ሀዋሳ:- እንደ ሀገር ያጋጠመውን የትምህርት ጥራት ችግር ለመፍታት የመማሪያ መጽሐፍትን ተደራሽ የማድረግና የመምህራንን አቅም የማጎልበት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ የሲዳማ ክልል ትምህርት ቢሮ ባካሄደው 4ኛ ክልላዊ የትምህርት ጉባኤ ተገኝተው እንደገለጹት፤ እንደ ሀገር ያጋጠመውን የትምህርት ስብራት ለመጠገንና የትምህርት የጥራት ደረጃን ለማሻሻል በርካታ የለውጥ ሥራዎች ተቀርጸው እየተተገበሩ ይገኛሉ።
በቀዳሚነት የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ አዲሱ የትምህርት ሥርዓት ትግበራም አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
ለአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊነት የመጽሐፍት ዝግጅት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እየተሰራጨ እንደሚገኝ አመልክተዋል። በሲዳማ ክልልም እስካሁን በተደረገው ጥረት አብዛኛው አካባቢዎች ላይ የመማሪያ መፅሐፍት ተደራሽ ተደርጓል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል የመምህራንን አቅም ከማጎልበት አንፃርም ባለፈው ዓመት ለሁለተኛ ደረጃ የተፈጥሮ ሳይንስና ለቋንቋ መምህራን እንዲሁም ለትምህርት ቤት አመራሮች ልዩ የአቅም ግምባታ ሥልጠና መሰጠቱን አስታውሰዋል።
ትምህርት ሀገራትን ከድህነት በማላቀቅ ወደ ብልፅግና ጉዞ የሚያመጣ ወሳኝ ጉዳይ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ምቹ በማድረግ ረገድም ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ጊዜያት በሲዳማ ክልልም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የተሠሩ ሥራዎች ውጤታማ እንደነበሩ አንስተዋል።
ተወዳዳሪ ዜጋ መፍጠር ራዕያችን ነው፤ ተወዳድሮ ማሸነፍ የሚቻለውም በእውቀት ነው ያሉት ደግሞ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ፤ የትምህርት ስብራት ከመሠረቱ ለመፍታት የገጠር ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥትም በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ እንደሆነ ጠቁመው፤ በዘርፉ እስካሁን ለተገኘው ውጤት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ድርሻ ከፍተኛ ነው። በክልሉ 20 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች በመንግሥት ሠራተኞች እገዛ መገንባታቸውን ለአብነት አንስተዋል።
በቀጣይም ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ምቹ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለው፤ ያለንን ሀብት አፍስሰን ትምህርት ቤቶችን መደገፍ ይገባናል ሲሉ ተናግረዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ ባራሳ በበኩላቸው፤ ከክልሉ ምስረታ በኋላ ትኩረት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል የትምህርት ዘርፉ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በጥናት በመለየት የታዩ ክፍተቶችን ለማረም ከፍተኛ ርብርብ ሲደረግ መቆየቱን አውስተዋል።
እንደ አቶ በየነ ገለፃ፤ የትምህርት ዘርፉ በአንድ ጊዜ ውጤት የሚታይበት ሳይሆን ዘላቂነት ባለው ርብርብ ቀጣይነት ያለው ለውጥ የሚታይበት ነው። ለዚህም እስካሁን በቁርጠኝነት በተሠሩ ሥራዎች የተመዘገበው ውጤት አበረታች ቢሆንም በቀጣይም መሠራት ያለባቸው በርካታ የቤት ሥራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
4ኛው ክልላዊ የትምህርት ጉባኤ በሀዋሳ ከተማ የተካሄደ ሲሆን በመድረኩ ላይ በየደረጃው ያሉ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዘርፉ አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች መገኘታቸው ታውቋል።
ቅድስት ገዛኸኝ
አዲስ ዘመንታኅሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም