ኤርሚያስ የማነ ብርሃን (ዶ/ር) የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በፍትሕ ሥርዓቱ ዘርፈ ብዙ ውጤታማ የማሻሻያ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፤ እየተከናወኑም ይገኛሉ፡፡ በተለይም የሕዝቡን የፍትህ ጥማት እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ሰፊ ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡
በ ሚኒስቴሩ የሪፎርም ሥራዎች ዙሪያ ከፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኤርሚያስ የማነ ብርሃን ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ በሃገር አቀፍ ደረጃ በፍትሕ ስርዓቱ ላይ ሪፎርም ማድረግ ያስፈለገበትን አብይ ምክንያትና ሪፎርሙ ያካተታቸውን ዋና ዋና ማሕቀፎች ቢያብራሩልን ?
ኤርሚያስ ዶ/ር፡- እንደሚታወቀው ለለውጡ ገፊ ከነበሩ ሃገራዊ ችግሮች መካከል በፍትሕ ዘርፉ በተለይም በዳኝነት አካላት ላይ ይነሱ የነበሩ የሕዝብ እሮሮና ምሬቶች ዋነኞቹ ናቸው። እሮሮና ምሬቶቹ ያስነሳቸው ሕዝባዊ ተቋውሞዎች ለዓመታት ሲንከባለሉ የቆዩ፤ የተወዘፉ ችግሮች ነበሩ።
በዘርፉ የፍትሕ ማጣት፣ የፍትህ ጉድለት፣ የዳኝነት በደል፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ አፋኝ፣ ጨቋኝ፣ አሳሪ ሕጎች፤ የፍትህ ስርዓቱ ፖለቲካዊ አድሎ ያለበት መሆኑ እነዚህና መሰል ጉዳዮች ናቸው ሕዝቡን ገፋፍተው ጎዳና እንዲወጣ፣ መንግሥትን እንዲቃወም፣ ሁለትና ሶስት ጊዜ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ያደረጉት። በተለይም ፍትሕ ይስፈንልን፤ የዳኝነት በደልን ይቁምልን የሚል ጥያቄ በሕዝቡ በስፋት ይነሳ ነበር።
በለውጡ ማግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምክር ቤት ንግግራቸው ከገለጿቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኛው የፍትሕ ስርዓቱን ስርነቀል በሆነ መልኩ መለወጥ ያስፈልጋል የሚለው ተጠቃሽ ነው። ሕዝብን መሰረት ያደረገና የሕዝብን ጥያቄ የሚመልስ የሕግ የበላይነት፤ ፍትሕን፣ የዳኝነት ነፃነትን እንመልሳለን በሚል በግልፅ የገቡት ቃል ነበር። በዚያ መሰረት ነው በፍትሕ ዘርፉ የሪፎርም ሥራ የተጀመረው።
ሪፎርሙ መተግበር ከተጀመረ ወዲህ ያመጣውን ለውጥ በሚመለከት በሁለት ከፍለን ማየት ይኖርብናል። አንደኛው ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ የተሰሩ ሥራዎች ናቸው። በተለይ ሃገራዊ ምርጫ ከመደረጉ በፊት የተከናወኑ ሥራዎችን ማየት ተገቢ ነው። በነዚህ ጊዚያት በሃገር አቀፍ ደረጃ የፍትሕ እና የዳኝነት ማሻሻያ ሪፎርሞችን ጀምረናል።
የሕግ የበላይነት፣ የዳኝነት ነፃነት፣ የሰብአዊ መብት መከበር የመሳሰሉት ላይ የመጡ ለውጦች ምን ይመስላሉ? ውስንነታቸውስ ምንድን ነው? የሚለውን በአግባቡ በመንግሥትም፣ በአጋር አካላትና በሕዝብም ተገምግሞ መልካም ነገሮችን ይዘን፣ ክፍተቶችን ለይተን ወሳኝ የሆኑ መሰረታዊ ለውጦችን ሊያመጡ የሚችሉ ጉዳዮችን በመለየት አዲስና የሶስት ዓመት የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ-ካርታ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ከተገባ አንድ ዓመት ተኩል ሆኖታል።
በእነዚህ ዓመታት ከሕግ፣ ከአሰራር፣ ከተቋም አንፃር በርካታ ለውጦችን ማስመዝገብ ችለናል። አፋኝ፣ ጨቋኝና አሳሪ የነበሩ ሕጎች፤ ሁልጊዜ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ስትነሳ አብረው ከሚጠቀሱ ችግሮች መካከል አንዱ የሆነው የሲቪል ማኅበረሰብ ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የፕሬስ ሕግ፣ የምርጫ ቦርድ ሕግ፣ የፀረ ሽብር አዋጅንና ሌሎችንም ሕጎችን የማሻሻል ሥራ ተሰርቷል።
በተጨማሪም ከፖሊሲ፣ ከምርመራ፣ ከደህንነት ተቋማት ጋር የተያይዞ የነበሩ አሰራሮች፣ ሲጠቀሙበት የነበሩት ሕጎችና አካሄድንም የማረቅ ሥራ በስፋት ተከናውኗል። በተለይም በፖለቲካ አመለካከታቸው የታሰሩ በቡዙ ሺ የሚቆጠሩ እስረኞች እንዲፈቱ የማድረግ ሥራም ተሰርቷል። እነዚህ ሁሉ በፍትሕ ሪፎርሙ ፓኬጅ ውስጥ የሚታዩ ናቸው። የዲሞክራሲ የሰብአዊ መብትና የሕግ የበላይነትን ጥያቄዎችን ለመመለስ መንግሥት የሄደባቸው ርቀቶች ናቸው። ይህንን ሲያደርግም ከፍተኛ ዋጋ ከፍሎ ጭምር ነው።
ጫካም ሆነ ውጭ የነበሩት ኃይሎች በአንድ ጊዜ መጥተው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ሂደት ውስጥ እንዲሳተፉ እድል የተሰጣቸው ፍትሕና የሕግ የበላይ እንዲሰፍን በማለም ነው። እንደምናውቀው የተለያዩ ኮሚሽኖችን በማቋቋም ብሔራዊ መግባባት፣ ይቅርታን፣ የድንበርና የማንነት ጥያቄዎችን ለመፍታት ሥራዎች ተሰርተዋል። የቡድን መብትን ከማስከበር አንፃር ደግሞ የሕዝቦችን የራስን እድል በራስ የመወሰን ሕገ-መንግስታዊ መብት ጋር የተያያዙ የክልሎች ጥያቄ በተጨባጭ እንዲመለሱ ጥረት ተደርጓል።
እነዚህ ለውጦች በተጨባጭ ሕዝቡ ከሚፈልገው የለውጥ ውጤት አንፃር የሕዝቡን ፍላጎት አርክተዋል ወይ? የሕዝቡን ምሬት ቀንሰዋል ወይ ? የሚለውን ነገር ለማየት ያስችለን ዘንድ ጥናት አስጠንተናል። በዳኝነት፤ በፍትሕ አካሉ፣ በፖሊሲና በሌሎችም አካላት የሚሰሩ ሥራዎች፤ የሚወጡ ሕጎች፣ የተቋሞች አደረጃጀትና አሰራሮች ምንይመስላሉ የሚለውን በማጤን፤ ሁኔታዎቹን ለመቀየር ሰፊ ሥራዎች ተሰርተዋል፤ አበረታች ውጤቶችን ማምጣት ችለናል።
ይህም ሆኖ አሁንም ቢሆን የሕብረተሰቡን እሮሮ፣ ምሬትና ቅሬታ ከመቀነስ አንፃር ብዙ የሚቀረን መሆኑን ተረድተናል። ጥራት ያለው፣ ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ሁሉን ያካተተ ግልፅ የሆነ የፍትሕ አገልግሎት መስጠት ላይ አሁንም ከፍተኛ ክፍተት አለብን።
ክፍተቶችን ታሳቢ በመድረግ፣ ሁሉን አቀፍ በሆነ መንገድ፤ የተገኙ መልካም ውጤቶችን፣ ሕገመንግሥቱን እና የሃገረ-መንግሥት ግንባታን መሰረት ባደረገ መልኩ፣ አካታች፣ ሁሉን አቀፍ፣ ከክልሎች ጋር አብሮ የሚሰራ የሶስት ዓመት የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ቀርፀናል።
ለዚህም ፍትሕ ሚኒስቴር፣ የዳኝነት አካሉ፣ የፌደራል የፍትሕና የሕግ ማሰልጠኛ ተቋም ከሄግ ኢንስቲትዩት ፎር ሎው ከሚባል ተቋም ጋር በመሆን የዳሰሳ ጥናት አካሄደዋል። ጥናቱ የሕዝባችንን ምሬትና ቅሬታ ለመፍታት ከተለመደውና ከቃላት ጨዋታ ውጪ ከተገልጋዩ ናሙና ተወስዶ የተሰራ ነው።
የሶስት ዓመቱ የትራንስፎርሜሽን እቅዱ ከሐምሌ 1/2016 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2018 ዓ.ም የሚተገበር ነው። ወሳኝና ሁሉን አቀፍ ርብርብ የምናደርግበት ፍኖተ ካርታም ወጥቶለታል። ይህ ፍኖተ- ካርታ አስር አምዶች ያሉት ነው፤ በፊት የነበሩ ለውጦችን መሰረት ያደረጉ፤ የሚነሱ ችግሮችን ሊቀንሱ የሚችሉና ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጡ እንደሚችሉ ታምኖባቸው የተቀረፁ ናቸው።
ከእነዚህም አምዶች መካከል የመሰረተ -ማኅበረሰብ ፍትሕን እናስፋፋለን የሚል ነው። ፍትህ መነሻውንም ሆነ መድረሻውን ዋና ግቡ ማድረግ ያለበት ሕብረተሰቡን ስለሆነ የማኅበረሰብ ፍትህን የማጠናከር ሥራ ትኩረት ተሰጥቶታል። ይህም ሲባል አደረጃጀት፣ ተቋም ላይ ሳይሆን በዋነኛነት የሕብረተሰቡ ፍትህን ለማግኘት የሚያስችለውን፤ የሚጠቀምበትን ውጤታማ አካሄድ በመለየት፤ እሱን ጥቅም ላይ የማዋል አስተሳሰብ ነው።
ይህም ሲባል ከመደበኛ የፍትሕ ስርዓት ውጪ ማኅበረሰቡ ለረጅም ጊዜ ሲጠቀምበት ውጤታማ የሆነ፣ የዳበረ፣ ተዓማኒነት ያለው የባሕላዊ የግጭት መፍቺያ ስርዓት የመጠቀም ባህሉ እንዲጎለብት የማገዝ ሥራ ነው። እንደሚታወቀው ከመደበኛው ፍርድ ቤት ውጪ 80 በመቶ የሚሆኑ ጉዳዮች ረጅም ጊዜ ባዳበሩ የባሕላዊ ፍርድ ስርዓት የሚዳኙ ናቸው።
ኦክስፎርድ የባሕላዊ የዳኝነት ስርዓትን በሚመለከት በሁሉም ክልሎች የዳሰሳ ጥናት አካሂዷል። አብዛኛው በሚባል ደረጃ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን መጠቀምን እንደሚመርጡ ተናግረዋል፤ ለዚህም እንደምክንያት ያነሱት ከጊዜና ከቅልጥፍና ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ነው። አጠቃላይ በመሬት ላይ ያለው እውነታም የሚያሳየው እሱኑ ነው።
ከዚህ አንፃር የማኅበረሰብ ፍትህን በሶስት ዓመት ውስጥ ቢያንስ በተቋም ደረጃ እውቅና እንዲሰጠው የማድረግ፤ የመደገፍ፣ ሞዴል ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቀርፆ ክልሎች እንዲመሩት እስከማድረግ የሚዘልቁ ሥራዎች ሰርተናል።
በአጠቃላይ ፍኖተ ካርታው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታምኖበት፣ በአፈ ጉባኤው በሚመራ አደረጃጀት አብይ ኮሚቴ፣ ቴክኒክ ኮሚቴ የዳኝነት ነፃነቱን በጠበቀ ደህንነት፤ የፍትህ አካላት፣ ፖሊስ፣ አቃቤ ሕግ፣ ማረሚያ ቤቶች እንዳሉ ሆኖ አጠቃላይ በሕዝብ ተወካዮች ፀድቆ እየተተገበረ ነው። በክልሎች ደግሞ በተመሳሳይ አደረጃጀት በሕግ አውጪው ምክር ቤት አፈጉባኤ አማካኝነት ሌሎችም አባል ሆነውበት እንዲደራጁ እየተደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሪፎርሙ በተለይም የዳኝነት ስርዓቱን በማሻሻልና ፍትሕ እንዲከበር ከማድረግ አኳያ ምንአይነት ሚና ይኖረዋል?
ኤርሚያስ ዶ/ር፡- የፍትሕ አካላት እምነት እንዲጣልባቸው የሙያ ብቃት እና ስነምግባር ሊኖራቸው ይገባል። ከዚህ ቀደም በቂ የሙያ ብቃት ፣ ስነምግባር የሌለው፤ ከሕጋዊ ገቢው በላይ ከፍተኛ ሃብት ያፈራ በፍትሕ፤ በዳኝነት፣ በፖሊስና በአቃቤ ሕግ በአጠቃላይ ለስርዓቱ አሉታዊ ምስልን የሚፈጥር፤ ሕዝቡ በስርዓቱ ላይ አመኔታ እንዳይኖረው የሚያደርግ፣ ለሮሮውም ለምሬቱም፤ ለተስፋ ማጣቱም በአንድም በሌላ መልኩ አስተዋፅኦ ያደረገበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። እነዚህን ችግሮች የማጥራት ሥርዓት ያስፈልጋል የሚለው ሃሳብ በእቅዱ ጎልተው ከተካተቱ ጉዳዮች ዋነኛው ነው።
ውጤታማ፣ ቀልጣፋ፣ ግልፅ፣ ወጪ ቆጣቢና አካታች የሆነ ስርዓት ለመፍጠር ሕግ ማውጣትና ተቋም መፍጠር ብቻ ሳይሆን አሰራሩን ዘመናዊ ማድረግ ይጠበቃል። ከዚህ አንፃር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በደንብ መጠቀም ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ በፖሊሲ፤ ፍርድ ቤቶችና በፍትህ ሚኒስቴር የሚታዩ ለውጦች አሉ። እነዚህ ሥራዎች የሶስት ዓመት ፍኖተ ካርታው አካል ናቸው። በአጠቃላይ በፍትህ ውጤታማ የሆነ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለመዘርጋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
ሌላው የፍትሕ ብሔር፣ የአስተዳደር ሕግና የወንጀል ፍትህን በአዲስ እይታ መታየት የሚለው ጉዳይ ነው። ያመጣናቸው ለውጦች የበለጠ ጠቃሚ እንዲሆኑ፤ የሕዝቡን ምሬት እንዲቀንሱ ማድረግ ያስፈልጋል። ምክንያቱንም ምንም ያህል ብናሻሽልም በሚፈለገው ደረጃ ምሬቱን ቀንሰናል ብለን አናምንም። ለዚህም ነው የትራንስፎርሜሽን እቅድ ማዘጋጀት ያስፈለገን።
አብዛኛው ማኅበረሰብ የእለት ተእለት ኑሮውን ሲከውን ከአስተዳደር አካላት ጋር ይገናኛል። አስተዳዳሪዎች የሚሰሩበት ሕግ፣ አሰራራቸው፣ የሚሰጡት ውሳኔዎች (ከፍርድ ቤት መለስ) ምን ይመስላሉ? ግልፅ ነው ወይ? ተጠያቂነት አለው ወይ? መመሪያ ሲወጣ የሚመለከታቸውን አካላት በማካተት ውይይት ይደረግበታል ወይ? የሚሉትንም ነገሮች ለመዳስስ ተሞክሮሯል።
ከዚህ ቀደም በነበረው አካሄድ መመሪያ ከወጣ በኋላ አንዱ ኃላፊ መሳቢያ ውስጥ ተቆልፎ ‹‹መመሪያው እንዲህ ይላል›› ነው የሚባለው፤ መመሪያ ስጡ ሲባልም ለመስጠት ፈቃደኛ አይሆኑም። አዋጅ 1183/2012 የወጣውም ለዚህ ነው። ከዚህ የበለጠ ደግሞ ማጠናከር ያስፈልጋል በሚል ነው፤ ፍኖተ ካርታው የተዘጋጀው። ይህ አዋጅ ከወጣ በኋላ ተፈፃሚነቱ በፌዴራል ደረጃ ነበር፤ በአዲስ እይታ ብለን አጠቃላይ በክልሎችም እንዲወጣ አድርገናል። በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ስድስት ክልሎች አውጥተዋል። አሁን ትላልቁ ክልሎች እንዲያወጡም ይጠበቃል።
ይህም አስተዳደር ፍትሕ ለኅብረተሰቡ ለመስጠት የሚያስችል ነው። ሆኖም መመሪያ ሲወጣ ከሕዝብ ጋር መወያየት ያስፈልጋል። የሚወጡ መመሪያዎች ከብሔራዊ ደህንነት ጋር የተያያዙ እስካልሆኑ ድረስ ተጠያቂነት የሰፈነበት መሆን አለበት። ሕገመንግሥቱ አንቀፅ 12 ላይ የመንግስት አሰራር ግልፅና ተጠያቂነት ሊኖረው እንደሚገባ ይደነግጋል። ደግሞም በአንድ ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ለመገንባት እና ሃሳቦች በግልፅ ተወያይተው ሲወጡ ነው ውጤታማ መሆን የሚቻለው። ዝም ብሎ እኔ አውቅልሃለሁ በሚል አሰራር፣ አዋቂ ነን የሚሉ ካድሬዎች ወይም ኃላፊዎች ብቻ ተሰብስበው የሚሰጡት የውሳኔ አካሄድ የትም አላደረሰንም።
ለውጡም ያስፈለገበት አንዱ ምክንያት ይሄ ነው። ይህንን እውን ለማድረግ ነው ክልሎች የአስተዳደር አዋጅ እንዲያወጡ የተደረገው። በቅርቡ ኦሮሚያና አማራ ክልሎች አዋጁን ለማውጣት ዝግጅት እያደረጉ ነው፤ ይህም የትራንሰፎርሜሽኑ አካል ነው። በጥቅሉ በግልፅና በተጨባጭ ሁኔታ አዋጁን አውጥቶ በሕጉ መሰረት እንዲተገበር ለሕዝቡ የተሻለ እድል የሚሰጥ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች አዋጅ በራሱ አወዛጋቢ ሃሳቦችን የያዘና ለአፈፃፀምም አስቸጋሪ እንደሆነ ያነሳሉ፤ እርሶ በዚህ ላይ የሚሰጡት ምላሽ ምንድን ነው?
ኤርሚያስ ዶ/ር፡- እንደተባለው አሻሚና አከራካሪ የሆኑት ነገሮች በዚህ አዋጅ ላይ ከአምስት በመቶ አይበልጥም። ከአዋጁ 95 በመቶ የሚሆኑ አንቀፆች በአግባቡ ቢተገበሩ ከአስተዳደር ፍትህ መጓደል ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ይፈታል ተብሎ የታመነባቸው ናቸው።
እርግጥ ነው በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የሚወጣ አዋጅ ፍፁምና ምሉዕ ሊሆን አይችልም። መሬት ላይ ተግባራዊ ሲሆንም የራሱ የሆነ ተግዳሮት ሊያጋጥመው፤ አዳዲስ ነባራዊ ሁኔታዎችንም ከግምት ውስጥ ላያስገባ ይችላል። ከአፈፃፀም፤ ከምዝገባ፤ ከሚጠበቁት ነገሮች፤ ከአጠቃላይ የፍርድ አፈፃፀም አኳያ ሊኖሩ የሚችሉ ክፍተቶች ሊኖሩ ይችላሉ። እነሱንም ለይተናቸዋል፤ በቅርብ የሚሻሻሉ ናቸው።
ግን አስረግጬ መናገር የምፈልገው አንዲቷን ጉድፍ ከመለየት ባሻገር ያለውን እንኳን በአግባቡ ብንተገብረው ከመንግሥት ተጠያቂነት ከማረጋገጥ ጋር ተያይዞ በሕዝብ የሚነሱ ቅሬታዎችን ይፈታል።
ለምሳሌ ከዚህ ቀደም አንድ መመሪያ አንድ ኃላፊ እንደፈለገ ያወጣ ነበር፤ አሁን ግን መመሪያ ከማውጣቱ በፊት የሚመለከታቸውን አካላት በማወያየት ሕዝቡ አስተያየት እንዲሰጥበት መደረጉ በራሱ ትልቅ ነገር ነው። መመሪያ ከመውጣቱ በፊት ሰዎች እንዲከራከሩበት እድል ይሰጣል።
የሚወጣው መመሪያ የሕዝብን ፍላጎት ያንፀባረቀ እና ተፈትሾ ያለፈ መሆን አለበት። ይህ በመሰረታዊነት የሕግ አውጪውንም ቅቡልነት የሚጨምር ነው። በተጨማሪም ይህንን ሂደት ሳያልፍ የሚወጣ መመሪያ ተቀባይነት የለውም ሲል የመሟገት እድልን ይፈጥራል። ግለፀኝነትንም ይፈጥራል።
በአጠቃላይ አዋጁ ችግሮች የሉበትም ማለት ባይሆንም ከዚህ ጋር ተያይዞ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመፍታት ግን ያግዛል። አሁን ስድስት ክልሎች ሲያወጡ ከፌደራል ተሞክሮ ወስደው ማሻሻያ አድርገው እንዲያወጡ ያደርጋል። በሌላ በኩል ከፍትሕ ተቋማት ውጪ ይሰጡ የነበሩ ዳኝነቶችን ወጥ በሆነ መልኩ ለመምራትና መልክ ለማስያዝ ያስችላል።
ደረጃውን በጠበቀ የሕጋዊነት መርህ፤ የመደመጥ መርህን፤ የመንግሥትን ወጪ በሚቆጥብ፤ ፍትሐዊ ውሳኔ ለመስጠት ያስችላል። ሁልጊዜም ቢሆንም አስተዳደራዊ ሲባል ከፍጥነት ከቅልጥፍና ጋር የሚያያዘው ነው። በመሆኑም ከፊል የዳኝነት ውሳኔ የሚሰጡ አካላትን ተቀራራቢ በሆነ አደረጃጀት፤ አሰራርና የሚያቀራርብ ስርዓት ለመዘርጋት ያስችላል። በቀጣዮቹ የትራንስፎርሜሽን ዓመታት የወንጀል ስነስርዓት ሕጉና የማስረጃ ሕጉ አዳዲስ ማሻሻያዎች ይዞ የሚመጣ ይሆናል። የፍትሐ ብሔር ፖሊሲያችንን ለማውጣት ጥናት እየተደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ፍኖተ ካርታው ለማከናወን ከለያቸው ጉዳዮች አንዱ የክልሎችንና የፌደራል መንግስቱን ግንኙነት በሚመለከት ነው፤ እስቲ ስለዚህ ጉዳይ ምንነት ያብራሩልን?
ኤርሚያስ ዶ/ር፡– ኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት የምትከተል ሃገር እንደመሆንዋ ውጤታማ የጎንዮሽና የተዋረድ ግንኙነት ያስፈልጋል። ለዚህም የክልልና የፌዴራል መንግሥት ግንኙነት የሚወስን አዋጅ ወጥቷል። በመንግስት ትኩረት ከተሰጠው የሶስት ዓመት የፍትህ ማሻሻያ መርሃ-ግብር ለሕብረተሰቡ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ካልናቸው ጉዳዮች አንዱ ውጤታማ የሆነ የጎንዮሽና የተዋረድ ግኑኝነትን እንዲጠናከር በመደረጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ሃገር አቀፍ የወንጀል ሪፖርት ማቅረብ ችለናል። ድሮ የአዲስ አበባን ብቻ ነበር የምናቀርበው። በመሆኑም ከተደራሽነት አንፃርም ሆነ ውጤታማ ግንኙነት በመፍጠር ረገድ አበረታች ሥራ ተሰርቷል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የማኅበረሰብ ባሕላዊ ማቋቋሚያ አዋጅ በመውጣቱ እንደ ኦሮሚያ ያሉ ክልሎች ቀድመው አዋጅ በመዘጋጀትና አደረጃጀቱንም በሺዎች በሚቆጠሩ ቀበሌዎች በማውረድ ከ300 ሺ እስከ 400 ሺ ጉዳዮችን በዓመት የሚያዩበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህ ሊሳካ የቻለው ውጤታማ የጎንዮሽና የተዋረድ ግኑኘትን የሚወስነው አዋጅ ተግባራዊ በመደረጉ ነው። በአጠቃላይ በድምር ውጤቱ የኅብረተሰቡን ምሬት ይቀንሳል የሚል እምነት አለ። በቀረው አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ባቀድነው መሰረት ለመጓዝ ከክልሎች ጋር እየተናበብን እንሰራለን።
አዲስ ዘመን፡- ከባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ጋር ተያይዞ በተለይ ከሰብአዊ መብት አያያዝና የሴቶችን እኩልነትን ማረጋገጥ ረገድ ክፍተቶች እንዳሉባቸው ይነሳል። እንዲህ አይነት የፍትህ ጥሰቶችን በምን መልኩ ነው የምትከታተሉት?
ኤርሚያስ ዶ/ር፡- በነገራችን ላይ ባሕላዊ የዳኝነት ስርዓቱ አሁን ላይ በመንግሥት ደረጃ እውቅና ተሰጥቶ ድጋፍ የሚደረግለት ቢሆንም ሕብረተሰቡ ለረጅም ጊዜ ሲጠቀምበት የኖረ ነው። በመሰረቱ አንድ ባሕል ችግሮችን የሚፈታበትን ዘዴ መንግሥት ሊቀይስለትና በይዘቱ ላይ ሊወስን አይችልም። ይህ ከሆነ ባህሉን እኛ ልንቀርፅለት ነው ማለት ነው። ከዚያ ይልቅ ከመርህ፤ ከአካታችነት፣ ከእኩልነት፣ ከሕግ የበላይነት አንፃር የሚኖሩ ግድፈቶችን፤ ውስንነቶችን እንዴት መፍታት ይቻላል? በሚለው ላይ ነው ትኩረት የምናደርገው።
ለምሳሌ የሴቶች እኩልነትን ለማረጋገጥ ሴቶች በባህላዊ ዳኝነቱም ሆነ በሌሎች ማሕበራዊ ኃላፊነቶች ላይ እንዲሳተፉ የማድረግ፤ የመደመጥ መብታቸው እንዳይጣስ ተደርጎ ነው ሞዴል ሕጉ የተቀረፀው። ይህ ሞዴል ሕግ ሲወጣ በሕገመንግስቱ የተደነገጉ የሕፃናት የሴቶችን መብቶችን የሚጣረስ መሆን እንደሌለበት ይታመናል። አፈፃፀም ላይ ግን ክፍተቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፤ ግን በሂደት አስተሳሰቡን የማስረፅ ሥራ ይሰራል።
በነገራችን ላይ ኦሮሚያ ክልል ቀድሞ ይህንን ሞዴል ባሕላዊ የዳኝነት ሥርዓት ስለጀመረ ለሌሎች ተሞክሮ ይሆን ዘንድ የአዋጪነት ጥናት በዓለምአቀፍ ድርጅት አስጠንተናል። በዚህም ጥናት እውነትን በማውጣት ረገድ እንዲሁም የፍርድ ቤትን ጫና መቀነስ ላይ በጎ ተፅዕኖ እየፈጠረ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። ያነሳሻቸው ችግሮችም እንዲሁ የታየ ሲሆን ኦሮሚያም ሆነ ሌሎች ክልሎች የሚማሩበት ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- የባሕላዊ ፍርድ ቤቶች የመደበኛ ፍርድ ቤቶችን የሥራ ጫና በተጨባጭ መቀነሱን በጥናት መረጋገጥ አለበት ብለው የሚያነሱ የሕግ አካላት አሉ፤ በዚህ ላይ የእርሶ ሃሳብ ምንድን ነው?
ኤርሚያስ ዶ/ር፡- በመርሕ ደረጃ ጫና ይቀንሳል የሚለውን መውሰድ አለብን። ግን በየትኞቹ ጉዳዮች የሚለውን ዝርዝር ነገር መለየት ያስፈልጋል። መደበኛ ፍርድ ቤት የሚመጡትን ጉዳዮች ለመቀነስ ሲባል ብቻ አይደለም ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች እንዲቋቋሙ የተፈለገው። ሕገመንግስታዊ መብትም ጭምር በመሆኑ ነው።
የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እኮ ሕገመንግስታዊ ነው። የባሕልና የቋንቋ ነፃነት ተብሎ የሚጠቀሰው እኮ ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ አይደለም። ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች የተቋቋሙት የመደበኛ ፍርድ ቤቶችን ጫና ለመቀነስ ብቻ ሳይሆን ሕገ-መንግሥታዊ መብት በመሆኑ ነው። ባሕልን የማሳደግ መብት ሲባልም ጭፈራና እስክስታ ብቻ አይደለም፤ ይልቁኑም ነበርና ትርጉም ሊሰጡ የሚችሉ እሴቶችን ለማስቀጠል ኢንቨስት ስናደርግም ጭምር ነው።
አዲስ ዘመን፡- በሃገሪቱ ይተገባራል የተባለው የሽግግር ፍትሕ ምን ላይ ይገኛል?
ኤርሚያስ ዶ/ር፡- በሃገሪቱ በተለያዩ ዘመናት የተከሰቱ ፣ የቀጠሉ፣ ተደራራቢ እና ሰፊ የተጎጂና የአጥፊ ወሰን ያላቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የእርስ በርስ ግጭቶች፣ ያልጠሩ ትርክቶች እና በደሎችን ለመፍታት በተለይም በእውነት፣ በእርቅ፣ በምህረት እና በፍትህ ላይ የተዋቀረ እና በግልፅ የሚመራ ሁለንተናዊ የሽግግር ፍትሕ ስልትን በተደራጀ፣ በተቀናጀ እና ውጤታማ በሆነ መልኩ በሃገር አቀፍ ደረጃ ለመተግበር ያስችል ዘንድ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሚያዚያ 9/2016 ዓ.ም እንዲፀድቅ ተደርጓል።
ፖሊሲውንም ለማስፈፀም የሚያስችል ዝርዝር ‹‹የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የአፈፃፀም ፍኖተ ካርታም ተዘጋጅቷል። በዚህ የአፈፃፀም ፍኖተ ካርታ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል የሽግግር ፍትሕን ለማስፈፀም የሚያግዙ የባለድርሻ አካላት ሚናን መለየት፣ የሽግግር ፍትሕ ተቋማትን በፖሊሲው መሰረት ለማቋቋም የሚያስችሉ ተግባራትን መፈፀም ለአብነት ለሽግግር ፍትህ አስፈላጊ የሆኑ እንዲወጡ ማድረግ፣ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ መድረክ መፍጠር የሚሉ ሃሳቦች ተካተዋል።
ከዚህ ባሻገር የሽግግር ፍትሕ ለማቋቋም የሚያስችሉ ሕጎችን የዘርፉ ባለሙያዎችን ባማስተባበር ማውጣት ተችሏል። ከእነዚህም መካከል የሽግግር ፍትሕ ልዩ ችሎት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ፣ የዓለምአቀፍ ጉልህ ወንጀሎች ረቂቅ አዋጅ፣ የሽግግር ፍትሕ ልዩ አቃቤ ሕግ ፅሕፈት ቤት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ፣ የእውነት አፈላላጊና የይቅርታ ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅና የተቋምና የሕግ ሪፎርም ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጆች ዝግጅት ተጠናቀዋል። በቀጣይም ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት የሚደረግባቸው ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- የፍትሕ ስርዓቱን ለማሻሻል የቱንም ያህል አዳዲስ ሕጎች ቢወጡም መሬት ላይ በተጨባጭ ለውጥ አልመጣም፤ አሁንም ስርዓቱ በብልሹ አሰራሮች የተተበተበ ነው ብለው የሚያነሱ አሉ፤ እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
ኤርሚያስ ዶ/ር፡- በነገራችን ላይ ዳኝነት በጣም ውስብሰብ የሆነ ስርዓት ነው። ከለውጡ በፊት ዳኞች የሚሾሙበት ሁኔታ በአብዛኛው በፖለቲካ ተፅዕኖ ነበር። በሪፎርሙ የዳኞች ሹመት፣ ምልመላ፤ ዝውውር ስርዓት ባለው መልኩ ለመምራት ይቻል ዘንድ በአዋጅ ደረጃ ፀድቆ እንዲተገበር ተደርጓል። አሁን ችግሩ ነፃነትና ተጠያቂነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው፤ ዳኝነት አካሉ ላይ አስተያየት መስጠት ተገቢ ባይሆንም ነፃነት ላይ ትኩረት ካደረግን የተባለው እሮሮ እውነት ነው። የፍኖተ ካርታው መነሻም ይኸው ነው።
አንዳንድ ቦታዎች ላይ ነፃነት በዝቶ አጉራዘለልነት የሚታይበት ሁኔታ ነበር፤ እጅግ አማራሪ የሆኑ ዳኝነትን በገንዘብ ለመሸጥ የሚደረጉ ሙከራዎች የሉም ማለት አልችልም። ይህ ማለት ግን መዋቅራዊ የሆነ ችግር ማለት አይደለም። ሆኖም ዳኞች ነፃነት ላይ አትኩረው ተጠያቂነትን በመተው እንዳሻቸው የሚሆኑበት ስርዓት አይቀጥልም።
በሕገ-መንግስቱም ተጠያቂነት ሊሰፍን እንደሚገባ የሚደነግግ በመሆኑ ዳኞችን የማጥራት ሥራ እንዲሰራ የተፈለገው። ይህም ሲባል ሙያዊ ብቃታቸውን፤ ስነ-ምግባራቸውና ገቢያቸውንም ጭምር የሚፈትሽ ነው። በእርግጥ በሙስና የተገኘ ገቢ በቀጥታ በስም ሊቀመጥ ስለማይችል ማግኘቱ ከባድ ነው። ሆኖም መፈተሸና ማጥራት ይገባል የሚለውን በመርህ ደረጃ ቅቡልነት አለው።
በመሆኑም ነፃነትን ብቻ እያውለበለብን ተጠያቂነትን ከኋላ ኪሳችን አድርገን የምንሰራው ሥራ ዞሮ ዞሮ ለሃገር አደጋ ነው። ምክንያቱም የፍትሕ ሪፎርሙ ከሃገረ-መንግስት ቀጣይነት፤ ከልማት፤ ከሕዝቦች አብሮ መኖር ፤ መዋቅራዊ በደል እንዳይኖር ከማድረግ አንፃር የሚሰራ ሥራ ነው። ፍትህ በሌለበት ልማት፣ ብልፅግና ቀጣይነትን እውን ማድረግ አይቻልም። በሰነዱም ተቀንሷል። በመሆኑም የሰራናቸውን ጥሩ ሥራዎች አጠናክረን መቀጠል አለብን።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ኤርሚያስ ዶ/ር፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 10 ቀን 2017 ዓ.ም