‹‹አዲስ አበባን የኮንፈረንስ ማካሄጃ ማማ ማድረግ እንችላለን››  – አቶ ጌትነት ይግዛው ንጉሴ በቱሪዝም ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮ መሪ ሥራ አስፈፃሚ

ትውልዳቸው በጎንደር ከተማ ቸቸላ ተብላ በምትጠራ አካባቢ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በድሮ አጠራሩ ልዕልት ተናኘወርቅ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በደርግ ዘመነ መንግሥት ስሙ ተቀይሮ ህብረት በተባለው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ተምረዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በፋሲለደስ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።

በወቅቱ በፋሲለደስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በነበራቸው የመማር ማስተማር ሂደት መሰረት ከ8ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የምርት ቴክኖሎጂ ተማሪ በመሆን በብረትና በንድፍ ሥራ በተግባር የተፈተነ ትምህርት ተከታትለዋል። በወቅቱ ከአዲስ አበባ የተግባረ ዕድ የሙያ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ጋር አቻ የሆነ የዲፕሎማ ሰርተፍኬት አግኝተዋል።

የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት እ.አ.አ በ1975 ዓ.ም ሲሆን፤ ከዚህ በኋላ የውጭ ትምህርት ዕድል በማግኘታቸው ወደ ምሥራቅ አውሮፓ ቡልጋሪያ በማምራት የቋንቋ ትምህርታቸውን በሲሊቨን ከተማ አጠናቅቀዋል። የትምህርትና የሥራ ዘመናቸውን ለመቀጠል ወደ ተደለደሉበት ከጥቁር ባህር ጥግ ወደምትገኘው የቱሪስት መናኸሪያ የቡርጋስ ከተማ በመሄድ በጀኔራል ኢቫን ቪናሮብ በመባል በተሰየመ ተንቀሳቃሽ የባህር ላይ ጋራዥና ግዙፍ የመርከብ ማምረቻ ፋብሪካ ኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ የትምህርትና የመስክ ስልጠና ሲወስዱ ቆይተዋል።

በቡልጋሪያ በዚህ የትምህርት መስክ ለሦስት ዓመት ተኩል ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ እ.አ.አ በ1977 ዓ.ም አገራችን ውስጥ በነበረው የድርቅና የርሃብ ሁኔታ ሳቢያ በቡልጋሪያ የነበረው ቆይታ ከባድ ሲሆንባቸው ትምህርታቸውን ሳያጠናቅቁ አቋርጠው ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ለመምጣት ተገደዋል።

የጎንደር ከተማ ባህል ሚኒስቴር ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ባወጣው የአብያተ-መንግሥታቱ አስጎብኚነት እ.አ.አ በ1982 የጎንደር አብያተ መንግሥታት አስጎብኚ ሆነው ተቀጥረዋል። አቶ ጌትነት ይግዛው በተለያዩ ጊዜያት ከቱሪዝም፣ ከቅርስ ጥበቃና ከታሪክ ገላጭነት ዘርፍ ጋር በተያያዘ በርካታ ሥራዎችን በመሥራት በፊልም ጭምር የተደገፈ አበርክቶ ያላቸው መሆኑን ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል። በተለይ በሀገር ውስጥ ከተሠሩት ታዋቂው “ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀዳማዊ ስልጣኔ” ዶክሜንተሪ ፊልም ተጠቃሽ ነው።

በኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን፣ በፋና ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንዲሁም በሌሎች የግል ሚዲያዎች በርካታ የዶክመንተሪ ሥራዎችን ለትውልድ ያበረከቱ ሲሆን፤ እንዲሁም ከስመ ገናና ታላላቅ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጋር ከቢቢሲ፣ ከዶቼቬሌ፣ ከቪኦኤ እና ከዲ ኤስ ቲቪ… ጋር የዶክመንተሪ እና የጉዞ ምክር ፊልሞችን አብሮ ለመሥራት በቅተዋል።

ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን፤ በቱሪዝምና ቅርስ አስተዳደርም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘዋል። የጎንደር ፋሲለደስ ቤተመንግሥታት አስጎብኚ በመሆን የተጀመረው ሥራ ጊዜውንና እድገቱን ጠብቆ የዓለም አቀፍ ቅርሱን በአስተዳዳሪነትና በዩኔስኮ የቅርስ ተጠሪ እስከመሆን የዘለቀ ኃላፊነትን ተቀብለው ሠርተዋል።

ዛሬ ደግሞ ከመንግሥት ሥራ በጡረታ ለመገለል ወራቶች ቢቀራቸውም በቱሪዝም ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ በስፋት የተለያዩ ኮንፈረንሶች እየተካሄዱ ናቸው። ዘንድሮ በዓመት ይዘጋጁ የነበሩ 24 ኮንፈረንሶች በሦስት ወራት ብቻ ተካሂደዋል።ኮንፈረንሶች በስፋት እየተካሄዱ ያሉት ለምንድን ነው? የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለማሳደግ ምን መታሰብ እና መሠራት አለበት? ስንል አቶ ጌትነት ይግዛው ንጉሴ ጋር ቆይታ አድርገን የዕለቱ የዘመን እንግዳ እንዲሆኑ አቅርበንላችኋል።

አዲስ ዘመን፡- አሁን በስፋት ኮንፈረንሶች እየተካሄዱ ያሉት ለምንድን ነው?

አቶ ጌትነት፡- በኢትዮጵያ ቱሪዝም 60 ዓመታትን አስቆጥሯል። በዚህም የተለመደ የቱሪዝም የገበያ ሥርዓት አለ። ይሔ የተለመደው የቱሪዝም ሥርዓት ባህላዊ ክዋኔዎችን እና የታሪክ ስፍራዎችን፣ በቁጥር የጎሉ የማይባሉ የተፈጥሮ ቦታዎች ላይ ብቻ በማተኮር የቱሪዝም ምርት አድርጎ የመሸጥ፣ የማስተዋወቅ እና የማልማት ሥራ ሲሠራ ነበር።

ከቱሪዝም ዘርፎች መካከል አንዱን ብቻ መሠረት አድርገን ስንሰራ ስለቆየን ለምን የኮንፈረንስ ቱሪዝም በዛ የሚል ጥያቄ መቅረቡ የሚያስገርም አይደለም። ነገር ግን የቱሪዝም ዘርፍ ብዙ ነው። ከእነዚህ መሀል አንደኛው የኮንፈረንስ ቱሪዝም ነው። ስብሰባዎችን መሠረት ያደረገ (ኤም ሚቲንግ) የሚባል ቱሪዝም አለ። ባለሀብት ቱሪስቶችን የሚስቡ ለቅንጦት የሚሆኑ የቱሪዝም ዘርፎችም አሉ።

ሌላው የሀገር መሪዎች የሚሳተፉበት (ሲ ኮንቬንሽን) አለ። ይህም ያው የቱሪዝም ዘርፍ ነው። ለምሳሌ የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ወይም የተባበሩት መንግሥታት፣ የዓለም የቅርስ ድርጅት፣ የዓለም የገበያ ድርጅት እና የመሳሰሉት በየሦስት ወሩ ወይም በየስድስት ወሩ እና በየዓመቱ የሚካሔደው ስብሰባ ኮንቬንሽን ይባላል። ትልቅ ደረጃ ያለው ሲሆን፤ በጣም አስፈላጊ የሀገር መሪዎች የሚገኙበት ነው።

ሌሎች ደግሞ ኤግዚቢሽኖች እና ሁነቶች አሉ። የጎዳና እና የአዳራሽ ሁነቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ሜዳ ላይ የሚደረጉም አሉ። እነዚህ የቢዝነስ ቱሪዝም ይባላሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን እስከ አሁን ተለምዶ የነበረው የባህል ቱሪዝም ነው። ለስድስት አስርት ዓመታት ታሪካዊ ቦታዎችን ማስጎብኘት እና በመጠኑም ቢሆን የተፈጥሮ ሀብትን ግብ አድርገው የሚመጡ ቱሪስቶችን ማስተናገድ ተለምዷል።

ዘመናዊው የቢዝነስ ቱሪዝም ግን ዘመናዊነትን ይጠይቃል። የሚሳተፈውም ዘመናዊ ቱሪስት ነው። ከተሞች ዘመናዊነትን የተላበሱ እና ያዳበሩ መሆን አለባቸው። የሕብረተሰቡ የባህል እና የኢኮኖሚ አቅም ተለክቶ የሚታወቅ መሆን አለበት። ለጉባኤ አንድ ሺህ ሰው ወይም 700 ሰው አንድ ከተማ ላይ ሲመጣ፤ የከተማዋ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተሳታፊውን መሸከም የሚችል መሆን አለበት። የባህል ሁኔታው፣ የትራፊክ እንቅስቃሴውም ሆነ የመዳረሻ ቦታዎች ተሳታፊውን በአንድ እና በሁለት ሰዓት ውስጥ መሸከም የሚችሉ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ከተማዎች ለዘላቂ ቱሪዝም መሠረት የሚጥሉ መሆን አለባቸው።

የቢዝነስ ቱሪዝም ላይ ቱሪስቱ የሚያስበው የሕይወት ትርፍን መሠረት አድርጎ በመሆኑ ለሚከፍለው ነገር አይጨነቅም። ከተመቸው የቆይታ ጊዜውን ይጨምራል። በዛ ጊዜ ብዙ ገንዘብ ያጠፋል። ቱሪስቱ ገንዘብ በሚያወጣበት ጊዜ ደግሞ ሀገሪቱ ተጠቃሚ ትሆናለች። ቱሪስቱም ገንዘብ በማጥፋቱ አይጨነቅም። የሚያስበው ለእርሱ ሕይወት ደረጃ ምቹ አገልግሎት ስለመኖሩ ብቻ ነው። የቢዝነስ ቱሪዝም ተሳታፊ ኢትዮጵያ ውስጥ ምቹ ካልሆነ ኬንያ፣ ሩዋንዳ ወይም ደቡብ አፍሪካ አልያም ወደ ግብጽ ይሄዳል።

የቢዝነስ ቱሪዝም ሲነሳ ጤናማ የቱሪስት አገልግሎት ሰጥቶ፤ ጤናማ የቱሪስት ገንዘብ ሀገራችን እንዲቀር የዓለም የቱሪዝም ሕግ በሚደነግገው መሠረት ለከፈለው ገንዘብ በሕይወት ደረጃ ልክ አገልግሎት መስጠት የግድ ነው። እንደቤቱ እንዲሰማው ማድረግ መቻል አለብን። ይህን ለማድረግ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች መኖር አለባቸው።

ሆቴሎች ኮከብ መያዛቸው ብቻ ሳይሆን ተመጣጣኝ ትልልቅ አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴሎች መኖር አለባቸው። ለሚከፍለው ገንዘብ ተመጣጣኝ የሆነ አገልግሎት የሚሰጡ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ቱሪስት ለመዝናናት ሲመጣ የሚከፍለው እሳት ውስጥ ተቃጥሎ የሚያመጣውን ገንዘብ ሊሆን ይችላል። በአጭር ወይም በረዥም ጊዜ ተበድሮ የሚከፍለውን ገንዘብ ይዞ መጥቶ ሊሆን ይችላል። በዓመት እና በወር ከሚያገኛት ገንዘብ ቆጥቦ ያጠራቀማት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ በትክክለኛው መልኩ ማስተናገድ እና የቱሪስቱን መብት ማክበር አለብን።

ከተባበሩት መንግሥታት የቱሪዝም ኮንቬንሽን መካከል አንዷ አንቀፅ የቱሪስት መብት መከበር እንዳለበት የሚሳይ ነው። አንቀፅ 29 ውስጥ ቱሪስቱ ለሚከፍለው ገንዘብ ዋጋ መስጠትና ተመጣጣኝ አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻል ያስፈልጋል ይላል። ይህን ማድረግ ሲቻል ቱሪስቱ ብዙ እንዲቆይ ይገደዳል። ብዙ ሲቆይ ብዙ ይበላል። ብዙ ሆቴል ይጠቀማል፤ ለትራንስፖርት ብዙ ይከፍላል። ለአስጎብኚዎች ይከፍላል። ይህ ሕጉን ጠብቆ ጤናማ የቱሪስትን ገንዘብ መሰብሰብ ጥቅሙ ብዙ ነው። ለሀገር የኢኮኖሚ፣ የልማት፣ የገፅታ ግንባታ ፋይዳው የጎላ ነው።

አንድ ቱሪስት ሀገሪቱ ውስጥ መጥቶ ከረካ ለሌሎችም ‹‹ሂዱ ወደ ኢትዮጵያ ምን የመሰለች ሀገር መሰለቻችሁ? ሕዝቡስ ምን ዓይነት ሕዝብ መሰላችሁ? የሰው ገንዘብ የማይፈልግ፤ ባህሉን ያከበረ፤›› ብሎ ያስተዋውቅልናል። ይህ እንዲሆን ለቢዝነስ ቱሪዝም የሚመጡ ሰዎችን መንከባከብ ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን፡- በእርግጥ ለዘመናዊ ቱሪስት ምቹ ሁኔታ ፈጥረናል?

አቶ ጌትነት፡- አንዳንዶቹ የኑሮ ስታንዳርዳቸው በቀን ሁለት ሰዓት ብስክሌት መንዳት ሊሆን ይችላል። ብስክሌት ለመንዳት የሚነዳበት መንገድ መዘጋጀት አለበት። ሞተር መንዳት የሚፈልግ ካለም የሞተር ኮቸር መንገድ መዘጋጀት አለበት። በቀን አንድ ሰዓት በእግር የመራመድ ልማድ ያለው ቱሪስት ሊኖር ይችላል። ስለዚህ በእግር የመንቀሳቀሻ መንገድ ያስፈልጋል።

ከተሞቻችን እንደሚታወቁት በጣሊያን ዘመን የተቆረቆሩ፤ መንገዳቸውም በዛ ዘመን በነበረው የሕዝብ እና የመኪና ቁጥር ልክ ያሉ ናቸው። አሁን ላይ የሕዝብም ሆነ የመኪና ቁጥር እጅግ ጨምሯል። መንገዶቻችን ግን አሁንም ጣሊያን እንደሰጠን የምንላቸው የመኪና መንገድ ነው። የእግረኛም ሆነ የብስክሌት መንገድ የለም። በዊልቸር የሚሔዱ ሰዎች የሚጓዙበት መንገድ የለም። መንገዶቻችን ከብትም መኪናም ሰውም ሁሉም በአንድ ላይ የሚሔድባቸው ናቸው።

አሁን የሚሠራው የከተማ ልማት ይህንን ለማስተካከል ነው። በእርግጥ ውድ እና ብዙ ካሳን የሚያስከፍል ቢሆንም፤ ከፕሮጀክቱ በላይ ገንዘብ የሚጠይቅ ቢሆንም፤ ዳውን ታውን ብለን ሌላ ከተማ መመስረት ቢቻልም፤ ጥንታዊ ከተሞችም ቢሆኑ ለብስክሌት መሔጃ፣ ለሳይክል መሔጃ፣ ለሞተር ብስክሌት መሔጃ፣ ለውልቼር መሔጃ ያስፈልጋቸዋል።

አዲስ አበባ ብቻ ሳትሆን ሌሎችም ከተሞቻችን በዘመናዊነት የተቆረቆሩ ባለመሆናቸው የመኖሪያ ዞን፣ የጤና ዞን፣ የማህበራዊ አገልግሎት ዞን የሚገኝባቸው

አይደሉም። ስለዚህ ከተሞቻችንን አፍርሰን ለመሥራት ተገደናል።

አዲስ ዘመን፡- በዋናነት የኮንፈረንስ ቱሪዝም እንዲስፋፋ ምን መሠራት አለበት?

አቶ ጌትነት፡- በቀጣይም አዲስ አበባ የቢዝነስ ቱሪዝም፣ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል መሆን አለባት ብለን እናስባለን። እስከ አሁን ድረስ በአፍሪካ ቀዳሚውን ቦታ የያዘችው ደቡብ አፍሪካ ናት። በመቀጠል ሩዋንዳ ናት። ሩዋንዳ ከዛ ሁሉ መከራ ወጥታ ዛሬ የቱሪስት መናኸሪያ መሆን ችላለች። እነርሱ ላይ ለመድረስ አንደኛ በሕግ አግባብ ለመንቀሳቀስ ተቋም ያስፈልጋል። ይህንን ለመስራት በቱሪዝም ሚኒስቴር ሥር የኮንቬንሽን ቢሮ ተመስርቷል።

ኬንያ ውስጥ የኮንቬንሽን ቢሮ ከ50ሺህ እስከ 60ሺህ ሠራተኞችን የሚያስተናግድ ነው። ዓመታዊ የኮንቬንሽን ሥራ የሚሠራበት የራሱ ማዕከል አለው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ግን ይለያል። የኮንቬንሽን ሥራ ላይ ማተኮር ሀገራዊ የቱሪዝም ዕድገት ከዘጠና በመቶ በላይ ከፍ እንዲል አስተዋፅኦ ማድረግ ይችላል። ስለዚህ ኢትዮጵያ በሀገር ደረጃ ተነሳሽነቱን ወስዳ በዚህ ዙሪያ በስፋት እየሠራች ያለችው ለዚህ ነው።

በ2016 ዓ.ም በዓመት ውስጥ 24 ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ተካሂደዋል። በ2017 ዓ.ም ግን በሩብ ዓመት ውስጥ ወደ 27 ጉባኤዎች ተዘጋጅተዋል። በዚህ ዓመት ብቻ ወደ 100 ጉባኤዎች ይስተናገዳሉ ብለን እንጠብቃለን። ስለዚህ አዲስ አበባ የእነዚህ ጉባኤዎች ተሳታፊ እንግዶች በሰላም መጥተው በሰላም እንዲሔዱ፤ ያመጡትን ገንዘብ እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲያስቀሩ፤ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ቦታዎቻችንን ጎብኝተው እንዲሄዱ የማድረግ፤ አዳዲስ የመዳረሻ ልማቶችን፣ የሸገር ልማቶችን፣ ገበታ ለሀገርን ጎብኝተው እንዲሄዱ ለማነቃቃት ሠርታለች፤ ወደ ፊትም ትሠራለች።

እ.አ.አ ከ2024 እስከ 2027 አዲስ አበባ ተለይተው የወጡ ወደ 290 የሚሆኑ ሁነቶችን ታስተናግዳለች ተብሎ ይታሰባል። እነኚህ ሁነቶች የሚካሄዱት በቱሪዝም ሚኒስቴር ብቻ አይደለም። እያንዳንዱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የየራሱን ወስዷል። የሴቶች ጉዳይ በሴቶች ተቋም፣ የግብርና ጉዳይ በግብርና ሚኒስቴር፣ የመከላከያ ሃሳብ በመከላከያ ሚኒስቴር ፣ የፍትሕ ጉዳይ በፍትሕ ሚኒስቴር ዓለም አቀፍ በዓሎች፣ ቀኖችን፣ መታሰቢያ ጉባኤዎች፣ ኤግዚቢሽኖችን ሁሉም በየበኩሉ ያዘጋጃል።

እያንዳንዱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ከስድስት እስከ ሰላሳ የሚደርሱ ሁነቶችን ለማዘጋጀት ዕቅድ ወስዷል። ይሔ ፕሮግራም ካላንደር ላይ ወጥቶ ተበትኗል። ሰሞኑንም የትራንስፖርት ሚኒስቴር ይኸው ፕሮግራም ተሰጥቶት ነበር። አረንጓዴ ኢኮኖሚን መሠረት አድርጎ በዓለም የሚመረቱ መኪናዎች ላይ ያተኮረ ሁነት በትራንስፖርት ሚኒስቴር አማካኝነት ተካሂዷል። በዚህም የገበያ ትስስሮች ይፈጠራሉ። ጭስ የማያወጣ መኪና የአየር ብክለትን ለመከላከል፣ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለማዳበር አሁን እየተፈጠሩ ያሉ በረሃማነትን ለመቀነስ ያለው ፋይዳ ተንሸራሽሯል።

የአፍሪካ የመሠረተ ልማት ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እና አመራሮች በአፍሪካ ኅብረት አማካኝነት ስብሰባዎች አካሂደዋል። ስለዚህ 700 ሰው በአንድነት በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ መታደም ማለት፤ ሆቴሎች እና ሎሎችም በቱሪዝም ዘርፍ ላይ የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። እስከ 2027 ወደ 290 ጉባኤዎች ማስተናገድ እንደ ዕቅድ ይያዝ እንጂ ከዛም በላይ ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- ይህንን ለማለት ያነሳሳዎ አሁን ያለው ሁኔታ ለኮንቬንሽን ምቹ በመሆኑ ነው?

አቶ ጌትነት፡- አዎ! ነገር ግን ኢትዮጵያ የራሷ ብሔራዊ የኤግዚቢሽንና የኮንቬንሽን ማዕከል ያስፈልጋታል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህንን ሥራ እየሠራ ነው። የፌዴራል መንግሥት የኮንቬንሽን ቢሮ በአዋጅ ደረጃ መጥቶ ይሔን ብቻ የሚሠራ ተቋም ተቋቁሟል። በቀጣይ የሕግ ሥርዓቱ አልቆ ለብቻው ተቋም ሆኖ ይወጣል የሚል እምነት አለኝ። ስለዚህ የኢትዮጵያን ቱሪዝም ለማሳደግ ከታሪካዊ፣ ከባሕላዊ እና ከተፈጥሯዊ መዳረሻ ባሻገር፤ የቢዝነስ ቱሪዝም መስተናገድ አለበት። ለዚህም ብዙ ዕድሎች አሉ።

በተጨማሪ አዲስ አበባ ውስጥ ወደ 134 አካባቢ ኤምባሲ ጽሕፈት ቤቶች አሉ። የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ናት። የኢሲኤ ማዕከል ናት፤ በተባበሩት መንግሥታት ሥር ያሉ የዩኔስኮ፣ የዓለም የንግድ ድርጅት፣ የሴቭ ዘ ችልድረን እና የመሳሰሉት ቢሮች አሉ። ይህ እንደመልካም አጋጣሚ የሚወሰድ ነው። ይህንን የቢዝነስ ቱሪዝም ለማስፋፋት ስለሚቻል፤ እነዚህን ተጠቅመን ብንዘገይም መነሳታችን ጥሩ ነው።

መንግሥት፣ መገናኛ ብዙኃን እና የግል ዘርፍ ሁሉም ዘመናዊ ቱሪዝምን ለማሳደግ መረባረብ ይገባቸዋል። በአንድ ቱሪዝም ውስጥ ተወስና የነበረችውን ሀገር በዘመናዊ መልኩ ወደ ቢዝነስ ቱሪዝም በማምጣት በስፋት ቱሪስቶችን ማስተናገድ መቻል አለብን። ከዚህ በኋላ ሀገር ሰላም ከሆነች፤ የገፅታ ግንባታ ላይ በደንብ ከሠራን አዲስ አበባ ብቻ ሳትሆን ሌሎች ከተሞች ላይም ቢዝነስ ቱሪዝምን በማስፋፋት ኢትዮጵያ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ዲክሽነሪ የርሃብ፣ የጦርነት እና የፖለቲካ ምሳሌ የሆነችበትን ሁኔታ መቀየር እንችላለን።

ከዚህ በፊት የነበሩት በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገቡትን ቦታዎች ለ60 ዓመታት ተጠቅመንባቸዋል። አሁን ደግሞ በአዲስ መልክ ገበታ ለሸገር እና ገበታ ለሀገር እነጎርጎራን እና ወንጪን የመሳሰሉትን እያዳበርን እያሰፋን ተቋማዊ እያደረግን ዘመናዊ ቱሪዝምን ለቀጣይ ትውልድ የምናሻግራቸው አድርጎ መፈፀም ይገባል።

ይህ በአንድ በተወሰነ ቱሪዝም ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ዘርፈ ብዙ የቱሪዝም ሥራዎች ላይ በመሠማራት ገፅታችንን መገንባት ይገባናል። ከቱሪዝም በስፋት አትራፊ የሆነች ሀገር መገንባት ያስፈልገናል።

አዲስ ዘመን፡- ቱሪዝምን ለማሳደግ በብዙ መልኩ መታሰብ እንዳለበት ሲገልጹ፤ ለተገቢው ክፍያ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል። ከዚህ አንፃር ምን ታዝበዋል?

አቶ ጌትነት፡- ነገ የፈለግንበት ላይ ለመድረስ ዛሬ መሥራት ያስፈልጋል። ገንዘብ የመግባቢያ መሣሪያ ነው። ከፍላጎታችን ጋር የሚያገናኘን መሳሪያ ብር ነው። ይህ የመግባቢያ መሳሪያ እስካልተቀየረ ደረስ የህይወት አካላችን ነው። የኢትዮጵያ የሆቴል አገልግሎት ሰጪነት ታሪክ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። በፊት እንደ አሁኑ ላይ በመላ ሀገሪቱ በሺህ የሚቆጠሩ ባለኮከብ ሆቴሎች በአዲስ አበባ ደረጃ ደግሞ ወደ 260 የሚጠጉ ባለኮከብ ሆቴሎች አልነበሩንም። አሁን ግን እነኚህ ሁሉ አሉን።

የመጀመሪያው የሆቴሎች ኮከብ አሰጣጥ የቴክኒክ ኮሚቴ አባል ነበርኩኝ። በዚህ ዘርፍ ላይ ወደ 35 ዓመት ሠርቻለሁ። ኮከብ ሲሰጥ አሜሪካን ካለው ባለኮከብ ሆቴል ጋር ተመሳሳይ ነው። አሜሪካን ሆቴል ውስጥ ለሚሰጠው አገልግሎት የሚከፈለው ገንዘብ እና ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ባለኮከብ ሆቴል ለሚሰጠው አገልግሎት የሚከፈለው ገንዘብ በዓለም አቀፉ የቱሪዝም ድርጅት ሕግ መሠረት አንድ ዓይነት መሆን አለበት። 250 ዶላር ከሆነ፤ ሁለቱም ሀገር ላይ ክፍያው ተመሳሳይ መሆን አለበት። ሁለቱም ባለሦስት ኮከብ ከሆኑ ሁለቱም ጋር ክፍያው ብቻ ሳይሆን አገልግሎቶቹ ተመሳሳይ መሆን አለባቸው።

ኮከብ ስንሰጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በመስፈርቱ መሠረት ሆቴሎች ማግኘት አልቻልንም። ሸራተን አዲስ ትልቁ ሆቴላችን ቢሆንም፤ በሰዓቱ የነበረው ዲፓርትመንት አስራ አንድ ብቻ ነበር። ባለአንድ ኮከብ ሆቴል መስፈርቱ ቢያንስ 12 ዲፓርትመንት ሊኖረው ይገባል። ከዛ በታች ከሆነ አንዱን ሙያ አንዱ ዲፓርትመንት በተደራቢነት ይሠራል ማለት ነው። ሸራተን ሲለካ ከሁለት እና ከሦስት ኮከብ ማለፍ አልቻለም። ሂልተንም ሁለት ኮከብ ብቻ ሆነ።

በኢትዮጵያ ትልልቅ አሉ የምንላቸው ሆቴሎች እንደዛ ከሆኑ፤ ምን ሊፈጠር ይችላል? ብለን ተጨነቅን። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ባለኮከብ ሆቴል የላትም ከተባለ የአፍሪካ ኅብረት ተሳታፊዎች እና ቱሪስቶች ኢትዮጵያ ውስጥ አያድሩም ማለት ነው። ባለኮከብ ሆቴል የለም ማለት፤ ቱሪስቱ ለከፈለው ገንዘብ ተገቢውን አገልግሎት አያገኝም ማለት ነው።

እ.አ.አ በ1976 ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የቱሪዝም ድርጅት የኮንቬንሽንን ፈርማለች። እ.አ.አ. በ1974 ደግሞ የዩኔስኮ ፈራሚ ናት። እነዚህን ሕጎች ደግሞ ከራሷ ሕግ ጋር አቆራኝታ ዓለም አቀፍ ሕግን በሀገሯ ደረጃ መተግበር ግዴታዋ ነው። ስለዚህ ባለኮከብ ሆቴል የለም ማለት ገበያዋን መስበር ነው። ሆቴሎቻችን ደግሞ ኮከብን እስከ ወሰዱ ድረስ ከአሜሪካ ሆቴሎች ጋር መወዳደር አለባቸው።

የሆቴሉ አንድ ክፍል የኤሌክትሪካል ኢንጂነር፣ የውሃ ኢንጂነር እና ሌሎችም ኢንጂነሮች እንዲኖሩት ይጠበቃል። አልጋው ስፋቱ፣ የክፍሉ ቀለም፣ የአልጋው አቀማመጡ ምን ዓይነት ነው? ማብሪያና ማጥፊያዎቹ በምን በኩል ናቸው? አምፖሉ ስንት ቮልት ነው? የሽንት ቤት መጠቀሚያው፤ ገላ መታጠቢያው እያንዳንዱ ይታያል። ሲንኩ እንዴት ነው? ለአንድ ክፍል ብቻ በጣም ብዙ ኢንጂነር ያስፈልገዋል። ስለዚህ ጊዜ ተሰጥቷቸው አስተካክለዋል? አላስተካከሉም የሚለው በክትትል ተጣርቶ በሂደት እየተስተካከለ ሔዷል።

አዲስ ዘመን፡- አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሆቴሎች የሚጠበቅባቸውን ደረጃ ያሟሉ ናቸው ብሎ መናገር ይቻላል?

አቶ ጌትነት፡- ኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም አንድ ባህል አለ። ባለሙያውና ባለሀብቱ ፍቅር የላቸውም። አይተማመኑም። ባለሆቴሎች የሚቀጥሩት ባለሙያውን ሳይሆን ዘመዳቸውን ነው። የሚቀጥሩት በባህል ያወቀውን ሳይሆን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የተማረውን ሊሆን ይገባል። ዓለም አቀፍ የሆቴል አገልግሎት ደረጃን ያወቀ ባለሙያ መሆን አለበት።

ባለሙያው ከዩኒቨርሲቲ የተመረቀ መሆን መቻል አለበት። ዘመዴ ስለሆነ እንግዳዬን አይወስድብኝም ብሎ በልምድ የሚያስተዳድረውን መቅጠር ከቀጠለ አገልግሎቱ ደረጃውን የጠበቀ አይሆንም። ባለሙያ ብቻ አይደለም፤ አጠቃላይ ሆቴሉ ከማብሰያው እሳት ቢነሳ የእሳት አደጋ ማጥፊያ አለው? ማብሰያው የተሟላ ነው? የሚጠቀመው ዘይት ምን ዓይነት ነው? ምግቡ የተፈጥሮ ነው ወይስ የተዳቀለ? ምግብ አብሳዮቹ የሚለብሱት ልብስ ምን ዓይነት ነው? ቅንድብ እንኳ በየደቂቃው ይሠበራል። ሰው ይህንን ለማረጋገጥ የሚያነበው መጽሐፍ ውስጥ ምን ያህል ፀጉር እንዳለው ማየት ይቻላል። ባተኮርን ቁጥር ቅንድባችን ይነጫል፤ ጨጓራ ደግሞ ከማይፈጫቸው ነገር ውስጥ ትልቁ ፀጉር ነው። ማብሰያ ክፍል ፀጉር ሳይሸፈን ሰዎች መግባት የለባቸውም።

አስተናጋጆችም ምግብ ይዘው ሲሄዱ መጠንቀቅ አለባቸው። ጓንት እና ማክስ መጠቀም ያስፈልጋል። እጅ በአንድ ሰዓት ውስጥ አንድ ሺህ አምስት መቶ ጊዜ ወደ ፊት እንደሚሔድ ጥናቶች ያሳያሉ። እጅ የማይነካው ነገር የለም። ይህንን ሁሉ ሳይንሳዊ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። እንመርምር ካልን መሻሻል ያለበት ነገር ብዙ ነው።

ቀደም ሲል የዓለም የቱሪዝም ድርጅት ሂልተን እና ሸራተንን አይቷቸው ነበር። አሜሪካን ውስጥ አንድ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል እጅግ ትልቅ ከመሆኑ ብዛት ሠራተኞቹ ሚሊዮን ሊደርሱ ይችላሉ።ሁሉም አገልግሎቶች እዛው ሆቴሉ ውስጥ ተሟልተው ይገኛሉ። ለመኪና ዘይት መግዛት፣ መድኃኒት ለመግዛት፣ ምርመራ ለማድረግ፣ መኪናን ጋራዥ ለመውሰድ፣ የትኛውም አገልግሎት እዛው ሆቴል ውስጥ አለ። እኛ ሀገር በ100ሺህ የሚቆጠር ሠራተኛ ያላቸው ምን ያህል ሆቴሎች አሉ? የሚለው ያጠያይቃል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመጡት በዕድሜ የገፉ የቻይና፣ የጣሊያን፣ የአሜሪካ እና የእስራኤል ቱሪስቶች ናቸው። እነርሱ ቢመጡም ብዙ ገንዘብ ይዘው አይመጡም። 15ሺህ ዶላር ይዘው ይመጡና የ20 ብር ሽሮ ቤት ይፈልጋሉ። ነገር ግን ከዛ ይልቅ ስለአገልግሎቱ የሚጨነቁ ስለገንዘብ የማይጨነቁ ቱሪስቶችን ማስተናገድ አለብን። ይህ እንዲሆን አሁን የተወሰኑ ለውጦች አሉ። በአንድ ሌሊት ባቢሎን አልተገነባችም። በቀጣይ ትልቅ የተቋም ግንባታ ያስፈልገናል።

አዲስ ዘመን፡- ቱሪዝም ዘርፍ ላይ ዘመኑን እንዳሳለፈ ባለሙያ ዘመናዊ ቱሪስት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ምን መሠራት አለበት?

አቶ ጌትነት፡- ለአንድ ተቋም ትልቅ መሠረቱ የሕግ አግባብ ነው። የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮ መቋቋም፤ የኮንቬንሽን ማዕከል መገንባት አለበት። ይህ ትልቅ ጥቅም አለው። ሌላው ሥርዓት ነው። ተቋሙ ብቻውን ሆኖ ምንም አይሠራም። መዋቅር ያስፈልገዋል። ፈጣሪ ለሰው ጭንቅላት አንገት እጅ እግር ብሎ እንዳስቀመጠው፤ የእያንዳንዱ ሥራ መለየት እና ትክክለኛውን ባለሙያ ማስቀመጥ ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ የዓለም የሲቪል ሰርቪስ ኮንቬንሽን ፈራሚ ናት። ያንን ያከበረ ትክክለኛ ባለሙያ በትክክለኛው ቦታ መቀመጥ አለበት። ሕግ፣ ሥርዓት ወይም መዋቅር እና ሰው ብቻቸውን ምንም አይሠሩም። ሰው ሆነን እንድንራመድ የሚያደርገን ነገር ደም ነው። የተቋም ደም ደግሞ በቂ በጀት ነው። ማሰራት የሚችል፤ ከሌብነት የፀዳ በግልፅ የሚሰላ የገቢ ምንጭ ያስፈልጋል። ከዚህ በኋላ የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረዥም ጊዜ ስልጠናዎችን መስጠት ያስፈልጋል።

ልምዶችን ማሰባሰብ እና ማብዛት ያስፈልጋል።ለምን ደቡብ አፍሪካ አንደኛ ሆነች? እንዴት ሩዋንዳ ተከተለች? ለምን ከአሜሪካ፣ ከፈረንሳይ፣ ከእንግሊዝ ጋር እኩል አልሆንም? የሰው ልጅ የደረሰበትንም ይዘን መቅረብ አለብን። ለዛ የጥቅማ ጥቅም ፓኬጆችን ማስፋት ይጠበቅብናል። ተቋም ማለት ሀገር ነው። 22 ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አሉ። የኢትዮጵያን እድገት የሚወስኑት እነዚህ ናቸው። ሕዝብ እንደሕዝብ ከዓለም ሕዝብ ጋር የሚያሰልፉት ከእነ ተጠሪ ተቋማቸው እነዚህ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ናቸው።

ቱሪዝም የአንድ የመንግሥት ተቋም ሥራ አይደለም። በቱሪዝም፣ በማስተዋወቅ፣ በግል ዘርፉ በማህበራት መካከል የሚደረግ የኢኮኖሚ የማህበራዊ የሥነምህዳራዊ ሌላው ቀርቶ የፖለቲካው ልውውጥ ነው። እነዚህ በመተባበር ሀገርን መሥራት ይቻላል። ሀገራችንን በቱሪዝም ዘርፍ ልንሠራት የምንችለው በጋራ ነው። ሁሉም ድርሻ አለው። ሁሉም ከሠራ አዲስ አበባን የኮንፈረንስ ማማ ማድረግ እንችላለን። በርካታ ጉባኤዎችን፣ ኤግዚቢሽኖችን እንዲሁም ኮንቬንሽኖችን ማስተናገጃ ትሆናለች። ከዘርፉ የምናገኘው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ሥነምህዳራዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅም የተሻለ ይሆናል። ይህ የሚገኘው ኢኮኖሚው፣ ፖለቲካው፣ ማህበራዊው እና ቴክኖሎጂው ያደገ ሲሆን ነው። በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሀገራዊ ምርትና ምርታማነት ማምጣት ስንችል ነው። ያለበለዚያ ውጤታማ ለመሆን ያዳግተናል።

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሠግናለሁ።

አቶ ጌትነት፡- እኔም አመሠግናለሁ።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You