የነዳጅ መኪናውን ወደ ኤሌክትሪክ መኪና

በአርባዎቹ እድሜ መጀመሪያ ላይ የሚገኝ ጎልማሳ ነው፡፡ ውልደቱም ሆነ እድገቱ ወሊዲያ ከተማ ልዩ ስሙ መቻሬ በሚባል አካባቢ ነው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ለቴክኒክና ሙያ ነክ ነገሮች የተለየ ፍቅር ያለው በመሆኑ የሚያገኘውን ሁሉ ቁሳቁስ ፈቶ መልሶ መገጣጠም፤ የተሰበሩትን መጠገን ያስደስተውም ነበር፡፡

አቶ ዘመኑ ሲሳይ የሚባለው ይህ ጎልማሳ፣ በልጅነቱ ወላጆቹ የቀለም ትምህርት እንዲማር ትምህርት ቤት ቢልኩትም፣ እሱ ግን ምርጫው በአካባቢው ከሚገኙ የእንጨትና ብረታ ብረት ሥራ ከሚሰሩ ፋብሪካዎች ደጅ መዋል ነበር፡፡ ደብተሩን ይዞ ከማጥናት ይልቅም ከፋብሪካዎቹ እንጨት ለምኖ ክራርና መሰል ቁሳቁስን መስራት ያዘወትር እንደነበር ይናገራል፡፡

ይህ ፅኑ ፍላጎቱ አድጎ ገና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለ በሳምንት ለተወሰኑ ሰዓታት በእንጨት ቤቶቹ ተቀጥሮ በመስራት አስር ብር ያገኝም ጀመር። በወላጆቹ ጫና እስከ ሰባተኛ ክፍል ቢደርስም የትምህርት ውጤቱ ዝቅተኛ በመሆኑ ‘አካባቢ ሲቀይር ይለወጣል’ በሚል ተስፋ የእናቱ ቤተሰቦች ካሉበት ከሚሴ ከተማ ተላከ፡፡

እዚያም ቢሆን በትምህርቱ መበርታት አልቻለም፤ እንደ ምንም ስምንተኛ ክፍልን ለማጠናቀቅ ቢሞክርም ለትምህርት ፍላጎት ስላልነበረው ጠንክሮ ስላልተማረም የስምንተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ማለፍ አልቻለም፡፡ የያኔው ታዳጊ የአሁኑ ጎልማሳ ዘመኑ ግን በፈተና መውደቁ ግድ አልሰጠውም፡፡

ስለትምህርቱ ከማሰብ ይልቅ ከአንድ እንጨት ፋብሪካ ተቀጠረና በሳምንት 40 ብር ማግኘት ጀመረ፤ ሙያውን በደንብ መልመድ ሲችል ወደ ወልዲያ ተመልሶ የራሱን የእንጨት ቤት ከፈተ፡፡ በክራር እጁን ያፍታታው አቶ ዘመኑ የተለያዩ የቤት ውስጥ ቁሳቁስን በመስራት በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት አገኘ፡፡ ለዚህም ሥራው የሚረዱትን እንደ መላጊያና መሰነጣጠቂያ ያሉ ማሽኖችን ፍለጋ ማንንም መለመን አላስፈለገውም፤ ይልቁንም እነዚህኑ ማሽኖች በራሱ እጅ አስመስሎ ሰራ። ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሚያያቸውን መሳሪያዎች አስመስሎ የመስራት የተለየ ስጦታ ያለው አቶ ዘመኑ፤ በተለይም ከውጭ በውድ የሚመጡና ለሰዎች ችግር ፈቺ ናቸው ብሎ የሚያምንባቸውን ቁሳቁስ ሁሉ ያለምንም ስልጠናና ትምህርት በአንድ ጊዜ እይታ ብቻ በመስራትም ብዙዎችን ማስደነቅ የጀመረው ገና በለጋ እድሜው ነው፡፡

‹‹መስራት የሚፈልገውን አስቀድሜ በጥንቃቄ ስለማየውና ስለማጠናው ስሰራውም ብዙ ሳልቸገር አሳካዋለሁ›› ሲል በልበ ሙሉነት ይናገራል፡፡ የወዳደቁ ቁሳቁስን ብቻ በመጠቀም የተለያዩ መሳሪያዎችን የሰራው ይህ የፈጠራ ባለሙያ፤ ከሰራቸውም መካከል ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀስበትን ሳይክል፣ የተለያዩ የእንጨት ማሽኖች፣ የብረት መበየጃ፣ የሽንኩርት መፍጫ፣ የሊጥ ማቡኪያና የመሳሳሉት የቤት ውስጥ ቁሳቁስ ይጠቀሳሉ፡፡

ይሁንና በ1997 ዓ.ም ተካሂዶ ከነበረው ሃገር አቀፍ ምርጫ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት የእሱም ድርጅት ሆነ የብዙዎቹ ፋብሪካዎች የሥራ እንቅስቃሴ ተቀዘቀዘ፡፡ ሁኔታው ስላላማረውም ሁሉን ነገር ትቶ ቀየውን ለቆ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ያስባል፤ አስቦ ብቻ አልቀረም፡፡

አንድ ማለዳ ተነስቶ ባገኘው የሕዝብ ትንስፖርት ከአዲስ አበባ ከተማ ይከሰታል፡፡ የትውልድ ቀዬው ሳለ ዝናዋን የሰማላት አዲስ አበባ ግን እንዳሰበው እጇን ዘርግታ አልተቀበለችውም፤ እንደተመኘውም ማደሪያው ፎቅ ቤት ሳይሆን የኮልፌ ከረንቡላ ቤት በረንዳ ሆነ። ችግር በበዛ ቁጥር ብርታቱን በመጨመር የበለጠ በመስራት ያምን ስለነበር ለአዲስ አበባ የቀን ሐሩር ሌት ቁር አልተበገረም፡፡ ጥቂት ቀናት በረንዳ ቆይቶ የብዙሃኑን የኑሮ ዘይቤ ለመቃኘት ሞከረ፤ በኋላም ከሃገሩ ቋጥሯት ከመጣው 820 ብር ውስጥ በ120 ብር ቤት ተከራየ፤ ከታላቅ ወንድሙ ካገኘው የ2ሺ500 ብር ድጋፍ የራሱን ሥራ ለመስራት ወጠነ፡፡

‹‹በ300 ብር የመስሪያ ቦታ ተከራየሁና የዳቦ፣ የሽንኩርት ማሽኖችን እንዲሁም የእንጨትና የብረት በርና መስኮቶችን ሁሉ መስራት ጀመርኩ›› በማለት ያስታውሳል፡፡ ሁሉን መሞከር የሚወደው ዘመኑ ቃሊቲ አካባቢ በመምጣት ደግሞ ጎሚስታ ቤት ከፈተ፡፡ ይሁንና ከሚያገኘው በላይ ግብር እንዲከፍል በመጠየቁና ፍትሕ በማጣቱ ጎሚስታ ቤቱን ለመዝጋት ተገደደ፡

በደረሱበት ተደራራቢ ችግሮችና የስነ ልቦና ጫና ምክንያት ከአንድ ዓመት በላይ ገዳም መቆየቱን ይናገራል። ከብዙ ፀሎት በኋላ አዲስ አበባ ተመልሶ ከያኔዋ ሴት ጓደኛው (የአሁኗ ባለቤቱ) ጋር በመሆን ምግብ ቤት ከፈተ፤ ሥራ መናቅ የማያውቀው ዘመኑ በምግብ ሥራም ሆነ በእንጀራ ጋገራ አይታማም፡፡

የትዳር አጋሩ ከሆነችው ጓደኛው ጋር በመሆን የከፈቷትን ምግብ ቤታቸውን በሁለት እግሯ ለማቆም ደፋ ቀና ማለቱን ተያያዘው፡፡ የቴክኒክ እውቀቱን በመጠቀም የሻይ ማሽን ሰራ፤ ይህንን ጊዜ የምግብ ቤቱም ገበያ እየደራ ደንበኞቹም እየተበራከቱለት መጡ፡፡ ግን ደግሞ ችግሩ በዚህ አላበቃም፤ ቤቱን ያከራዩት ግለሰብ ምግብ ቤቱን መልመዱን ሲመለከቱ ራሳቸው ሊሰሩበት አስበው አስለቋቋቸው፡፡

በዚህ ምከንያት ወደ ጎሚስታው ሥራ ተመልሶ ገባ። ብዙም ሳይቆይ መንግስት የሰጠውን እድል ተጠቅሞ ከሌሎች ሰዎች ተደራጅቶ የብረታ ብረት ሥራ ጀመሩ። ‹‹ግን አብረውኝ ተደራጅተው የነበሩ ሰዎች ቶሎ ገንዘብ ማግኘት የሚፈልጉ ስለነበሩ፤ ሥራው እንዳሰቡት ሳይሆን ሲቀር ተራ በተራ እየለቀቁ መጨረሻ ላይ ብቻዬን መስራት ቀጠልኩ›› ይላል፡፡ በተሰጠው የመስሪያ ቦታ የብሎኬት ማምረቻ ማሽን፣ ሽንኩርት መፍጫና የዳቦ ማቡኪያ ማሽኖችን ማምረት ቀጠለ፡፡ በዚህም አልተወሰነ፤ ብዙ አምራቾች የሚቸገሩበትን ነገር በማጤን ያገለገሉ ጀነሬተሮችን በማደስ በማከራየትና በመሸጥ ገቢውን ማሳደግ ቻለ።

ምንም እንኳ በቀለም ትምህርቱ ገፍቶ ባይሄድም ለአዳዲስ ነገሮችና ለፈጠራ ሥራዎች ልቡ ክፍት የሆነው ይህ የፈጠራ ባለሙያ፤ ወቅቱን ባገናዘቡና የሕዝብ ችግር ፈቺ በሆኑ ነገሮች ላይ ጥናት ማድረግ ይጀምራል፡፡ ሩቅ ሳይሄድም በየሳምንቱ ከአራት ሺ ብር ያላነሰ የነዳጅ ወጪ የምታስወጣውን ቮልስ ዋገን መኪናውን በምን መልኩ ወጪዋን ሊቀንስ እንደሚችል ማሰላሰል ቀጠለ። በሌላ በኩል መኪናዋ እድሜ ጠገብ በመሆኗ ወደፊት ከአገልግሎት ውጪ የምትሆንበት አጋጣሚ ሊፈጠር ስለሚችል ሁለቱንም ችግሮች መፍታት ያስችለው ዘንድ ወደ ኤሌክትሪክ መኪናነት ለመቀየር አለመ፤ አልሞ ብቻ አልቀረም፤ ሕልሙን እውን ማድረግ ቻለ፡፡

‹‹መጀመሪያ የተለመደውን የመኪና ባትሪ አድርጌ፤ ሞተርና ሌሎችንም አስፈላጊ ቁሳቁስ ከሰዎች ላይ ገዛሁና ገጣጥሜላት ስሞክራት የተወሰነ ርቀት ተጉዛ ቆመች፤ ይህም የሆነው የተጠቀምኩት ሊድ አሲድ ባትሪ ስለነበርና እንዲህ አይነቱ ባትሪ ደግሞ ጥቅም ላይ የሚውለው ለመንደርደሪያ ብቻ ስለነበር ነው›› በማለት የመጀመሪያ ሙከራውን ያስረዳል፡፡

ይህ ሁኔታም ተስፋ አላስቆረጠውም፤ በሁለተኛው ሙከራውም ሌላ አይነት ባትሪ ቀይሮ ያለነዳጅ ሞከራት፤ አሁንም ካለፈው በተሻለ ጥቂት ተጉዛ ቆመች፡፡ ይህን የአቶ ዘመኑን የቀን ተቀን ሙከራ ያዩ አንዳንድ ሰዎች የማሾፍና ተስፋ የሚያስቆርጡ አስተያየቶች ይሰነዝሩበት እንደነበር ያስታውሳል፡፡

በዚህም አልተበገረም፤ ካሰበበት ለመድረስ ሌት ተቀን መትጋቱን ቀጠለ፤ አንድ የኤሌክትሪክ ባለሙያ አማከረና ረጅም ጊዜ ሊቆይ የሚችል ባትሪ ገዝቶ ገጠመለት፤ እንደተመኘውም ሳሪስ ከሚገኘው የመስሪያ ቦታው አቃቂ ወደሚገኘው ቤቱ ደርሶ መመለስ ቻለ፡፡ ይህም ይበልጥ ሞራል ሰጠው፤ በየቀኑ ቻርጅ እያደረገ ከቤት መስሪያ ቤት፣ ከመስሪያ ቤት ወደ ቤት መመላለሱን ቀጠለ፡፡

ከዚህ የተሻለ ረጅም ጊዜ የሚቆይ ‘ሌቲየም’ የተባለ ባትሪ እንዳለ ሰዎች ቢጠቁሙትም ዋጋው የሚቀመስ አልሆነለትም፡፡ በመሆኑም በእጁ ያለው ባትሪ ራሱን በራሱ ቻርጅ የሚያደርግበትን ስርዓት ፈጠረ፡፡ በአዲስ መልክ ሞተሯ በኤሌክትሪክ እንዲሰራ ተደርጎ የተቀየረላት የአቶ አመኑ ቮልስ መኪና አሁን ባለችበት ሁኔታ ሁለት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ቻርጅ በማድረግ እስከ 120 ኪሎ ሜትር መጓዝ ትችላለች፡፡ ዘመን አሁንም መጠበቡን አላቆመም፡፡ የበለጠ ለማሻሻልና ለማዘመን ቀን ሌት ተሌት እየተጠበባት ነው፡፡ በዚህም ሞተር ወይም ዲናሞን ጨምሮ 80 በመቶ የሚሆነውን የመኪናውን ክፍል በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

የነዳጅ ተሽከርካሪን ወደ ኤሌክትሪክ መቀየር የቻለው ይኸው የፈጠራ ሰው ለሃገሩ ባመጣው አዲስ ግኝት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ላይ በሚዘጋጀው ነጋድራስ በተሰኘው የሥራ ፈጠራ ውድድር ላይ አሸንፎ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ተሸላሚ ሆኗል፡፡ በተጨማሪም 10 ሚሊዮን ብር ያለምንም ኮላተራል መበደር የሚችልበት እድል ተመቻችቶለታል፡፡

ይህ የፈጠራ ሰው ከዘጠኝ ወር አድካሚ ምልልስ በኋላ የኢትዮጵያ አዕምራዊ ንብረትም የባለቤትነት እውቅናም (ፓተንት ራይት) አግኝቷል፡፡ ይህንን ድንቅ የፈጠራ ሥራ የተመለከቱ 12 ሺ የሚልቁ ሰዎች መኪናቸውን ወደ ኤሌትሪክ እንዲቀይርላቸው ጥያቄ እንዳቀረቡለትም ይናገራል፡፡

ይህን ጥያቄ ለመመለስም ሆነ አገልግሎት ላይ ለማዋል ግን በቅድሚያ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ፈቃድ ያስፈልገዋል፡፡ ለእዚህም ለሚኒስቴሩ ማመልከቻ ማቅረቡን ጠቅሶ፣ ይሁንና ላለፉት አምስት ወራት ምንም አይነት ምላሽ አለማግኘቱን ነግሮናል፡፡

‹‹ፈቃዱ የሚያስፈልገው ይህች እኔ ወደ ኤሌክትሪክ መኪና የቀየርኳት ቮልስ ዋገን መኪና የምትታወቀው በነዳጅ በመሆኑና አሁን ያለችበትን ሁኔታ የሚያሳይ ፈቃድ ከሚኒስቴሩ ሊሰጣት ስለሚገባ ነው፤ ለዚህም ሰኔ 26 ቀን 2016 ዓ.ም ማመልከቻ አስገብቻለሁ፤ እስካሁን ግን ምንም አይነት ምላሽ አላገኘሁም›› ይላል፡፡

አሁንድ ሰዎች እዚህ ሁሉ ደረጃ ላይ ደርሶም ሥራውን ለማመን እንዳልፈለጉ ጠቅሶ፣ ጥቂቶቹም እንደሚሳለቁ ይናገራል፡፡ ‹‹ቮልስ መኪናዬ ላይ ‘የኤሌክትሪክ መኪና’ መሆኗን የሚገልጽ ፅሁፍ አድርጌያለሁ›› ሲል ገልጾ፣ ይህን የተመለከቱ አንዳንዶች ‘ምኞት ነው’ እያሉ እንደሚሳለቁበትም ይገልጻል፡፡ ‹‹ሌሎችም አስቁመውኝ ፈትሸን ካለየን ብለው የሚሟገቱኝ አሉ›› ሲል ጠቅሶ፣ ‹‹ይህ ሁኔታ እንዲህ አይነቱን ቴክኖሎጂ የውጭ ዜጋ ካልሰራው አልያም ከውጭ ካልመጣ ለመቀበል የሚቸገሩ እንዳሉ ያመለክታል›› ብሏል፡፡

ይህም የራስን ሃብት ካለማወቅና ማክበር ካለመፈለግ እንደሚነጭ አስታውቆ፣ እንዲህ አይነቱ ንግግር የፈጠራ ባለሙያዎችን ተስፋ ሊያስቆርጥና ወደ ኋላ ሊጎትት እንደሚችልም አመልክቷል፡፡ ‹‹ እኔ ማንም ምንም ቢለኝ ግድ የለኝም፤ እየሰራሁ ነው፤ አሁን ሙከራዬን ጨርሼ 12 ሺ 700 ሰዎች መኪናቸውን ወደ ኤሌትሪክ እንዲቀይርላቸው ጠይቀውኛል፤ ለዚህም የሚሆነኝን ቦታ አዘጋጅቻለሁ፤ የምጠብቀው የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴርን ይሁንታ ብቻ ነው›› ሲልም አስታውቋል፡፡

እሱ እንዳለው፤ ከዚህ ቀደም ለመኪናዋ የነዳጅ በሳምንት አራት ሺ ብር፤ በዓመት ደግሞ ከ180 ሺ ብር በላይ ያወጣ ነበር፤ ወደ ኤሌትሪክ ከቀየራት ወዲህ ግን 120 ኪሎ ሜትር (ለሁለት ቀናት) ተጉዞ 16 ብር ብቻ ነው ወጪ የሚያደርገው፡፡ በሳምንት ሶስት ጊዜ ቻርጅ ካደረጋት ደግሞ በ40 ብር እንዳሻው መጠቀም ይችላል።

በሌላ በኩል ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ተገዝተው የሚመጡት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባትሪዎች አንድ ላይ ተያይዘው የተሰሩ በመሆናቸው ችግር ሲደርስባቸውም ሆነ አቅማቸው ሲዳከም ጉዳት የሚደርስባቸው አንድ ላይ መሆኑን ያስረዳል። የእሱ የፈጠራ ውጤት የሆነችው የኤሌክትሪክ መኪና ግን አምስት ባትሪዎች ያሏትና በተናጠል የተገጠሙ ናቸው፡፡ ይህ መሆኑም የአንዱ ኃይል ሲያልቅ ከሌላኛው እየወሰደ (እርስ በርስ ቻርጅ እየተደራረጉ) ረጅም መንገድ መጓዝ የሚያስችል ነው፡፡ ይህም ከአላስፈላጊ ወጪ የሚታደግ በመሆኑና ባልተወሳሰብ ግብዓት የተሰራ መሆኑ የተለየ ያደርገዋል ባይ ነው፡፡

ይህችን መኪና መጀመሪያ ሲሰራ ለነዳጅ የሚያወ ጣውን ገንዘብ ለማዳን ነበር፤ አሁን ደግሞ እንደ መንግስትም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መጠቀም ፋይዳው ብዙ ነው፡፡ ሃገር ለነዳጅና ለመለዋወጫ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ የሚታደግ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቼ እየሰራሁ ነው ሲልም ያብራራል፡፡

አቶ ዘመኑ ይህን የፈጠራ ሥራውን በአሁኑ ወቅት በሚኒባስና የብዙሃን ትራንስፖርት በሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ላይ ሙከራ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህም የሕዝቡን የትራንስፖርት ችግር ለመፍታት እንደሚያስችል ያስረዳል፡፡ ‹‹በቀጣይም ለመኪኖቹ የራሳቸውን ቻርጀር አብሮ የመግጠም እቅድ አለኝ›› ይላል፡፡

በተጨማሪም አዳዲስ መኪናዎችንም ለመስራት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን፤ ለናሙና ያህልም አንድ መኪና በመስራት ላይ እንደሆነ ይጠቁማል። ‹‹ሁሉንም ነገር ከውጭ ከምናመጣ የተወሰኑትን አምጥተን ሌላውን በራሳችን አቅም እዚሁ ሃገራችን ውስጥ መስራት መቻል አለብን›› ሲል ይጠቁማል። ከዚህ ባሻገርም ያገለገሉና ከጥቅም ውጪ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን በመጠገንና ወደ ኤሌክትሪክ በመቀየር ሃገሪቱ በዘርፉ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ መታደግ፤ የአየር ብክለትን መቀነስ ብሎም ለበርካቶች የስራ እድል መፍጠርን ያነገበ ዓላማ ይዞ እየሰራ ይገኛል፡፡

‹‹እኔ ብቻዬን መስራት አልፈልግም፤ ይህ ሥራ ሰፊና ብዙዎችን የሚያሳትፍ ትልቅ ኢንዱስትሪ ነው፤ የትንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴርን ይሁንታ አግኘቼ ሥራውን ከጀመርኩኝ፤ የመኪናው የተለያዩ ክፍሎች በሌሎች አካላት እንዲመረቱ በኮንትራት የሚሰሩበትን ሁኔታ አመቻቻለሁ›› ሲልም ጠቁሟል፡፡ እስካሁን ለ11 ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠሩን ገልጾ፣ ወደፊት ግን ከ350 የሚልቁ ዜጎችን የሥራ እድሉ ተጠቃሚ ለማድረግም እቅድ መያዙንም አስታውቋል፡፡

‹‹በሃገራችን የፈጠራ ሥራን የማበረታታት ባህል እምብዛም አልነበረም›› የሚለው አቶ ዘመኑ አሁን ላይ በተለይ የፋይናንስ ተቋማት አዲስ የፈጠራና የሥራ ሃሳብ ላላቸው ዜጎች ያለምንም ኮላተራል ብድር ማግኘት የሚችሉበት እድል ማመቻቸታቸው እንደሱ ላሉ የፈጠራ ባለሙያዎች ተስፋ የሚሰጥና የበለጠ ለመስራት የሚያሳሳ እንደሆነ ይናገራል፡፡

በሽልማቱ ያገኘውን ገንዘብና ከባንክም ብድር በመጠየቅ ድርጅቱን የማስፋት እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ጠቅሶ፣ ለዚህም ይረዳው ዘንድ በአሁኑ ወቅት ስድስት ሺ ካሬ የሚሆን የመስሪያ ቦታ ተከራይቶ የሥራ ፈቃዱን እየተጠባበቀ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ታታሪው ይህ የፈጠራ ባለሙያ የፈጠራ ውጤቱ ለሃገር የሚያበረክተውን በጎ አስተዋፅኦ በመረዳት ትራንስፖርና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴርም ሆነ ሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ትብብራቸውን እንዲያቀላጥፉለት መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You