ኅብረት ሥራ ማሕበራት የአባሎቻቸውን በተለይ የማሕበረሰቡን በአጠቃላይ የኑሮ ጫና በማቃለል ይታወቃሉ:: ከኑሮ ውድነት፣ ከምርቶች ዋጋ መናርና መውደቅ ጋር ተያይዞ መንግሥት መፍትሄ ሲያስቀምጥ ዋጋ እንዲረጋጋ አስተዋጽኦ በማድረግ ለመንግሥት ቀኝ እጅ በመሆን ለሀገር እየሰሩም ይገኛሉ፡፡ በተለይ ኑሮ በከበደበት በዚህ ዘመን፤ የሁሉም ማሕበረሰብ ጭንቀት የሆነውን የኑሮ ውድነት የሚያስከትለውን ችግር ለማቃለል መንግሥት ጥረት ሲያደርግ የሸማቾችና የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማሕበራት ሚና ከፍተኛ ሆኖ ቆይቷል፡፡
የኅብረት ሥራ ማሕበራት ብዙ አይነት ናቸው፡፡ እነዚህም የአርሶ አደሮች፣ የሸማቾች፣ የገንዘብ ብድርና ቁጣባ የኅብረት ሥራ ማሕበራትን በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ የዛሬው ንግድና ግብይት አምዳችን በአርሶ አደሮች የኅብረት ሥራ ማሕበራት ላይ ያጠነጠነ ነው፡ ፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን የተሻለ የሥራ እንቅስቃሴና አፈፃፀም አላቸው እንዲሁም የኑሮ ውድነቱን በማቃለል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እየተወጡ ያሉ ማሕበራት ልምድና ተሞክሯቸውን ለሌሎች እንዲያካፍሉ አድርጓል፡፡ ለዚህም ባመቻቸው የመስክ ምልከታ፤ በኦሮሚያ ክልል የሚገኘውን ሉሜ አዳማ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየንን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ በጋዜጠኞች ቡድን ጎብኝቷል።
በወቅቱም የዩኒየኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳዬ ቸሩ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ ዩኒየኑ በዋናነት በግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር አርሶ አደሩ የላቡን እንዲያገኝ ከማድረግ በዘለለ ገበያን በማረጋጋት ሰፊውን ማሕበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል። የአርሶ አደሩ የምርትና ምርታማነት ዋነኛ ማነቆ የግብዓት አቅርቦት እጥረት መሆኑን ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ዩኒየኑ ይሰራል፡፡
ምርትና ምርታማነት ሲያድግ አርሶ አደሩ ለምርቱ ተገቢውን ዋጋ የሚያገኝበት የገበያ እድል ይፈጠራል:: የዩኒየኑ የገበያ ችግሩን በመቅረፍ የአባል አርሶ አደሮች ምርት ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ ለማስቻል፤ ምርቱን ከአርሶ አደሩ ሰብስቦ እሴት የተጨመረበት ምርት ለሸማች ኅብረት ሥራ ማሕበራት፤ ለመንግሥት ድርጅቶች፣ ለትምህርት ቤት ምገባ… ወዘተ ያቀርባል ሲሉ አብራርተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ዩኒየኑ በቀን 360 ኩንታል ወይም 36 ቶን የስንዴ ዱቄት የሚያቀነባብር ፋብሪካ አለው:: በዓመት እስከ 80 ሺህ ኩንታል ስንዴ ከአባላቱ ይሰበስባል፤ ይህን ምርትም እሴት ጨምሮ በቀን እስከ 180 እና 190 ኩንታል ደረጃውን የጠበቀ የስንዴ ዱቄት ያቀርባል። በዚህም እሴት የተጨመረበት ምርት ለገበያ በማቅረብ አርሶ አደሩ ለምርቱ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ እያስቻለ ነው፡፡
ዩኒየኑ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ለ10 ዓመታት የዘለቀ የገበያ ትሥሥር ፈጥሮ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የስንዴ ዱቄት እንደሚያቀርብ አቶ ካሳዬ ጠቁመው፤ ከአየር መንገዱ ጋር በዓመት እስከ 100 ሚሊዮን ብር የሚደርስ የገበያ ትሥሥር ተፈጥሯል። ይህን ያህል ከውጭ ይገባ የነበረን ምርት በሀገር ውስጥ በመተካት ሀገሪቱ ታወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ማዳን ተችሏል ብለዋል።
ከአየር መንገዱ ባለፈ ደግሞ በተለይ በአዲስ አበባ የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት በከተማዋ ከሚገኙ ሸማች ኅብረት ሥራ ማሕበራት ጋር የገበያ ትሥሥር በመፍጠር የስንዴ ዱቄት ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ዩኒየኑ ምርቱን ለማሕበራቱ እስከ ደጃቸው ድረስ ነው የሚያቀርበው። ይህም በከተማዋ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ከማረጋጋት አኳያ የራሱ ድርሻ እንዳለው ይገልጻሉ፡፡
የስንዴ ዱቄቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማሕበረሰቡ ከማቅረብ በዘለለ፤ ዩኒየኑ በሞጆ ከተማ በቀን 20 ሺህ ዳቦ የማምረት አቅም ያለው የዳቦ መጋገሪያ አለው። ዩኒየኑ ግራሙና ጥራቱ የተጠበቀ ዳቦ እያመረተ አንድ ዳቦ በጣም በዝቅተኛ ዋጋ በአራትና በአምስት ብር ለማሕበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ እርሻን እስከ ጉርሻ አድርሷል፡፡ በተለይ ደግሞ ዝቅተኛ ኑሮ ያለው ማሕበረሰብ ቢያንስ ዳቦ በልቶ እንዲያድርና የዋጋ ንረቱን እንዲቋቋም እያገዘ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ምክትል ሥራ አስኪያጁ እንዳስታወቁት፤ ዩኒየኑ ተረፈ ምርትን ወደ መኖ በመቀየር የመኖ ምርት ዋጋን ከማረጋጋት ባለፈ የከብት ማደለብ ሥራ በስፋት ያከናውናል:: የቦረና ዝርያ ያላቸውን ከብቶች ከቦረና ገዳ ዩኒየን በማምጣት ለሦስት ወር ያህል አደልቦ ለአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ሐረርጌ … ወዘተ ገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባል። በዚህ መሠረት የአዲስ አበባ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማሕበራት ትስስር ፈጥረው ተጠቃሚ ናቸው። በተለይ ዓመት በዓል ሲደርስ የአዲስ አበባ ሸማቾች ቅድሚያ እንዲያገኙ በማድረግ በከተማዋ በበዓላት ወቅት ካለው ፍላጎት አኳያ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት የበኩሉን ሚና ይጫወታል። ስለዚህ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ፣ ጤንነቱ የተረጋገጠ ስጋ ማሕበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ በተቻለ መጠን እየሠራ ነው። .
ዩኒየኑ ከስምንት ዩኒቨርሲቲዎችና ከበርካታ የፌዴራልና የክልል የመንግሥት ተቋማት ጋር የሰብል ምርቶች የገበያ ትስስር አለው፡፡ በዚህም ተቋማቱ በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራቱን የጠበቀ ምርት እንዲያገኙና በተቋማቱ የሚገለገሉ የማሕበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ ይገኛል።
የላም ወተት፣ የዶሮ እንቁላልና ስጋ እንዲሁም የእንስሳት መኖ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማሕበረሰቡ በሰፊው ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ ካሳዬ ጠቁመው፤ በስንዴ ላይ የተጀመረውን እሴት የመጨመር ሥራ አጠናክሮ በማስቀጠል ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ። በጤፍ፣ በሽንብራና በቦለቄ ምርት ላይ እሴት በመጨመር ለገበያ ለማቅረብ እየሰራ እንደሆነ ጠቅሰው፤ የነጭ ቦለቄ ምርት በስፋት ኤክስፖርት በማድረግ ሀገሪቱ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ አቅዶ እየሠራ እንደሆነ አብራርተዋል።
አቶ ካሳዬ፤ አርሶ አደሩ ከእጁ መንቀሳቀሻ ገንዘብ አጥቶ በሚቸገርበት ወቅት ሕገ-ወጥ ደላሎች ለችግሩ የደረሱ መሲህ መስለው ገንዘብ በመስጠት ወዙን አንጠፍጥፎ ባመረተው ምርት ዋጋ እንዳይወስን እንደሚያደርጉ ገልጸው፤ በዚህ መልኩ ሕገወጥ ደላሎች ወደ አርሶ አደሩ ጓዳ ገብተው ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት ይፈጥራሉ። በመሆኑም ዩኒየኑ የሕገ-ወጥ ደላላ ጣልቃ ገብነትን ለመቁረጥና ሁሉም አባላት ምርታቸውን ሳይሸራርፉ ወደ ኅብረት ሥራ ማሕበራት እንዲያመጡ ለማስቻል አርሶ አደሩ ገንዘብ በሚፈልግበት ወይም በተቸገረበት ወቅት ገንዘብ የሚያገኝበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ለምርቱ ራሱ አርሶ አደሩ ዋጋ የሚተምንበት አግባብ ለማስፈን ከኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክና አዋሽ ባንክ ጋር እየተሰራ እንደሆነም አመላክተዋል።
አባላት ምርት በሚደርስበት ወቅት እህል ሰብስበው ወደ ማሕበራቸው እንዲያመጡ የብድርና የመጋዘን አገልግሎት እንደሚሰጥም ጠቅሰዋል። በአንፃሩ ደግሞ በድርቅ ወይም በልዩ ልዩ የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት የአባላት ሰብል ሲጠፋ ወይም ሲጎዳ፤ የመድህን ሽፋን ያቀርባል ሲሉም ገልጸው፣ ዩኒየኑ በተለይ በሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት ሕብረተሰቡ እንዳይበዘበዝና ለችግር እንዳይጋለጥ በቁርጠኝነት እየሠራ እንደሚገኝ ምክትል ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
ሌላው አባል አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የኑሮ ውድነቱን በማረጋጋት ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ የኦሮሚያ ግብርና ኅብረት ሥራ ማሕበራት ፌዴሬሽን ነው። የፌዴሬሽኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብነት ታረቀኝ እንደገለጹት፤ ፌዴሬሽኑ የአርሶ አደሩን ሕይወት ለመቀየርና የኑሮ ውድነቱን በማቃለል ማሕበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በዋናነት አምስት ትልልቅ ሥራዎችን ያከናውናል።
የመጀመሪያ ሥራው ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ማሾ እና የመሳሰሉ የቅባት እህሎችን ከአባል ዩኒየኖች ሰብስቦ አጥቦና ቀሽሮ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ነው የሚሉት አቶ አብነት፤ በሚያገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ደግሞ አባላት ዩኒየኖችና መሰረታዊ ኅብረት ሥራ ማሕበራት የሚጠይቁትን እንደ ደብተር፣ ቆርቆሮ፣ .. ወዘተ የመሳሰሉ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያቀርብ አስረድተዋል።
ሌላኛው እንደ ሀገርም ብሎም እንደ ክልልም የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ ከፍተኛ የአግሮ- ኬሚካል ወይም ፀረ-ተባይ ኬሚካል ግብዓት ከውጭ በማስገባት በተመጣጣኝ ዋጋ ለአባላቱ እንደሚያቀርብ የሚናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ በዚህም ከክልሉ አባላት ባልተናነሰ ከአማራ፣ የአፋር፣ የትግራይ … ወዘተ ክልሎች አርሶ አደሮች ፌዴሬሽኑ ከሚያቀርበው ግብዓት ተጠቃሚ ናቸው ይላሉ። በተጨማሪም በሀገር ውስጥ የማይመረቱና በአርሶ አደሩ ዘንድ ተፈላጊ የሆኑ የእንስሳት መድሃኒቶችን ከውጭ አስገብቶ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያቀርብም ጠቁመዋል።
የግብርና ምርቶችን በማቀነባበር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ሀገርን ከውጭ ምንዛሪ ወጪ የመታደግ ሥራ ሌላኛው የፌዴሬሽኑ ተግባር እንደሆነ አመላክተው፤ እሴት በመጨመር አርሶ አደሩ የምርቱ ዋጋ ራሱ መተመን የሚችልበትን ነባራዊ ሁኔታ መፍጠር ተችሏል ብለዋል።
አቶ አብነት፤ ከዚህ በፊት የግል የብቅል ፋብሪካዎች የገብስ ምርት ዋጋን የማውረድ አዝማሚያዎች ይታይባቸው እንደነበር ገልጸው፤ ይህም አርሶ አደሩ የልፋቱን እንዳያገኝ ሲያደርገው ቆይቷል ይላሉ። የዛሬ አምስት ዓመት ፌዴሬሽኑ በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን የአሰላ ብቅል ፋብሪካን ከገዛ ወዲህ ከአርሶ አደሩ የቢራ ገብስ ሰብስቦ እሴት ጨምሮ/በማቀነባበር/ ለብቅል ፋብሪካዎች እያቀረበ ይገኛል ሲሉ አብራርተዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ፋብሪካው ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ 500 ሺህ ኩንታል ገብስ ከአርሶ አደሩ በመሰብሰብ፤ 370 ሺህ ኩንታሉን እሴት ጨምሮ ብቅሉን ለቢራ ፋብሪካዎች አቅርቧል። በዚህም ከ500 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለፋብሪካው በማቅረብ በገበያ ሰንሰለቱ ተጠቃሚ ሆነዋል። በምርታቸውም የተሻለ ዋጋ እያገኙ ነው። እንዲሁም አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለፋብሪካው ለማቅረብ ስምምነት በመፈራረማቸው ቀድመው የምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ የፀረ-ተባይ ኬሚካል እና የመሳሳሉ ግብዓት ተጠቃሚ መሆንም ችለዋል።
በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ የበቆሎ ዱቄት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ አለው፡፡ በመሆኑም የበቆሎ ምርትን ከአርሶ አደሩ ሰብስቦ እሴት በመጨመር የበቆሎ ዱቄት እንዲሁም ለቢራ ፋብሪካዎች ግብዓት የሚሆን “ኤስጂ” የሚባል ቅንጬ የመሰለ ምርት በዋናነት ለሀበሻና ሄኒከን ቢራ ፋብሪካዎች በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ወጪን እያስቀረ ነው።
የዱቄት ፋብሪካው በዓመት እስከ 250 ሺህ ኩንታል የበቆሎ ዱቄት በማምረት፤ እንደ ብርሃን ጮራ፣ ብሩህ ፋና እና ለመሳሰሉት ለአዲስ አበባ ሸማች ኅብረት ሥራ ማሕበራት ዩኒየኖች እንዲሁም ለትምህርት ቤቶች ምገባ ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባል። በአዲስ አበባ ሶስት እንዲሁም ገላን ከተማ ለሕብረተሰቡ የበቆሎ ዱቄት የሚያቀርብባቸው ሁለት ሱቆችም አሉት። ሕብረተሰቡ ወደነዚህ ሱቆች ጎራ ብሎ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቱን በመሸመት እየተጠቀመ ነው። ስለዚህ ፌዴሬሽኑ እሴት የተጨመረበት ምርት በማቅረብ አርሶ አደሩ ለምርቱ ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝና ተጠቃሚ እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ ገበያ በማረጋጋት ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከዚህ በበለጠ ፌዴሬሽኑ በቀጣይ ደግሞ እንደ ዘይት የመሳሰሉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እንዲሁም ሀገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ እያደረገች ባለችው ሽግግር የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ተግቶ እየሠራ መሆኑን የፌዴሬሽኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል መንግሥት የሚያስገባውን የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ከማሰራጨት ባለፈ ፌዴሬሽኑ በራሱ ከውጭ የአፈር ማዳበሪያ በማስገባት ለአርሶ አደሩ በሚፈልገው ወቅትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ፕሮጀክት ቀርፆ እየሠራ እንደሚገኝ አቶ አብነት ጠቁመዋል፡፡ ፕሮጀክቱም ወደ መሬት ወርዶ ገላን ከተማ ላይ ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ የግብርና ግብዓት የሚይዝ መጋዘን ተሠርቶ በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን አስታውቀው፣ በሚቀጥለው ዓመት የማዳበሪያ ምርቱን ለማስገባት ታቅዷል ብለዋል። ይህም የመንግሥትን ጫና ከማቃለል ባለፈ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት የሚያሳድግ እንደሆነ አስረድተዋል።
የሀገርና የሕዝብን ጥቅም ለማስከበር በትኩረት እየሰሩ ለሚገኙ ለእነዚህ ኅብረት ሥራ ማሕበራት በመንግሥት በኩል የሚደረገው ድጋፍና የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ስለዚህ መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሊሰጥና ድጋፍ ሊያደርግ፤ ማሕበራቱ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ይበልጥ መወጣት የሚያስችላቸውና ያሉባቸውን ማነቆዎች የሚፈታ ሕግና ፖሊሲ አውጥቶ ሊተገብር ይገባል እንላለን፡፡
ሶሎሞን በየነ
ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 9 ቀን 2017 ዓ.ም