– የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በመጪው ወር ሥራውን በይፋ ይጀምራል
አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ለመንግሥትና ለግል ዘርፉ የገንዘብ ምንጭ በመሆን ለምጣኔ ሀብት እድገት ጉልህ አስተዋፅዖ እንደሚያደርግ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) ገለጹ። ገበያው ከመጪው ጥር ወር 2017 ጀምሮ በይፋ ሥራ እንደሚጀምር ተጠቁሟል።
ተቋሙ ሥራ መጀመር የሚያስችለውን ካፒታል የማሰባሰብ፤ የሰው ኃይል የማደራጀት፣ የገበያውን መተዳደሪያ ደንቦች የማዘጋጀትና ለሕዝብ የማስተዋወቅ እንዲህም የገበያውን ቴክኖሎጂ ግዥ የመፈፀም ተግባር ማከናወኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በካፒታል ገበያዎች መሠረት በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ከአንድ ዓመት በፊት በጋራ ተቋቁሟል ያሉት ጥላሁን (ዶ/ር)፤ ለመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የገንዘብ ምንጭ በመሆን ለምጣኔ ሀብት እድገት ጉልህ አስተዋፅዖ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያን ለማስጀመር የሚያስችሉ አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ገልጸው፤ መንግሥት በየዓመቱ 300 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ገንዘብ ይበደራል። የብድሩን ክፍያም ይፈጽማል። ከዚህ አንፃር ለገበያው መሠረት የሚሆን የእዳ ሰነድ ከመንግሥትና ከግል ዘርፉ በቀላሉ ማግኘት እንደሚቻል ጠቁመዋል።
የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ መጀመር መንግሥት እና የግሉ ዘርፍ ለሚያከናውኗቸው ኢንቨስትመንቶች ካፒታል ለማሰባሰብ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ያሉት
ጥላሁን (ዶ/ር)፤ ዜጎች ከኩባንያዎች አክሲዮንና ሰነዶች በመግዛት ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል።
በሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ አክስዮን የሚሸጡ ኩባንያዎች በየጊዜው የሂሳብ ሁኔታቸው እየተገመገመ ይፋ የሚሆንበት አሠራር ተዘርግቷል። ይህም አክሲዮን የሚገዙ አካላት በመረጃ ላይ የተወሰነ የአክሲዮን ግብይት ለማከናወን የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በሀገሪቱ የካፒታል ገበያ ለመምራት በወጣው አዋጅ መሠረት የሚከናወን መሆኑንም አስረድተው፤ በገበያው ገንዘብን የሚወክሉ ሰነዶችንና አክሲዮኖችን በመሸጥና በመግዛት ውስጥ ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘት ይቻላል ነው ያሉት።
በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ሙሉ በሙሉ የተሟላ የኤሌክትሮኒክስ የገበያ ሥርዓት የላቸውም ያሉት ሥራ አስፈፃሚው፤ ኢትዮጵያ ይህን ማሳካት ከቻለች ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደጊዜ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ማደግም ለካፒታል ገበያው ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳለው ተናግረዋል።
ሰዎች በስልካቸው ላይ በሚጭኑት መተግበሪያ በቀላሉ የገበያ ድርሻዎችን መግዛት እና የገዙትንም መሸጥ የሚችሉበት ሥርዓት ይፋ እንደሚሆንም አስታውቀዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም