በአዲስ አበባ ፦ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱትን ጥቃቶችን ለመቀነስ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠሉን የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ሴቶች ህጻናትና ማበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የማህበራዊ ዘርፍ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ወይዘሮ ገነት ቅጣው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ በከተማው የሚደርሱትና የሴቶችና ህጻናት ጥቃትን ለመቀነስ ቢሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እየሠራ ነው ፡፡
በከተማው ውስጥ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱትን ጥቃቶች ለመከላከል የማህበረሰቡ ግንዛቤ ብዙ ይቀረዋል ያሉት ሃላፊዋ ፣ በተለይ በቤተሰብ ደረጃ ስለ ችግሩ አስከፊነት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።
በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በቅርብ ቤተሰብ፣ በአሳዳጊ፣ በቤተሰብ አባልና በጎረቤትም ጭምር እንደሆነ የጠቆሙት ሃላፊዋ ፣ በተለይ ህጻናት ላይ የሚደርሱት ጥቃቶች ይንከባከቡኛል፣ ከጥቃት ይከላከሉልኛል በሚሏቸው የቤተሰብ አባላት መሆኑ ችግሩን አሳሳቢ እንደሚያደርገው አስታውቀዋል።
እነዚህ ጥቃቶች እንዳይደርሱ ከፍተኛ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ የጠቆሙት ወይዘሮ ገነት ፤ ቢሮው ለችግሩ ቅድሚያ ሰጥቶ በስፋት እየሠራ እንደሚገኝ አመልክተዋል። የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም፣ ህብረተሰቡን በብሎክ፣ በአንድ ለአንድ በማግኘት፣ የተለያዩ የሕዝብ አደረጃጀቶችን በመጠቀም፣ በሥልጠናዎች የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራዎች ተጠናክረው እየተሰጡ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የሚደርሱትን ጥቃቶችን በማጋለጥ ኅብረተሰቡ በጣም ተበባሪ እንደሆነ ፤ የብሎክ ጥቃት ተከላካይ ኮሚቴዎች ጥቃት ለሚደርስባቸው የሚከራከሩ፣ ማህበረሰቡን የሚመክሩ፣ በእድሮችና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የደረሱት ጥቃቶች እንዲጋለጡ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል።
ጥቃቶቹን ለመከላከል ትልቅ ፈተና የሆነው ችግሩ ቤተሰብ ውስጥ ተደብቆ እንዲቀር የመፈለግ ሁኔታዎች ናቸው ያሉት ሃላፊዋ ፤ በማህበረሰቡ ደረጃ የተሻለ ግንዛቤ ቢኖረውም፣ በቤተሰብ ደረጃ ብዙ ይቀራል።ማህበረሰቡ እንዴት ቤተሰቤ ላይ ልጠቁም የሚለውን አስተሳሰብ ሰብሮ ጥቃት አድራሾችን አሳልፎ ለሕግ እንዲሰጥ ብዙ መሥራት ይፈልጋል ብለዋል ።
በሴቶችና ህጻናት ላይ ብዙ ዓይነት ጥቃቶች እንደሚደርሱም ያመለከቱት ወይዘሮ ገነት ፤ ጾታን መሠረት ያደረገ፣ ህጻናት መጣልና ሌሎች በርካታ ጥቃቶች ይደርሳሉ።የሕግ ጉዳዮችን ከፍትህ ቢሮ ጋር፣ የጤና ጉዳዮችን ከጤና ቢሮ ጋር በመሆን ተባብረን ችግሩን በጋራ ለመቅረፍ እየሠራን እንገኛለን ብለዋል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም