በየዘመናቱ የነበሩ የኢትዮጵያ መንግሥታት እንደዘመናቸው የሚያለያዪቸው በርካታ ነገሮች ቢኖሩም በወደብ እና በባሕር ጉዳይ ግን ተመሳሳይ አቋም ነበራቸው። ሁሉም በሚባል መልኩ ኢትዮጵያ የባሕር በር መብቷን እንዳታጣ እና ከዓለም ጋር ተቆራርጣ እንዳትቀር የበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ይህም ሆኖ የኢትዮጵያን ማደግ በማይፈልጉ ኃይላት ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር እንድትርቅ ተደርጓል። ለዘመናትም ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ድርሻ እንዳልነበራት ሆን ተብሎ በተሰራጪ ትርክቶች ኢትዮጵያና ቀይ ባሕር ተቆራርጠው ኖረዋል።
ከሕዝቡ ልብ ውስጥ ቀይ ባሕርን ማውጣት ባይቻልም ስለቀይ ባሕር ማሰብና ማውራት እንደ ሀጢያት የተቆጠረባቸው ሶስት አስርት ዓመታትም ታልፈዋል። በነዚህ ዓመታት ስለወደብና ባሕር በር ማውራት ሆነ የኢትዮጵያን የባለቤትነት መብት መጠይቅ እንደነውር ከመቆጠር ባለፈ ጸብ አጫሪ አስብሎም በነገረኛነት ያስፈርጅም ነበር።
የኢትዮጵያን የወደብ እና የባሕር ባለቤትነት መብት የሚጠይቁ እና ግንዛቤ የሚፈጥሩ ጽሑፎች እንዳይታተሙ ተከልክለዋል፤ ፊልሞች እና መሰል የኪነጥበብ ሥራዎችም እንዳይታዩ ታግደዋል። በዚህም ሀገሪቱ የባሕር በርም ሆነ ወደብ እንደማይገባት ተደርጎ ሲቆጠር ቆይቷል።
ይህ ደግሞ ሀገሪቱን እና ሕዝቦቿን ለበርካታ ቀውሶች ዳርጓቸዋል። የኢትዮጵያ ወደብ አልባነት በሕዝቦቿ ላይ የሥነ ልቦና ጫና ከመፍጠር አንስቶ ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ችግሮች አጋልጧታል። የሀገሪቱን ክብርና ዝናም ዝቅ አድርጓል።
ለበርካታ መሠረተ ልማቶች ይውል የነበረ ከ1ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሀብት ለወደብ ኪራይ በየዓመቱ እንድታወጣ አስገድዷታል። ይህም በልማት ድህነትን አሸንፎ ለምታደርገው ጥረት ትልቅ ተግዳሮት ሆኖባታል። በሀገሪቱ የሸቀጦች ዋጋ እንዲንርና የኑሮ ውድነትም እንዲባባስ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል።
ሀገሪቱ የምትገኝበት የብዙዎችን ቀልብ በሚስበው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከመሆኑ አኳያ ከባሕር የመራቋ እውነታ ቀደም ሲል በነበራት ተጽእኖ ፈጣሪነቷ ላይ ጥላ ሆኖባታል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ወደብ አልባ ከሆኑት 16 ሀገራት አንዷ ብትሆንም ወደብ አልባ የሆነችባቸው አመክንዮዎች ግን ታሪካዊም ሆነ ሕጋዊ መሠረት የሌላቸው ናቸው። የኢትዮጵያ ሕዝብ 126 ሚሊዮን ደርሷል። በአጠቃላይም በኢትዮጵያ የሚኖረው ሕዝብ የባሕር በር የሌላቸውን ሀገራት ሕዝብ 1/3ኛውን ይሸፍናል። ይሄንን የሚያህል ሕዝብ ይዞ የባሕር በርና ወደብ የተነፈገ ሀገር የለም።
ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ኢትዮጵያ በባሕር በር የተከበበች ሀገር ነች። ከላይ እንደጠቀስኩት በሴራ እና በተሳሳተ ትርክት ከቀይ ባሕር እንድትርቅ ከመደረጓ በስተቀር በአፈጣጠሯ ለቀይ ባሕር የቀረበ ነው። በሶስተኛ ደረጃ በታሪክም ሀገሪቱ በቀይ ባሕር ላይ ባለይዞታ ሆና የቆየች ነች፤ ለዚህም በርካታ ማስረጃዎች መጥቀስ ይቻላል።
ሀገሪቱ በግፍ ከታሪካዊ እና ሕጋዊ ይዞታዋ እንድትነቀል ከመደረጓ ውጭ ፤ የባሕር በር ባለቤት እንዳትሆን የሚከለክላት አንዳችም ዓለም አቀፍ ሕግ የለም። ኢትዮጵያ ወደብ አልባ የሆነችበትም ሆነ ከቀይ ባሕር እንድትርቅ የተደረገበት መንገድ ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሠረት የሌለው ነው።
ይህም በመሆኑ አሁን ላይ ያለምንም መሸማቀቅ ፍትሃዊ የሆነውን የወደብ ማግኘት ጥያቄያችንን በዓለም አደባባይ ድምጻችንን ከፍ አድርገን በማሰማት ላይ እንገኛለን፤ በዚህም ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እያገኘን ነው።
ይህ የባሕር በር እና የወደብ የማግኘት መብት ጉዳይ የለውጡ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ ማግስት ጀምሮ በትኩረት ከሠራባቸውና ለውጥ ካመጣባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው። መንግሥት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለዘመናት ቁጭት ፈጥሮ የነበረውን የባሕር በር ጥያቄ በመመለስና ስብራትን በመጠገን ታሪካዊ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል። ለ27 ዓመታት ያህል ፈርሶ የቆየውን የባሕር ኃይል እንደገና በማደራጀት ኢትዮጵያ እንደገና የባሕር ኃይል እንዲኖራት እየሠራ ነው።
ከዚሁ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ ከ33 ዓመታት በኋላ የባሕር በር የምታገኝበት አማራጭ ተገኝቷል። ሰላማዊ አማራጭን ሲከተል ቆየው የኢትዮጵያ መንግሥት ከሶማሊ ላንድ ጋር የባሕር በር የሚገኝበትን መግባቢያ ሰነድ (Memorandum of understanding) ተፈራርሟል።
ይህ የመግባቢያ ሰነድ ሲተገበር አካባቢያዊ መረጋጋት የሚያመጣና ኢትዮጵያም በቀጣናው ላይ አለኝ የምትለውን የባለቤትነት ጥያቄ መልስ እንዲገኝ በር የሚከፍት ነው። ቀጣናዊ ሰላምን በማስፈን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የተረጋጋ እንዲሆን በር ይከፍታል።
ከሶማሊ ሪፐብሊክ ጋር ሰሞኑን በአንካራ በተደረገ ውይይት ሀገራቱ የደረሱበት ስምምነቱ፤ ሀገሪቱ ከባሕር በር እና ከወደብ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የጀመረችው ሰላማዊ ጥረት ተጨማሪ ስኬት ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
በአንካራ ስምምነት የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ተገቢ እና ፍትሃዊ መሆኑን ታምኖበታል። ኢትዮጵያ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይዛ እና እ.ኤ.አ በ2030 ወደ 150 ሚሊዮን ሕዝብ ባለቤት ሆና፤ በምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ ገንብታ እና በሚቀጥሉት ዓመታት በዓለም ላይ ከፍተኛ እድገት ከሚያስመዘግቡት ሀገራት ተርታ ተሰልፋ በአንድ ወደብ ላይ ጥገኛ ሆና መቀጠል አትችልም።
አሁን ሀገሪቱ ላይ የባሕር በር ሆነ የወደብ አገልግሎት ጥያቄዋ ፍትሃዊ በመሆኑ ከግብጽ እና መሰሎቿ በስተቀር ሁሉም ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል። ግብጽና መሰሎቿ ግን ቀድሞውኑ ሀገሪቱን የባሕር በር በማሳጣት ሂደት ግንባር ቀደም ከመሆናቸው አኳያ አሁናዊ አቋማቸው ተጠባቂ ነው።
ሀገሪቱ እያደገ የሚሄደውን የሕዝብ ቁጥሯን ለመመገብ እና የኢኮኖሚ ጥያቄዋን ለመመለስ የአማራጭ ወደቦች ባለቤት መሆን አለባት። ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ ሰላማዊ አማራጮችን እየተጠቀመች ነው።
የኢትዮጵያ ጥያቄ መልስ እንዳያገኝ የሚመኙ እና በሕዳሴው ግድብ የተሸነፉ ሀገራት ጉዳዩን የተለየ መልክ በመስጠት በሰላም አስከባሪ ስም ምስራቅ አፍሪካ ድረስ በመምጣት ቀጣናውን የግጭት ማዕከል ለማድረግ እየጣሩ ነው።
እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ያነሱት ጥያቄ ፍትሃዊ ነውና ጥያቄውን በአግባቡ ከመመለስ ውጭ አማራጭ የለም። ኢትዮጵያውያን ያነሱት ትክክለኛ የመልማት እና የማደግ ጥያቄዎች ናቸው። እነዚህን ጥያቄዎች በጭራሽ ማስቆም አይቻልም።
በአንካራው ድርድር ኢትዮጵያ ያሳካችው ሁለተኛው ጉዳይ ከሶማሊ ላንድ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ የሚቀደድ አለመሆኑ ነው። ኢትዮጵያ ከሶማሊ ላንድ ጋር የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ባለበት እንዲቀጥል ስምምነቱ አካቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በአንድ ወቅት በፓርላማ ተገኝተው ይህን ጉዳይ አንስተው እንዳብራሩት ‹‹በኛ እና በሶማሊ ላንድ መካከል የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት ለሁሉም ጎረቤቶቻችን ያቀረብነው ጥያቄ ነው። ሁሉን ለምነን፤ ጠይቀን ምላሽ ስናጣ ከመለሰልን አካል ጋር ተፈራረምን እንጂ ከሶማሊያ አንድነት ጋር የተያያዘ ጥያቄ አይደለም›› ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ከአንካራው ድርድር ኢትዮጵያ ያተረፈች ሶስተኛው ጉዳይ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ያበረከተችው አስተዋጽኦ እውቅና እንዲሰጠው ማድረጓ ነው።
ሶማሊያ ከፍጥረቷ ጀምሮ ባለመረጋጋትና በግጭት ውስጥ የምትኖር ሀገር ነች። ከዚያም አልፎ መንግሥት አልባ ሆና ዘመናትን ተሻግራለች። በእነዚህ የመከራ ዓመታት ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሶማሊያ ሕዝብ ጎን ተለይቶ አያውቅም።
በፊት ‘AMISOM’ አሁን ደግሞ ‘ATMIS’ እየተባለ በሚጠራው የአፍረካ ኅብረት የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ በኩል ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም ጉልህ አስተዋጽኦ ስታደርግ ቆይታለች። በዚህ ተልዕኮም አብዛኛውን የሶማሊያ መሬት በመሸፈንና ከጥቃት በመከላከል የሶማሊያ ሕዝብ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ፤ የሶማሊያ መንግሥትም ተረጋግቶ መንግሥታዊ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።
በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደተናገሩት 60 በመቶ የሚሆነውን የሶማሊያ ክፍል የሚጠብቀውና ከአልሻባብ ጥቃት የሚከላከለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነው።
ኢትዮጵያ በሶማሊያ ጠንካራ መንግሥት እንዲፈጠር መስዋዕትነት ስትከፍል ቆይታለች። አልሻባብ የሁለቱም የጋራ ጠላት መሆኑ ደግሞ ሁለቱ ሀገራት በጋራ እንዲቆሙ የሚያስገድድ ነው።
የኢትዮጵያን የሶማሊያ ግንኙነት ከዚህም በላይ ነው። የሁለቱ ሀገሮች ሕዝቦች በሁለት ሀገሮች የሚኖሩ አንድ ሕዝቦች ናቸው። ዕጣ ፈንታቸው የተሳሰረ ነው። ወደ 16 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ሶማሊያ እ.ኤ.አ. በ2020 ወደ 294 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ሸቀጣ ሸቀጥ ከኢትዮጵያ አስገብታለች። የንግድ ልውውጡም እያደገ እንደሚሄድ ይታመናል።
በአንካራው ድርድር የባሕር በር ጥያቄዋ ፍትሃዊ መሆኑ ታምኖበታል፤ ከሶማሊ ላንድ ጋር የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ባለበት እንዲቀጥል ተወስኗል፤ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሕዝብ እና መንግሥት የዋለችው ውለታ እውቅና እንዲሰጠው እና እንዲዘከር ሆኗል።
በስምምነቱ ዙሪያ በርካታ ተቋማት እና ታዋቂ ፖለቲከኞች ጭምር እውቅና እየሰጡት ነው። የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መንግሥት መካከል የተደረሰውን ስምምነት ከደገፉት ተቋማት አንዱ ነው።
ድርድሩን አስመልክቶ የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ በቱርክ አደራዳሪነት በኢትዮጵያና በሶማሊያ መንግሥት መካከል የተደረሰውን ስምምነት ኢጋድ በአዎንታዊ ጎኑ ይመለከተዋል ብለዋል።
ድርድሩ በሁለቱ እህትማማች ሀገራት መካከል የቆየውን ማህበራዊ ትስስር ለማጠናከር እና የሀገራቱን የሁለትዮሽ ጉዳዮች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል። ወደ መግባባት እንዲደረስ ያደረጉትን የሁለቱን ሀገራት መሪዎች አድንቀዋል። በአፍሪካ ቀንድ የጋራ ችግሮችን ለመፍታት እና ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች አስፈላጊ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ስምምነቱ እንዲፈፀም የሁለቱ ሀገራት መሪዎችን እንዲወያዩ በማድረግ ከፍተኛ ጥረት ላደረጉት የቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን ምስጋና አቅርበዋል። የኢጋድ አባል ሀገራት የሆኑት ኢትዮጵያና ሶማሊያ የደረሱበት ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን እና በሁለቱ ሀገራት መካከል ዘላቂ ትብብር እንዲኖር ኢጋድ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑንም አመልክተዋል።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም