
ኢትዮጵያ 27 ብሔራዊ ፓርኮች እንዳሏት የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን መረጃ ያመለክታል። ከእነዚህ መካከል የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ አንዱ ነው። ፓርኩ ሀገሪቱ ካሏት ብሔራዊ ፓርኮች በቆዳ ስፋቱ ትልቁ ሲሆን፤ በውስጡ የያዛቸው ሀብቶች በጣም በርካታ ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ በሌሎቹ የሀገሪቱ ክፍሎች አይገኙም።
ፓርኩ እስካሁን ባለው ሁኔታ በሚገባ እየተጠበቀና እየለማ አይደለም፤ በዚህ የተነሳም ለሚገኝበት ክልልም ፣ለማህበረሱበም ሆነ ለሀገርም ጥቅም እየሰጠ አይደለም። ፓርኩ በደርግ መንግሥት ዘመን በአካባቢው የደቡብ ሱዳን ነጻ አውጪ ጦር ካምፕ እንዲሁም የስደተኞች ካምፕ የነበረበት በመሆኑም የዱር እንስሳቱና የደን ሀብቱ ለስጋት ተጋልጦ ኖሯል። ከዚያ ወዲህም በክልሉ የሚከሰቱ ግጭቶችም እንዲሁ ሌላው ፓርኩ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳረፈ ስለመሆኑ ይገለጻል፡፡
ይህን ሰፊ ብዝሃ ህይወት ያለውን ፓርክ ለመጠበቅ፣ ለማልማት እንዲሁም የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ሰሞኑን ተፈርሟል። ስምምነቱ የተደረገው ደቡብ ሱዳንን ጨምሮ በአፍሪካ 12 ሀገሮች በፓርክ ጥበቃና ልማት በአጠቃላይ ማስተዳደር ስራ ላይ ከሚሰራው ለትርፍ ካልተቋቋመው መንግሥታዊ ካልሆነው አፍሪካን ፓርክስ ከተሰኘው ድርጅት ጋር ነው። ስምምነቱን የጋምቤላ ክልል ርእሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ፣ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩማራ ዋቅጅራና የአፍሪካን ፓርክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ፒተር ፌርንሄድ ናቸው የተፈራረሙት። በዱር እንስሳቱ ላይ የተደቀነውን ስጋት ለማስቀረት፣ መሰረተ ልማት ለመገንባት እንደሚያስችልም ታምኖበታል።
ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት የተገኙት የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ስምምነቱ የፓርኩ ችግሮች እንዲፈቱ፤ በትራንስፖርትና በሌሎች መሰረተ ልማቶች ተደራሽ እንዲሆን ፣ምርምሮችና ጥናቶች እንዲካሄዱበት በር እንደሚከፍት አስታውቀዋል።
ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ ፓርኩ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች በቂ ትኩረት አላገኘም። በዚህ ላይ የተፈጥሮ ችግር ተጨምሮበት የዱር እንስሳቱ ቁጥር የመቀነስ፣ ለጎብኚዎች ምቹ አለመሆን ሁኔታ ሲስተዋልበት ቆይቷል። በዚህ መነሻነትም ይህን ፓርክ እንዴት አድርገን በማሻሻል ለጎብኚዎች፣ ለክልሉና ለማህበረሰቡ እንዲሁም ለሀገር እንዲጠቅም ማድረግ እንችላለን በሚለው ላይ ለበርካታ ዓመታት ጥናቶች ተደርገዋል። በጥናቶቹ ላይ በመመስረትም ‘አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካዊ መፍትሄ’ በሚለው የሀገራችን መርህ መሰረት ‹‹አፍሪካ ፓርክስ›› ከተባለው ድርጅት ጋር ፓርኩን ለመጠበቅና ለማልማት የሚያስችል ስምምነት ተደርሷል፡፡
እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ከክልሉ ጋር ጋምቤላ ላይ ምክክር አድርገን የደረስንበት መግባባት ፓርኩ ያሉበት ችግሮች እንዲቀረፉ ለማድረግ ፓርኩ ያለበት አካባቢ ማህበረሰብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያስፈልጋል ሲሉ ሚኒስትሯ ጠቅሰው፤ በአብዛኛው የክልሉ ማህበረሰብ ዘንድ ፓርኩ ምን ያህል ከፍተኛ ስለመሆኑ መረዳቱ እንዳለ ገልጸዋል፡፡
‹‹ከፓርኩ መጠቀም ላይ ገና ብዙ አልተሰራም፤ ፓርኩ ስራ መፍጠር አለበት›› ሲሉ አስገንዝበዋል። የቱሪስት መዳረሻ መሆን አለበት፤ ለዚህም ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታዎች መፈጠር አለባቸው። የአስፈላጊ መሰረተ ልማቶች ግንባታ መካሄድ ይኖርበታል። መንገዶች፣ የተለያዩ መዳረሻዎች መሰራት አለባቸው ብለዋል፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረት መሰረተ ልማቶችን በመገንባት የክልሉን ማህበረሰብ በተለይ ወጣቶችን ከፓርኩ ተጠቃሚ ማድረግ አንድ ነገር መሆኑን ጠቅሰው፣ ሕዝቡም ፓርኩ የእኔም፤ የሀገርም ሀብት ብሎ እንዲይዘው ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ስምምነቱ በክልሉ ርእሰ መስተዳድር ደረጃ እንዲካሄድ የተደረገበት ምክንያትም ለዚህ መሆኑን ተናግረዋል።
ስምምነቱ ለሌሎች ፓርኮች እንደ ሀገር ደግሞ ለቱሪዝም ዘርፍ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ያላየናቸው የቱሪዝም ሀብቶችን መግለጥ፣ ያየናቸውን ደግሞ መጠቀም ከዚያም አሻሽለን እንዴት እንስራባቸው የሚለው ላይ አንድ እርምጃ ወደፊት ሊያራምድን ይችላል ሲሉም አስታውቀዋል።
ሚኒስትሯ እንደገለጹት፤ የግሉን ዘርፍ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ማሳተፍ አልተለመደም፤ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ የፓርኩን አስተዳደር ስራዎች እንዲሰራ ከማድረግ አኳያ ከዚህ በፊት በተወሰነ መልኩ የተሞከሩ ነገሮች ቢኖሩም በዚህ ልክ ሲሰራ ግን አሁን የመጀመሪያው ነው። ለሌሎችም አካባቢዎች ትምህርት ሊሆን በሚችል መልኩ አሁን የተጀመሩትን ስራዎች በማየት ሌሎች አካባቢዎች ላይ ተግባራዊ ሊሆን የሚችልበትን እንፈልጋለን ማለት ነው።
የጋምቤላ ክልል ርእስ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ ስምምነቱ ለክልሉ ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ እንዲሁም ለምሥራቅ አፍሪካ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አስታውቀዋል። በክልሉ የዱር እንስሳት ብቻ ሳይሆኑ አራት ትላልቅ ወንዞች፣ ኩሬዎች ሀይቆች በእነዚህም ውስጥ በርካታ ብዝሃ ሕይወት እንዳለ አመልክተው፣ ስምምነቱ ለክልሉ ሕዝብ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አስታውቀው፣ ትልቅ ኃላፊነትም ይዞ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡
ለስምምነቱ መፈጸም ቁርጠኛ መሆናቸውንም ጠቅሰው፣ ‹‹ስራው የኢትዮጵያውያንና የሀገራችን ስራ እንደመሆኑ ፓርኩ በክልሉ ውስጥ ቢገኝም ከመላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሆነን ይህን ፓርክ ወደቀድሞ ገጽታው ለመመለስ መስራት ይኖርብናል›› ብለዋል፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረት የመጀመሪያ ስራ የሚሆነው ከሶስት እስከ አራት ዓመት ባለው ጊዜ የመሰረተ ልማት ግንባታ እንደሚከናወን ጠቅሰው፣ ከዚያም ወደ ዋናው ፓርኩን የማልማት ስራ እንደሚገባ ተናግረዋል። ለእዚህ ስራም የክልሉ ሕዝብ ወይም በፓርኩ ክልል ውስጥ ያለው ማህበረሰብ ትብብር ማድረግ እንደሚኖርበት አስገንዝበው፤ ስራው የሕዝቡ መሆኑን ማሳወቅ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡
ከሌሎች ክልሎች ፓርኮች ጋር ሲነጻጸር ክልሉ በሙሉ ፓርክ ነው ብሎ መናገር ያስችላል ያሉት ርእስ መስተዳድሯ፤ ‹‹ምክንያቱም የትኛውም የክልሉ አካባቢ ብትንቀሳቀስ የዱር እንስሳትን ታገኛላችሁ ብለዋል። እንስሳቱ ከሰዎች እንቅስቃሴዎች በሚመነጩ ድምጾች ሳቢያ ሊርቁ እንደሚችሉ አመልክተው፤ ይህ እንዳይሆን የእንስሳቱን አካባቢ ከሰው እንቅስቃሴ ነጻ ለማድረግ ይሰራል›› ብለዋል።
በፓርኩ በትንሹ ቀጭኔ፣ ዝሆን፣ አንበሳ ይገኛሉ ሲሉም ጠቅሰው፣ ዝሆን በአሁኑ ሰዓት ወደታች የሸሸበት ሁኔታ ይታያል ብለዋል። ‹‹ያ እንዲሆን ያደረገው ከደርግ ጊዜ አንስቶ አካባቢው የደቡብ ሱዳን ነጻ አውጭ ሠራዊትና ስደተኞች መስፈራቸው የነበረ መሆኑ ነው፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ ከወንዙ ውጪ ያሉት እንስሳት ጥቃት እየደረሰባቸው ከአካባቢው ይሰደዱ ነበር›› ብለዋል። ያን አይነት ችግር በአሁኑ ወቅት እንደሌለም ተናግረው፣ ስደተኞችም ስርአት ተበጅቶላቸው እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል፡፡
ፓርኩን ለማስተዳደርና ለማልማት ስምምነት የፈረመው አፍረካን ፓርክስ በደቡብ ሱዳንም እንደሚሰራ ጠቅሰው፣ የዱር እንስሳቱ በሁለቱም ሀገሮች የሚኖሩ እንደመሆናቸው ስራው በተናበበ ሁኔታ እንዲሰራ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩማራ ዋቅጅራ እንዳሉት፤ ስምምነቱ የተደረገው የዱር እንስሳትንና መኖሪያ አካባቢያቸውን ለመጠበቅ፣ለማልማትና በዘላቂነት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማስቻል ነው። እንዲህ አይነቱ ስራ ከብዙ አካላት ጋር አብሮ መስራትን ይፈልጋል። ለመንግሥት አካል ብቻ የሚተው አይደለም። ይሄ የመጀመሪያው ነው፤ በቀጣይም ተመሳሳይ የትብብር መድረኮች እናመቻቻለን ብለዋል፡፡
ለዚህ አጋርነት የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ የተመረጠበት ዋናው ምክንያት ሀገሪቱ ካሏት ብሄራዊ ፓርኮች በቆዳ ስፋቱ ትልቁና በውስጡ የያዛቸው ሀብቶችም በጣም በርካታ በመሆናቸው ነው። አንዳንዶቹ ደግሞ በሌሎቹ የሀገሪቱ ክፍሎች አይገኙም ሲሉ አስታውቀዋል።
አሁን ባለበት ሁኔታ በተገቢው መንገድ ተጠብቆ እየለማና ለሀገርም ለክልሉም ለማህበረሰቡ ጥቅም እየሰጠ እንዳልሆነ ተናግረው፤ ዋናው ምክንያት የሀብት ውስንነት በመኖሩ ነው፤ የቆዳ ስፋቱ ትልቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሰፊ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት እንደሚፈልግ አስታውቀዋል፤ ስምምነቱ ለቱሪዝሙም ፓርኩንም ውጤታማና በተሻለ መልክ ለማስተዳደር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ስምምነቱ ብሔራዊ ፓርኩን በጣም ተጠቃሚ ያደርጋል፤ ብሔራዊ ፓርኩ ባግባቡ ተጠበቀ ማለት ይለማል ማለት ነው፤ ለማ ማለት ደግሞ ለአካባቢው ማህበረሰብም፣ ለክልሉም ለሀገርም ጥቅም ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል። እንደ ኢትዮጵያ በዚህ ስምምነት መሰረት አንድ ሞዴል ፓርክ ሊኖረን ይችላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ሲሉም አቶ ኩመራ ጠቁመዋል፡፡
‹‹በሀገሪቱ ወደ 27 የሚደርሱ ብሔራዊ ፓርኮች ይገኛሉ። ሌሎች የጥበቃ አይነቶችም አሉ›› ሲሉ ጠቅሰው፤ ስለዚህ ጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ለኢትዮጵያ ሞዴል ደረጃውን የተጠበቀ እንደ ሀገርም የምንኮራበት አንድ ብሔራዊ ፓርክ በቀጣይ ይኖረናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል። እዚህ ላይ ውጤት ስናሳይ ልምድና ተሞክሮው ወደ ሌሎች ብሔራዊ ፓርኮች እየሰፋ ይሄዳል:: ለምሳሌ ከሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ከሌሎች አጋር አካላት ጋር ለማስተዳደር ፣ የባሌ ተራሮች፣ የጨበራ ጩርጨራ፣ ፣የኦሞ ብሔራዊ ፓርኮችንም በተመሳሳይ ለማስተዳደርና ለማልማት ንግግር እያደረግን ነው ሲሉም አስታውቀዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር የዱር እንስሳት ሀብቶችን ትጋራለች፤ ምክንያቱም የዱር እንስሳት ድንበር የላቸውም፤ የፖለቲካ ወሰን የላቸውም፤ የራሳቸው ፍላጎት አላቸው፤ በዚያ መሰረት ይንቀሳቀሳሉ። በደቡብ ሱዳን ስድስት ሚሊዮን እንስሳት ይገኛሉ የተባለው የኢትዮጵያም ጭምር ናቸው። ስለዚህ በጋራ መጠበቅና ማልማት ያስፈልጋል። ዋና ዳይሬክተሩ ድርጅቱ ተሞክሮውን ወደ እዚህ በማስፋት ስራውን ውጤታማ ያደርጋል ብለን እናምናለን ይላሉ።
ፓርኩን ለማስተዳደር የአጋርነት ስምምነት የተፈራረመው የአፍሪካን ፓርክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ፒተር ፌርንሄድ እንዳሉት፤ ድርጅቱ ቴክኒካል ፣ የፋይናንስና ፓርኩን ማስተዳደር የሚያስችል የባለሙያ አቅም በመፍጠር ለፓርኩ ድጋፍ ያደርጋል። የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ለመስራት፣ በፓርኩ አካባቢና ውስጥ የሚኖረውን ማህበረሰብ በዚህ ስራ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ እንዲሁም በፓርኩ ውስጥ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የሚሰሩ ለትርፍ የሚሰሩ ኢንተርፕራይዞች እንዲፈጠሩ ለማድረግም ይሰራል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንዳሉት ፤የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ፣ የደቡብ ሱዳኖቹ ጊሎና ቦማ ብሔራዊ ፓርኮች በጣም ሰፊ አካባቢን የሚሸፍኑና ኩታ ገጠም ናቸው። ክልሉ በጣም ትልቅና በአፍሪካ ወሳኝ የሚባል ስፍራ ነው። ፓርኮቹ የዱር እንስሳትን ጨምሮ በጣም በርካታ ብዝሃ ህይወት አላቸው።
ስምምነቱ በሀገር ደረጃ ቢካሄድም ፓርኩ ከሚያዋስናቸው ፓርኮች አኳያ ሲታይ ከጎረቤት ደቡብ ሱዳን ጋር አብሮ መስራትን የግድ እንደሚልም ሚስተር ፒተር አስገንዝበዋል፤ ኢትዮጵያ ላይ ውጤታማ ሆኖ ደቡብ ሱዳን ላይ ድክመት ከገጠመ አጠቃላይ አፈጻጸሙ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳርፍ አስታውቀዋል። ስራው ለየብቻ የሚፈጸም ቢሆንም ሁለቱ ሀገሮች በዚህ ጉዳይ ላይ አብረው መስራት አለባቸው ሲሉ አስገንዝበዋል።
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 6 ቀን 2017 ዓ.ም