉ?

ዳርእስከዳር (ዶ/ር)፡- ሶማሊያ ላይ የተፈጠረው ምንድን ነው? የሚለውን እንይ ከተባለ የኢትዮጵያ መንግሥት ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ፤ ሶማሊያ ውስጥ ሠላም ለማምጣት በሁለትዮሽ ስምምነትም፣ በተባበሩት መንግሥታትም ሆነ በአፍሪካ ኅብረት በኩል አብሮ እየሠራ ነው። 98 ላይ እስላማዊ ኅብረት ፍርድ ቤቶች ተፈጠረ። ሠላማዊ ወታደራዊ ቡድን ተመሠረተና መቋዲሾን እና አካባቢውን እስከ ባዲዋ መቆጣጠር ጀመረ። ከዛ ቀጥሎ ‹‹ኢትዮጵያን እወራለሁ አንዋር መስኪድ እሰግዳለሁ ማለት ጀመረ፡፡›› በሠላም ሃይማኖታዊ መሠረት አለኝ ብሎ ለመስገድ ቢመጣ ማንም አይከለክለውም ነበር። ነገር ግን ዓላማው መሬቱን ወርሬ የግሌ አደርጋለሁ የሚል ሆነ፡፡

ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃ እንደዚህ ዓይነት የአሸባሪ ኃይል ጉልበት ሲፈረጥም በተለይ ከ1994 ዓ.ም ወዲህ ማለትም አሜሪካን ላይ የናይን ኢለቨን የሽብር ጥቃት ከደረሰ ወዲህ ዓለም ሽብርተኛን የማትታገስበት ዘመን ነበር። ስለዚህ ከ1998 ዓ.ም በኋላ አልሸባብ እየተጠናከረ የተለያዩ አካባቢዎችን ሲይዝ፤ ከዛ ኢትዮጵያ እመጣለሁ ሲል፤ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚነካ ነበር። የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን በቀጣናው ላይ ትልቅ ሚና ያላትን የአሜሪካንንም ጥቅም የሚነካ ነበር። ስለዚህ ኢትዮጵያ ከሌሎች ኃያላን ሀገራት ጋር ምላሽ መስጠት ነበረባት፤ ስለዚህ ገባች። ከዛ ጊዜ ጀምሮ ሶማሊያ ውስጥ ሽግግር መንግሥት በመመሥረት፤ ሶማሊያን በመጠበቅ ብዙ ጥረት ሲደረግ ነበር።

አሁን ሶማሊያ ለደረሰችበት ስኬት ኢትዮጵያ ብዙ ዋጋ ከፍላለች። ከዛ ከኢትዮጵያ ጣልቃ መግባት በኋላ፤ በአፍሪካ ኅብረት ውሳኔ መሠረት ዩጋንዳ፣ ኬንያ እና ሌሎች ሀገራትም እንዲገቡ ተደረገ።

ኢትዮጵያ ከውጪ ያለውን ሠራዊቷን ሙሉ ለሙሉ ብታስወጣ መቋዲሾስ መቀጠል ትችላለች ወይ? ኢትዮጵያ ብትወጣ፣ ኬንያውያን፣ ታንዛኒያውያን ሊተኳት ይችላሉ? የሚለው ያጠያይቃል። እኛ ሠላም አስጠብቁ ካሉን ከማስጠበቅ ወደ ኋላ አንልም። የኢትዮጵያ መውጣት ሶማሊያን ምን ሊያደርግ እንደሚችል ይታወቃል። የኢትዮጵያ አለመግባት አልሸባብን ሊያጠነክረው ይችላል። ስለዚህ ኢትዮጵያ ልትገባ ትችላለች ወይም ሌሎች አማራጮች ሊኖሩ ይችላሉ። በቀጣይ ሁሉንም የምናየው ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሠግናለሁ።

ዶ/ር ዳርእስከዳር፡- እኔም አመሠግናለሁ።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You