ኢትዮጵያ በቀደመ ታሪኳ በቀይ ባሕር ላይ በምሥራቅ አፍሪካ ግዙፍ የፖለቲካና የንግድ ተፅዕኖ የነበራት ሀገር ነች። በቀደሙት ዘመናት የሥልጣኔ ቁንጮና ስመ ገናና ሀገር ከምሥራቅ አፍሪካ ተሻግራ ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ ከአውሮፓና ከእስያ ሀገራት ጋር ጠንካራ የንግድና የዲፕሎማሲ ግንኙነትም ስታደርግ ቆይታለች። ሀገሪቱ በቀይ ባሕር ዙሪያ ሁለንተናዊ ግንኙነት ስታደርግ የቆየችው በጊዜው የነበሯትን የባሕር በሮቿን ተጠቅማ ነበር።
የኢትዮጵያ ግዛት የነበረችው ኤርትራ በሕዝበ ውሳኔ ከተገነጠለች በኋላም የጎረቤት ሀገራት አማራጭ ወደቦችን በመጠቀም ከተቀረው ዓለም ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ታስቀጥል እንጂ በቀይ ባሕር ላይ የነበራት የደኅንነትና የፖለቲካ ተፅዕኖ በእጅጉ አሽቆልቁሎ ነበር። ይህ አካሄድ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት በሚፈለገው መጠን እንዳይፋጠን ከማድረግ ባለፈ በንግዱም ቢሆን ለከፍተኛ የወደብ ኪራይ ወጪ የዳረገ ነው።
ይህ ዘርፈ ብዙ ምክንያት ኢትዮጵያ የማይዋዥቅና አስተማማኝ የሆነ የንግድ እንቅስቃሴ የምታደርግበትን የንግድ ወደብ ጨምሮ ፖለቲካዊና ፍላጎቶቿን ጭምር የምታስተናግድበት ነፃ፣ ከጣልቃ ገብነት የተገደበ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት የሚጠቁም ነው።
ከኢኮኖሚና ንግድ አንፃር ጉዳዩን ከቃኘነው ኢትዮጵያ ከቀሪው ዓለም ጋር ያላትን የንግድ ትስስር ለማቀላጠፍና የገቢና የወጪ ንግድን ለማሳለጥ የጅቡቲን ወደብ በመጠቀም ረጅም ጊዜ አስቆጥራለች። አሁንም ቢሆን ‹‹የኢትዮጵያን ወጪና ገቢ ምርት በማሳለጥ ረገድ የጅቡቲ ወደብ ዋነኛ የልብ ትርታ ነው›› ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ በዋጋ መናርና በተለያዩ ምክንያቶች በየጊዜው የሚጨምረው የኪራይ ዋጋ የኢትዮጵያን ዘላቂ ልማት የሚያረጋግጥ አይደለም። ወደቡ ከንግድ ፍላጎቶች ባሻገር የኢትዮጵያን በቀይ ባሕር ላይ ያላትን ተፅዕኖ ለማሳደግ ፋይዳ ያለው ባለመሆኑም ሁለንተናዊ ጥቅምን ከማሳካት አንፃር ሚናው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
በንግዱም ቢሆን አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ የጅቡቲን ወደብ ብቻ በመጠቀም ኢኮኖሚዋን ማሳደግ አትችልም። በቀይ ባሕር ላይ ያላትን ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ለማሳደግም የኪራይ ወደብ ብቻ ተጠቃሚ መሆን በቂ አይደለም። በዚህ ምክንያት ከወደብ ባሻገር ቀደም ሲል በቀጣናው የነበራትን የቀይ ባሕር ተፅዕኖ የሚመልስ የባሕር በር ያስፈልጋታል።
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግሥት ከጅቡቲ ወደብ ባለፈ የአሰብና በርበራ ወደቦችን በጋራ አልምቶ ለመጠቀም በተለያዩ ጊዚያት ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቷል። ለንግድ እንቅስቃሴ ከሚደረገው የወደብ ኪራይ ስምምነት የዘለለ የሀገሪቱን የቀይ ባሕር ተፅዕኖ ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ የሚያጎላ ጥያቄ የለውጡ መንግሥት በአጀንዳነት እያቀነቀነ ነው። ይህ ጥያቄ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት በጉልህ የሚያሰምር ነው።
መንግሥት ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ተፈጥሯዊ፣ ሕጋዊና ታሪካዊ መብት እንዳላት ከማንሳት በዘለለም ለተግባራዊነቱ መሬት የወረደ እርምጃዎችን ወስዷል። ከሶማሌ ላንድ ጋር ለወታደራዊና ለንግድ አገልግሎት የሚውል የባሕር በር ማግኘት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ይሁን እንጂ ይህ እርምጃ በብዙዎች ዘንድ አቧራ ያስነሳ ነበር።
በተለይ ስምምነቱ ያልተዋጠላት ሶማሊያ ‹‹ሉዓላዊነቴ ተደፍሯል›› በማለት ክስ በማቅረብ ነገሩን በአግባቡ ካለመረዳት እና በሌሎች ሀገራት ጫና ውስጥ እንድትቆይና በቀጣናው ውጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ሆና ቆይታለች።
ጉዳዩ ከውጪ ብቻ ሳይሆን ከሀገር ውስጥም ጭምር ትኩረትን የሳበ ቢሆንም ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቷን ለማሳካት የሚፈለገውን ሕጋዊ እርምጃዎች እንደምትወስድ ያረጋገጠ ነበር። ይህ ታሪካዊ ውሳኔ በአንዳንድ የኢትዮጵያውያን ዘንድ አሉታዊ ጥርጣሬም የፈጠረ ነበር። ሶማሊያም በግብፅ በሚደርስባት ተፅዕኖ በመነሳትና በአጉል ጥርጣሬ ጥያቄውና አካሄዱ ሉዓላዊነቴን የሚዳፈር ነው በማለት ተደጋጋሚ ክስና ዛቻዎችን ስትሰነዝር ተደምጣለች።
እውነታው ግን ኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የኢኮኖሚ ደረጃ የሚመጥን የወደብ አገልግሎት እንዲሁም ከኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች የተሻገረ ፖለቲካዊ ተፅዕኖዋን በቀይ ባሕር ላይ የሚያጎላ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት በማመኗ በሠላማዊ መንገድ ጥያቄ ማቅረቧ ነው።
ከላይ ባነሳነው መሠረታዊ ምክንያት በተለይ የውጪ ኃይሎች በሚፈጥሩት ጣልቃ ገብነት እና ጫና በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ሙከራዎች ተደርገዋል። በዚህም አለመግባባቱን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ኢትዮጵያና ሶማሊያ በቱርክ አንካራ ለድርድር መቀመጣቸው ይታወሳል።
በሦስት ዙር በተካሄደው በዚህ ድርድር የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄና ፍላጎት እንዲሁም የሶማሊያን ሉዓላዊነት ባከበረ መልኩ እንዲፈፀም ስምምነት ላይ ተደርሷል። ስምምነቱ ለኢትዮጵያን ታላቅ የዲፕሎማሲ ድል ተደርጎ የሚወሰድ ነው። በአንካራው ስምምነት ኢትዮጵያም ሆነ ሶማሊያ በትብብር ለጋራ ብልፅግና ወደፊት መሥራት እንዳለባቸው ተገልጿል። በዚህም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያ ላነሳችው የባሕር በር ጥያቄ እውቅና አግኝታለች።
የአንካራው ድርድር በሉዓላዊ ሶማሊያ መንግሥት ስር ኢትዮጵያ አስተማማኝ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀና ዘላቂ የባሕር በር እንድታገኝ የሚያስችል፤ ለሁለቱም ሀገራት ጠቃሚ የሆኑ የኪራይ፣ የኮንትራትና ተመሳሳይ የንግድ አሠራር መንገዶችን በጋራ በመሆን ለማጠናቀቅ መስማማታቸው የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ እንደሚመልስ ይታመናል።
ከሁለቱ ሀገራት በሚውጣጡ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት በሚደረገው ቀጣይ ስምምነት ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር መተላለፊያ ለማግኘት የሚያስችል የተሟላ ስምምነት ላይ ከደረሱ ለሀገራችን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል። በተለይ በዚህ የወቅቱ የሀገራችን አንገብጋቢ ጥያቄ ዙሪያ ሶማሊያ እውቅና መስጠቷ በጋራ ለመልማት ያላትን ፍላጎት የሚያሳይና ለድርድሩ ተፈፃሚነት በር ከፋች ነው። ይህም በየካቲት ወር መጨረሻ ሁለቱ ሀገራት በቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ለሚያደርጉት ውይይት በተለይ ለኢትዮጵያ ትልቅ ግብዓት ሆኖ ያገለግላል።
ከዚህ ቀደም አትዮጵያ ሕዝቦቿን በኢኮኖሚና ለመለወጥና በቀይ ባሕር ዙሪያ ያላትን ሁለንተናዊ ተፅዕኖ ለማሳደግ የጋራ ተጠቃሚነትን መርሕ መሠረት ባደረገ መልኩ ሶማሊያን ጨምሮ የሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ያቀረበችው ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ ሲጥላላና ሲናናቅ ቆይቷል፤ ይህ ፍፁም ስህተት እንደነበር የቅርብ ጊዜዎቹ አለመግባባቶች ያመለክታሉ። ምክንያቱም አሁን ላይ የዚህች ታላቅ ሀገር የባሕር በር ጥያቄ ከማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ደርሷል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃም ምላሽ እንደሚያሻው እየታመነበትና ፈር እየያዘ መጥቷል።
ቀጣዩ የቤት ሥራ ቀጥተኛ የባሕር በር ተጠቃሚ የሚያደርገንን ጥያቄ በሠላማዊ መንገድ አጠናክሮ ማስቀጠል ነው። በተለይ ከሶማሊያ ጋር የተደረገው ስምምነት ተከትሎ የሚደረጉ ዝርዝር የአፈፃፀም ድርድሮችን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ባስጠበቀ መንገድ እንዲፈፀም መሥራት ይገባል። ስምምነቱ ሳይሸራረፍ ገቢራዊ ማድረግና ለተግባራዊነቱ ሌት ተቀን መሥራት ያስፈልጋል።
መላው ኢትዮጵያውያንም ለልጆቻቸው፣ ለልጅ ልጆቻቸውና ለመጪው ትውልድ የሚጠቅምና የቀድሞውን ኃያልነታችንን የሚመልስ የባሕር በር የማግኘት ሠላማዊ ጥያቄ እውን እንዲሆን በፍላጎት መደገፍ ይጠበቅባቸዋል። ጊዜው ከተናጠል ይልቅ በትብብር መሥራትን የሚጠይቅ ከመሆኑ አንፃር ሁሉም የቀጣናው ሀገራትም ቢሆኑ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት በጋራ አልምተው በጋራ የሚለወጡበትን አካሄድ ይከተላሉ ተብሎ ይጠበቃል!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 14 ቀን 2017 ዓ.ም