መቼም ቢሆን የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ ነው

የኢትዮጵያ መንግሥት ሀገሪቱን የባሕር በር ባለቤት ለማድረግ እያደረገ ያለው ጥረት የተለያየ ገጽታ እየተሰጠው ሲነሳ እና ሲጣል ሰንብቷል። ጉዳዩ ከውስጥ ትችት አንስቶ የጎረቤት ሀገራት ግልጽ ተቃውሞ አስተናግዷል። ጉዳዩ ላይ ሀሳባቸውን የሚሰነዝሩትን አካላት በሁለት ከፍለን ማየት እንዳለብን ይሰማኛል።

የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑና ኢትዮጵያዊ ሆነው መንግሥትንና ሀገርን መለየት የተሳናቸው ናቸው፤ ሁለተኛዎቹ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ሆነው ነገሩ ግራ ያጋባቸው፤ ለግራ መጋባታቸው ቆም ብለው በሰከነ መንፈስ ማሰብ ተስኗቸው ከራሳቸው አልፈው ሌሎችን ግራ ለማጋባት የሚሞክሩ ናቸው።

ኢትዮጵያዊ ያልሆኑት አካላት በግልጽ የሚታወቅ ዓላማና መዳረሻ አላቸው። መነሻ፣ መጨረሻቸውም ሀገሪቷን እፍኝ ስንዴ እየተወረወረላት ዘላለም በድህነት አረንቋና በብጥብጥ ውስጥ እንድትቆይ ማድረግ ነው። ይህንን የሚያደርጉት ግን ወፈፌ ሆነው ሳይሆን ስጋት እና ጥቅም ስላላቸው ነው።

ለዚህ እንደ ምሳሌ ግብፅን ማንሳት ይቻላል። የግብፅ መንግሥት ጠንካራና ራሷን የቻለች ኢትዮጵያን እንደ ማየት የሚያስፈራው ነገር የለም። ለዚህም ይመስላል የኢትዮጵያ መንግሥት በወደብ ጉዳይ ላይ መንቀሳቀስ ሲጀምር፤ ከሶማሊያ እና ከኤርትራ ጋር የማይዘልቅ ጋብቻ ለመፈጸም ሲዳክር የምናየው።

እንደሚታወቀው ግብፅ የሶማሊያን መንግሥትና ሕዝብ ለመታደግ በሚል ጦሯን ወደ ሀገሪቱ ማስገባቱን እናውቃለን። በአንጻሩ በእሥራኤልና ፍልስጤም ጦርነት የሚሰደዱ ንጹሐንን የግብፅ መንግሥት ወደ ሀገሩ እንዳይገቡ ሰባት አጥር አስቀምጦ እየከለከላቸው ይገኛል። ታዲያ ሰብዓዊነት ለግብፃውያን ምን ማለት ይሆን?

ከእነሱ ቀጥሎ ደግሞ እነ ስም አይጠሬ ጎረቤቶቻችንን ማንሳት ይቻላል። እነሱም እንደ ግብፅ ሁሉ በአንድ ወገን ኢትዮጵያ በሁለት እግሯ መቆም ከቻለች ስጋት ትሆንብናለች በሚል ቅዠት፤ በሌላ በኩል እንዳሻቸው ስደተኛቸውን እኛ ላይ ከመጫን ባለፈ በውስጥ ጉዳያችን ገብተው ለመፈትፈት እንዲመቻቸው ቀና ብለን መቆማችንን በጽኑ ይቃወሙታል።

ጥያቄው መሆን ያለበት እኛ ታዲያ ጉዳዩን እንዴት እናስተናግደው የሚለው ይመስለኛል። እዚህ ላይ እንግዲህ ከላይ ኢትዮጵያዊ ሆነው መንግሥትንና ሀገርን መለየት የተሳናቸው እና ኢትዮጵዊ ሆነው ነገሩ ግራ ያጋባቸው ያልኳቸውን ማየት የሚያስፈልገው።

ኢትዮጵያዊ ሆነው መንግሥትንና ሀገርን መለየት የተሳናቸው አካላት የባሕር በር ጥያቄውን ሲያጣጥሉት እየተመለከትን ነው። አብዛኛዎቹ ይህንን ሲሉ እንደ ምክንያት የሚያነሱት መንግሥት በቅድሚያ ምላሽ ሊሰጣቸው የሚገቡ ሀገራዊ የሕዝብ ጥያቄዎች መኖራቸውን ነው። በእርግጥም መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጣቸው የሚገቡ በርካታ ሀገራዊ ጥያቄዎች እንዳሉ የሚክድ ያለ አይመስለኝም።

የመጀመሪያው ነገር ግን የባሕር በር ጥያቄ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለውስጥ ችግሮቻችን መልስ የሚሰጥ መሆኑ ነው። የህዳሴው ግድብ በተጀመረበት ወቅት በወቅቱ የነበረው ወያኔ መራሹ ኢሕአዴግ የአሁኑንም ያህል ባይሆን በሀገር ልጆች ተመሳሳይ ተቃውሞ አስተናግዶ ነበር። በወቅቱም ሲነሳ የነበረው ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ችግሮች አሉብን የሚል ነበር። ነገሩ በድፍረትና በብልሀት ተጀመረና ከብዙ ውጣውረድ በኋላ ዛሬ ላይ ደረሰ።

በፍጻሜውም በችግር ተኩኖ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ሥራ መሥራት እንደሚቻል የሚያስተምር ድልም ለመሆን በቃ። ከዚህ ቀደም በሌላ ጽሑፌ እንዳሰፈርኩት በእርግጥ ዛሬ የትላንቱ ኢሕአዴግ የለም። ታላቁ የህዳሴ ግድብና ኢትዮጵያውያን ግን ከነሙሉ ተጠቃሚነታቸው አሉ።

ሌላው ኢትዮጵያዊ ሆነው ነገሩ ግራ ያጋባቸው አካላት ደግሞ የሚከተሉትን ነገሮች ሊፈትሹ እንደሚገባ ይሰማኛል። በቅርቡ በነዳጅ አቅርቦት ረገድ የተፈጠሩ ችግሮችን አስመልክቶ የመንግሥት አካላት ከሰጡት ምላሽ ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል ።

«ከዚህ ቀደም ቤንዚን ወደ ሀገር ወስጥ ይገባ የነበረው 80 በመቶ በፖርት ሱዳን ሲሆን፤ ቀሪው ሃያ በመቶ ደግሞ በጅቡቲ በኩል ነው። በአሁኑ ወቅት ግን በሱዳን በኩል ባለው ችግር የተነሳ መቶ በመቶ ቤንዚን እየቀረበ ያለው በጅቡቲ በኩል ነው። የጅቡቲ ያለው ተርሚናል ደግሞ ለዚህ ያህል መጠን የተዘጋጀ አይደለም፤ ችግሩ የተፈጠረውም በዚህ ምክንያት ነው”ብለዋል።

ይህ ክስተት ኢትዮጵያ በአንድ የባሕር በር ላይ ብቻ መንጠልጠሏ የትም እንደማያደርሳት ብቻ ሳይሆን በሠላማዊ መንገድ የተከፈለው መስዋዕትነት ተከፍሎ ራሷ የምታስተዳድረው የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት ያመላከተ ነው። አሁን የጠቀስኩት ችግር በየወቅቱ ሰበብ እየተፈለገ ከሚጨመረው የወደብ አገልግሎት ክፍያ በተጨማሪ ማለት ነው። ወደብ ሲነሳ ደግሞ ነዳጅ ብቻ ሳይሆን ጊዜ ከማይሰጠው የመድኃኒት አቅርቦት ጀምሮ ብዙ የሚያስተናግዳቸው ነገሮች መኖራቸውም ልብ ሊባል ይገባል።

በነገራችን ላይ የባሕር በር ጉዳይ ዘላቂና አስተማማማኝ ምላሽ ሊያገኝ የሚችለው በራስ የሚያስተዳድሩት የባሕር በር ሲኖር ብቻ ነው። ማለትም እንደ የደረቅ ወደብ ግንባታ ያሉ ጊዜያዊ ምላሾች ዘላቂ እና የተረጋጋ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ አይችሉም። ከዚህ ጋር በተያያዘ እንደ ሀገር ያለንን የቆዳ ስፋትና የሕዝብ ብዛት መመልከቱም ተገቢ ይሆናል።

ኢትዮጵያን እንደምናውቃት ሰፊ የቆዳ ስፋት ያላት ብቻ ሳትሆን በጣም ብዙና በየቀኑ የሚጨምር የሕዝብ ብዛትም ያላት ሀገር ናት። ኢኮኖሚያችን ደግሞ ምንም እንኳን በማደግ ላይ ቢሆንም፤ እንደማንኛውም ሀገር ከውጪ የምናስገባው ነገር ያስፈልገናል። ይህንን ሰፊና መሽቶ በነጋ የሚያድግ ፍላጎት በአንድ አማራጭ ብቻ ማስተናገድ የማይታሰብ ነው። በመልክዓ ምድር አቀማመጥም ለባሕር በር እጅግ በጣም ቅርብ ሆነን ባሕር በር የሌለን ብቸኛ አፍሪካዊ ሀገር እኛ ብቻ ሳንሆን አንቀርም።

በመሆኑም በጊዜያዊነት ካልሆነ በቀር የባሕር በር ማግኘታችን ተጠቃሚ የማያደርገው ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብዬ አላምንም። ባጭሩ መንግሥት ይሄዳል ይመጣል፤ ሕዝብ ግን ሁሌም ይኖራል። የባሕር በር ማጣታችን ግን ከግለሰብ እስከተቋማት የማይጎዳው የለም። ዛሬ የባሕር በር እንዳናገኝ የሚሞግቱ ጎረቤቶቻችን በአንድ የባሕር በር ስንዴና መድኃኒት ለማስገባት ስንጋጋጥ እንዳላየ ያልፉንና እነሱ እርስ በእርስ የምንጋጭበትን መሣሪያ በግመል ትከሻ በየጠረፉ ይልኩልናል። ምክንያቱም ሕልማቸው፤ ሥራቸው እኛን ቀና ብለን እንዳንሄድ ማድረግ ነው።

የባሕር በር ጥያቄ ትናንትም… ዛሬም….. ነገም …. በምንም ቀመር በየትኛውም መስፈርት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የቅንጦት ጉዳይ አይደለም የምንለው ለእዚህ ነው። ከውጭም ሆነ ከሀገር ውስጥ “አጀንዳ ለማሳት የተፈጠረች ተረት ተረት ነች” ለሚሉት በቅድሚያ መንግሥት ለምንም ብሎ ይጀምረው እኛ የጉዳዩን ተገቢነት ብቻ ልንፈትሸው ይገባል ለማለት እወዳለሁ።

የባሕር በር ለማግኘት በሚደረግ ሂደት የሚጎዳ ኢትዮጵያዊ አይኖርም። ካለም ተባብረን መታደግ የእኛ ኃላፊነት ይሆናል። እውን መንግሥት የባሕር በር ጥያቄን አቅጣጫ ለማሳት ቢጀምረው እንኳን ከጥቅሙ አኳያ «በአንድ አፍ» ብለን እንዲጨርሰው መደገፍ ሳይሆን ማስገደድ ይጠበቅብናል። ይህ ሁሉ ካልተሳካልን ደግሞ ጥያቄው የሕልውና መሆኑን በመረዳት ለመጪው ትውልድም ለቀጣዩ መንግሥትም የአደራ ውርስ ልናደርገው ይገባል።

ተስፋይ መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You