‹‹የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ሊቀለበስ አይችልም››- ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ በክሪ (ዶ/ር)

ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ በክሪ (ዶ/ር) የታሪክ ምሁር

ኢትዮጵያ፣ አገራት በግዛታቸው ውስጥ ያለውን ውሃ ሌሎችን አገራት በማይጎዳ መልኩ ለሚፈልጉት አገልግሎት ሊያውሉ ይችላሉ የሚለውን መሰረታዊ መርህ ተከትላ ታላቁን የዓባይ ግድብ በመገንባት ስኬታማ መሆን ችላለች፡፡ በእርግጥ ዛሬ ስኬታማ ትሁን እንጂ ያለፈችባቸው ጎዳናዎች በብዙ ፈተናዎች የታጨቁ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ ከግድቡ ጋር በተያያዘ በምታደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ ሲያጋጥማት የነበረው ፈተና ከባድ ቢሆንም በሰከነ እና በተረጋጋ መንፈስ በፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርህ በትዕግስት እያለፈች ዛሬ ስለመድረሷ የመንግስቷ ቁርጠኝነት የሕዝቧ ትጋት መሆኑ የሚረሳ አይደለም፡፡

ይህች ታላቅ አገር፤ ዛሬም ሌላ ፍትሃዊ ጥያቄ አንግባ የባሕር በር ይገባኛል ስትል ወደአደባባይ ወጥታለች፡፡ ይሁንና የባሕር በር ጥያቄን ካቀረበችበት ጊዜ ጀምሮ ልክ እንደ ዓባይ ግድብ ጅማሬ ላይ እንዳጋጠማት ፈተና ሁሉ ዛሬም ከፊት ለፊቷ የተጋረጠባት ተግዳሮት ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ቀደም ሲል ግድቡ ለኢትዮጵያ ከሚያበረክተው ዘርፈ ብዙ ጥቅም በተጨማሪ ለጎረቤት አገሮችም ፋይዳው በርካታ መሆኑን ስታስታውቅ የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ ውጤት ላይ ሲደረስም ተግባራዊ የሆነው ይኸው የተናገረችው እውነት ነው፡፡ ቢሆንም ከእውነታ ጋር መጋፈጥን የሞት ያህል ስትሸሽ የቆየችው ግብጽ ትናንት ግድቡ እንዳይሳካ ደፋ ቀና ስትል ነበር፤ ዛሬ ደግሞ የናይል የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት ሕግ ሆኖ ሕጉ በአፍሪካ ኅብረት ተቀባይነት በማግኘቱ የናይል ወንዝ ኮሚሽን ጠንካራ ሆኖ እንዳይሰራ ለማድረግ በመሯሯጥ ላይ ናት፡፡

በሌላም በኩል ልክ እንደ ሕዳሴው ግድብ ሁሉ የባሕር በር ጥያቄም እንዳይሳካ በመጣር ላይ ትገኛለች፡፡ ዓባይም ሆነ ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ የታሪክ አካል ቢሆኑም እንደ ግብጽና መሰል አገሮች እንቅፋት ለመሆን የሚያደርጉት ሩጫ ፈተናው ምን ያህል ነው? ኢትዮጵያ ጥንካሬዋን አስጠብቃ መሔድ የምትችለውስ እንዴት ነው? የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችን በማካተት አዲስ ዘመን ከታሪክ ምሁሩና ተመራማሪው ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ በክሪ (ዶ/ር) ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርቧል፡፡

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የታሪክ ምሁር እንደመሆንዎ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር እና ከዓባይ ጋር ያላት ቁርኝት የሚገለጸው እንዴት ነው?

አየለ (ዶ/ር)፡- ቀይ ባሕር እና ዓባይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ቁርኝት በጣም ጠንካራ ስለመሆኑ ታሪክ ራሱ ምስክር ነው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ታሪክ በጊዜ ከፍለን ስናይ የጥንቱ የሚባለው አለ፤ መካከለኛው እንዲሁ አለ፤ የአሁን ዘመን ታሪክ የሚባለው ደግሞ አለ፡፡ የጥንቱን የኢትዮጵያ ታሪክ ስንመረምር ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ትስስሮሽ ያላት መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡

እንዲህ ሲባል ለምሳሌ የአክሱምን ስልጣኔ (ግዛት) (በእርግጥ ከዚያም በፊት ስልጣኔው ነበር) በምናስተውልበት ጊዜ ታላቅ አገር ተብሎ የሚቆጠር ነበር፡፡ ለአክሱም ግዛት ስልጣኔውም፣ የብልጽግና ምንጩም ንግድ ነበር፡፡ የንግድ ዋናው መሰረት ደግሞ አክሱም ላይ የከተማው ከተማ ብቻ ሳይሆን “አዱሊስ” የሚባል የባሕር በር በአክሱም ቁጥጥር ስር ነበር። እናም የአዱሊስ መኖር ለንግዱ መስፋፋት ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነበር።ለምሳሌ ወደኢስያ፣ ወደሰሜን አፍሪካም ሆነ ወደተለያዩ ቦታዎች የሚደረጉ ንግዶች በራሳቸው የትራንስፖርት ስርዓት የባሕር ማጓጓዣ እያጓጓዙና ከፍተኛ ንግድ እያካሔዱ የቆዩ በመሆናቸው በጣም ዝነኛ እና ታዋቂ ነበሩ፡፡

በወቅቱ በዓለም ላይ ካሉ አራት ታላላቅ ግዛቶች አንዱ አክሱም ነበር፡፡ ስለዚህ እሱ ቁርኝት (ትስስር) እስከመጨረሻው ድረስ ሔዶ በተዘዋዋሪ መንገድ ይሁን በቀጥታ ቁጥጥሩ ሳይበርድ ግለቱን እንደጠበቀ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የቆየ ነበር። ከቀይ ባሕር ጋር ያለን ቁርኝትም በቅርቡ በሚያስብል ሁኔታ እኤአ ከ1993 በኋላ ተቋረጠ እንጂ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያም የባሕር በር የነበራት አገር መሆኗ የሚታወስ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የባሕር በር የሌላት አገር በመሆኗ በመሬት የተከበበች ለመሆን ተገዳለች፡፡

ዓባይን በተመለከተ ምስጢሩ ምንድን ነው ከተባለ ዓባይ የሚመነጨው ከኢትዮጵያ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ማለት 85 በመቶውን ውሃ የምናመነጨው እኛ ነን፡፡ ይህ እኛንና ዓባይን ጥብቅ ቁርኝት ያለን ስለመሆኑ የሚያሳይ ነው፡፡ እኛ ግን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ጥቅም ላይ አላዋልነውም። የዓባይን ግድብ ለመጀመሪያ ጊዜ በገደብንበት ጊዜ በዓለም ላይ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፤ ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ በመገደብ ለመጀመሪያ ጊዜ ለራሷ ጥቅም ለማዋል እንቅስቃሴ ጀመረች ተብሎ ይወራ እንጂ ኢትዮጵያ ያደረገችው ትግል ግን ከባድ የሚባል እንደሆነ የሚታወስ ነው። በተለይም ግብጽ እና ሱዳን ኢትዮጵያ መወሰኗን ከሰሙ በኋላ ጉዳዩን ለማስተጓጎል ብዙ ርቀት ሔደዋል፤ ይሁንና ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡

የኢትዮጵያ የግድብ ግንባታ የዓባይ ላይ ብቻ የሚቆም አይደለም፡፡ በቀጣይም ዓባይ ከኢትዮጵያ ጋር የበለጠ ቁርኝት እንዲኖረው ተደርጎ በመሰራቱ ወደፊትም ሌሎች ግድቦች እየተገደቡ ዓባይ በተፈለገው ሁኔታ የኢትዮጵያ እድገት ለማፋጠን እገዛ የሚያደርግ ነው፤ ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ የምትጠቀመው ደግሞ ብቻዋን ሳይሆን ከሌሎቹ ጋር በፍትሐዊነት መርህ ላይ ተመስርታ ነው፡፡

እኛ የጂኦፖለቲካዊ ጥቅማችንን አውቀን የምንቀሳቀስ ሕዝብ ነን፡፡ ያንን ጥቅማችንን ለማስጠበቅ በመጀመሪያ ደረጃ ዓባይ ላይ መገደባችን መልካም የሚባል ነው፤ እሱ ግን በቂ ባለመሆኑ ሌሎች ግድቦች መገደብ አለባቸው። ስርዓት ባለው መንገድ ያንን ውሃ መቆጣጠር ስንችል ጎረቤቶቻችንም ያከብሩናል። ከእኛም ጋር በትብብር ለመስራት ተመልሰው መምጣታቸው አይቀሬ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከዓባይ ግድብ በኋላ ሌላ ግድቦችንም እንደምትገነባ በተደጋጋሚ ስትገልጽ መቆየቷን እንዴት ያዩታል?

አየለ (ዶ/ር)፡- ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ በምታደርገው ግድብ ብቻ ተወስና የምትቀመጥ ሀገር አይደለችም፡፡ የባሕር በር ጥያቄ ማቅረቧ እውን ነው፡ ይህ ደግሞ ተፈጻሚ እንዲሆን ተፍ ተፍ ማለቱም ልክ ነው፡፡ ምክንያቱም ወደ 130 ሚሊዮን የሚገመት የሕዝብ ቁጥር ይዛ ያለ ባሕር በር መኖር የማይታሰብ ነገር ነው፡፡ ይህ ለማንም ግልጽ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል ያሉትን እውነታዎች መገንዘብ ያስፈልጋል። በአካባቢያችን ያሉ አገሮች የተባበሩት መንግስታት አባል የሆኑ ሉዓላዊነታቸው የተከበረ ስለሆነ ዘዴ መፈለግ አለብንና ቀደም ሲል ከሱማሌላንድ ጋር የተፈራረምነው ስምምነት ለዚያ ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡

ምክንያቱም እኛ የባሕር በር ያስፈልገናል ብለን ወስነናል፡፡ ይሁንና የባሕር በር አስፈላጊያችን ነው ስንል ማግኘት የምንፈልገው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ነው፡፡ ለምሳሌ የሱማሌላንድ ፈቃደኝነት ባይኖር ኖሮ ስምምነቱ ሊፈረም አይችልም ነበር። መስማማቱና መፈረሙ ትክክል ሆኖ ሳለ ይህ ለምን ተደረገ በሚል የስምምት ፊርማችንን ባኖርን ማግስት በአንዳንዶቹ አካባቢ ጸብ ያለሽ በዳቦ በሚመስል አካሔድ አንዱን በሌላው ላይ ለማነሳሳት የተደረገ ጥረት መኖሩ የማይካድ እውነታ ነው፡፡ ይሁንና ወዲህም ተሮጠ ወዲያ ኢትዮጵያ ያነሳችውን የባሕር በር ጥያቄ ስኬታማ ሳታደርግ ከዓላማዋ ዝንፍ እንደማትል መረዳቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የባሕር በር አካሔዱ ምን ይመስላል ?

አየለ (ዶ/ር)፡– አካሔዱ ጥሩ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በሱማሌላንድ የተደረገው የመንግስት ለውጥ ለደረስነው ስምምነት ምንም ለውጥ የሚያመጣ አይደለም፡፡ ሁለቱም አቋማቸውን አልቀየሩም፡።ይህ የሚያሳየን ደግሞ ሱማሌላንድ ብሔራዊ ጥቅሟን አውቃ እሱ ብሔራዊ ጥቅሟ ከኢትዮጵያ ጋር መተሳሰብ መሆኑን ወስና እየቀጠለች ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ግብጽን ጨምሮ አንዳንድ አገራት ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳይኖራት በብዙ ይጥራሉ። ይህ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳታገኝ መሰናክል አይሆንም ይላሉ?

አየለ (ዶ/ር)፡- እንደ እኔ ግምት መሰናክል ሊሆን አይችልም፤ እርግጥ ነው አንዳንዶች እንቅፋት ለመፍጠር መሞከራቸው አይቀርም። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም ሲያደርጉ የነበረው ነገር አለ፡፡ እሱን ስናስተውል ለዚህም ያንኑ ተግባራቸውን ይጠቀማሉ ብለን እናስባለን፡፡ ከዚህ በፊት የቀይ ባሕር ፎረም ብለው አቋቁመው ኢትዮጵያ እዚያ ፎረም ውስጥ እንዳትገባ ሲያደርጉ የነበረው ጥረት አለ፡፡

በተቻላቸው መጠን ኢትዮጵያ የምትዳከምበት ሁኔታ ላይ ያላቸውን አቅም ሁሉ በማሰባሰብ ዓላማዋን እንዳታሳካ የሚተጉ ናቸው፡፡ በተለይ ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ ያላት ዓላማ አገራችን ኢትዮጵያ ስኬታማ እንዳትሆን ማሰናከል ነው፡። አገሪቱ ቀይ ባሕር ላይ ወዲህ ወዲያ ብትልም ከጅቡቲም ከሱማሊያም ከኤርትራም ጋርም በማበር የተለያዩ ሴራዎችን ስታሴር ብትቆይም ነገሮች በፈለገችው መጠን ሊሔዱላት አልቻሉም፤ ሁሌም ቢሆን የእሷ ዋና ዓላማ የዓባይ ወንዝ ነው። ዓባይን እንዳይነካ በመፈለጓ ብቻ ኢትዮጵያን ለማዳከም ትሮጣለች፡፡

ለምሳሌ ራስ ገዟ ሱማሌላንድን ብንወስድ ግብጽ ሱማሌላንድን ከወሰኗ እንድትሰጣትና በዚያም መሰረት ለመስራት ብትጠይቅም ሱማሌላንድ ግን ፈቃደኛ ሳትሆን ቀርታለች፤ በመሆኑም እዚያ መግባት አልቻለችም፡፡ ይሁንና በሱማሌላንድ ሁኔታዎች ባይመቻቹላትም የእሷ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያን ከልማት ማስተጓጎል በመሆኑ ሴራዋን ቀጥላለች፡፡

ግብጽም ሆነች ሌሎቹ ሴራ ውስጥ የመግባታቸው ዋና ቁልፉ ጉዳይ ኢትዮጵያን ሰላም ለማሳጣት ነው። እነርሱ ሊያጣጥሏት የፈለጓት ራስ ገዟ ሱማሌላንድ በተለይ በቅርቡ በተደረገው ምርጫ እንዳየነው በዓለም ላይ ትልቅ አድናቆትን ያተረፈ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሱማሌላንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ማግኘቷን አመላካች ነው፡፡

ብዙ ጊዜ ግብጽ ኢትዮጵያ እንድትረጋጋ ፍላጎት የላትም፤ በተለያየ መንገድ ቢቻላት ኢትዮጵያን ሰላም ለማሳጣት ትሞክራለች፡፡ ከአንዱ ቦታ ወደሌላ ቦታ መሳሪያ ማዛዟሯም በአንድ ወቅት ስራዬ ብላ ተያይዛው እንደነበር ይታወቃል። ከእዚኽኛውና ከእዚያኛው ጋር ወታደራዊ ስምምነት ማድረጉንም አጥብቃ ይዛ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡

እሷ አንዱን ከሌላው ጋር ለማጋጨትም ሆነ እርስ በእርስ ለማናከስ የትኛውንም መስዋዕትነት ትከፍላለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ሱዳንንም በማተራመስ ላይ ናት፡፡ ሱዳን ጦርነት ውስጥ ከገባች አንድ ዓመት ሆኗታል፤ እስካሁንም ከገባችበት የዕርስ በዕርስ ጦርነት ውስጥ መውጣት ተስኗታል፡፡ ግጭቱ መረጋጋት ሲገባው ይልቁኑ እየተባባሰ ይገኛል፡፡ ሱዳን ከግጭት አለመውጣቷ ብቻ ሳይሆን በዕርስ በዕርስ ጦርነት የተነሳ እያለቀ ያለው ብዙ ሕዝብ ነው፡፡ በሱዳን ውስጥ የተከሰተው ጦርነት የመምጣቱ አንዱ ምክንያት ውስጣዊ አለመረጋጋት ባለመኖሩ ምክንያት ነው፡፡

በእኛ በኩል አገራችን ሰላም የሰፈነባትና የተረጋጋች እስከሆነች ድረስ የውጭ ኃይሎች የምንላቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያን ሊዳፈሩ አይችሉም፡፡ ስለዚህ በቀጣናው ውስጥ ያለን ተሰሚነታችን የሚጨምረው በተለይ የውስጥ ችግሮቻችንን በአግባቡ መፍታት ስንችልና፤ ችግሮቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ አምጥተን መነጋገር ስንችል ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በተለይም አለብን ለምንለው ችግር መፍትሔው፤ ድርድር ውስጥ ራሳችንን ተሳታፊ ማድረግ ስንችል ነው፡፡

ድርድር ሲባል ደግሞ በውስጡ መስጠትም መቀበልም ያለው ነው፡፡ በድርድር ውስጥ ለመስጠትም ለመቀበልም ዝግጁ ከሆንና እምነት ካሳደርን አዲስ መስመር ከፈትን ማለት ነው፡፡ ይህ ሲሆን የተፈጠረው ውስጣዊ ችግር መረጋጋት ይችላል፡፡ ችግር ሲረጋጋ ሰላም ደግሞ ቦታውን ይይዛል፡፡ ውስጣዊ ሰላም ሲኖር ከሌሎች ጋር የሚኖረን ውጪያዊ ሰላም ይበልጥ ይጎለብታል፡፡ በተመሳሳይ በቀጣናው ያለን ሚና ከፍ እያለ ይሄዳል፡፡

እኔ እንደማስተውለው ግን በአሁኑ ወቅት ትልቁ ችግራችን በውስጣችን ያለው አለመረጋጋት እና ዕርስ በዕርስ መገፋፋት ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህ ነገሮች ከዚህ በኋላ መቀጠል አይኖርባቸውም። ወደሰላም ፊትን ማዞርና ለአገር ሰላም መስራት ለትውልድ መስራት ነውና ለዚህ መልካም ዓላማ ራስን ማስገዛት ተመራጭ ነው፡፡ ለዚህ መልካም ዓላማ ራስን ከሰላም ጋር ማስማማት ተቀዳሚው ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ሰላም ስኬታማነት ትልቁን ኢንሼቲቭ መውሰድ ያለበት መንግስት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያ ባቀረበችው በባሕር በር ጥያቄዋ ላይ ጥላ ያጠላሉ ብለው ያስባሉ? ምን ይመስልዎታል?

አየለ (ዶ/ር)፡- የአሜሪካን ፖለቲካ በቅርብ እንደሚከታተል ሰው ከወዲሁ እንዲህ ይሆናል ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፡፡ ምክንያቱም መርህ ተከትለው ይህን ያደርጋሉ፤ ይህን ደግሞ አያደርጉም ብሎ ለመተንበይ የሚያስቸግር ነው፡፡ ይህን ለማለት የተገደድኩበት ምክንያት ከዚህ በፊት የአሁኑ ተመራጭ ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ጊዜ “ግብጽ የዓባይን ግድብ በቦምብ መደብደብ አለባት” ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡

ነገር ግን እኔ የእርሳቸውን ሐሳብ ስመረምር የአሜሪካ ፖለቲካ ተቀያያሪነት ያለው ሊሆን ይችላል፡፡ እናም በአሁኑ ጊዜ ዶናልድ ትራምፕ ስለራስ ገዟ ሱማሌላንድ ምርጫ ያላቸውን አድናቆት መግለጻቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ለእኔ የሚያሳየው ፕሬዚዳንቱ ቀደም ሲል በአፍሪካ ላይ የነበራቸው ሐሳብ እንደተቀየረ ነው፡፡

በእኔ ግምት አሁንም ድረስ ግብጽ ከአረብ አገሮች መካከል ተጽዕኖ ፈጣሪ ስለሆነች አስፈላጊያቸው እና ከሁለት እስከ ሶስት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት መሳሪያ ከአሜሪካ ስለምትወስድ ግብጽን ሙሉ በሙሉ ሊያገልሏት አይችሉም ባይ ነኝ፡፡

ነገር ግን የሚስተዋለው ነገር በአካባቢው ያለው ረብሻ በተለይ በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል ካለው ግጭት በኋላ የቀይ ባሕር መርከቦች መተላለፍ፣ መንቀሳቀስ አደጋ ላይ ስለወደቀ ለዚያ ደግሞ ኢትዮጵያ በጣም አስፈላጊ ስለሆነች ከአገራችን ጋር ጥሩ የሚባል ወዳጅነትን ስለሚያጠናክሩ የተደረጉትንም ስምምነቶች እውቅና ሊሰጡ ይችላሉ የሚል ተስፋ አለኝ፡፡

እርግጥ ነው ኢትዮጵያ የባሕር በር ይገባኛል በሚል እያቀረበች ያለው ጥያቄ ግብጽን የመሳሰሉ ሀገራትን እያናደደ ያለ ነው፡፡ ግብጽ በአደባባይ እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ ንዴቷ ከልክ ያለፈ መሆኑን የሚያሳይ ድርጊት ነው፡፡ እነዚህ አገራት ንዴታቸው ሊበርድ የሚችለው ከጊዜ በኋላ የተወሰነው ውሳኔ እነርሱንም ጭምር ሊጠቅም እንደሚችል ሲያስተውሉ ነው የሚል አመለካከት አለኝ፡፡

በእኔ ግምት ጥር ወር ላይ መንበራቸውን የሚይዙት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢትዮጵያን በሱማሊያ አካባቢ መገኘትን የሚፈልጉት ይመስለኛል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ለሱማሊያ መረጋጋት የከፈለችው መስዋዕትነት የሚገለጸው እንዴት ነው?

አየለ (ዶ/ር)፡- ኢትዮጵያ ለሱማሊያውያን የከፈለችው መስዋዕትነት ብዙ ነው፡፡ የከፈለችው ዋጋ በገንዘብ የሚተመን አይደለም፡፡ ምክንያቱም ክቡር የሆነውን የልጆቿን ሕይወት እስከመገበር ነውና፡፡ እሱ ጉዳይ የሱማሊያውያንን ሁኔታ መቀየር ችሏል። በአሁኑ ወቅት ሱማሊያውያን እያስተዳደሩ ያሉ ፕሬዚዳንቷ ሰሞኑን በአንካራ ተገኝተው ስምምነት ለይ ደርሰዋል፡፡ ተፈጥሮ የነበረውንም ችግር አብርደዋል። መቼም ቢሆን ኢትዮጵያውያን እና ሱማሊያውያን ዕርስ በዕርስ በጠላትነት የሚፈራረጁ አይደሉም፡፡ በዚያድባሬ ወቅት የነበረው ሁኔታ ዛሬ ተቀይሯል፡፡ ስለዚህም ነው የግብጽ ወደሱማሊያ ሔዶ መንደፋደፍ ሱማሊያውያን የዚያን ያህል ዋጋ የማይሰጡት ብዬ አስባለሁ፡፡

ግብጽን ብንወስድ እውነተኛ አጋር አለመሆኗን ማስተዋል ይቻላል፡፡ እሷን የሚጠቅም ከሆነና እሷ የማትፈልገው ሀገር እድገት እንዳያሳይ (ኢትዮጵያ ማለት ነው) ስትሻ የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም፤ ግብጽ 40 ሺ የሚጠጉ ፍልስጤማውያን በጋዛ ሲያልቁ ምንም ትንፍሽ ያላለች አገር ናት፤ እንዲያውም ብዙዎች ከሞት ለማምለጥ ሲሸሹ እና ቁስለኞች መሔጃ ቦታ ሲፈልጉ ድንበሯን ግጥም አድርጋ ዘግታ የቆሰሉ ገብተው እንዳይታከሙ በማድረግ ማንነቷን አሳይታለች፡፡

ግብጽ በእኛም ላይ የምታደርገው ሴራ የገዛ ሕዝቧ እንዳይነሳባት በመስጋት ነው፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቋል። ይህ በመንግስት እና በሕዝብ ተሳትፎ ማብቂያውን ያገኘው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በኋላ፤ ሌሎች የሕዳሴ ግድቦች እንደሚቀጥሉ አሳምራ ታውቃለች። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከሕዳሴ ግድብ በተጨማሪ ሌሎች ግድቦችን እንደምትሰራ እያስታወቀች እንደምትገኝ ይታወቃልና ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ለግብጽ የሚያዋጣት ነገር ቢኖር ከወራት በፊት ተፈርሞ ሕግ የሆነው የናይል ትብብር ማሕቀፍ ስምምነትን ፈርሞ መቀበል ነው። ይህን የትብብር ማሕቀፍን ተቀብላና ከኢትዮጵ ጋር ተባብራ ብትሰራ ለእርሷ መልካም ይሆናል፡፡ ይህን ካደረገች ተጨማሪ ውሃ የምታገኝ ይሆናል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ዋናው ቁምነገር ነው ብዬ የማምነው በአቋሟ መጽናት አለባት፡፡ የተስማማነውን ነገር ሥራ ላይ እንዲውል በማድረጉ በኩል አሁን የመጣችበት ሁኔታ መልካም ነው፤ ይህንኑ አጠናክሮ መቀጠል ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን አገራችን እንዲረጋጋ የተከፈለውን ያህል ዋጋ በመክፈል ሰላምን ማምጣት ይጠበቅብናል። በተለይ ሀገርን ከእድገት የሚገታው በውስጥ የሚፈጠረው የዕርስ በዕርስ ጦርነት እንደመሆኑ ያንን አካሔዳችንን መግታት መቻል አለብን፡፡

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ እውቅና እያገኘ ነው ብለው ያስባሉ?

አየለ (ዶ/ር)፡– በእኔ እምነት የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ሊቀለበስ አይችልም፡፡ እኛ መገንዘብ ያለብን የባሕር ጥያቄ ስንል አንደኛ ከባሕር ጋር ያለን ታሪካዊ ቁርኝታችን በጣም ረጅም ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ከአክሱም ስልጣኔ ብንጀምር ሁለት ሺ ዓመት ያስቆጠረ ነው። የባሕር በር ያጣነው አሁን በቅርቡ ነው፤ ማለትም ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችው ከሶስት አስርት ዓመት በፊት ነው፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄዋን ይዛ ስትንቀሳቀስ ሁሉ ነገር ምቹ ሆኖ ይቀጥላል ላይባል ይችላል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ ታላቅ አገር እንደመሆኗ የባሕር በር ሳይኖራት መቀጠል ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን ገና ይህን ጥያቄ ባነሳችበት ወቅት የተለያየ ሴራ ሲሴርባት እንደነበር ማስተዋል ተችሏል፡፡ እንዲያም ሆኖ ኢትዮጵያን ካነሳችው ጥያቄ ወደኋላ ሊመልሳት የሚችል ነገር አይኖርም፡፡ የያዘችው ጥያቄ ትክክለኛና ምላሽ የሚያሻው በመሆኑ ያንን ዓላማ ሊቀለብስ የሚችል አይኖርም፡፡

ምክንያቱም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚዋም መበልፀግ ትፈልጋለች፤ በማኅበራዊ ጉዳይም የበለጠ ስኬታማ መሆን ትፈልጋለች፤ በሁለንተናዋ መሻሻልን ትሻለችና ከምንም በላይ ድኅነትን ማጥፋት ግቧ እንደመሆኑ እነዚህ ሁሉ ጉዳዮቻችን ስኬታማ ይሆኑ ዘንድ የባሕር በርን ማግኘት ይኖርባታል፡፡ ስለዚህ ይዘን የተነሳነው ጥያቄ ትክክለኛ በመሆኑ በእኔ ግምት የባሕር በር ጥያቄያችን ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱ እሙን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለሁልጊዜ ትብብርዎ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

አየለ (ዶ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You