አመድ አፋሽ እያደረገ ያለው ሕገ ወጥ ደላላና ኬላ

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በሰሞኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያቸው፤ የግብይት ሥርዓቱን በማበለሻሸት ትልቅ ድርሻ የያዘውን የደላሎች ጣልቃ ገብነት ለመቀነስ እየተደረገ ያለው ጥረት ገልጸዋል። የደላሎች እጅ ረዥም በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ የተሠራውና እየተሠራ ያለው ሥራ መልካም ቢሆንም አሁንም ገበያው ከሕገወጥ ደላሎች እጅ አልወጣም። አሁንም የደላሎች ጡንቻ ፈርጥሞ የሚታይበት አካባቢ ስላለ በዚህ ረገድ ተጀመሩ የተባሉ የሕግ ማስከበርና ዕርምጃዎች በያዝ ለቀቅ ሳይሆን ባልተቋረጠ መንገድ ከተሄደበት ለውጥ ሊመጣ ይችላል ብለዋል።

በገበያ ውስጥ የምርት እጥረት እንዲፈጠርና የዋጋ ንረትን የሚያባብሱ ናቸው ብለን ከምንጠቅሳቸው ውስጥ ምርት በመሸሸግና ጊዜ ጠብቆ ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት አንዱ ነው። የኮንትሮባንድ ንግድ፣ የደላሎች ጣልቃ ገብነትና የመሳሰሉ ሁኔታዎች ለገበያ ያለመረጋጋት ምክንያት ስለመሆናቸው በተደጋጋሚ የሚጠቀስ ነው። የብር የመግዛት አቅም መዳከምና ሌሎች ለዋጋ ንረት ምክንያት ናቸው የሚባሉ ሰው ሠራሽ ውንብድናዎችም ችግሩን በማባባስ የየራሳቸው አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ይለናል የአማርኛው ሪፖርተር ጋዜጣ።

እስካሁን ከምንሰማቸው ሕገወጥ ተግባራትና የተለመዱ ተግዳሮቶች ባሻገር ሕገወጥ የተባሉ ኬላዎች እየተፈጸሙ ነው የተባለው ችግር ደግሞ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ አዲስ ተግዳሮት ሆኖ መጥቷል። ሰሞኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝው ስለመሥሪያ ቤታቸው የሥራ አፈጻጸም ገላጸ ካደረጉት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ስለሕገወጥ ኬላዎች የተናገሩትና ችግሩንም ለማስቆም የተቸገሩ መሆኑን የገለጹበት መንገድ የሁኔታውን አሳሳቢነት አመላክቷል።

ሕገወጥ በተባሉ ኬላዎች ዙሪያ የሰጡትን ማብራሪያ ቃል በቃል እንዲህ የሚል ነበር። ‹‹አሁንም የቀረጥና የኬላ ችግር አንገብጋቢ መሆኑን ይህ ምክር ቤት እንዲገነዘብ እንፈልጋለን። እስከ ትናንትናው ድረስ በኢትዮጵያ ኬላ ይነሳ ተብሎ በመንግሥት ደረጃ ቢወሰንም የተለያዩ ሰበባሰበቦች እየተፈለጉ 283 ሕገወጥ ኬላዎች በመላ አገሪቱ ተንሰራፍተው ይገኛሉ። እነዚህ ኬላዎች በሙሉ የምርት ነፃ ዝውውርን የሚገድቡ የሎጀስቲክስ ቅልጠፋውን የሚገድቡ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና ያላቸው መሆኑን ፓርላማውም አውቆ በራሱ ትግል ማድረግ አለበት ብዬ አስባለሁ። በእኛ በኩል ለሚመለከታቸው አካላት አሳውቀናል። ዕርምጃ ይወሰዳል ብለን እናስባለን።

ኬላ ተነስቷል ይባላል ግን በዚህ በኩል ደግሞ ቺንጋ ይወጠራል። በእኛ በኩል ያደረግነው ጥናት ድሬዳዋን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች 283 [ኬላ] ውጠራ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ይኼ ሲነሳ ነው እንግዲህ የዋጋ ንረት የሸቀጦች ዋጋ ሊቀንስ የሚችለው እንጂ በየጣቢያው ዋጋ የሚጨምሩ ኑሮ የሚያባብሱ ጉዳዮች እየተቀመጡ ሊሆን አይችልም። በእኛ በኩል የተቻለንን እያደረግንና ጥናቱን ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በጋራ ሆነን ነው ያጠናነው። ይህ ጥናት ቦታ አለው። መረጃ አለው። የሚታወቅ ጉዳይ ነው፤›› በማለት ይህንን ከአቅም በላይ የሆነባቸውን ችግር ለመቅረፍ ፓርላማውም እንዲተባበር የጠየቁበት ነበር።

የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በአንድ ወቅት ይፋ ባደረገው ጥናት ምርት ሸማቹ ጋ የሚደርሰው እስከ 60 በመቶ ዋጋ ተጨምሮበት ይላል። ሸማቹ ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እያስከተሉ ካሉ የግብይት ችግሮች አንዱ በመላ ሀገሪቱ የተወጠሩና የተዘረጉ ሕገ ወጥ የገመድ ኬላዎች ናቸው። የዚህ ዋጋ ጭማሪ ሌላው ምክንያት ምንም እሴት የማይጨምረው ደላላ ነው። አምራቹ ባመረተው ምርት ተጠቃሚ ካለመሆኑ ባሻገርም ሸማቹ ላልተገባ የዋጋ ጭማሪ ይዳረጋል።

በአገራችን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ተጃምለው የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ የዕለት ተዕለት ኑሮ ፈተና እያደረጉት ነው።ዳሩ ግን ከአምራቹና ከሸማቹ ቁጥር የማይተናነሰው ደላላ ገበያውን አንቆ አላላውስ ከማለት አልፎ በመዳፉ ስር ማድረጉ በእንቅርት ላይ ቆረቆር ሆኗል።መንግስት የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ የሚያደርገው ጥረት በሕገ ወጥ ደላላ የተነሳ አመድ አፋሽ እያደረገው ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ሆነ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሕገ ወጥ ደላላን ከግብይት ሰንሰለቱ ለማስወጣት ያግዛል ያሉትን መመሪያ ቢያዘጋጁም ወደ ሥራ ስላልገባ ችግሩ ተባብሶ ቀጥሏል። በነጻ ገበያ ስም ገበያው ስድ መለቀቁና የትርፍ ሕዳግ አለመወሰኑ ሌላው ችግር ነው።

የአገራችን ኢኮኖሚ በአዳም ስሚዝ የኢኮኖሚክስ ሀ ሁ በፍላጎትና አቅርቦት ሳይሆን በደላላ የሚዘወር ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ገበያው ካለበት መዋቅራዊ ችግር ባልተናነሰም በገበያው የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ክፍተት መኖሩ ችግሩን አወሳስቦታል። በዓለማችን ባልተለመደና ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በአገራችን የተሰገሰገው ደላላ በገበያውና በኢኮኖሚው ላይ አዛዥና ናዛዥ ሆኗል። ደላላው በመንግሥት ውስጥ ያለ ሌላ የገበያ መንግሥት ሆኗል። ምንም አይነት ጊዚያዊና ዘላቂ መፍትሔ ቢቀመጥ ደላላውን ከኢኮኖሚ መዋቅር ማስወጣትና በሕግና በሥርዓት እንዲመራ ካልተደረገ ከዚህ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት አዙሪትና ቀለበት ሰብሮ መውጣት አይቻልም።

በእያንዳንዳችን ሕይወት አዛዥ ናዛዥ የሆነው “ድለላ!?” የቃሉ ትርጉም ምን ማለት ይሆን!? ምንም እንኳ በሥነ ልሳን አስተምህሮ በስያሜውና በተሰያሚው መካከል የባህሪ ግንኙነት እንደሌለ ቢበየንም፤ የቃሉ ግብርና ምግባር ስለተማታብን፣ ስለተጣረሰብን ትርጉሙን እንመልከት። የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም ያዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት፤ “ደላላ”ን፦ ‘ገንዘብ እየተከፈለው ተፈላላጊዎችን (ሻጭና ገዥን፣ አከራይና ተከራይን፣…) አገናኝ፣ አስማማ፤’ በማለት ይተረጉመዋል።

በመደለል ሥራ ላይ የተሰማራ ሰው፤ አታላይ፣ በውሸት አግባብቶ ለማሳመን የሚሞክር፤ “ድላል”ን ደግሞ ለደላላ የሚከፈል ገንዘብ በማለት ይተረጉማል። የደስታ ተክለወልድ ዘሀገረ ወግዳ በ1970 ዓ.ም የአማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ፤ ደለለ፦ አሞኘ፣ አታለለ፣ ሸነገለ፣ የማያደርገውን አደርጋለሁ አለ፤ ደላላ፦ አመልካች፣ ጠቋሚ፤ ድላል፦ ለጠቋሚ፣ ላስማሚ የሚሰጥ ገንዘብ ሲል ይተረጉመዋል። ይሄኛው ትርጉም ከቀደመው ይልቅ የአገራችንን ደላላ ቁልጭ አርጎ ይገልፀዋል።

የእንግሊዝኛውን ትርጉም ‘broker’ ስረወ ቃል ስንመለከት “brocour” ከሚለው የፈረንሳይኛ ቃል የመጣ ሲሆን፤ ከ14ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የቋንቋው አካል መሆኑን ሜሪያም ዌቢስተር የእንግሊዘኛ መዝገበ ቃላት ያወሳና ትርጉሙም፦{bro·ker: a person who helps other people to reach agreements, to make deals, or to buy and sell property (such as stocks or houses)} ነው ይለናል። የአማርኛውም ሆነ የእንግሊዘኛው መሰረታዊ ትርጉም ተቀራራቢ ቢሆንም፤ “ድለላ” ሲነሳ አብሮ ማታለል፣ መሸንገል፣ ማሞኘት፣ በውሸት አግባብቶ ማሳመን፤ የሚሉ አሉታዊ አንድምታዎች ግዘፍ ከመንሳት አልፈው “ድለላ” በተነሳ ቁጥር ቀድመው ወደ አዕምሯችን የሚመጡት እነዚህ አሉታዊ ብያኔዎች ናቸው። በአገራችን ያለውን አብዛኛውን ደላላም ይገልፁታል ተብሎ ይታመናል። ሆኖም እጅግ ያነሱና በጣት የሚቆጠሩ ቢሆኑም ታማኝ፣ ሀቀኛና መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው ደላሎች መኖራቸው ግን ሊዘነጋ አይገባም።ድለላ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮችን ሳይቀር እንዴት እያወከ እንደሆነ ላነሳሳ፤

1.ኢኮኖሚያዊ፦ኢኮኖሚያችን ከሌሎች አገራት ለየት ያደርገዋል ብዬ ከማምንባቸው ግርምቶች ቀዳሚው፤ በአዳም ስሚዝ የኢኮኖሚክስ ሀ ሁ ዝቅተኛ መስፈርት በሆኑት ፍላጎት/ demand እና አቅርቦት/supply አለመዘወሩ ነው። ከጉልት እስከ ጅምላ ንግድ፣ ከጎጥ እስከ ፌዴራል፣ ከሽንኩርት ማሳ እስከ አትክልት ተራ፣ ከሚዛን ተራ እስከ እህል በረንዳ፣ ከአንድ ክፍል ጭቃ ቤት እስከ ተንጣለለ ቪላና ፎቅ፣ ከአንድ ጥማድ መሬት እስከ ጋሻ መሬት፣ ከአራጣ ብድር እስከ ባንክ ብድር፣… ከታች እስከ ላይ በተሰገሰጉ ህልቁ መሳፍርት ደላሎች ሳምባ የሚተነፍስ ኢኮኖሚ መሆኑ ነው።

አንድ ወዳጄ በዚያ ሰሞን እንዳጫወተኝ ከሆነ ከለውጡ በፊት የደላላ እጅ ሀይ ባይ በማጣቱ እረዝሞ እረዝሞ አገራችን በምትፈርማቸው ብድርና እርዳታ ሳይቀር ፈርቅ እስከመያዝ ደርሶ ነበር። እግራችን እስኪቀጥን ብንዞር የደላላ እጅ ያልገባበት የኢኮኖሚ ዘርፍ የለም። ከላይ ከትርጉሙ እንደተመለከትነው የድለላ ሥራ ሻጭና ገዥን ማገናኘት ለዚህም ድላል (የአገልግሎት ክፍያ) መቀበል ቢሆንም፤ የአገራችን ደላላ ግን በዓለም ታይቶም ተሰምቶም በማያውቅ ሁኔታ ዋጋ ቆራጭ፣ ተማኝ፤ ገበያ መሪ እስከመሆን ደርሷል።

አሁን ያለው የእህል፣ የአትክልት፣ የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ፤ የመኪና የንግድም ሆነ የኪራይ ቤት ክፍያ፣ የመሬት ዋጋ፣… የተቆረጠው፣ የተተመነው በገበያ ሳይሆን በደላላ ነው። በዚህም ገበያ አመጣሽ ሳይሆን፤ ደላላ ዘራሽ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት አስከትሏል። በዚህ የተነሳ ዜጋው በኑሮ ውድነት ፍዳውን እያየ ነው። የሸቀጡ፣ የምርቱ፣ የአገልግሎቱ አምራች፣ አቅራቢም የሚገባውን ጥቅም እያገኘ አይደለም።

ከሸማቹም፣ ከሻጩም በሁለት ቢላዋ እየበላ ያለው ሕገ ወጥ ደላላው ነው። ዛሬ በመላው አገራችን ያሉ አርሶ አደሮችም ሆኑ አርብቶ አደሮች በተደጋጋሚ የሚያነሱት ጥያቄ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው የሚወተውቱ ናቸው። ለገበያ ከሚቀርቡ እንስሳትም ሆነ ተዋጽኦ ተገቢውን የድካማቸውን ዋጋ እንዲያገኙ ሲወተውቱ፣ ሲማፀኑ በየሚዲያው ብንሰማም፣ ብንመለከትም መፍትሔ ባለማግኘታቸው ዋጋ የሚቆርጥላቸው ደላላው ነው። በምርቱ ተጠቃሚዎች እነሱ ሳይሆን ደላላው ነው። አርባ ምንጭ ገበሬው ኪሎ ሙዝ 20 ብር ባልሞላ ዋጋ እንዲሸጥ፤ አዲስ አበባ ላይ ደግሞ 60 ብር እንዲሸጥ የወሰነው ገበሬው ሳይሆን ደላላ ነው። አርሶ አደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ የድካሙ፣ የላቡ ተጠቃሚ ካለመሆኑ ባሻገር፤ ደላላ አመጣሽ የሆነው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት የኢኮኖሚውን ወደለየለት ቀውስ እያንደረደረው ነው።

ሕገ ወጥ ደላላው ያለ አዛዥ ናዛዥ ገበያውን በብቸኝነት መቆጣጠሩ፤ መንግሥት በነፃ ኢኮኖሚ ስም መነሻ ዋጋ ወይም ጣራ ተመን እና የትርፍ ሕዳግን /profit margin/ አለመወሰኑ፤ ከሕገ ወጥ ደላላው ጋር እሳትና ጭድ ሆኑ የኑሮ ወድነቱን እያቀጣጠለ፤ በዜጋው ላይ ብሶትን፣ ምሬትን ተስፋ መቁረጥን እየከዘነ ይገኛል። በዓለማችን የነፃ ገበያ አባት የምንላቸው ምዕራባውያን ሳይቀሩ የትርፍ ሕዳግንም ሆነ የመነሻ ዋጋ ደረጃን እየወሰኑ፤ ገበያውን እየተቆጣጠሩ ባለበት፤ እኛ ለዛውም ያልሰለጠነውን ኢኮኖሚ ስድ መልቀቃችን ዛሬ ለምንገኝበት የኑሮ ውድነት ዳርጎናል።

2.ማሕበራዊ፦ባለፉት ዓመታት ምሳሌ፣ አርዓያ የሚሆን ቤተሰብ፣ ተቋም፣ መሪ በየደረጃው አለመፈጠሩ፤ የግብረ ገብ ትምህርት አለመሰጠቱ፤ ፈሪአ እግዚአብሔር (ፈጣሪ) ያለው ትውልድ አለመታነፁ ዛሬ ለምንገኝበት የማሕበራዊ ቀውስ አፋፍ አድርሶናል። ውሸት፣ ሌብነት፣ ዘረፋ፣ ማጭበርበር፣ መካድ፣ ጥሎ ማለፍ፣… ነውር መሆናቸው ቀርቶ የሚያሸልሙበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። የዚህ ትውልድ፣ ማሕበራዊ ቀውስ ውጤት የሆነው አብዛኛው ደላላም መዋሸትን፣ ማታለልን፣ በአቋራጭ መክበርን ሙያ እስከማድረግ ተግቷል። ገንዘብ እስካገኘ ድረስ ለዜጋው ለወገኑ ደንታ ቢስ ሆነ። እህት ወንድሞቹን በማይጨበጥ ተስፋ እየደለለ ለስደት፣ ለመከራ ዳርጎ በበርሀ፣ በባህር አለቁ። በአረመኔዎች እጅ ወድቀው የአካላቸውን ክፍል አጡ። ሕገ ወጥ ድለላው በዚህ የሚያበቃ አይደለም።

በአገራችን እየተስፋፋ በመጣው የወሲብ ንግድም ግንባር ቀደም ተዋናይ ነው። ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ ልጃገረድ ሕፃናትን ሳይቀር ለሕገ ወጥ የወሲብ ንግድ እስከማቅረብ፣ የዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎችን ለዚህ ሕገ ወጥ ተግባር እየመለመለ የፎቶ አልበም አዘጋጅቶ የሚያቀርብ አረመኔ ደላላ በየዩኒቨርሲቲዎቻችን በሮች ማግኘት እየተለመደ መምጣቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ዛሬ ዛሬ ደግሞ አዲስ የድለላ ዘርፍ ማለትም ስለ የማህፀን ኪራይ /surrogacy/ ደላሎች መስማት ከጀመርን ውለን አደርን፤ ልጅህን ለልጄ ማለት እየቀረ ተጋቢዎች ራሳቸው ወስነው ትዳር መመስረት እየተለመደ ቢመጣም፤ አሁን ሶስት ጉልቻ በደላላም ተጀምሯል። ምን አለፋችሁ ድለላ ያልገባበት የሕይወታችን ቅንጣት የለም።

በእንቅርት ላይ እንዲሉ በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች እየተሸረሸረ በመጣው ማሕበራዊ ተራክቦ ላይ ሥነ ምግባር የሌለው ሕገ ወጥ ደላላ በአናቱ ተጨምሮበት ቀውሱን እያባባሰው ነው።

ራሳቸውን ሕጋዊ ብለው የሚጠሩትም ሆነ ሕገ ወጥ ደላላዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በዜጋው፣ በአገሪቱ ላይ እያሳደሩት ያለውን አሉታዊ ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖ ለማስወገድ መንግሥት የዘነጋውን፣ ችላ ያለውን ኃላፊነቱን ዛሬ ነገ ሳይል መወጣት ሊጀምር ይገባል። በድለላ የሚዘወረው ኢኮኖሚ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ የሆነው ሸማች፣ ሕዝብም ኢኮኖሚውን ከድለላ ምርኮ ነፃ ለማውጣት የድርሻውን ማበረከት ይጠበቅበታል። የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ የሚመለከታቸው የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን መጠየቅና ከጥልቅ እንቅልፋቸው መቀስቀስ ይጠበቅበታል። የዘርፉ ልሒቃንም የአደጋውን ስፋት በጥናት ተንትነው ሊያስረዱ ይገባል።

ከዚህ ጎን ለጎን መንግሥት በየደረጃው ከጎጥ እስከ ፌዴራል፣ ከሽንኩርት፣ ከቲማቲም እስከ ጅምላ ንግድ ገበያውን፣ የንግድ ሥርዓቱን በኔት ወርክ ተደራጅቶ እያተራመሰ ያለውን ሕገ ወጥ የድለላ ኃይል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በቃህ!!! ሊለው ይገባል። መንግሥት በአጭር ጊዜ መሰረታዊ ሸቀጦችን አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ ከደላላ ነፃ በማድረግ፤ ሸማቹና ሻጩ ያለደላላ በገበያ ሥርዓት በቀጥታ እንዲገበያዩ መደላደሉን ሊፈጥር ይገባል። ከዚህ በመቀጠል የገበያ ሰንሰለቱን ከሕገ ወጥ ደላላ መዳፍ ፈልቅቆ ነፃ አውጥቶ ሕግን ማስከበር ይጠበቅበታል። በመቀጠል ሕጋዊ ደላላው የሚገዛበት ሕገ ደንብ እና እንደአስፈላጊነቱ የሥነ ምግባር መመሪያ ሊዘጋጅ ይገባል። የደላላ ክፍያና ድለላ የሚፈቀድባቸውና የሚከለከልባቸው ምርቶችና አገልግሎቶች በሕግ በማያሻማ ሁኔታ መለየት አለባቸው።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You