የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት የጸደቀው ከ88 ዓመት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 9 ቀን 1923 ዓ.ም ነበር፡፡
አጼ ኃይለሥላሴ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ከተባሉ በኋላ ተክለሃዋሪያት ተክለማርያምንና ብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደስላሴን ሕገመንግሥት አርቅቀው እንዲያቀርቡላቸው ትዕዛዝ እንደሰጧቸው የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ራሳቸው ንጉሱም «ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ» በተሰኘ መጽሐፋቸው ስለመጀመሪያው ሕገመንግሥት አዘገጃጀት ያሰፈሩት ተከታዩ ሀሳብ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡
«ለአገዛዛችን ሕግ እንዲኖረው ለወራሾቻችንም በሕግ የተመሰረተ አገዛዝ ለማቆየት ሕዝባችንም የመንግሥቱን ሥራ ተካፋይ ሆኖ እንዲከታተል ለማድረግ አስበን፤ ገና የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽና ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ ሆነን ሳለን፣ ሕገመንግሥት ቢቆም ለመንግሥቱም ለሕዝቡም ትልቅ ጥቅም የሚያመጣ መሆኑን ለንግስት ዘውዲቱ አስታውቀን ነበር፡፡ ነገር ግን ያለ ሕገመንግሥት አገርን መግዛት ጥቅማቸው የሆነ አንዳንድ ትላልቆች መኳንንቶች ሕገመንግሥት የቆመ እንደሆነ የንግስት ዘውዲቱን ማዕረግና ሥልጣን የሚያጎድል እያስመሰሉ ስለተናገሩ በዚህ ምክንያት አሳባችን ሳይፈጸም ቆየ፡፡
… ነገር ግን ንግስት ዘውዲቱ ካረፉ በኋላ ዘውዱንና ዙፋኑን በሚገባ ስለወረስን ቀድሞ በእንደራሴነት ሳለን አስበነው የነበረውን ሕገመንግሥትን ለማቆም ቆረጥን፡፡ ስለዚህ የልዩ ልዩ አገሮችን ሕገመንግሥት መርምረን የውጭ አገር ልማድና ትምህርት ያላቸውን ካገሩም ውስጥ ያውራጃውን ልማድና የቀድሞውን ታሪክ የሚያውቁ ሰዎች መርጠን፣ ከዚሁ ከውጭ አገሮች ሕገመንግሥት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚስማማው ተመርጦ እየተዋጣ እንዲቀርብልን አዘዝን፡፡ ተጽፎም ቀርቦ እኛ ከመረመርነው በኋላ መሳፍንቱ ፣ ሚኒስትሮችና መኳንንቶች በአንድነት መርምረውት ለፊርማ እንዲያዘጋጁት አደረግን … »
በዚህ መንገድ በጃፓን ሥራ ላይ የነበረውን የማጅ ዘውዳዊ ሕገመንግሥት መሠረት በማ ድረግ እንደተቀረጸና በርካታ ሀሳቦች ከማጅ ሕገመንግሥት ተወስደው እንደተካ ተቱበት የሚነገርለት ሕገመንግሥት ላይ መሳፍንቱ፣ መኳንንቱና ሚኒስትሮች እንዲወያዩበት ተደረገ። ነገር ግን መኳንንቱና ሚኒስትሮቹ በአንድ ወገን መሳፍንቱ በሌላ ወገን ሆነው ስምምነት ላይ መድረስ ሳይሆንላቸው ቀረ፡፡ አጼ ኃይለሥላሴ በሁለቱ ወገኖች የተፈጠረውን አለመግባባትና ልዩነቱን ያስታረቁበትን መንገድ እንደሚከተለው ይገልጹታል፡፡
«የመሳፍንቱ ሀሳብ ኢትዮጵያ በየትልልቁ አውራጃ ተከፍሎ ለመሳፍንቱ ለልጅ ልጅ የሚያልፍ ርስት እየሆነ እንዲሰጥ በንጉሠ ነገሥቱና በመንግሥቱ ላይ ትልቅ የወንጀል ሥራ ሰርተው ካልተመሰከረባቸው በቀር ዘራቸው እንዳይነቀል በየውስጣቸውም ያለው የያውራጃው ባላባት የያዘውም ግዛት ርስት ሆኖለት ለመሳፍንት እየገበረና እየታዘዘ እንዲኖር ነበር፡፡ በጠቅላላም የፊውዳል መንግሥት ማለት ነው፡፡ የሚኒስትሮቹና የመኳንንቱ ሀሳብ ግን ኢትዮጵያ በየትልልቁ አውራጃ ተከፍሎ ለመሳፍንትና ለባላባቶች ለልጅ ልጅ የሚያልፍ ርስት ሆኖ ከተሰጠና ሹመት በዘር ይሁን ከተባለ ወደፊት የሚነሳው ትውልድ እንደምን ሊሆን ነው? ቢማርስ ቢያገለግልስ ሹመትና ግዛት ካላገኘ ኢትዮጵያ አገሬ ናት ለማለት እንደምን ይቻላል? አሁን ያሉት ባላባቶች ጥፋት ካልተገኘባቸው ባገር ገዥነት ብቻ ይቆዩ ፣ ጥፋት ተገኝቶባቸው ቢሻሩ ወይም ቢሞቱ ግን በግዛታቸው ዕውቀትና ችሎታ ያለው ማንም ኢትዮጵያዊ እንዲሾምበት ይሁን እንጂ ግዛታቸው ለልጅ ልጅ የሚያልፍ ርስት መሆኑ በሕገ መንግሥት ሲጻፍ አይታየንም የሚል ነበር፡፡ እኛም ለዚህ ሥራ የመደብናቸው ሰዎች በአሳብ አለመስማማታቸውን ባየን ጊዜ ሁለቱም ወገኖች አሳባቸውን በጽሑፍ እንዲያቀርቡ አድርገን ከመረመርን በኋላ ንጉሰ ነገስቱ ለመሳፍንቱም ቢሆን ለሌሎችም የመንግሥት አገልጋዮች ቢሆን ርስትና ጉልት ለመትከል ይችላል የሚል አንድ ክፍል በሕገ መንግሥቱ ይጻፍና ወደፊት አገልግሎታቸው እየታየ እንደሚያስፈልግ ይደረጋል እንጂ የፊውዳል መንግሥት በዓለም ላይ መቅረቱን እያወቅን አሁን እንደገና ያንኑ አጽንተን በሕገመንግሥት መጻፍ የማይገባ መሆኑን ለመሳፍንቱ አስረድተን ተጣርቶ ተጥፎ እንዲፈረም ይሁን በማለት ነገሩን ቆረጥን፡፡ »
ሐምሌ 9 ቀን 1923 ዓ.ም እንዲፈረምና በአዋጅ እንዲነገር የተደረገው ሕገመንግሥት በመጀመሪያው ምዕራፍ «ስለ ኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መንግሥትና ስለ ንጉሰ ነገስቱ ትውልድ» በሚል ርዕስ ስር ተከታዮቹን አምስት አንቀጾች ይዟል፡፡
1ኛ የኢትዮጵያ መሬት ከወሰን እስከ ወሰን በሙሉ የንጉሰ ነገስቱ መንግሥት ነው፡፡ በንጉሰ ነገስት ግዛት ውስጥ በዜግነት የሚኖር የኢትዮጵያ ተወላጅ ሁሉ ባንድነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡
2ኛ የኢትዮጵያ መሬቱም ሕዝቡም ሕጉም በጠቅላላው የንጉሰ ነገስት መንግሥት ነው፡፡
3ኛ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስትነት ከኢየሩሳሌም ንጉስ ከሰለሞንና ንግሰተ ሳባ ከተባለችው የኢትዮጵያ ንግስት ከተወለደው ከቀዳማዊ ምኒልክ ነገድ ተያይዞ ከመጣው ከንጉስ ሳህለ ስላሴ ዘር ከተወለደው ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትውልድ እንዳይወጣ በሕግ ተወስኗል፡፡
4ኛ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ዙፋንና ዘውድ በንጉሰ ነገስቱ ቤተ መንግሥት እንደተጻፈው ሕግ ለንጉሰ ነገስቱ ልጆች ይተላለፋል፡፡
5ኛ ንጉሰ ነገስቱ የነጋሲ ዘር በመሆኑና ቅብዓ መንግሥት በመቀባቱ ክብሩ የማይቀነስ ፤ ማዕረጉ የማይገሰስ ፤ ኃይሉ የማይደፈር ሆኖ በቆየውም ልማድ ባዲሱም ሕግ በሚገባው ክብር ሁሉ ይከበራል። ክብሩንም ለመንካት በድፍረት ለተነሳ ሰው በሕግ እንዲቀጣ ተወስኗል፡፡
ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው ይህ ሕገመንግሥት በ11 ምዕራፎች የተከፋፈሉ 85 አንቀጾች ነበሩት፡፡ የታሪክ ተመራማሪዎች አጼ ኃይለሥላሴ በሕገመንግሥቱ ሥልጣናቸውን ለማጠናከር በማሰብ ነባሩን ሥርዓት በሕግ ከማጽናትና ለራሳቸው ፍጹማዊ ሥልጣንን ከማጎናፀፍ ውጪ ያከሉት ነገር የለም ይላሉ። ለአብነት ጥላሁን ብርሃነ ሥላሴ የተባሉ ጸሐፊ «የ20ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ» በተሰኘ መጽሐፋቸው፡-
«ጃንሆይ ምንም እንኳን ሕገመንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰጠሁ ቢሉም ራሳቸው ከሕግ በላይ የነበሩ አስተዳዳሪ ነበሩ፡፡ አሰራራቸው ከደንብና ከሥርዓት ውጪ እንደፈለጋቸውና እንዳሰኛቸው ነበር። ከኢጣሊያን አገር የ150 ሚሊዮን ዶላር ብድር እንዳይቀበሉና በተደረገላቸው የጉብኝት ጥሪ መሰረት ጣሊያን ኢትዮጵያን ይቅርታ ሳትጠይቅ ለጉብኝት እንዳይሄዱ ተብለው ቢከለከሉም የግል ውሳኔ አድርገው ጥቅምት 27 ቀን 1963 ዓ.ም የጣሊያንን አገር በይፋ ጎበኙ፡፡ በዚህም ጉብኝት የቫቲካንን ጳጳስ ሄደው አይተዋል፡፡ የቫቲካን ጳጳስ የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን ሊወር ሲመጣ መድፍን ሳይቀር የባረከ ሲሆን፤ በመንበሩ የተተካው የዘመኑ ጳጳስ እስካሁን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ አልጠየቀም፡፡» ብለዋል፡፡
በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት በታተመው «ፍሬ ከናፍር ዘ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ» የተሰኘ በየጊዜው ንጉሱ የተናገሯቸውን ንግግሮች በያዘው መጽሐፍ ፣ ንጉሡ ሐምሌ 9 ቀን 1923 ዓ.ም ሕገመንግሥቱ ሲጸድቅ ባደረጉት ንግግር ጠቀሱት ተብሎ ከሰፈረው ሀሳብ ውስጥ «ሕግ ለሰው ከሁሉ የበለጠ የሚጠቅም መሆኑን ማንም አይስተውም። መከባበርም መጠቀምም የሚገኙት በሕግ መተካከል የተነሳ ነው፡፡ ግፍና በደልም የሚበዙት ሕግ ባለመቆሙ ነው፡፡» የሚለው ይገኝበታል፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ10/2011
የትናየት ፈሩ