የማዕድን ልማት ፋይዳው ብዙ ነው::ሀገር ከዘርፉ የውጭ ምንዛሬ፣ የኢንዱስትሪ ግብቶችንና የመሳሰሉትን እንድታገኝ ያስችላል፤ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች እና ባህላዊ አምራቾች፣ ለማዕድን አዘዋዋሪዎች የገቢ ምንጭ በመሆን ያገለግላል::
በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘርፉ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ይታወቃል::በዓለም ከ50 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ መሰማራታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ::እነዚህ ሰዎች የማዕድን ሥራ የገቢ ምንጫቸው ነው፤ በዚህ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ያስተዳድራሉ::ማዕድን በማውጣት ሥራው የሚያገኙት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ግን እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ::
በኢትዮጵያም ቁጥሩ በውል አይታወቅም እንጂ በጣም በርካታ ዜጎች በባሕላዊ ማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ ተሰማርተዋል:: እነዚህ ሰዎች ማዕድን በማውጣት ሥራ የሚተዳደሩ ቢሆኑም፣ ማግኘት የሚገባቸው ጥቅም ሳያገኙ፤ ሀገርም እንደ ሀገር ማግኘት ያለባትን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ሳታገኝ ቆይተዋል:: ባሕላዊ ማዕድን ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች በመደገፍ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያደርጉ ቀጣይነት ያላቸው ሥራዎች መስራት እንዳለባቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ::
ባለፈው ሕዳር የማዕድን ሚኒስቴር ባዘጋጀው ሦስተኛው የማዕድን ኤክስፖ ላይ ባሕላዊ የማዕድን አምራቾችን የተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቧል:: በጥናታዊ ጽሁፉ ባሕላዊ ማዕድን የማውጣት ሥራ በኢትዮጵያና በዓለም ያለበት ሁኔታም ተዳሷል፤ የመፍትሔ ምክረ ሀሳብም ቀርቦበታል::
ጥናታዊ ጽሁፉን ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክ ጂኦሎጂስት ፕሮፌሰር ወራሽ ጌታነህ ናቸው:: እሳቸው እንዳሉት፤ ጥናታዊ ጽሁፉ በኢትዮጵያ ባሕላዊ ማዕድን አውጪዎች ያሉበት ሁኔታ ለመረዳት ያስችላል:: ጥናቱ ከሌሎች ዓለም አገራት ጋር በማነጻጻር አሁን ያለበት ደረጃ ያሳያል:: ለዓለም፣ ለሀገር፣ ለአካባቢ፣ ለማኅበረሰብ እንዲሁም ከግለሰብ እስከ ቤተሰብ ድረስ ያለውን የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ቃኝቷል::
ባሕላዊ የማዕድን ማውጣት ሥራው በዝቅተኛ የሰው ኃይል፣ በአነስተኛ እውቀት እና በግለሰብ ደረጃ የሚሰራ ነው:: ይህ ደግሞ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ዓለም አቀፍ ድረስ ያለውን ኢኮኖሚ እንዴት ሊደግፍ ይችላል? እንዴትስ እድገት ያመጣል? የሚለው የዓለም አገራት ተሞክሮን ከኢትዮጵያ ጋር በማነጻጸር ዳሰሳ የተደረገበት እንደሆነ ያመላክታሉ::
በጥናቱ እንደተመላከተው፤ ባሕላዊ ማዕድን የማውጣት ሥራው ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለው:: የመጀመሪያው በዘርፉ የተሰማሩ በርካታ ሰዎች መኖራቸው ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲኖር ያደርገዋል:: በዓለም በባሕላዊ ማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ በቀጥታ የተሰማራው ቁጥር 50 ሚሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል:: ይህ ሲባል ደግሞ ለአብነት አንድ ሰው አምስት የቤተሰብ አባላት አሉት ብለን ብንወስድ አምስት በሃምሳ ሲባዛ በዚህ ላይ ኑሮአቸው የተመሠረተው 250 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች አሉ እንደማለት ነው:: ይህ ደግሞ ትልቅ የኢኮኖሚ አንድምታ ያለው ነው ሲሉ ያስረዳሉ ::
ባሕላዊ ማዕድን ማውጣት ሲባል ማዕድን የሚያወጡትን ብቻ የሚያጠቃልል አይደለም፤ ለማዕድን አውጪዎቹ አገልግሎት የሚያቀርቡ ሌሎች ሰዎችም ስላሉ ሌላ ተያያዥ የሆነ ቢዝነስ የሚፈጥር መሆኑን እንደሚያመላክት ይገልጻሉ::ለአብነት ሲጠቅሱ የትራንስፖርት፣ የምግብ፣ የማደሪያ (መጠለያ) አገልግሎት የሚሰጡ እንዲሁም የማዕድን ማውጫ እቃዎችን መሰል አገልግሎቶችን የሚሰጡ በርካቶች መሆናቸው ጠቅሰው፣ ከእነዚህ ጋር ትስስር ያለው ሌላ ኢኮኖሚ ይፈጥራል ሲሉ ያስረዳሉ::
ፕሮፊሰሩ እንደሚሉት፤በኢትዮጵያ በባሕላዊ ማዕድን ማምረት ላይ የተሰማሩ ሰዎች ብዛት ትክክለኛ አሀዝ ባይታወቅም፣ አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ሰዎች በዚህ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል ተብሎ ይገመታል:: ይህ ሲባል ቤተሰባቸውን ጨምሮ በዚህ ላይ ኑሮአቸው የተመሰረተ ከአምስት እስከ 7 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች አሉ እንደማለት ነው:: በዚህ ቢዝነስ ዙሪያ የተሰማሩና ሌሎች አካላት ሲደመሩ ደግሞ ከ10 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ኢኮኖሚው በዚህ ላይ የተመሠረተ መሆኑን መረዳት ይቻላል::እንደ ኢትዮጵያ 10 ሚሊዮን ሕዝብ ማለት 10 እስከ 15 በመቶ ሕዝብ ኑሮውን በዚህ ላይ አድርጓል ማለት ነው፡፡
ለአካባቢው እድገት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆን ደግሞ ሁለተኛው ጠቀሜታው ነው::የማዕድን ሥራ መጀመሩን ተከትሎ ብዙ ጊዜ የመሠረተ ልማቶች ይሰራሉ፤ ጥርጊያ መንገድ ይሰራል፤ ይህን ተከትሎም መኪና ይገባል፤ መንደርም ይመሠረታል፤ መንደሩ ወደ ከተማ ያድጋል::
አሁን በኢትዮጵያ የሚታየው ጅማሮ ይህንን ያመለክታል::በአገሪቱ የማዕድን ማውጣት ሥራን ምክንያት አድርገው የተቆረቆሩና የተገነቡ በርካታ ከተሞች እንዳሉም ይገልጻሉ::ይህም የአካባቢው የቢዝነስ እንቅስቃሴ እንዲበዛ እንደሚያደርግ ጠቅሰው፤ ገበያውን ብለው ከተለያዩ አካባቢ ሰዎች እንደሚመጡም አመልክተው፣ ይህም በአካባቢ ልማት ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ሦስተኛውና ትልቁ ጠቀሜታው የውጭ ምንዛሪ ምንጭ በማድረግ ማዕድንን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ነው:: በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ላላባቸው ማእድን የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ነው::ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ወርቅ ትልቅ ድርሻ እንዳለው አመልክተው፣ አሁን ላይ ደግሞ የጌጣጌጥ ማእድናት፣ ታንታለም የመሳሳሉት ማዕድናት ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ እየተገኘ ነው፡፡
እንደሚታወቀው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለውጭ ገበያ ቀርበው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ከሚታወቁ ምርቶች መካከል ከቡናና ከቅባት እህሎች ቀጥሎ ማዕድን ይጠቀስ ነበር:: አሁን የማዕድኑ ዘርፍ ቀዳሚ መሆን ጀምሯል፤ በደንብ ማልማትና ማስተዳደር ከተቻለ በቀጣይም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት የውጭ ምንዛሪ ችግር ለመቅረፍ ይጠቅማል:: የውጭ ምንዛሪ በአንድ አገር ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ ምን አይነት ለውጥ እንደሚያመጣ ይታወቃል፤ ማዕድን በዚህ መልኩ ጥቅም ያመጣል የሚል ዓለም አቀፋዊም ሆነ ሀገራዊ እውነታ ላይ የተመሰረቱ ትንታኔዎች እንዳሉም ያመላክታሉ::
እንደ ታዳጊ ሀገር በኢትዮጵያ በባሕላዊ ማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ ብዙ ችግሮች ይታያሉ የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ የመጀመሪያው የሕግ ማሕቀፍ ችግር እንደሆነ ይገልጻሉ:: ይህ ሲባል ሕግ የለም ማለት ሳይሆን ሕጉ በአንድ አይነት ሁኔታ በሁሉም አካባቢዎች አይተገበርም ሲሉ ያብራራሉ:: ይህም ሕገወጥ የማዕድን ማውጣት ሥራና ግብይት እንዲኖር ያደርጋል ይላሉ::
ሕግ ሥራ ላይ ካልዋለ የማዕድኑ ምርት ታክስ እንደማይደረግ ተናግረው፣ ሕግ የግድ ሥራ ላይ ካልዋለ ማዕድኑ ከሕገ ውጪ በሆነ ሁኔታ ወደ ውጭ የሚወጣባቸው መንገዶች ይበዛሉ ብለዋል::እሳቸው እንዳብራሩት፤ የኢትዮጵያ ወርቅ እና ሌሎች ማዕድናት ሕገወጥ በሆነ መንገድ በድንበር እንደሚወጡ ይነገራል:: በዚህም ሕገወጦች ይጠቀሙበታል፤ መንግሥትና የአገሪቱ ዜጎች አይጠቀሙበትም:: ሕገወጥ የማዕድን ዝውውር አለ ማለት እንደ ሀገር ማግኘት የሚቻለውን በርካታ ጠቀሜታ ያሳጣል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሕግ ሥራ ላይ እንዳይውል የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች እንዳሉም ጠቁመዋል::ሕግ ሥራ ላይ እንዳይውል ከሚያደርጉት መካከል የመጀመሪያው ሰላምና መረጋጋት አለመኖር ነው::እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገሮች በተለይ በማዕድን ማውጫ አካባቢዎች ላይ መረጋጋት ሳይኖር ሲቀር ሕጉን ለመተግበር እንደሚያስቸግር ይገልጻሉ፡፡
ሌላው ችግር በማዕድን ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች የእውቀት ክፍተት መሆኑን ገልጸው፣ ማዕድን እንዴት ይወጣል? እሴት እንዴት ይጨመራል ስለሚሉትና ስለማዕድን ቢዝነስም ጥልቅ እውቀት ያላቸው ባለመሆናቸው፣ የሚያገኙትን ገንዘብ እንዴት አድርገው ወደሚያዋጣ ቢዝነስ መቀየር እንዳለባቸው እንደማያውቁ ተናግረዋል፤ በዚህ የተነሳም የሚያገኙትን ገንዘብ ወደ ሀብትነት ሳይቀየሩ እንደሚባክንባቸው ያስረዳሉ፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ እውቀቱ ቢኖራቸው ግን ገንዘቡን ሌላ ቦታ ላይ ኢንቨስት ያደርጋሉ፤ እንደገናም ቋሚ ነገሮች ላይ እንዲውል ቋሚ የገቢ ምንጭ በመቀየር መጠቀም ይችሉ ነበር:: ማዕድን ተሸጦ የሚገኝ ገንዘብ እንዲባክን አያደርጉም:: አንዳንድ ማዕድን የሚወጣባቸው ቦታዎች በጣም ሩቅ መሆናቸውም ሌላው ገንዘቡን የሚያስቀምጡባቸው ባንኮች ላያገኙ ይችላሉ፤ ይህ ችግር ባንኮችም እየተስፋፉ መምጣታቸውን ተከትሎ እየተፈታ ይገኛል::
ባሕላዊ የማዕድን አውጪዎች ገንዘብ (ካፒታል/ የላቸውም የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ ማንኛውንም ሥራ መነሻ ካፒታል እንደሚያስፈልገው ሁሉ ማዕድን የማውጣቱ ሥራም ካፒታል እንደሚጠይቅ ይናገራሉ:: መነሻ ካፒታል የሌላቸው በርካታ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ አንዳንዶቹ አካፋና ዶማ መግዛት የማይችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል::
እንደ ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ፤ የገበያ ችግርም ይስተዋላል:: ብዙ ጊዜ ማዕድን አውጭዎች ከምርታቸው ተገቢውን ጥቅም አያገኙም:: ከእነሱ ይልቅ ደላሎች አልያም ሕገወጦች ናቸው የሚጠቀሙት:: አውጪዎቹ ስለገበያው አያውቁም፤ ምናልባትም አንድ ሚሊዮን ብር የሚሸጥ አንድ የጌጣጌጥ ማዕድን በሃምሳና በመቶ ሺ ብር ሊሸጡት ይችላሉ:: ይሄ በገሃድ የሚታይ ሀቅ ነው:: አንዳንዶቹ ድንጋይ ይህንን ያህል ሃምሳ ሺ ብር ካወጣ ምን ያስፈልጋል እስከማለት ይደርሳሉ::አለማወቃቸው እንጂ ያ ማዕድን በሚሊዮን ብር ሊሸጥ የሚችል ነው:: ይሄ ከገበያ መረጃ አለመኖር ሊመነጭ የሚችል ችግር ነው፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ የገበያ መረጃ አለመኖር ብቻ ሳይሆን የገበያ አቅርቦቱም በራሱ ሌላኛው ችግር ነው:: ማዕድናቱን ገበያ አውጥተው የሚገዛቸው ካጡ በማይረባ ዋጋ ይሸጡታል:: በተለይ በገጠር ገበያዎች በተለምዶ እንደሚባለው ከዘጠኝ ሰዓት በኋላ ሁሉም ነገር ይረክሳል፤ ምክንያቱም ሻጩ ወደ ገበያ ይዞ የወጣውን ወደ ቤቱ ከሚመለስ ባገኘው ዋጋ ሸጦ መመለስን ይመርጣል፤ የማዕድን አውጪዎች ችግር ይሄ ነው:: ደላሎቹ ደግሞ የሚገዛቸውና አማራጭ ሲያጡ በርካሽ ዋጋ ይሸጣሉ በሚል አውቀው ዝም ይሏቸዋል ›› ሲሉ ፕሮፌሰሩ ይገልጻሉ:: ይህም የአካባቢውን ሕዝብ እየጎዳ ያለ ትልቅ ችግር መሆኑን ጠቅሰው፤ ዜጎችና ሀገር ሊጠቀሙበት የሚችሉትን ሀብት የሕገወጦች ሲሳይ እንዲሆን እያደረገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ባሕላዊ የማዕድን አውጪዎች ከማዕድን ዘርፉ ተጠቃሚ ሆነው ሀገርንም እንዲጠቅሙ ለማድረግ መፍትሔው የሚደረገው ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሆነም ፕሮፌሰሩ ያመላክታሉ::‹‹በሰው ልጅ ታሪክ መንግሥት ያስፈልለገበት ዋንኛው ምክንያቶች ሰላምና ጸጥታ ለማስከበርና የጋራ ሀብትን ለማስተዳዳር ነው፤ ይህ ደግሞ መንግሥት ለአንድ ሀገርና ሕዝብ ሊያደርገው የሚገባ ነው ›› ይላሉ
እሳቸው እንደሚሉት፤ ችግሩን የመፍታቱ ሥራ መጀመሪያ ሕግና ሥርዓትን መዘርጋትና ሥራ ላይ እንዲውል ማድረግን ይጠይቃል:: ሁለተኛ ዘርፉ ለአገር ካለው ከፍተኛ ጠቀሜታ አንጻር እየታየ ለአምራቾቹ አስፈላጊው ድጋፍ መደረግ አለበት:: ባሕላዊ ማዕድን አውጪዎች የገንዘብ አቅም ሆነ እውቀት ስሌላቸው በተደራጀ መልኩ ድጋፍ ሊደርግላቸው ይገባል:: ይህ ሥራ ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም፤ የግል ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ሲቪክ ማህበራት ለማዕድን አውጪዎች ድጋፍ ቢያደርጉ እነርሱም በቀላሉ ከደህነት ይወጣሉ፤ ሀገርንም ይጠቅማሉ:: የሕግ የበላይነትን ማስፈን እና ድጋፍ ማድረግ ብዙ ችግሮች ይቀርፋል::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 11 ቀን 2017 ዓ.ም