ዜና ሀተታ
አባገዳ ሹምቡሎ ዴኮ የአርሲ ሊጣ አባገዳ ናቸው። አባገዳ ሀገር ሰላም እንድትሆን መሥራት ከፈጣሪ የተሰጠው ድርሻ ነው ይላሉ። ለሀገር ሰላም እና አንድነት ለማምጣት በሚደረገው ሀገራዊ ምክክር አስተዋጽኦ ማድረግ ግዴታቸው መሆኑን ፤ ምክክሩ እንደ ሀገር ያሉብንን ያለመግባባት ችግሮች የምንፈታበት ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱን ይናገራሉ።
ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ ምክክሩ የእኔ ሃሳብ ብቻ ተቀባይነት ማግኘት አለበት ሳንል የሌሎችን ሃሳብ በማክበር እና በመደማመጥ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት አለብን የሚሉት አባገዳ ሹምቡሎ፤ እንደአባገዳ በሀገራዊ ምክክሩ ሃሳባቸውን በመስጠት እንዲሁም ምክክሩ በተሳካ መልኩ እንዲከናወን እንደሚሠሩም ይናገራሉ።
ፉሮ ኡሾ ደግሞ ከሻሸመኔ ወረዳ የመጡ ሀደስንቄ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ ሀደስንቄነት ከፈጣሪ የተሰጣቸው ሰላምን የማውረድ ሥልጣን ነው። በወንድማማቾች መሀከል ሰላም እንዲሆን፣ ደም መፋሰስ እንዳይኖር እና ፍቅር እንዲወርድ መሥራት ሀደስንቄዎች የሚታወቁበት እንደሆነም ይናገራሉ።
ሀደስንቄዎች አለመግባባት ሲኖር በትራችንን አስቀምጠን በምክክር እንዲፈታ እናደርጋለን የሚሉት ሀደስንቄዋ፤ በሀገራችን ያለውን አለመግባባት ለመፍታት በሚደረገው ሀገራዊ ምክክርም ያለንን ተቀባይነት ተጠቅመን የበኩላችንን ለማድረግ ተዘጋጅተናል ነው ያሉት።
የአርሲ ሊጣ አባገዳ የሆኑት ቡሹሼ ቡታም የሀገራዊ ምክክሩ ተሳታፊ ናቸው። እንደ አባ ገዳ በአካባቢያቸው በተሰጣቸው ክብር ጥፋቶች ሲኖሩ በመገሰጽ እንዲሁም አለመግባባቶች ሲኖሩ ሲፈቱ መቆየታቸውን ያወሳሉ። አለመግባባቶች ሲኖሩ በውይይት መፍታት ለኢትዮጵያውያን አዲስ እንዳልሆነም ይናገራሉ።
በመመካከር የማይፈታ ችግር የለም የሚሉት አባገዳው፤ እንደ ሀገር ቁጭ ብለን ስንመካከር ያልተግባባንባቸውን ነገሮች በመፍታት ግጭቶችን እና አላስፈላጊ ጦርነቶችን እናስቀራለን ይላሉ።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል በማሳተፍ እያደረገ ያለውን የምክክር ሂደት የሚያደንቁት አባገዳው፤ ያሉ ችግሮችን ፊትለፊት ተገናኝቶ በመመካከር እና በመከባበር ችግሮች እንደሚፈቱ ነው የገለጹት።
ጥላቻ ጠፍቶ እና መከባበር ሰፍኖ ማየት የዘወትር ፍላጎቴ ነው የሚሉት አባገዳው፤ ሀገራዊ ምክክሩ ይህንን የሚያሳካ በመሆኑ እንደአባገዳ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን ከፈጣሪ የተሰጠኝን ኃላፊነት እወጣለሁ ይላሉ።
ሪሀና ሀሰን ደግሞ ከሀረርጌ ቦኬ ለሀገራዊ ምክክሩ የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ አዳማ የተገኙ ሀደስንቄ ናቸው። ሀገራዊ ምክክሩ ተሰባስበን በሀገራችን ባሉ ችግሮች ላይ እንድንመካከር ትልቅ እድል ሰጥቶናል የሚሉት የሀረርጌዋ ሀደስንቄ፤ እድሉ እንዳይባክን እንደሀደስንቄ የበኩሌን አደርጋለሁ ይላሉ።
ሰላም ሁሉም አብዝቶ የሚፈልገው ነገር ነው የሚሉት ሀደስንቄ ሪሀና፤ ሰላም እንዲመጣ ሁሉም ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የበኩሉን ሚና እንዲጫወት እንደሚመክሩም ይገልጻሉ።
በኢትዮጵያ ባህል የማህበረሰብ መሪዎች ትልቅ ክብር አላቸው። ጸብ ቢፈጠር በማስታረቅ፣ ጥፋት ተሠርቶ ቢመለከቱ በመቆጣት ይታወቃሉ። ወጣቶችን በመምከር እና በመገሰጽም መስመር የማስያዝ ሃላፊነት ማህበረሰቡ ሠጥቷቸዋል ሲሉም አባገዳዎች እና ሀደስንቄዎች ያመለክታሉ።
በኦሮሚያ ባህል አባገዳዎች እና ሀደስንቄዎች በማህበረሰቡ በተሰጣቸው ሃላፊነት በተለይ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በመምከር እና ሰላም እንዲወርድ በማድረግ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ይታወቃል።
መዓዛ ማሞ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11 2017 ዓ.ም