ጊዜው የአዝመራ ስብሰባ ነው፤ በሃገራችን የተለያየ አቅጣጫ ለሚንቀሳቀስ ሰው፤ የደረሰ ምርት ሲታጨድ፣ ሲሰበሰብ፣ ሲከመር ወይ ደግም ሲወቃ ሊመለከት ይችላል። እንዲህ ማለቴ ሁሉም ቦታ ተመሳሳይ እንዳልሆነ ግንዛቤ ይያዝልኝ።
በየቦታው ሲዘናፈል የቆየው ምርት ግን ወደጎተራ የሚከተትበት ወቅት በመሆኑ በርከት ያለ ቦታ የሚያጭዱና የታጨደውን ወቅተው ምርቱን እዛው እጅ በእጅ ለአምራቹ የሚያስረክቡ ማሽኖች በየማሳው ሲርመሰመሱ መታየታቸው እውን ነው።
በእርግጥ የሚያጭዱና የሚወቁ ማሽኖች በየማሳው ተፍ ተፍ የማለታቸው ምስጢር በየአካባቢው ያለው አርሶ አደር ጤፉን፣ ስንዴውንም ሆነ ገብሱን በኩታ ገጠም ማረስ በመቻሉ ነው። ይህ የኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴን ተግባራዊ ለማድረግ ግን ብዙ ተደክሞበታል።
በቀበሌው ውስጥ ካለው የግብርና ባለሙያ ጀምሮ እስከ ፌዴራል ግብርና ሚኒስቴር ድረስ እንደ ቀላል የማይታይ ልፋትን ጠይቋል። ዛሬ አርሶ አደሩ ጥቅሙ ስለገባው በጋራ ማረስን ምርጫው አድርጓል። የአስተራረስ ዘዴው ተቀባይነት ስለ ማግኘቱም በርካታ ማሳያዎችን እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል።
ነገር ግን በጥቅሉ የግብርና ሚኒስቴር መረጃን ማየቱ ገላጭ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። የሚኒስቴሩ መረጃ እንደሚያሳየውም፤ ዘንድሮ በመኸር ወቅት ከታረሰው ከ20 ነጥብ አራት ሚሊዮን ሔክታር መሬት 11 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሔክታር መሬት የታረሰው በኩታ ገጠም ነው። ይህ አኀዝ ከቁጥር የዘለለ ነው።
ለረጅም ጊዜ በራሱ ምርጫና ፍላጎት የፈለገውን ሲዘራ የኖረን አርሶ አደር አሳምኖ ወደዚህ ውጤታማ ወደሆነው የአስተራረስ ዘዴ ማምጣት ብዙ ልፋትን ጠይቋል። በአሁኑ ወቅት የእርሻ ጊዜ ሆኖ የእርሻ ትራክተሮች እንደ አጫጆቹና መውቂያዎቹ ማሽኖች በየማሳው ባይርመሰመሱም በባለፈው የእርሻ ጊዜ በትራክተር የታረሰው መሬት ወደ አምስት ሚሊዮን ሔክታር ነበር ።
እንደእነዚህ አይነት ለውጦች ስንመለከት ግብርናችን እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ በዝናብ ላይ ተንጠልጥሎ የመጓዙ ነገር እያበቃለት የመምጣቱ ነገር እውን እየሆነ ነው ማለት ይቻላል። ለዚህ ደግሞ በዋንኛነት የሚጠቀሰው መንግሥት ዘርፉን በብዙ መልኩ መደገፍ የሚያስችሉ ወሳኝ ርምጃዎችን መውሰዱ ነው።
በተለይም የተለያዩ ኢንሼቲቮችንና አዲስ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ መቅረጹ ብዙ ርቀት መሔድ አስችሏል። ይህ የመንግሥት ጥረት ግብርናውን ኮሜርሻላይዝድ በማድረግ እና በማዘመን ለኢንዱስትሪ ግብዓት እና ለወጪ ንግድ በቂ የሆነ ምርት እንዲመረት በመደረግ ላይ ይገኛል።
መንግሥት ተግባራዊ እደረገ ያለው የግብርና ፖሊሲ ሃገራችን በዘርፉ ያላትን ሃብት አሟጦ መጠቀም የሚያስችል ነው። የግብርናው ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረሰበትን ሁኔታ ያገናዘበ፣ ምርታማነትን በጥራትም በብዛት የማስፋቱን አካሔድ የሰነቀ ነው። ከዚህም እልፍ ሲል መጪውን ዘመን መዋጀት የሚያስችለው ነው ለማለት ያስደፍራል።
ፖሊሲው፣ የአምራቹንም የአስመራቹንም ዓይን የሚገልጥ ነው። ባለፉት አምስት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ የተገኘው ስኬት አስገራሚ ነው። መሬቱም ውሃውም የነበረ እና ያለ ነው፣ ይህ እንዴት ሆነ ብሎ መጠየቅ መልካም ነው።
አርሶ አደሮችም ቢሆኑ ምናልባት ከዓመት ዓመት ቁጥራቸው ይጨምር እንደሆን እንጂ እነርሱም ወትሮም የነበራቸውን መሬት ይዘው የቀጠሉ ናቸው። ታዲያ የተቀየረው ምንድን ከተባለ የተቀየረው አመለካከት ነው። ከአይቻልም ወደይቻላል መንፈስ መምጣት መቻል ነው።
ቀደም ሲል በሥራ ላይ የነበረው የገጠር ልማት ፖሊሲ፣ የግብርናን ምርታማነት እና ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ ብሎም የገጠር መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት እና ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት ጉልህ ድርሻ እንዲያበረክት በመታሰቡ በአዲሱ ፖሊሲ ሊተካ ችሏል።
ነባሩ ፖሊሲ በአዲስ መተካት ካስፈለጉ ነገሮች ውስጥ አንዱ፣ ቀደም ሲል ሃገራችን ትከተለው የነበረው የግብርና መር የልማት ፖሊሲ ወደ ብዝኃ ዘርፍ የልማት ፖሊሲ አቅጣጫ በመቀየሩ ነው። ሌላው ደግሞ ገበያን መሠረት ያደረገ የግብርና ምርት አቅርቦትን በማስፋትና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪነትን ከፍ ለማድረግ ነው።
በተለይም ከዘርፉ ተለዋዋጭ ባሕሪያት ጋር የሚመጡ ለውጦችን ለማስተናገድ እንዲሁም የዘርፉን መልካም አጋጣሚዎችና የመልማት አቅም በስፋት በመጠቀም የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ማረጋገጥ ከብዙዎቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
በርግጥ አሁን ላይ የግብርናው ዘርፍ በርካታ ስኬቶችን በማስመዝገብ ላይ ነው መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፤ ለምሳሌ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ወደትግበራ የገባውን የስንዴ ኢንሼቲቭ መጥቀስ ይቻላል። ይህ የስንዴ ኢንሼቲቭ በአሁኑ ወቅት አስገራሚ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑ ይታወቃል።
የስንዴ ውጤት ብቻ ሲስተዋል አምና በ2016 ላይ 230 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ማምረት ተችሏል። ከዚህ አኳያ ስንዴ ኤክስፖርት ማድረግም ተጀምሯል። በዚህ ውስጥ አይነተኛ ሚና የተጫወተው ደግሞ የመስኖ ስንዴ እንደሆነ ግልጽ ነው።
ለንጽጽር ያመች ዘንድ ከአራት ዓመት በፊት በመስኖ የተመረተው ስንዴ 700 ሺ ኩንታል አካባቢ ብቻ እንደነበር መረዳቱ በቂ ነው። የአምና የ2016 በጀት ዓመት ሲታይ ደግሞ ከሦስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ላይ 107 ሚሊዮን ኩንታል ማግኘት መቻሉን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከአንድ ወር በፊት ካወጣው መረጃ መረዳት ይቻላል።
መንግሥት በወሰደው ከፍተኛ ውሳኔ ለዓይን የሚያጠግብ ለውጥ መታየት መጀመሩን አለመመስከር ደግሞ ንፉግነት ነው። በእርግጥ ትናንት “እነዚህንና እነዚያን እቅዶች ከሕዝብ ጋር ሆኜ እተገብራቸዋለሁ” ብሎ እቅዱን ይፋ ሲያደርግ፤ ብዙዎች “የማይተገበሩ እቅዶች ይፋ እየሆኑ ነው” በማለት ዳር ቆመው እቅዱን እንደቅዠት ሲቆጥሩ እንደነበር ይታወሳል።
ይሁንና መንግሥት የእነርሱን ይሁንታ በመፈለግ ጊዜ የሚያጠፋበት ምንም ምክንያት ስለሌለው ወደተግባር ገብቶ በስንዴ ኢንሼቲቭም ሆነ በሌላው መስክ ትልቅ ታሪክ መሥራት ችሏል። እውነታው ሀገሪቱ በግብርናው ዘርፍ አዲስ ታሪክ እያስመዘገበች ስለመሆኑ ተጨባጭ ማሳያ ነው።
ወጋሶ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 10 ቀን 2017 ዓ.ም