ለቀጣናው ሠላም እና ልማት ኢትዮጵያ የጀመረችውን ጥረት ማገዝ የግድ ነው!

የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ሕዝቦች ከውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ጋር በተያያዘ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ለማለፍ የተገደዱ ናቸው። ያለፉትን ስድስት አስርተ ዓመታት ለማየት ብንሞክር እንኳን፤ የሀገራቱ ሕዝቦች ታሪክ የሚያጠነጥነው በግጭቶች እና ግጭቶች በሚፈጥሯቸው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች ዙሪያ ነው።

በርግጥ የቀጣናው ሀገራት ሕዝቦች የፀረ ቅኝ ግዛት ትግላቸው በድል በተጠናቀቀ ማግስት ዕድገት እና ብልፅግናን ተመኝተው፣ ለዚህ የሚሆን መነቃቃት መፍጠርም ችለዋል፤ መነቃቃቱ ግን በውጭ ኃይሎች የተጠና ጫና እና ጣልቃ ገብነት ተጠልፎ ፤ አካባቢው ዛሬም ግጭት፣ ድህነት እና ኋላ ቀርነት በሚፈጥሯቸው ውስብስብ ችግሮች እየተፈተነ ይገኛል።

በአንድ በኩል በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈጠሩ የአካባቢውን ሀገራት ሕዝቦች የሚከፋፍሉ ትርክቶች፤ በሌላ በኩል ትርክቶቹ ተጠቃሚ ያደርጉናል በሚል ተስፈኛ የሆኑ፤ በአካባቢው ልዩ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች በሚፈጥሯቸው ውዥንብሮች የቀጣናው ሀገራት ሕዝቦች ዘላቂ ሠላም አግኝተው ወደ ልማት እንዳይመጡ ሆነዋል።

በርግጥ የአካባቢው ሀገራት በተናጠል ካላቸው የተፈጥሮ ፀጋ አንጻር ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች መትረፍ እንደሚችሉ ይታመናል። በተለይም ያላቸውን አቅም አቀናጅተው ለጋራ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መንቀሳቀስ ቢችሉ ፈጣን ሊባል የሚችል ልማት በማስመዝገብ ለሕዝቦቻችው እፎይታ መፍጠር ይችላሉ።

በአካባቢው ካለው የተለያየ መልክዓ-ምድር እና አየር፤ የውሃ እና የማዕድን ሀብት፤ ሰፊ የግጦሽ እና የሚታረስ መሬት፣ የእንስሳት ሀብት እና ለልማት የተነቃቃ ወጣት ኃይል አኳያ አካባቢው በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም ሆኖ መውጣት የሚያስችለው እንደሚሆን ይታመናል።

ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ በቀጣናው ያሉ ሀገራት መሪዎች፣ ሕዝቦቻችውን ወደ ግጭት አዙሪት ከሚከት አክሳሪ አስተሳሰብ ወጥተው፣ እነዚህን አቅሞችን ወደ ተጨባጭ ልማት መቀየር ወደሚያስችል አዲስ የትብብር እና አብሮ የማደግ እሳቤ ማሻገር፤ ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠር ይኖርባቸዋል።

የቀጣናው ሀገራት መሪዎች ላለፉት ስድስት አስርተ ዓመታት የሄዱበት መንገድ፤ የሀገራቱን ሕዝቦች በግጭት አዙሪት ውስጥ ከመክተት እና ያልተገባ ዋጋ ከማስከፈል ያለፈ ያተረፈላቸው ነገር የለም። እያንዳንዱ ግጭትም የሕዝቦቻቸውን በሠላም የመኖር እና በልማት የመለወጥ ሰብዓዊ መብት ከመሸርሸር እና ጠባቂ ከማድረግ ያለፈ ፋይዳ አልነበረውም።

ዛሬም ቢሆን ችግሩ በመሠረታዊነት የአካባቢውን ሀገራት ሕዝቦችን እየተፈታተነ ነው፤ ከውጪ ጣልቃ ገብነት እና ከሀገራት መሪዎች ያልተገባ ባሕሪ አኳያ የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች ሠላም እና የልማት ፍላጎቶች ተጨባጭ መሆን አልቻለም። ከዚያ ይልቅ አካባቢው በግጭት አዙሪት፤ በድህነት እና በኋላ ቀርነት ብዙ ያልተገባ ዋጋ እየከፈለ ነው።

ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት ዋነኛው አቅም ያለው ስለ ሠላም እና ልማት ተስፈኛ በሆነው የቀጣናው ሕዝብ እጅ እንደሆነ ይታመናል። ሕዝቡ አንድም የመሪዎችን ያልተገባ ባሕሪይ በመግራት፤ ከዛም ባለፈ የውጪ ጣልቃ ገብነትን መከላከል የሚያስችል ቁርጠኝነት በመፍጠር የራሱን ዕጣ ፈንታ በራሱ የሚወስንበትን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መጀመር ይኖርበታል። የኢትዮጵያ መንግሥት የጀመራቸውን ጥረቶች ማገዝ የግድ ይሆናል። ከዚህም ባለፈ የአባቶቹን የወንድማማችነት መንፈስ ዳግም ሕይወት እንዲዘራ ማድረግ ይጠበቅበታል።

ከሁሉም በላይ የውጪ ጣልቃ ገብነትን መቋቋም የሚችል ማኅበረሰባዊ ስብዕና መገንባት፤ ጉርብትናንና ከዚያም በላይ ወንድማማችነትን የሚሸከም የትብብር ማሕቀፍ መፍጠር እና ለስኬታማነቱ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ አሁን ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት የጀመራቸውን ጥረቶች ማገዝ የግድ ይሆናል!

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You