ራስ ገዝነትን ከአንድ ወደ ሁለትና…

የዩኒቨርሲቲዎች የራስ ገዝ አስተዳደር በውጪው ዓለምም የተለመደ ነው። ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ከሚተዳ ደሩባቸው መርሆዎች አንዱ የራሳቸውን ወጪ በራሳቸው በመሸፈን፣ በራሳቸው የአስተዳደር ነፃነት ገለልተኛ ሆነው መተዳደር ነው። በተለይም የፖለቲካ ተጽዕኖ እንዳያርፍባቸው የመማር ማስተማሩ ሂደት በመማር ማስተማሩ ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ እንዲሆን ታሳቢ ያደረገ ነው።

በራስ ገዝ አስተዳደር ውስጥ የሚገኘው ነፃነት ደግሞ በተቋማዊ፣ በአስተዳደራዊ እና በአካዳሚያዊ ነፃነት የሚገለጽ ሲሆን፤ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን ያለ መንግሥት ምደባ በራሳቸው የመግቢያ ፈተና እንዲቀበሉ፣ የራሳቸውን ሠራተኞች መቅጠር እና ማሰናበት እንዲችሉ፣ ግዢን ጨምሮ የራሳቸው የፋይናንስ እንቅስቃሴ እንዲያስተዳድሩ እድል የሚፈጥርላቸው ነው። ይህም ማለት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የራሳቸውን የአስተዳደር መዋቅር፣ የሰው ኃይል ምደባ፣ ቅጥር እና ደመወዝ የሲቪል ሰርቪስን ሕግ መከተል ሳይጠበቅባቸው ለራሳቸው በሚያሠራቸው መልኩ እንዲያዘጋጁ አስተዳደራዊ ነፃነት እና ሥልጣንን ያጎናጽፋቸዋል።

የዩኒቨርሲቲዎች ዋነኛ ትኩረት ትምህርት እና ትምህርት ብቻ ሲሆን፤ ምን ማስተማር እንዳለባቸው፤ የትኛውን ሥርዓተ ትምህርት መቅረጽ እንዳለባቸው፣ አዲስ የትምህርት ክፍል መክፈት ካስፈለጋቸው ማንንም ሳያስፈቅዱ፣ ካደረጉት ጥናትና ምርምር ተነስተው ያመኑበትንና ለሀገር ይጠቅማል ብለው ያሰቡትን እንዲተገብሩት እድል ይፈጥርላቸዋል። በተመሳሳይ የጥናት እና ምርምር ዘርፎችን መወሰን ካለባቸው ከየትኛውም ጫና እና ጣልቃ ገብነት ሳይኖርባቸው መሥራት እንዲችሉም ያስችላቸዋል። እንደ ሀገርም ይህ ነገር ታሳቢ ተደርጎ በርካታ ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል። ከዚህም መካከል አንዱ በተወካዮች ምክር ቤት ይህንን የሚመለከት አዋጅ ወጥቶ ወደ ተግባር እንዲገባ መደረጉ ነው።

በሀገራችን በአዋጅ ጭምር ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችሉ መስፈርቶች የተቀመጡ ሲሆን፤ ሥራው የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን እስከሚችሉ ድረስ የተደነገገበት ነው። ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ገቢ ለማመንጨት በንግድ ሥራ ላይ መሰማራትን ጭምር እንዲያገኙ ይፈቅድላቸዋልም።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ዩኒቨርሲቲዎች አሁን ያሉበት እና ወደፊት ሊኖራቸው የሚችለው የፋይናንስ አቅም እንዲሁም ከአመራር ጀምሮ እስከ ትምህርት ክፍል ያለው የሰው ኃይል አደረጃጀት ተፈትሾ እንጂ “እንዲሁ ስለፈለጉ” ራስ ገዝ አይሆኑም። ምክንያቱም የሚሰጣቸው እድል ሰፊ እንደመሆኑ መጠን ተማሪዎችንም ሲቀርጹ በዚያው ልክ መሆን ይገባዋል። ለትምህርት ጥራትም ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

ለአብነት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ቀዳሚ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለማድረግ ሲታሰብ ብዙ የሚያሟላቸው መስፈርቶች ያሉትን ነገሪ (ዶ/ር) ሲጠቅሱ፤ ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ከ1942 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ደርግ መምጣት ድረስ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ነበር። በዚህ በአስቆጠረው የረጅም ዓመታት ጉዞውም በዘርፉ ጉምቱና ብቃት ያላቸውን ተማሪዎች አፍርቶ ለሀገር አበርክቷል። ዩኒቨርሲቲው በሰው ሀብት እና በአስፈላጊ መሠረተ ልማቶች የተደራጀ ነው። ይህ ደግሞ ለትምህርት ጥራት ማደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ይታመናል ሲሉ አብራርተዋል።

እርሳቸው እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው አሁን ላይ በርካታ ነገሮችን እየቀየረ ይገኛል። አንዱ ከመንግሥት የተመደቡለትን ተማሪዎች በተወሰነ መልኩ ተቀብሏል። እነዚህ ተማሪዎች ከ500 በላይ ውጤት ያመጡ ሲሆን፤ ዩኒቨርሲቲው ውጤታቸው ብቻ በቂ ነው ብሎ ወደ ትምህርት እንዲገቡ አልፈቀደም። የራሱን ፈተና በማውጣት ብቃታቸውን ካረጋገጠ በኋላ ነው ዩኒቨርሲቲውን እንዲቀላቀሉ ያደረጋቸው። በርግጥ እነዚህን ተማሪዎች በራሱ ሳይሆን በመንግሥት በጀት እንደሚያስተምራቸው እሙን ነው። የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ምንም እንኳን የራሳቸውን ገቢ ያመነጫሉ ቢባልም ከመንግሥት የሚመደብላቸው በጀት ሙሉ በሙሉ ይቋረጣል ማለት አይደለም። ስለሆነም የሚቀበላቸውን ተማሪዎች መንግሥት በሚሰጠው በጀት እየደጎመ የሚያስተምራቸው ይሆናል።

አሁን ላይ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የተሻለ አቅም ያላቸው እና ተወዳዳሪ የሆኑ ተማሪዎችን በብዛት ለማስገባት እየተጣሩ ይገኛሉ። ሀገር አቀፍ ፈተናውም ይህንን በብዙ መልኩ የሚያሻሽለው ነው። ተማሪዎች ተወዳድረው ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ ብቻ ሳይሆን ከታች ጀምሮ ለትምህርታቸው ትኩረት እንዲሰጡ ያስችላቸዋል። መወዳደር እንዲችሉ፣ የአሰቡት ደረጃ ላይ ለመድረስ እንዲማሩ እድል ይፈጥርላቸዋል። በተማሪዎች ብቃት መሠረት ከወላጆችም ጭምር እንዲመጣ እድሉን ያመቻቻሉ። በተለይም ዩኒቨርሲቲ መግባት በውድድር ማሸነፍ እንደሆነ ሁሉም እንዲረዳው ያደርጋል።

ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ብቃት ያላቸው መምህራንን በተሻለ ደሞዝ እና የሥራ ሁኔታ ሊይዙ የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥርላቸዋል፤ በተሻለ መምህር መማርም ለተሻለ ሥራ ያበቃልና ተማሪዎች ራስ ገዝ የሆኑ ትምህርት ቤቶችን እንዲመርጡ፤ እዚያም ለመግባት ተወዳዳሪ ተማሪ እንዲሆንም ያስችላቸዋል።

የትምህርት ጥራት መረጋገጥ የሚችለው በተማሪው ልፋት ብቻ አይደለም። የመምህሩ የማስተማር ብቃትን፤ ለተማሪዎች የሚሰጠውን ጊዜንም መሠረት ያደርጋል። የመምህራንን ጉዳይ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከተው አንድ ቦታ የሚሠራ መምህር ኑሮን ለማሸነፍ ስለማይችል ሌላ ሁለት ሦስት ቦታ እንዲያስተምር ይገደዳል። ስለዚህም ለተማሪዎቹ የትምህርት ማስተማሪያ (ሀንድ አውት) ሰጥቶ ሊለያቸው ይችላል። እስከ አሁንም ሲሠራበት የቆየው ይህ አሠራር ነው። አሁን ግን ራስ ገዝነት ይህንን ሁኔታ በብዙ መልኩ እንደሚያሻሽለው በተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ማብራሪያ ያሳያል። አንዱ የመምህራን ደመወዝ ጉዳይ ነው። ለመምህራን እንደብቃታቸው ክፍያ እንዲያገኙ፣ ጥናት እና ምርምር እንዲሁም አካዳሚያዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ዕድልን ይሰጣል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት ትምህርት ተቋማት የሚሠሩ መምህራን ከሌሎች ሀገራት አንጻር ዝቅተኛ ደመወዝ ነው የሚከፈላቸው። በራስ ገዝ አስተዳደር ግን ለመምህራን ተመጣጣኝ ክፍያ ይከፈላል ተብሎ ይታሰባል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ መምህራን ብቃታቸውን፣ ክህሎታቸውን፣ ጊዜያቸውን እና ዕውቀታቸውን በሙሉ የትምህርት ሥራው ላይ እንዲያውሉ ያስችላቸዋል።

ከዚህ አንጻርም ነገሪ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ “የመጀመሪያ ትውልድ” የሚያሰኙት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ራስ ገዝነት ይሸጋገራሉ። እነዚህም ሀሮማያ፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ ባሕር ዳር፣ ሐዋሳ፣ አርባ ምንጭ እና መቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች ሲሆኑ፤ እስከ ሁለት ዓመት “እንደ የዝግጅታቸው” ወደ ራስ ገዝነት ያድጋሉ።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ይህ እድል ይሰጣቸዋል ከተባሉ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ ነው። በዚህ ዙሪያ የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር) ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል። እርሳቸው እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው የረጅም ጊዜ ልምድ ያለውና ትላልቅ ምሁራንን ያፈራ ከመሆኑ አኳያ ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችል አቅም አለው። ለዚህም አቅዶ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። አሁን ላይ በዋናነት የሰነዶች ዝግጅት ላይ እየተሠራ ነው። አጠቃላይ የዩኒቨርሲቲውን ፕሮግራሞች የሚከለሱበት ሰነድ ተዘጋጅቶ የዩኒቨርሲቲው ፕሮግራሞች ላይ ክለሳ ለማድረግ ሰነዱ ለሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ቀርቦም ግብዓት ተገኝቶበታል።

በቀጣይ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት እንዲያየው ፕሮግራም መያዙን የጠቀሱት ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ፤ ሰነዱ ከፀደቀ በኋላ በዚሁ መነሻነት አጠቃላይ በዩኒቨርሲቲው ያሉ ኮሌጅና ትምህርት ክፍል ፕሮግራሞች ላይ ክለሳ ተደርጎ ራስ ገዝ ለመሆን በሚያመች መልኩ ፕሮግራሞችን እናደራጃለን ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉንም ፕሮግራሞች ይዞ ላይቀጥል ስለሚችል አግባብነት ያላቸውን ፕሮግራሞች ይዞ ለመሄድ ሰነዱ አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ። እስከ ታኅሣሥ አጋማሽ 2017 ዓ.ም ለሥራ ዝግጁ እንደሚሆንም ያስረዳሉ። የራስ ገዝ ማበልፀጊያ ስትራቴጂያዊ እቅድም እየተዘጋጀ መሆኑን አመልክተው፤ እቅዱ እስከ ታኅሣሥ መጨረሻ 2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚጠናቀቅ፤ በዕቅዱ ላይም የሚመለከተው አካል ሁሉ አስተያየት ሰጥቶበት፣ ሥራ አመራር ቦርዱ እንዲያውቀው ተደርጎና ተተችቶ ጥር ወር 2017 ዓ.ም በዚህ መነሻነት የምንመራበትን ሰነድ አፅድቀን ሥራ እንጀምራለን ብለዋል።

ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት፤ በአጠቃላይ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ሕግ ተከልሶ ሙሉ በሙሉ ወደ ማለቁ ደርሷል። ለሴኔት ሥራ አስፈፃሚ ቀርቦ የመጨረሻ ትችት ይቀርብበታል። ከዚህ በኋላም ወደ ሥራ እንደሚገባ ጠቁመዋል። በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስ ገዝነት የሚሸጋገርበትን ጉዞ በተመለከተ በዝርዝር ተተንትኖና ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ የሚገባበት ሁኔታ እንደሚኖር ነው ያስረዱት።

ዩኒቨርሲቲው ከሀዋሳ ውጭና ሀዋሳ ከተማ ውስጥ ወደ ሰባት የሚሆኑ የተለያዩ ካምፓሶች እንዳሉት የገለጹት ችሮታው (ዶ/ር)፤ ከስፋቱ አንፃር ውጤታማ አድርጎ በልኩ መምራቱ ላይ ተግዳሮት ሊኖር እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ይገልጻሉ። ይህም ቢሆን እንደ አጠቃላይ በተያዘው በጀት ዓመት እነዚህን ሰነዶች የማፀደቅ ሥራ ተሠርቶ በ2018 ዓ.ም ሰነዶቹን ሙሉ በሙሉ ተግባር ላይ እንደሚውሉና 2019 ዓ.ም ላይ ሙሉ በሙሉ ራስ ገዝ ለመሆን በመንግሥት ለማፀደቅ እና ሥራ ለመጀመር ዝግጁ መሆኑን ያብራራሉ። በተጨማሪም ከአካባቢው መስተዳድር ጋር ተነጋግረውና ራስ ገዝ ለመሆን ያሏቸውን ጉድለቶች መንግሥት አግዟቸው በተደራጀ ሁኔታ ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚመለከታቸውን አካላት ድጋፍ ለመጠየቅ ማሰባቸውንም ያስረዳሉ።

ሌላው ራስ ገዝ የመሆን እቅዱን ለመተግበር ጉዞ የጀመረው ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፤ ከሁለተኛው ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የሚመደብ ነው። ዩኒቨርሲቲው እንደ ሌሎቹ ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉ የራሱን የራስ ገዝና የተግባር ዩኒቨርሲቲ ሽግግር ዳይሬክቶሬት አቋቁሞ መሥራት ጀምሯል።

የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር ዶክተር ሰይድ መሐመድ እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው ላለፉት 15 ዓመታት በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ትምህርቶችን ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፤ በቅርቡ በተደረገው የዩኒቨርሲቲዎች ልየታ መሠረት የተግባር ሳይንስ ዘርፍን ይዞ እንዲቀጥል ነው የተደረገው። የራስ ገዝነትን መስፈርት ከዚህ አኳያ እየታየ የሚተገበር ይሆናል። ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማቋቋም ራስ ገዝ መሆን የሚያስችሉትን ተግባራትም ጀምሯል። እንደ ሀገር በተቀመጠው የራስ ገዝነት መስፈርት መሠረት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በማድረግ ላይ ይገኛል።

የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ መሆን የትምህርት አሰጣጥ፣ የውስጥ ገቢን ማሳደግ፣ የተማሪዎች አስተዳደር፣ የአስተዳደር መዋቅር ማስተካከል፤ ኮርሶችን መለየትና መሰል ጉዳዮችን በራስ ለመፈጸም ያስችላል። የራሱን መመሪያዎች ለመተግባር እና ከሲቪል ሰርቪስ አሠራር ነፃ ለመሆን ትልቅ እድል የሚሰጠው ነው። እንዲሁም የሀገርን ፍላጎት መሠረት በማድረግ አዳዲስ ሥርዓተ-ትምህርቶችን በመቅረጽና ነባሮችን በማሻሻል ተማሪዎችን በስፖንሰር፣ በግልና በነፃ የትምህርት እድል ተቀብሎ ለማሰልጠን የሚያግዝ ነው። ይህ ደግሞ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ በእውቀትና ክህሎት የዳበረ የሰው ኃይል ለማፍራት የተሻለ እድል ይፈጥራል። ስለሆነም ዩኒቨርሲቲው ይህንን ታሳቢ በማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል።

ዩኒቨርቲዎችን ራስ ገዝ ለመሆን ከሚያስገድዱ ምክንያቶች መካከል አንዱ የራስን ገቢ ማመንጨት ሲሆን፤ ከዚህ አንጻር ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ስለመሆኑን ይናገራሉ። የተለያዩ ሰነድ ከማዘጋጀት ባሻገር ከተቀመጠው መስፈርት አምስት ኢንተርፕራይዞችን ማቋቋም ውስጥ አንዱን አቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል። ይህም ‹‹መገዘዝ›› ኢንተርፕራይዝ የሚባለው እንደሆነም አንስተዋል።

መስፈርቶችን መሠረት በማድረግም የተቋቁመው አብይና ንዑሳን ኮሚቴዎች የተለያዩ ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል። ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ እንዲሆን የሚያደርጉ ማንኛውንም ተግባር እውን ለማድረግ ትኩረት ሰጥተው ይሠራሉ። በጥቂት ዓመታት ውስጥ የራስ ገዝነትን ቦታ እንደሚቆናጠጡትም እምነታቸው ነው።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You