የጋሞ ብሔረሰብ በሀገራችን ደቡባዊ ክፍል በአዲሱ ደቡብ ክልል ጋሞ ዞን ይገኛል። በዞኑ የተለያዩ ነባር ብሔረሰቦች የሚገኙ ሲሆኑ፣ በዋና ከተማዋ አርባ ምንጭ እነዚህን ብሔረሰቦች ጨምሮ የሀገሪቱ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በፍቅር እና በመከባበር ይኖራሉ።
የጋሞ ብሔረሰብ የራሱ ማንነት መገለጫ የሆኑ ባህሎች ባለቤት ነው። ከትውልድ ወደ ትውልድ በቅብብሎሽ የመጣ የሚያጋጥሙትን ግጭቶች እና አለመግባባቶች የሚፈታበት ለሌላው ማኅበረሰብ ተምሳሌት ሊሆን የሚችል ሀገር በቀል የግጭት አፈታት እንዲሁም አስገራሚ ባህላዊ የሕዝብ አስተዳደር ስርዓት ባለቤትም ነው።
እምቅ የማንነቱ መለያ ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነውን ባህላዊ የሕዝብ አስተዳደር ስርዓቱን ገፅ ገለጥ አድርገን የቻልነውን እና የተረዳነውን ባህላዊ ክዋኔ ከትበን ለአንባቢያን ለማቋደስ ቦታው ድረስ በመሄድ በአካል ተመልክተናል፤ የባኅሉን አዋቂ ሽማግሌዎች፣ ምሁራን እና ጥናት እና ምርምር እያደረጉ ያሉ አካላትን ሀሳብ አሰባስበንና ያጠናከርነውን በዛሬው ባኅልና ቱሪዝም አምድ ይዘን ቀርበናል።
በጋሞ ድቡሻ ላይ የ3ኛ ዲግሪ መመረቂያ ፅሁፋቸውን የሰሩት ዶ/ር ተመስገን ምንዋጋው እንደጠቀሱት፤ በጋሞ ማሕበረሰብ ዘንድ በተለይም ውሸት እንደ ትልቅ ሀጢያት ይቆጠራል፤ በዋሸው ሰው ላይ ከፍ ያለ መገለል አለፍ ሲልም መለኮታዊ ቁጣ ሊያስከትል ይችላል። በፅሁፉ እንደተጠቀሰው፤ የጋሞ አባቶች ማሕበረሰቡ ማድረግ እና አለማድረግ ያለበትን ግብር በቃላዊ መንገድ ከጥንት ጀምረው ሲያስተምሩ እና ሲጠብቁ ኖረዋል፤ በመተግበር ላይም ይገኛል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጋዜጠኞች ቡድን በአካባቢው ተገኝቶ ያናገራቸው አባቶች እንደገለፁት፤ ለጋሞ ማሕበረሰብ ባህላዊ እና መንፈሳዊ እሳቤ እና ክዋኔዎች መሰረታቸው ከፈጣሪ ጋር የተገናኘ ሚቶሎጂ ነው። በዚህም የጋሞ ማሕበረሰብ እርስ በእርሱ ተከባብሮ እና ተሳስቦ እንዲኖር የሚያስችል ሕግ ፈጣሪ ለቀደሙ አባቶች ሰጥቷል። ይህም ሕግ በሕዝቡ መተግበር አለበት። ካልተተገበረ፣ ከተሻረ እና ወደ ጎን ከተተወ ግን ሀጢያት ወይም መርገምት ይሆናል። ይህ ማንም ሰው መተላለፍ የማይገባው ደርጊት በሁሉም ሕዝብ ዘንድ ይታወቃል፣ የተጠቀሱትን ሕጎች መጣስ ጎሜ ይባላል።
ጥናታዊ ፅሁፉ እና የተደረጉ ቃለመጠይቆች እንደሚያሳዩት በጋሞ ብሔረሰብ ባህል አንድ ሰው የተከበሩ ሕጎችን ሊጥሶ ሊገኝ የሚችልበት ሁኔታ ያጋጥማል። ጉዳዩ ለምን ጣሰ ሳይሆን ከጥሰቱ በኋላ የሰራውን ጥፋት ወደ ድቡሻው ሄዶ ጉዳዩን ለሚመለከታቸው ሽማግሌዎች መናዘዝ ይኖርበታል፤ በዚህም የሚወሰንበትን ካሳ መክፈል እና ምርቃት ማግኘት አለበት። ይህ ሂደት ደግሞ ጎሜ ከበራ ይባላል።
ዶ/ር ተመስገን እንደገለጹት፤ ሀጢያት ወይም ጎሜ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሊፈፀም ይችላል። በባህሉ ምንም አይነት ሀጢያት ቢሰራ አባቶችን በመቅረብ በድቡሻ አደባባይ ላይ በመናዘዝ ከመርገምት መዳን ይቻላል። ብዙ ጊዜ ግን የሚሰሩት የሀጠያት አይነቶች ሀጢያት ሰሪውን እንዳይናዘዝ ሊፈታተኑት ይችላሉ። ይሄን ግልፅ የሚያደርግ አንድ ጉዳይ እስኪ ላማሳያነት እናንሳ።
ለምሳሌ አንድ ሰው ነፍስ ቢያጠፋ እና ማንም ሰው ባያየው ግን ካለምንም ማስረጃ ቢጠረጠር ጉዳዩ ከተፈፀመ በኋላ አባቶች ነገሩን በንቃት መከታተል ይጀምራሉ። አቶ ታፈሰ ዋልኤ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጫሞ ካምፓስ የማሕበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ ናቸው። በጋሞ ድቡሻ ላይ ጥናት በማድረግ ላይ ሲሆኑ ባኅሉንም በደምብ የሚያውቁ ከማሕበረሰቡ የተገኙ ምሁር ናቸው።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ በጋሞ ባኅል በማሕበረሰቡ ውስጥ የሚፈጠሩ ማናቸውም ጉዳዮች ለውይይትም ሆነ ለመፍትሄ የሚሰበሰቡት በአካባቢው ለዚሁ ጉዳይ በተዘጋጀ ሰፊ ሜዳ ሲሆን፣ ይህም ሜዳ ወይም አደባባይ ድቡሻ ይባላል። ዱቡሻ የሚከለለው በዘፈቀደ አይደለም። አቶ ታፈሰ በተለይም ከ ዘ ኢትዮጵያን ሔራልድ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ አንድ ድቡሻ የሚመሰረተው ከፍ ያለ ቦታ ተመርጦ ነው። ይህም ማለት ከፍ ብሎ ሲሰራ አካባቢውን ከላይ ሆኖ ለማየት አመቺ እንዲሆን ለማድረግ ነው። ሔራልድ ምክንያቱን ለማወቅ የበለጠ ማብራሪያ ጠይቆ የተሰጠው ምላሽ ከፍ ባለ ቦታ ላይ በጎሜ ከበራ ወቅት ለሂደቱ አስፈላጊ ጉዳዮችን ለማየት እንዲቻል መሆኑን ለመረዳት ችሏል። በዚህ ሂደት ውስጥ አንድ ግለሰብ ሀጠያቱን መስራት አለመስራቱን ሲጠየቅ እንደ ታዛቢ የሚቆጠሩ ተፈጥሮዊ ጉዳዮች አሉ። እነዚህም ተራሮች፣ ወንዞች፣ መቃብሮች፣ ዛፎች፣ ወፎች እና በመጨረሻም ሰማይ ናቸው። አቶ ታፈሰ ድቡሻ ሲሰራ ለነዚህ ተፈጥሮዎች እይታ የተመቸ መሆኑ ታሳቢ ተደርጎ ነው ብለዋል።
ቀደም ብለን ወዳነሳነው ጉዳይ ስንመለስ በጋሞ ባሕል አንድ ሰው ካጠፋ እና ከተጠራጠረ መረጃ ኖረም አልኖረም በራሱ ጊዜ ወደ አባቶች ቀርቦ በደል ፈፅሜያለሁ ብሎ ይናዘዝና በባሕሉ መሰረት ጎሜ ከበራ ይደረግለታል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ግን ግለሰቡ ዝምታን ከመረጠ፣ ማስረጃ ኖረም አልኖረም ግለሰቡን ወደ ድቡሻው እንዲቀርብ በቤተሰብ ወይም በጎሳው ይልኩበታል። ግለሰቡ ቀርቦ ወንጀሉን ፈፅመሀል ወይስ አልፈፀምክም ተብሎ ይጠየቃል። አልፈፀምኩም ብሎ ሲሄድ አባቶች በቤተሰቡ እና በጎሳው እንዲመከር እውነቱን እንዲናገር እንዲያግዙት አሳስቦ ይልካል።
በሚቀጥለውም ሲጠየቅ አሁንም ሊክድ ይችላል፤ ሊያምንም ይችላል። ካመነ በባኅሉ መሰረት ጎሜ ከበራው ይካሄዳል። ካላመነ ግን አሁንም እንዲያስብበት የጥሞና ጊዜ ይሰጠዋል። እንዲህ እያለ የሰውዬው ልብ እስኪሸነፍ ይሞክራሉ። ይህ የማይሆን ከሆነ አሉ አቶ ታፈሰ ወደ መጨረሻው ደረጃ ይኬዳል።
በዚህ ደረጃ ላይ የአካባቢው ማሕበረሰብ፣ የድቡሻው ሀለቃ፣ እና ለዚህ ጉዳይ የተመረጡ ሽማግሌዎች ወደ ድቡሻው ይመጡና ቦታቸውን ይይዛሉ። በዚህ ሰዓት በሀጢያቱ የተጠረጠረው ግለሰብ ወደ ፊት አንዲቀርብ ይደረጋል። የተመረጡት አባቶች ከግለሰቡ ፊት ለፊት ይቀመጣሉ። የእነዚህ ሽማግለዎች ሚና የግለሰቡን ማናቸውንም አካላዊ እና መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ወይም ለውጦች መከታተል ነው። ሁሉም የተሰበሰበው ማሕበረሰብ በፀጥታ ጉዳዩን ይከታተላል። ከዛ አለማድረጉን በመሀላ እንዲያረጋግጥ የሚያደርጉ ሽማግሌዎች ይጀምራሉ። ወደ መሀላው ከመሄዳቸው በፊት አሁንም ደግመው ይጠይቁታል። ወንጀሉን ፈፅመሀል አልፈፀምክም ብለው ከጠየቁ በኋላ በቀጥታ ወደ መሀላው ይኬዳል።
የሚያስምሉት ሽማግሌዎች ትዕዛዝ መስጠት ይጀምራሉ። እንደቆመ ያለው ተጠርጣሪ መመልከት ያለበትን በቅደም ተከተል ይጠየቃል። ተራሮችን ተመልከት፣ የራሳቸው ክብር እና ሞገስ አላቸው፣ ወፎችን ተመልከት ፈጣሪ ለራሳቸው በሚሆን ልክ በክብር ፈጥሯቸዋል፣ እዚህ የተሰበሰቡትን ሰዎች ተመልከት እነሱም የራሳቸው ክብር እና ሞገስ ደርበዋል።
ተመልከት እነዚያ መቃብሮች ውስጥ ዘሮቻችን በክብር አርፈዋል፣ እያሉ በአካባቢው የሚታዩትን ተፈጥሮዎች እየዘረዘሩ የተፈጥሮን ድንቅነት በማሳየት ልቡን ለማሸነፍ ይሞክራሉ። በመጨረሻ ወደ ሰማይ ቀና እንዲል ይጠይቁታል። ይሄን ሁሉ በክብር የፈጠረ ፈጣሪን ተመልከት። እሱ ሁሉን ያያል፤ ሁሉን ያውቃል ካሉት በኋላ ወደ እርግማን እና ምረቃ ስነ ስርዓት ይሄዳሉ።
እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርሱም ግለሰቡ እየዋሸ ከሆነ በደምብ ይታወቃል አሉን 8 ደሬዎችን በንግስና የሚያስተዳድሩት ካዎ ታደሰ። ከነገሩን የእርግማን ዝርዝሮች ውስጥ እጅግ ከባድ እና አስጨናቂ ብለን የለየናቸውን አቅርበናል። ይሄን በደል አድርሰህ ከሆነ ዘርህ ብን ብሎ ከምድረ-ገፅ ይጥፋ፣ ዘርተህ አትጨድ፤ ወልደህ አታሳድግ፤ ተናግረህ አትሰማ፤ ሰረትህ አትብላ፤ የነካኸው ሁሉ አይበርክት፣ ብርድ ሆኖ ሳለ አንተን ሀሩር ውስጥ እንዳልህ ሙቀት ያቃጥልህ፣ ሙቀት ሆኖ ሳለ በብርድ እንዳለህ የሚያንቀጠቅጥ ብርድ ይሁንብህ፣ ከምድር ብን ብለህ እንድትጠፋ ያድርግህ እና ሌሎችንም እጅግ የሚሰቀጥጡ እርግማኖች ሲያደርሱ ግለሰቡ እየዋሸ ከሆነ፣ ያነጋገርናቸው አባቶች እንዳረጋገጡልን፣ መንቀጥቀጥ ይጀምራል። ላብ ላብ ይለዋል፡፤ አይኑ ይቅበዘበዛል፣ ይወራጫል ባጠቃላይ ይረበሻል።
ይሄን በአትኩሮት የሚከታተሉት ሽማግሌዎች ግለሰቡ ለመማል ከመወሰኑ በፊት አንድ ሌላ ተጨማሪ እድል እንዲሰጠው ሀሳብ ያቀርባሉ። የድቡሻው ኃላፊ ሀሳቡን ካፀደቀው ጉዳዩ በሌላ ዳኝነት እንዲታይ ይታዘዛል። ካላመነበት ግን እንዲምል ይደረግ እና ጉዳዩ ይዘጋል።
በሌላ ደሬ ድቡሻ ላይ በተለይም በቦንኬ ሂደቱ ትንሽ ይለያል። በዚህ ዴሬ ድቡሻ ተጠርጣሪው ከላይ እንደተጠቀሰው እድል ሲሰጠው ይቆይ እና በመጨረሻ ለመሀላ ሲደርስ እርግማኑን እራሱ እንዲረግም በሚያስችል መልክ የሚደረግ ኩነት አለ።
አቶ ቢረጋ ጋነችሬ የቦንኬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ እንደተናገሩት፤ በመሀላው ወቅት ግለሰቡ አላምንም ካለ እሳት እና ውሃ ይቀርብለታል። ከዛ ውሃውን አንስቶ እንዲይዝ ይጠየቃል። የሚያስምሉት ሽማግሌዎች ወደ እሱ ጠጋ ይሉ እና በደሉን ወይም ወንጀሉን አልፈፀምኩም ፈፅሜ ከሆነ ዘሬ ልክ እንደዚህ እሳት ከምድር ላይ ይጥፋ ብለህ ውሃውን እሳቱ ላይ ጨምር ይሉታል። ስለዚህ ውሳኔው የራሱ ይሆናል። ግን በውሸት ቢምል ምን ይፈጠራል ብለን ጠየቅን።
ምንም እንኳን ተጨማሪ ጥናቶች እና ሳይንሳዊ ትንታኔዎች በእጅጉ የሚያስፈልጉ ቢሆንም ሁሉም የተጠየቁ ሽማገሌዎች እና ምሁራን የተለያዩ ምሳሌዎችን እና ገጠመኞችን እያነሱ እንደነገሩን እርግማኑ በትክክልም በተግባር ይታያል። ለዚህም ማሳያ የሚሆኑ በርካታ ምሳሌዎችን ከተመራማሪዎችም ሰምተናል።
በደሉን የፈፀመ ወይም ሀጢያት ያደረገ ሰው በራሱ ጊዜ ወይም በአባቶች የማናዘዣ ስልት በደሉን ካመነ የሚጠበቅበትን የካሳ እና የበደል ማሻሪያ ገንዘብ ወይም ድርጊት እንደ በደሉ አይነት እና ክብደት በፍትሀዊነት ሽማግሌዎች ይፈርዱበታል። የቀረበው ፍርድ ትክክለኛ እና ሚዛናዊ መሆኑን የድቡሻው ሀለቃ አመዛዝኖ ያፀድቃል። ከዛ ለምሳሌ ግድያ ከሆነ የገዳዩ ቤተሰብ እና ጎሳ ሂደቱ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ቆመው እና አንገታቸውን ደፍተው በፀፀት ሲታዩ የተበዳይ ቤተሰብ እና ጎሳ ቁጭ ብለው ፍርዱን እና መሀላውን ይታደማሉ።
በባኅሉ መሰረት በዳይ ግለሰቡ እና ጎሳው ካሳውን ይዘው ይቀርባሉ። በእንደዚህ አይነት ጎሜ ላይ ሀጢያቱ እንዲፀዳ ብዙ ጊዜ በግ ይታረዳል። ዶ/ር አዲሱ አዳሙ በዚህ ላይ ሲያብራሩ እንዳሉት፤ በግ የመልካምነት ምሳሌ ስለሆነ ከልብ ይቅር ለመባባል ይታረዳል። ከዛ በደሙ እና በፈርሱ ላይ ሁለቱ ወገኖች እንዲረማመዱ ይደረጋል። ከዚህ ስርዓት በኋላ ምንም አይነት ቅሬታም ይሁን በቀል በፍፁም አይታሰብም። ሁለቱም እንደ በፊቱ ወንድማማቾች ሆነው ይቀጥላሉ። ሀጢያቱም በከበራው ይፀዳል።
ምንም እንኳን በዘመናዊ ሕግ ወንጀልን የፈፀመ ሰው ተመጣጣኝ ቅጣት ቢያገኝም ከልብ ይቅር መባባል እና በነበረው ግንኙነት መቀጠል ግን ብዙ ግዜ አይኖርም። ይሄ ግን በጋሞ ድንቅ ባህል የሚቻል ቀላል ግን ውጤቱ ጥልቅ የሆነ ኩነት ነው። የሰው ልጅ በደልን ይፈፅማል፣ ግን ከልብ ይቅር የማይባባል ከሆነ ለሌላ በደል ይጋበዛል። የጋሞ ረቂቅ አባቶች ይሄን ተገንዝበው ባህሉን በዚህ ልክ አቆይተውናል። መጠቀም ማበልፀግ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን በፍቅር አብሮ የመኖር እና ያለመኖር ጉዳይ ነውና በጊዜ ወርቃችንን እንጠቀምበት እንላለን።
በመቅደስ ታዬ (ፒ ኤች ዲ)
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13 ቀን 2017 ዓ.ም