ዜና ሐተታ
በዓለም ላይ ከሦስት ሴቶች አንዷ ለፆታዊ ጥቃት ተጋላጭ መሆኗን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል። በዓለማችን ላይ ከ15 እስከ 49 የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙና የፍቅር ግንኙነት ውስጥ ከሆኑ ሴቶች መሐል 27 በመቶ በአጋራቸው ፆታዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው ይኸው መረጃ ያመለክታል። በሀገራችንም ሁኔታው ተመሳሳይ ሲሆን ባስ ሲልም በቅርብ ቤተሰብ የሚፈጸም ፆታዊ ጥቃትን መሸፋፈን ይታያል።
የኒው ብራይት ኮሙኒቲ ዴቨሎፕመንት ሴንተር ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ፀዳለ ክንፉ፤ ከቀናት በፊት በትዳር አጋሯ ጥቃት የደረሰባት የልጆች እናት አግኝታ ነበር። ባልየው በሚስቱ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲያደርስ የቆየ ሲሆን በእለቱም የቅርቧ ሰዎች “ለልጆችሽ ብለሽ አይደል እስከዛሬ የቻልሽው አሁንም ለልጆችሽ ብለሽ ቻይው” ሲሏት እንደነበር በቁጭት ታስታውሳለች።
እንደ ሥራ አስኪያጇ ገለጻ፤ እናት ለልጆቿ መኖር የምትችለው እሷ ስትኖር ነው። እሷ እንድትኖር ደግሞ ከጥቃት መጠበቅ አለባት። በተደጋጋሚ ቻይው እየተባሉ በርካቶች ዘላቂ አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ሞራላቸው ተጎድቷል።
እንደ ወይዘሮ ፀዳለ ማብራሪያ፤ ትዳር ሊቆም የሚችለው አጓጉል ድርጊቶች ሲፈጸሙ ቻይው በማለት፤ አይቶ እንዳላየ በማለፍ፤ ሰምቶ እንዳልሰማ በመሆንና ሁሉንም ሸክም ወደሴቷ በማምጣት አይደለም። ወንዱንም ትዳርህ እንዲቆም፤ ልጆችህ እንዲኖሩ፤ ሀገር እንድትቀጥል ጥቃት አታድርስ፤ ለትዳርህ ብለህ ቻለው፤ ጥቃት እያደረሱ መኖር አይቻልም፤ የሚል ማኅበረሰብ መፈጠር አለበት።
እንደማኅበረሰብ ወንዶች ጥቃት ሲያደርሱ ቻይው እየተባለ በዝምታ መታለፉ ለውጥ እንዳይመጣ አድርጓል። ማኅበረሰቡ ይሄንን ይበቃል! ትክክል አይደለም፤ ማለት ከቻለ ነገሮች ይለወጣሉ ስትል ትገልጻለች።
በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች መብት ስርጸት ባለሙያ አቶ ሙሉዓለም ጌታ እንደሚናገሩት፤ በሀገራችን አብዛኛው ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በቅርብ ቤተሰብ የሚፈጸሙ ናቸው። ከቤተሰብ ውስጥ ጥቃቱ ከአባት ይጀምራል። አባት ልጁን እየደፈረ ያለበት ሁኔታ አለ። ከዛም ወንድም አጎት እያለ ይቀጥላል። እነዚህ ሰዎች የራሳቸውን አካል ነው ጉዳት እያደረሱ ያሉትና ይህንን አውቀው ከድርጊታቸው መቆጠብ አለባቸው።
እንደ አቶ ሙሉዓለም ማብራሪያ፤ በኅብረተሰቡ ዘንድ በቅርብ ቤተሰብ የሚፈጸም ጥቃት ሲያጋጥም ለተጠቂ ድጋፍ ከመስጠትና ለሕግ አካላት ከማሳወቅ ይልቅ ዞረው ይገናኛሉ በማለት ዝምታን መምረጥ አለ። ፆታዊ ጥቃት የሴትን ሰብዓዊ መብት መጣስ ነውና በማንም ተፈጸመ በማን መፈጸሙን ያወቁ አካላት ለሕግ አካላት ማመልከት አለባቸው። ባልና ሚስት ናቸው ነገ ዞረው ይገናኛሉ በማለት ዝም መባል የለበትም።
ወንጀል ስለሆነ ወንጀሉን ማጋለጥና ለሕግ አካል አሳልፎ መስጠት ይገባል። እነሱ ነገ ተመልሰው ቢገናኙም ድርጊቱ ጥፋት እንደሆነ ማወቅ አለባቸው። ጥቃቱ የደረሰው በትዳር አጋር ከሆነና ተገቢውን ቅጣት አግኝተው ወደ ትዳር የሚመለሱ ከሆነ ጥቃቱ ድጋሚ አይፈጸምም። ተሸፋፍኖ ዝም ሲባል ነገም ሌላ ጥቃት እንዲፈጸም ማበረታታት ነው ሲሉ ያብራራሉ።
የእሸት ችልድረን ኤንድ ዩዝ ዲቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን ሥራ አስኪያጅና የሜን ኢንጌጅ ኢትዮጵያ ስትሪም ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ሲሳይ ታረቀኝ የሚመሩት ሜን ኢንጌጅ 27 ድርጅቶችን በአባልነት የያዘ ንቅናቄ ሲሆን ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል ወንዶች አጋር መሆን አለባቸው በማለት እንደሚንቀሳቀሱ ይገልጻሉ።
እንደ አቶ ሲሳይ ማብራሪያ፤ የሴቶች ጥቃትን ለመከላከል በሀገራችን የፆታ እኩልነትን ለማምጣት የተሠሩት ሥራዎች በአብዛኛው ሴቶች ላይ ያተኮረና ወንዶችን የዘነጋ ነው። የሜን ኢንጌጅ ንቅናቄ ይሄንን ክፍተት ለመሙላት በማሰብ ወንዶች የሴቶችን መብት እንዲያውቁና እንዲያከብሩ ለማድረግ ያለመ ነው።
በሀገራችን ሴት ልጅ የትዳር አጋሯ ሲደበድባት “ባሏ አይደል ምን ችግር አለው” የሚል ተገቢ ያልሆነ አስተያየት ይሰጣል። ይሄና መሰል አመለካከቶች በግንዛቤ እጥረት የተነሳ በመሆኑ ለመቀየር የግንዛቤ መፍጠር ሥራዎች ያስፈልጋል ይላሉ።
ሆኖም በማኅበረሰቡ ዘንድ ሥር የሰደደ አመለካከት በመሆኑ በአንድ ጀንበር አይቀየርም የሚሉት አቶ ሲሳይ፤ ከለከፋ ጀምሮ ጥቃት መሆኑን ማስረዳት ያስፈልጋል። ለከፋ ጥቃት የማይመስለው ብዙ ሰው እንደሆነ ይናገራሉ። ምንም እንኳን ባሏ ቢሆን፤ ፍቅረኛዋም ቢሆን መብቷንና ፍላጎቷን ማክበር እንዳለበትና በአካሏ የማዘዝ መብት የእሷ መሆኗን ማስረዳት ያስፈልጋል። ለዚህም ከቤተሰብ ጀምሮ፣ በትምህርት ቤት ተማሪዎች እንዲያውቁት ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በተለይ ታዳጊዎች ከልጅነታቸው አንስቶ እያወቁት እንዲመጡ ቤተሰብም ሴትና ወንድ ልጅን እኩል የማሳደግ ባሕል ሊያዳብር ይገባል። ይህም በተወሰነ ድርጅትና ግለሰቦች እንቅስቃሴ ሳይሆን በሁሉም ሰው ጥረት የሚመጣ መሆኑን ጠቁመዋል።
የፆታ ጥቃትን በተመለከተ እራሱን የቻለ ሕግ ሊኖር ይገባል ብለን እናምናለን፤ የሚሉት አቶ ሲሳይ፤ ለዚህም የሥርዓተ ፆታ ሕግ ያስፈልጋል ብለዋል። የሴቶችም ሆነ የወንዶች መብትና ግዴታዎች በዝርዝር ሊሰፍሩ ይገባል በሚል የአድቮኬሲ ሥራ እየሠራን ነው ይላሉ።
እንደ አቶ ሙሉዓለም ገለጻ፤ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ከሴቶች አንጻር ያሉ ሕጎች ያሉባቸው ክፍተቶች ተለይተዋል። ባሉት ሕጎች ላይ ያልተካተቱና አሁን ላይ የመጡ የወንጀል ተግባራት አሉ። የነበሩትም ተሻሽለው በቀጣይ አስተማሪ የሆነ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል የሕግ ማሕቀፍ እንዲዘጋጅ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየተሠራበት እንደሆነ ይጠቁማሉ።
እንደ አቶ ሲሳይ ማብራሪያ፤ አዲስ ሕጎችን ከማውጣት ባሻገር ያሉት ሕጎች የአፈጻጸም ችግር አለባቸው። ለረዥም ጊዜ ሲባል የቆየው የአፈጻጸም ክፍተት ከንግግር ባለፈ የማስተካከያ ጊዜው አሁን ነው። አስፈላጊ የሆኑ ግን የሌሉ ሕጎች ሊወጡና ያሉትም ሕጎች በትክክል ሊተገበሩ ይገባል። በፆታዊ ጥቃት ላይ ችግሩ እራስ ላይ እስኪደርስ የመጠበቅ ሁኔታ አለ። የሕግ አካላት ችግሩን እንደራሳቸው በማየት የተፋጠና ፍትሕ እንዲሰጥ መትጋት አለባቸው።
እንደ ወይዘሮ ፀዳለ ገለጻ፤ የሃይማኖት አስተምሕሮዎቻችን ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ እየተተረጎሙ ነው። ሃይማኖታዊ አስተምሕሮዎቻችን ላይ የወንዶችን የበላይነት የሚሰብክ ነገር ባይኖርም ሰዎች እንደሚመቻቸው እየተረጎሙት ነው። የሃይማኖት ተቋማትም ይሄንን በጽኑ መቃወምና ትክክለኛውን ትርጓሜ ማኅበረሰቡ ጋር እንዲደርስ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው።
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8 / 2017 ዓ.ም