የአሽከርካሪዎችን ቅሬታና የትራፊክ ሕጉን ለማስታረቅ

ዜና ሐተታ

ስሙን ዘነበ አዲስ ሲል ያስተዋወቀኝ አንድ የራይድ አሽከርካሪ ለዓመታት በማሽከርከር ሙያ ላይ ቆይቷል። እንደ እሱ ዕምነት ሁሌም ቢሆን የትራፊክ ሕጎችን አክብሮ በመጓዝ ጠንቃቃ ከሚባሉት ሾፌሮች አንዱ ነው። በዚህ ምክንያትም እስከዛሬ ሕግ ጥሶ ለጥቃት የተዳረገበት አጋጣሚ አልነበረም።

ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ ግን በርካታ የትራፊክ ፖሊሶች ያለአንዳች በቂ ምክንያት አሽከርካሪዎችን በማሳደድ በገንዘብ እየቀጡ ነው ይላል። እሱም ቢሆን የችግሩ ሰለባ መሆኑን ይናገራል። ዘነበ በአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀናት ብቻ ለስድስት ጊዜ ‹‹ደንብ አላከበርክም›› በሚል በትራፊኮች ተከሶ ተቀጥቷል።

እሱ እንደሚለው የተላለፈበት ቅጣት ፈጽሞ ያልተገባና አስተውሎት የጎደለው ነው። ‹‹ማንም ቢሆን ባጠፋው ልክ መቀጣት እንዳለበት አምናለሁ›› የሚለው ዘነበ፤ ያለአግባብ ጥፋተኛ መባል ግን ከአስተማሪነቱ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል ሲል ተናግሯል ።

ሌላው ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የከባድ መኪና አሽከርካሪም የሰሞኑን የትራፊክ ፖሊሶች ክስና ቅጣት ላይ ቅሬታውን ያሰማል። አሽከርካሪው ለዚህ የሚያነሳው ምክንያት ‹‹አንዳንድ ትራፊኮች ለመቅጣት ሲሉ ይጠቀሙበታል›› የሚለውን ያልተገባ ስልት ነው። እንደ እሱ አስተያየት ትራፊኮች በደንብ ልብሳቸው ቆመው ሕግና ሥርዓት ሲያስከብሩ ማየት ለተመልካች ጭምር ክብርና ትርጉም አለው። አንዳንዶቹ ግን ራሳቸውን ከእይታ ሰውረውና በአሳቻ ቦታ ተደብቀው አሽከርካሪዎችን ለመቅጣት የሚዘጋጁ ናቸው። እንዲህ ማድረጋቸው ለክስና ቅጣት እንዲያመቻቸው ነው የሚለው አሽከርካሪ፤ ማንም ባጠፋው ልክ መቀጣት እንዳለበት ዕምነቱ እንደሆነ ይናገራል።

እንደ ዘነበ ገለጻ፤ አንዳንድ ትራፊክ ፖሊሶች አሽከርካሪዎች በሚቆሙባቸው የተለያዩ ሥፍራዎች ሰበብ እየፈለጉ መቅጣትን ልምድ አድርገውታል። ቅጣቱም በሕክምና ቦታዎች፣ በቅርበት ድጋፍ የሚሹ ደንበኞችን ችግር ሳይቀር ከግምት ያስገባ አይደለም። ይህን በመፍራት መብራት ጥሰው የሚሄዱ፣ በፍጥነት የሚያሽከረክሩ፣ መከሰስን ከልምድ ቆጥረው ራሳቸውን ለቅጣት የሚያዘጋጁ ግዴለሽ አሽከርካሪዎችን አበራክቷል ባይ ናቸው ።

የአሽከርካሪዎችን ቅሬታ በተመለከተ በሰሞኑን በተለያዩ አካባቢዎች ባደረግነው ቅኝት ተመሳሳይ አጋጣሚዎችን አስተውለናል። ትራፊክ ፖሊሶች በርካታ አሽከርካሪዎችን እያስቆሙ ይቀጣሉ፣ ታርጋ ይፈታሉ። በዚህ ዙሪያ ከተለያዩ አሽከርካሪዎች የሚሰማው ሀሳብ ደግሞ በትራፊክ ፖሊሶች ላይ የሚያነጣጥር ቅሬታን የያዘ ነው። አብዛኞቹ ሾፌሮች ‹‹የትራፊክ ፖሊሶች ያለአግባብ ይቀጡናል፣ ያሳቅቁናል››። በሚል ወቀሳ የሚያሰሙ ናቸው። እነሱ ጥቂት የማይባሉ የትራፊክ ፖሊሶች እኛን ከማስተማር፣ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ይልቅ መቅጣትን ያስቀድማሉ ብለው ያምናሉ።

በከተማችን አሽከርካሪዎች አጋጥሞናል ለሚሉት የመንገድ ላይ ቅጣት ምላሽ የሰጡት በአዲስ አበባ ፖሊስ ትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ የትራፊክ ሙያና ሕዝብ ግንዛቤ ዲቪዢን ኃላፊ ኢንስፔክተር ሰለሞን አዳነ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ ቁጥጥሩ በከፍተኛ ትኩረት እየተሠራ ቢሆንም የአደጋው መጠን ግን ካለፉት ጊዜያት ባነሰ መልኩ እየቀነሰ አይደለም። በየጊዜው ደንብ የሚተላለፉና ሕግ የሚጥሱ አሽከርካሪዎች ተበራክተዋል። ችግሩን ለመታደግ ፖሊስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ከመስጠት ባለፈ ጠንካራና ተደራሽ የሚባል የሕግ ማስከበር ሥራን እየተተገበረ ይገኛል።

እንደ ኢንስፔክተር ሰለሞን አገላለጽ፤ ሁሉም የደንብ መተላለፎች የትራፊክ አደጋን ያስከትላሉ። በዘንድሮው የመጀመሪያው ሩብ ዓመት በነበረው ቁጥጥርም 652 ሺ 445 አሽከርካሪዎች ደንብ በመተላለፋቸው ተቀጥተዋል። ይህ ማለት አሽከርካሪዎቹ እንደሚሉት ሳይሆን የግንዛቤ ማስጨበጫ ያገኙትን በርካቶችን ቁጥር ሳያካትት ነው።

የትራፊክ ፖሊሶች ከቀኑ እንቅስቃሴ ባለፈ ሌሊቱን ጨምሮ 24 ሰዓት ቁጥጥር ያካሂዳሉ ያሉት ኃላፊው፤ ይህም ለትራፊክ አደጋ የተሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚጠቁም ነው ብለዋል።

አሽከርካሪዎቹ ደጋግመው ስለሚያነሱት ቅሬታ ምላሽ ሲሰጡም የትራፊክ መምሪያው ዋና ዓላማ በየጊዜው በአደጋ የሚጠፋውን ሕይወትና ንብረት መታደግ እንጂ ገንዘብ መሰብሰብ ላይ ያነጣጠረ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

በተለያዩ ጊዜያት ቅሬታዎች እንደሚነሱ የሚያምኑት ኃላፊው፤ ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠትም ለትራፊኮች የአቅም ግንባታ ሥልጠናና የሥራ መመሪያ በመስጠት የድጋፍና የክትትል ሥራ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል። ማንኛውም ጤናማ ጥቆማ ቢደርስ ግን መምሪያው እያረመና እያስተካከለ ለመሄድ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

የዘንድሮው የትራፊክ ቁጥጥርና የመስክ ምልከታ ግምገማ የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋን የሚያስከትሉ የደንብ ጥሰቶች በስፋት መኖራቸውን አመላካች ሆኗል። አደጋው በከተማችን የሚካሄደውን የኮሪደር ልማት ጭምር ሰለባ ያደረገ ነው፤ ችግሩን በተለየ ትኩረት ለመፍታትም በስፋት እየተሠራበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ጠብቀው የሚያሽከረክሩ እንዳሉ ሁሉ የሕግ ጥሰት በሚፈጽሙት ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ይሆናል የሚሉት ኢንስፔክተር ሰለሞን፤ የቁጥጥር ሥራውን ከዓለም አቀፉ የትራፊክ ሕግ ማሕቀፍ ጋር በማያያዝም በሀገራችን ጠንካራ ሕግ ከጠንካራ የሕግ ማስከበር ጋር በእኩል ሊቀናጅ ግድ እንደሚል ጠቁመዋል።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 8 / 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You