በሀገሪቱ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ የሚገኙ ልዩ ልዩ ተግባሮችን ተከትሎ በየዓመቱ የሚገኘው የምርት መጠን መጨመሩን ቀጥሏል:: መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ ከአንድ ዓመት በፊት የተገኘው ከ500 ሚሊየን ኩንታል የሚልቅ ዓመታዊ ምርት፣ ባለፈው ዓመት ወደ 700 ሚሊየን አካባቢ ከፍ ብሏል:: ዘንድሮ ደግሞ ይህ አሀዝ ከዚህ እንደሚልቅ ይጠበቃል::
ምርትና ምርታማነቱ ቀደም ሲል ይጨምር የነበረው የእርሻ መሬት በማስፋፋት ነበር:: ይህ አንድ መንገድ ነው:: በዚህ መንገድ በየዓመቱ በዘር የሚሸፈነው ማሳ መጠን ሲጨምር ቆይቷል፤ አሁንም እየጨመረ ነው፤ እንደሚጨምርም ይጠበቃል:: ሀገሪቱ ካላት ለእርሻ ሥራ ሊውል የሚችል መሬት አኳያ ሲታይ የተጠቀመችው ገና ውስኑን እንደመሆኑ በእርግጥም ገና ይጨምራል፤ እሰየው! ይጨምር!
ለግብርናው ምርትና ምርታማነት እየጨመረ መምጣት ሌላው መንገድ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ነው:: ከእነዚህ ቴክኖሎጂዎች መካከል አንዱ ማዳበሪያ ነው:: መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት ለማዳበሪያ አቅርቦት ለእዚያም በድጎማ ለማቅረቡ ሥራ ቅድሚያ እየሰጠ ሲሰራ ቆይቷል::
የውጭ ምንዛሪ እያለም በአንዳንድ ጫናዎች የተነሳ ማዳበሪያ ከውጪ ኩባንያዎች ማግኘት ፈተና በሆነበት ዓመት ማዳበሪያ ለመግዛት ያልወጣ ያልወረደበት ቦታ የለም:: ለማናቸውም በሚልም አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲጠቀም አጥብቆ እያሳሰበ ማዳበሪያውን እጁ እንደገባ ሲያቀርብ እንደነበርም ይታወሳል::
ማዳበሪያ ወደብ ከደረሰ በኋላም በአስቸኳይ አርሶ አደሩ ዘንድ እንዲደርስ ለማድረግ በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ በኩል የሚከናወኑ የተጠናከሩ ሥራዎች መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ማደግ ምን ያህል ዋጋ እየከፈለ አንደሚገኝ በሚገባ ያመላክታል::
የግብርና ምርምር ማዕከላት ያፈለቋቸው አዳዲስ ዝርያዎች /ቴክኖሎጂዎች/ ወይም የምርምር ውጤቶች ለግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት መጨመር የራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል:: ማዕከላቱ በየዓመቱ ከሚያዘጋጃቸው የመስክ ጉብኝቶች መረዳት የተቻለውም ይህንኑ ነው፣ በእርግጥም ቴክኖሎጂዎቹ ለምርትና ምርታማነት መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል::
ከምርምር ተቋማት የሚወጡ ቴክኖሎጂዎች ለግብርና ምርትና ምርታማነት መጨመር ምን ያህል አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ የዘርፉ ባለሙያዎች ብዙ የሚሉት ቢኖርም፣ በመስክ ጉብኝትና በመሳሰሉት የተገኙ መረጃዎች አስተዋጽአቸው ከፍተኛ ስለመሆኑ መናገር ያስችላሉ::
አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ፣ አርሶ አደሩ እነዚህን ቴክኖሎጂዎች እንዲጠቀም በመስራት በዘርፉ ለውጥ መምጣት ተችሏል:: በእነዚህ ቴክኖሎጂዎች አንዳንዶች ፈጥነው ተግብረው ተለውጠውባቸዋል፤ በዚያው ልክም አንዳንዶች ደግሞ በጥርጣሬ ሲመለከቱ፣ ቴክኖሎጂዎቹን ሲገፉ ቆይተው ሲቆጩም ተደምጧል:: እናም ከዚህ መቅረት ምን ያህል ሊጎዳ አንደሚችል መገመት አይከብድም::
ይህ ሥራ በሔክታር የሚገኘው ምርት እየጨመረ እንዲመጣ፣ አዳዲስ የምርምር ውጤቶች በአርሶ አደሮች ማሳ እንዲሞከሩና ከዚህም ሌሎች አርሶ አደሮች ተሞክሮና ልምድ ቀስመው በቀጣዩ ዓመት ቴክኖሎጂዎቹን እንዲጠቀሙ ለማድረግ ተችሏል:: ተሞክሮዎቹን ይበልጥ ማስፋትና ሥራ ላይ እንዲውሉ በማድረግ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: ቴክኖሎጂዎቹ ውጤት ስለማምጣታቸው የአርሶ አደሮችን ማሳ አርሶ አደሮች እንዲሁም መገናኛ ብዙሃንና ግብርናውን የሚመሩ አካላት እንዲጎበኙ በማድረግ ለውጡን ለማስረዳት ተሰርቷል::
አርሶ አደሩ እያደር ቴክኖሎጂዎቹን ወደ መጠቀም እየገባ ባለበት ሁኔታ ምክንያቱ ምን ይሁን ምን በውል ባይታወቅም የምርጥ ዘር እንዲሁም የማዳበሪያ አቅርቦት መቆራረጥ ያጋጠመባቸው ወቅቶች እንዳሉ ይታወቃል:: ይህን ክፍተት ለመሙላትም ብዙ ተሰርቷል::
ማዳበሪያና ምርጥ ዘር መጠቀም የምርትና ምርታማነት ማሳደጊያ መንገዶች መሆናቸው ዛሬም ቀጥሏል፤ ነገም እንደዚያው ነው:: ለነገሩ ቴክኖሎጂ መጠቀሙ ተጀመረ እንጂ አይደለም እላይ ወገቡም አልደረሰ:: እነዚህ መንገዶች ምርትና ምርታማነቱን እያሳደጉት እዚህ ደርሰዋል:: ገና ምርትና ምርታማነቱን ይበልጥ ለማሻገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ሥራ ከገቡትና ውጤታማ ከሆኑት የስንዴ መስኖ ልማትና ኩታ ገጠም እርሻ እንዲሁም ሜካናይዜሽን ጋር በመሆን ታምር ይሰራሉ::
አሁን አሁን ደግሞ እነዚህ መንገዶች እንዳሉ ሆነው ለምርትና ምርታማነቱ እድገት አስተዋጽኦ በማበርከት በከፍተኛ ደረጃ እየተጠቀሱ ያሉት እነዚህ ኩታ ገጠም እርሻ፣ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ ሜካናይዜሽን የተባሉት የግብርናው ዘርፍ የእለት ተእለት አጀንዳዎች በእርግጥም በሀገሪቱ ግብርናውን ትራንስፎርም ለማድረግ ለተያዘው ርብርብ ትልቅ አቅም እየሆኑ ናቸው::
እንደሚታወቀው እነዚህን ሁሉ ርብርቦች ተከትሎ በሀገራችን የግብርና ምርትና ምርታማነት እያደገ መጥቷል:: ይህ ለውጥ ግን እስከ አሁንም እንደሚባለው ሀገሪቱ ካላት ለእርሻ አገልግሎት ሊውል የሚችል እምቅ አቅም፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለአግሮ ኢንዱስትሪዎች ግብአት እንዲሁም ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ከሚያስፈልጋት የግብርና ምርት አኳያ ሲታይ የምርትና ምርታማነቱ እድገት ገና ውሃውም አልሞቀ የሚያሰኘው ነው:: ይሄ አምናም ካቻምናም ከዚያም ቀደም ሲልም ሲባል የቆየ ነው፤ ነገም ሊባል የሚችል ነው::
ይህ ማለት ግን በዘርፉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተከናወኑ ሥራዎች የተገኙ ድሎችን ብድግ ብለን፤ ቆመን አናመሰግንም ማለት አይደለም:: በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተመዘገበው ታምር እንዴት ተደጋግሞ አይነሳ፣ እንዴት ተደጋግሞ አይደነቅ:: ይደነቃል፤ ገና ይደነቃል::
ከመረጃዎች መረዳት አንደተቻለው፤ የሀገሪቱ ዓመታዊ የስንዴ ምርት ግኝት ባለፈው ዓመት 250 ሚሊየን ኩንታል ደርሷል፤ መኸርም በልግም መስኖም ብሎ ማለት ነው:: ይህን አሀዝ ዘንድሮ 300 ሚሊየን ኩንታል ለማድረስ ታቅዷል:: የተመጣበት መንገድም እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮችም ይህ እንደሚሳካ የሚያመላክቱ ናቸው::
በእዚህ ስኬት ውስጥ ደግሞ ከፍተኛውን ሚና እየተጫወተ ያለው በቅርቡ በዚህ የለውጥ ዘመን ወደ ሥራ የገባው የስንዴ መስኖ ልማት ያመጣው የምርትና ምርታማነት እድገት ነው:: ይህ ታምር ተደጋግሞ ሊደነቅ ይገባዋል:: ይህን ስኬት እኛ ብቻ ሳንሆን ፈረንጆቹም እያደነቁት ናቸው::
በዚህ ስንዴ ልማት ሀገር ዓመታዊ የስንዴ ፍላጎቷን ሸፍናለች፤ ይህ ብቻ አይደለም፤ ለጎረቤት ሀገሮችም በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ችላለች:: በየዓመቱ ስንዴ ከውጭ ለመግዛት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ አስቀርታለች:: ስንዴ ከውጭ ለመግዛት ያለው ውጣ ውረድ፣ በስንዴው ጥራት ላይ የነበረው ጥርጣሬ፣
የሀገሪቱን የስንዴ ልማት ስኬት መንግስት ብቻ አይደለም ሁሌም በምርጥ ተሞከሮነት የሚጠቅሰው፤ የአፍሪካ ልማት ባንክ አንስቶ አይጠግብም፤ የታንዛኒያ ልኡካን ቡድን ሰሞኑን፣ቀደም ሲል የናይጄሪያ ልኡካን ቡድን ይህን ተሞክሮ ለመቅሰም ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል:: ፋኦ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጠው ሸልማት፣ ሀገሪቱ በቅርቡ ባስተናገደች ከረሃብ ነጻ ዓለም የመፍጠር ጉባኤ ሀገሪቱ በግብርናው ዘርፍ በአጠቃላይ በመስኖ ስንዴ ልማት ያሳየችው ለውጥ የተጠቀሰበት ሁኔታ የስንዴ ልማቱ በተለይ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ በአደባባይ የመሰከሩ ናቸው::
ሰፋፊ ለመስኖ እርሻ ሊውል የሚችል መሬት እንዲሁም ለመስኖ አገልግሎት ሊውል የሚችል ግድብና ወንዝ ባለው በቆላማው የሀገሪቱ አካባቢ አሀዱ ብሎ የጀመረው ይህ የስንዴ መስኖ ልማት ቆላ ደጋ ወይናደጋ ሳይል ተስፋፍቷል:: በየትኛውም ሥነምኅዳር ለመስፋፋት የሚያስችሉ ከበቂ በላይ ምቹ ሁኔታዎች የተፈጠሩለት ነውናም ገና ይስፋፋል::
ሀገሪቱ ምን ያህል ለሜካናይዜሽን እርሻ ባይተዋር ሆና እንደኖረች ይታወቃል:: የግብርና ባለሙያዎች ሁሌም ምክረሀሳብ ሲሰጡበት የቆዩት ይህ ቴክኖሎጂ አሁን እየተስፋፋ መጥቷል:: አርሶ አደሮች እየተደራጁም በግላቸውም ባለሀብቶች ኢንተርፕራይዝ እያቋቋሙም ትራክተሮችን ኮምባይነሮችን ወደ ገጠር እያስገቡ ናቸው:: መንግስትም በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል ለእዚህ ተግባር ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል::
በአንዳንድ የኩታ ገጠም አርሻ በተስፋፋባቸው አካባቢዎች በትራክተር ሲታረስና ማሳ በዘር ሲሸፈን፣ የደረሰው ሰብል በኮምባይነር ሲታጨድና ሲወቃ፣ ምርቱ በከባድ መኪኖች ወይም ማሳ ላይ በተዘጋጁ የምርት ማሳረፊያ ሥፍራዎች ላይ እንዲቆይ ሲደረግ መመልከት የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመረው ጉዞ እምርታ እየታየበት ስለመሆኑ ለመመስከር ማሰብን አይጠይቅም::
ይህ ቴክኖሎጂ ከዓመት ዓመት እየጨመረ ነው:: ፍላጎቱም እንደዚሁ እየጨመረ ነው:: ምርትና ምርታማነቱም በእዚያው ልክ እንደሚጨምር ይጠበቃል:: የኩታ ገጠም እርሻም ከዓመት ዓመት መጨመሩን ቀጥሏል:: በደርግ ጊዜ ሰው በጣም ሲወፍር እንደመንግሥት እርሻ ሰፋህ ይባል ነበር:: አሁን ይህን አይነት ሰው ሲያጋጥም እንደ ኩታ ገጠም እርሻ ሰፋህ ሊባል ይችላል::
በቀጣይም መስፋፋት ይኖርበታል:: አብዛኛው የሀገሪቱ የእርሻ መሬት በአነስተኛ ማሳ ባላቸው አርሶ አደሮች እጅ ውስጥ እንደመሆኑ ይህን ደግሞ ሜካናይዝድ በሆነ መንገድ ለማልማት የግድ ኩታ ገጠም እርሻ እንደማስፈለጉ ኩታ ገጠም እርሻውን ለማስፋፋቱ ሥራ የበለጠ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል::
ግብርናው ለእርሻ አገልግሎት ሊውል የሚችል ሰፋፊ መሬት ወዳለበት ቆላማው አካባቢ እስከሚዘልቅ ድረስ ማድረግ የሚቻለውም ይህንኑ ነውና ኩታ ገጠም እርሻን ማስፋፋቱ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል:: ከፍ ብዬ እንደጠቀስኩት በኩታ ገጠም እርሻ ሊታቀፍ የሚችል እጅግ በርካታ መሬት በአርሶ አደሮች እጅ ያለ እንደመሆኑም ኩታ ገጠም እርሻን ማስፋፋት ላይ በትኩት ሊሰራ ይገባል::
ግብርናው እየዘመነ ያለው በሰብል ልማት ብቻ አይደለም:: በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዶ/ር በጉጂ ከጎበኙት ዘመናዊ የቡና እርሻ መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው:: ይህ በሔክታር 60 ኩንታል ቡና ያስገኛል የተባለ የቡና ዘመናዊ ልማት በሔክታር የሚመረተውን ቡና ከ10 ኩንታል ወደ 60 ኩንታል የሚያሳድግ ነው::
ይህን እርሻ በቴሌቪዥን ተከታትለነዋል:: የሚመለከታቸው አካላት ይህን እርሻ ለምን እስከ አሁን እንዳላሳዩን ማብራሪያ ቢሰጡን መልካም ነው:: አንዳንድ ሰዎች አይተው ያምናሉ፤ ወደ ልማቱም ሊሳቡ ይችላሉ:: እነዚህ አይነቶቹ ሰዎች ይህን ልማት አይተው ልማቱን እንዲያስፋፉ ማድረግ ላይ መሰራት ነበረበት:: አሁንም አይረፍድም ተሞክሮው እንዲሰፋ ሊደረግ ይገባል::
በቅርቡ ሜድሮክ ኢትዮጵያ/ሆራይዘን ፕላንቴሽን/ ከአንድ የውጭ ኩባንያ ጋር ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችል ስምምነት መፈረሙ ይታወቃል:: ይህም በሔክታር በሚገኝ የቡና ምርታማነት ላይ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያስችል ታምኖበታል:: ኩባንያው የቡናን ምርታማነት ለማሳደግ ያከናወናቸው ሥራዎችና የተገኘው ምርታማነት ብዙም ሳላላረካው ወደዚህኛው ልማት ለመግባት እንደወሰነ በወቅቱ የወጣ መረጃ ያመለክታል:: በልማቱ አብሮ ሊሰራ የገባው አንድ ታዋቂ የውጭ ኩባንያ እንደመሆኑ ከዚህም ብዙ እንጠብቃለን::
እናም ግብርናው መቀየሩን ቀጥሏል:: ለውጡን ለመመስከር የግድ የዘርፉ ባለሙያ መሆን አያስፈልግም፤ ኢኮኖሚዋ ግብርና በሆነ ሀገር ውስጥ መፈጠርና መኖር፣ ገጠሩን በትኩረት መከታተልና የመሳሰሉት ይበቃሉ፤ ለእዚህም ነው ‹‹ባናርስ እናጣምዳለን – በእርግጥም ግብርናው እየተለወጠ ነው›› ማለቴ::
በስንዴ መስኖ ልማት ላይ ብቻ አልተገደበም፤ በሩዝ፣ በለውዝ፣ በሻይ ልማት፣ ከፍ ብሎ እንደተመለከተውም በቡናውም ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ ነው:: በሁሉም በተያዙት ርብርቦች ገና ብዙ ለውጥ እናያለን::
ዘካርያስ
አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 11 ቀን 2017 ዓ.ም