አዲስ አበባ፡- ኤርትራውያን ስደተኞች በኢትዮጵያ አላግባብ ክፍያ እየተጠየቁና ዲፖርት እየተደረጉ ነው በሚል የሚሰራጨው መረጃ ሐሰተኛ ነው ሲል የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በኢትዮጵያ የሕግ ጥሰት የፈፀሙ የውጭ ዜጎችን በተመለከተ ትናንት በሰጠው ማብራሪያ እንደገለጸው፥ ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ ጥላ ከለላ መሆን የቆየ ታሪኳና ባሕሏ እንደሆነና የኤርትራ ዜግነት ያላቸው ስደተኞችን ጨምሮ የበርካታ ሀገራት ዜጎች በጥገኝነት ይገኛሉ። በመሆኑም በስደተኝነት የተመዘገበ ማንኛውም የኤርትራዊ ዜግነት ያለው ሰው ያለ ፈቃዱ ከሀገር እንዲወጣ እና ተገቢነት የሌለው ክፍያ እንዲከፍል የተደረገ ሰው የሌለ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን ብሏል።
እውነታው ይህን ሆኖ እያለ በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ያለ አግባብ ክፍያና ዲፖርቴሽን እንደሚፈጸምባቸው ተደርጎ መዘገቡ ከእውነት የራቀ ነው ያለው መግለጫው፤ መንግሥት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለው መልካም ጉርብትናና ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ካለው ቁርጠኛ አቋም በድንበር አካባቢ ከሚደረጉ ነፃ የሰዎች እንቅስቃሴ መፍቀድ በተጨማሪ መግቢያ ቪዛ ሳይጠየቁ በቀን ማኅተም (ያለ ቪዛ ከፍያ) ገብተው ለ90 ቀናት እንዲቆዩ መፍቀዱ ይታወቃል ሲል ገልጿል።
በተለይ ከኤርትራ (አሥመራ ወደ አዲስ ኣበባ ኢትዮጵያ) የሚመጡ ኤርትራውያን ለ90 ቀናት ያለ ቪዛ ክፍያ በቀን ማኅተም ገብተው እንዲቆዩ ማድረጉ በሁለቱም ሕዝቦች መካከል ያለው ግንኙነትና ወንድማማችነት ለማጠናከር ምን ያህል ቁርጠኛ አቋም እንዳለው ለመገንዘብ ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኤርትራውያን ስደተኞች በጥገኝነት እንደሚኖሩ ይታወቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ ሚዲያዎች በተሳሳተ፣ ሚዛኑን ባልጠበቀ እና ኃላፊነት በጎደለው አግባብ ተቋማችን ኤርትራዊ ዜግነት ያላቸውን ሰዎች የተለየ በደል እና አድልዎ እየፈጸመባቸው እንደሆነ፣ ለመውጪያ ቪዛ የተጋነነ ክፍያ እንደሚጠየቁ፣ በስደተኝነት የተመዘገቡ ኤርትራውያን ዲፖርት እየተደረጉ እንደሆነ አድርገው ሲዘግቡ ተስተውሏል ያለው ማብራሪያው፤ በርካታ የውጭ ሀገር ሰዎች በሕገወጥ መንገድ ድንበር ጥሰው ወደ ኢትዮጵያ በመግባትና ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ ሀገር ውስጥ ሲቆዩ
የሚስተዋሉ ሲሆን፣ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የውጭ ሀገር ሰዎች የሥራ ፈቃድና መኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው ባልተፈቀደላቸው የሥራ መስክ ከመሰማራት ጀምሮ በሕገወጥ የማዕድን ዝውውር፣ በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ በአደገኛ እፅ ዝውውር፣ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በኮንትሮባንድ፣ በሐሰተኛ ሰነዶች ዝግጅት ወዘተ የመሳሰሉ የሀገራችን ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት የሚጎዱ ተግባራት ላይ በመሰማራት ከባድ እና የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ሲፈፅሙ መገኘታቸውን ማረጋገጥ ችለናል ብሏል።
በተለይ በርካታ ኤርትራውያን በሕገወጥ መንገድ ወደ ሀገር በመግባትና በሕጋዊ መንገድ ገብተው ከተፈቀደላቸው የጊዜ ገደብ በላይ በመቆየት በሕገ-ወጥ መንገድ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ይታወቃል። የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እነዚህን አካላት ወደ ሕጋዊ መንገድ ለማስገባትና ለመመዝገብ በተደጋጋሚ ጥሪ ማድረጉ የሚታወቅ ቢሆንም ተመዝግበው ወደ ሕጋዊ ሥርዓቱ የገቡ ግን በጣም ጥቂት ናቸው ነው ያለው።
ስለሆነም የሀገርን ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም በሚጎዳ መልኩ ሕገ ወጥ ተግባር ላይ ተሠማርተው የሚገኙ የውጭ ሀገር ዜጎች በተመለከተ የሚከተሉትን ነጥቦች ማጉላት አስፈላጊ ነው ያለው የአገልግሎቱ ማብራሪያ፤ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድና የሥራ ፈቃድ ሳይኖራቸው ሐሰተኛ ወይም የተጭበረበረ ማንነት በመያዝ ለውጭ ሀገር ዜጎች ባልተፈቀዱ የሥራ መስኮች በመሰማራት በሕገወጥ መንገድ ከትንሽ ሱቅ ችርቻሮ እስከ ያልተፈቀዱ ትላልቅ ሥራዎች ተሰማርተው መገኘታቸውን ገልጿል።
በርካታ የኤርትራዊ ዜግነት ያላቸው ዘመድ ለመጠየቅ በማስመስል ከዱባይ፣ ከኤርትራ፣ ከዑጋንዳ በመመላለስ የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦች በሻንጣ በማስገባትና በማስወጣት የኮንትሮባንድ እና ሌሎች ሕገወጥ ተግባራት ሲያከናውኑ ተገኝቷል።
በተለያዩ ሀገራት ከሚገኙ ሌሎች ሕገ-ወጥ ደላሎች ጋር በመተሳሰር በርካታ ፍልሰተኞችን በሕገ-ወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩና በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ሲያከናውኑ ተገኝቷል።
ለተለያዩ ሕገወጥ ተግባራት የሚያገለገሉ ሐሰተኛና የተጭበረበሩ የጉዞና የይለፍ ሰነዶች፣ ማኅተሞች፣ የባንክ ቡኮች በማዘጋጀትና በመጠቀም ሕገ-ወጥ ተግባራት ሲፈጽሙ ተገኝተዋል።
የተለያዩ ሐሰተኛ ሰነድና ማንነት በመጠቀም ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ሲያከናውኑ እና ከሕግ ውጭ ሰነዶችን ሲጠቀሙ መገኘታቸው።
ስለዚህ ማንኛውም የውጭ ሀገር ዜጋ የሀገራችንን ሕግ ተላልፎ ከተገኘ በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆን ይታወቃል።
በመሆኑም ሕጉ ተፈጻሚ የሚሆነው በሁሉም የሚመለከታቸው የውጭ ሀገር ሰዎች እንጂ በአንድ ሀገር ዜጋ ብቻ ተፈጻሚ የሚደርግ አሠራር ተደርጎ በአንድ አንድ ሚዲያዎች መዘገቡ ስህተት ነው።
ስለሆነም ለኤርትራውያን ዜጎች እንደማንኛውም የጎረቤት ሀገር ዜጎች በቀን ማኅተም ገብቶ በተፈቀደለት የጊዜ ገደብ (90) ቀናት ቆይቶ ለሚሔድ ሰው ምንም ዓይነት የቪዛ ክፍያ እንደማይጠየቅ ለመግለጽ እንወዳለን።
ከተፈቀደለት የጊዜ ገደብ ቆይተው የሚጣልባቸው ቅጣት ቢሆንም የኤርትራ ዜግነት ያላቸው ሰዎችን ጨምሮ ለጎረቤት ሀገራት እንዲከፍሉት የሚጠየቀው ክፍያ በእጅጉ (በ200 በመቶ) የቀነሰ ሆኖ እያለ ለኤርትራውያን የተለየና የተጋነነ ክፍያ እንደሚጠየቁ ተደርጎ መዘገቡ ከእውነታ የራቀ ነው።
በተመሳሳይ መልኩ ኤርትራውያን ስደተኞችን በተመለከተም ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ ጥላ ከለላ መሆን የቆየ ታሪኳና ባሕሏ እንደሆነና የኤርትራ ዜግነት ያላቸው ስደተኞችን ጨምሮ የበርካታ ሀገራት ዜጎች በጥገኝነት እንደሚገኙ ይታወቃል።
በመሆኑም በስደተኝነት የተመዘገበ ማንኛውም የኤርትራዊ ዜግነት ያለው ሰው ያለ ፈቃዱ ከሀገር እንዲወጣ እና ተገቢነት የሌለው ክፍያ እንዲከፍል የተደረገ ሰው የሌለ መሆኑን አስታውቆ፤ እውነታው ይህን ሆኖ እያለ በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ያለ አግባብ ክፍያና ዲፖርቴሸን እንደሚፈጸምባቸው ተደርጎ መዘገቡ ከእውነት የራቀ ነው ሲል አስገንዝቧል።
የሀገራችንን ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም በመጠበቅ ሕጋዊ የውጭ ሀገር ሰዎች እንቅስቃሴን ለማረጋገጥ ለሚሠራው ሥራ ላይ ሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻና ተባባሪ አካላት ከጎናችን እንዲቆሙ ጥሪያችን እያቀረብን በተለይ ሚዲያዎች ሚዛናዊ በመሆን የሀገራችንን ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም በጠበቀ መልኩ አወንታዊ ሚና እንዲወጡ እናሳስባለን ሲል አስታውቋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም