ስምምነቱ ለኢትዮጵያ እና ለሶማሊያ ሕዝብ ቀጣይ ሁለንተናዊ ትብብር ትልቅ ድል ነው!

የባሕር በር የማግኘት መብት እንደ ሀገር የሕልውና ጉዳይ ስለመሆኑ በብዙ ተብሎለታል። ችግሩ ሀገር በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ በነበረችባቸው ወቅቶች በተጨባጭ ተስተውሏል። መንግሥትም ጉዳዩ የሕልውና ጉዳይ መሆኑን በማሳወቅ በችግሩ ዙሪያ የነበረውን የሦስት አስርተ ዓመታት ዝምታ በአደባባይ ሰብሮ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ አጀንዳ አድርጎታል

እውነታውን ታሳቢ በማድረግም መንግሥት በሠላማዊ መንገድ፤ ሰጥቶ በመቀበል መርሕ የሀገሪቱን የባሕር በር የማግኘት መብት ለማሳካት የተለያዩ ስትራቴጂክ አማራጮችን ቀርጾ ወደ ሥራ ከገባ ወራቶች ተቆጥረዋል። በእነዚህ ጊዜያትም ከሁሉም በላይ የሀገሪቱ የባሕር በር ፍላጎት ፍትሐዊ እና ሕጋዊ መሆኑን በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንዛቤ መፍጠር ችሏል።

ከዚህም ባለፈ ቀደም ባለው ጊዜ ከሶማሌ ላንድ ጋር በባሕር በር እና በወደብ አገልግሎት ዙሪያ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል። ስምምነቱ ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ እና የሶማሌ ላንድ ሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያጸና፤ ለቀጣናው ሀገራት አዲስ የትብብር ምዕራፍ ተደርጎ የተወሰደ ነው።

በተለይም የኢትዮጵያ መንግሥት የቀጣናውን ሀገራት የተፈጥሮ ፀጋዎች በጋራ በማልማት፤ በአካባቢው ያለውን ድህነት እና ኋላቀርነት ለዘለቄታው በመቅረፍ አካባቢው አዲስ የኢኮኖሚ አቅም ሆኖ እንዲወጣ ለጀመረው ስትራቴጂክ እንቅስቃሴ ተጨባጭ ማሳያ ጭምር ነው።

ኢትዮጵያ ዙሪያዋን ካሉ ጎረቤት ሀገራት በጠንካራ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ከዚያም ባለፈ የደም/ ወንድማማችነት ትስስር ያላት ሃገር ናት። ከሃገራቱ ሕዝቦች ጋር ያላት ቁርኝትም የዛሬን ብቻ ሳይሆን ከነገ ዕጣ ፈንታቸው ጋር የተሳሰረ፣ ቀጣይ ዘመናትንም ታሳቢ ያደረገ ነው።

የአንዳቸው ሠላምም ሆነ የሠላም እጦት ለሌላኛው፤ የአንዳቸው ድህነት እና ኋላ ቀርነትም ሆነ ማደግ እና መበልፀግ ለሌላኛው የሚተርፍ ነው። ይህ ደግሞ ባለፉት ዓመታት በክፉም በደጉም በቀጣናው በተጨባጭ የታየ ነው።

የትኛውም የኢትዮጵያን ሕልውና አደጋ ውስጥ የሚከት ነገር በአንድም ይሁን በሌላ የጎረቤት ሀገራትን የሚመለከት ነው። ሀገሪቱ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ከምትጋራው ሰፊ ድንበር እና ካላት የሰው ቁጥር አንጻር በሀገሪቱ ላይ በየትኛውም መንገድ የሚፈጠር ችግር አይመለከተኝም ማለት የሚቻል አይሆንም።

በሶማሊያ ባለፉት ሦስት አስርተ ዓመታት የተፈጠረውን ብንመለከት፤ በሀገሪቱ የተፈጠረው መንግሥት አልባነት፣ ከሶማሊያ ሕዝብ አልፎ ለቀጣናው ከዚያም በላይ የዓለም አቀፍ ስጋት ምንጭ ሆኗል። ችግሩን ለመከላከል በተደረገው ጥረትም ከማንም በላይ የቀጣናው ሀገራት ተሳትፎ ከፍ ያለ ነው።

በሶማሊያ የተከሰተው መንግሥት አልባነት በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ በጎረቤት ሀገራት ሠላም እና ደኅንነት ላይ ስጋት የፈጠረ ነው። ችግሩ በጎረቤት ሀገራት ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሊያስከትል የሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖም ቀላል አይደለም።

የኢትዮጵያ መንግሥት የባሕር በር ጉዳይ ለሀገሪቱ የሕልውና ጉዳይ ነው ሲል፤ እንደሀገር ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ብቻ ሳይሆን አደጋው ለቀጣናው ሊተርፍ የሚችል ትልቅ ስጋት መሆኑን ጭምር፤ ይህንን ቀጣናዊ አደጋ መሻገር የሚቻለው በመርሕ ላይ በተመሠረተ ሠላማዊ ድርድር ነው ለማለት ነው።

የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ ነው ሲባል፣ ይዞት ሊመጣ የሚችለው ችግር በቀጣናው ሠላም እና ደኅንነት ላይ ሆነ በቀጣናው የሕዝቦች የመልማት ፍላጎት ላይ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ የቱን ያህል ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት የሚከብድ አይደለም።

ሀገሪቱ ካለችበት ተጨባጭ እውነታ አኳያ የባሕር በር የማግኘት መብት አላት። ይህ መብቷ በዓለም አቀፍ ሕግ የሚደገፍ ነው። ዓለም አቀፍ ሕግ የሚደግፋት ኢትዮጵያ ስለሆነች ሳይሆን ከተቀመጠ ዓለም አቀፍ መርሕ አኳያ ነው።

የቀጣናው ሀገራት የሕዝባችንን ዕጣ ፈንታ የሚጋሩ ከመሆናቸው አንጻር፣ ሁኔታውን ከየትኛውም አካል ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆኖ፤ በሰከነ መንፈስ የሀገራቱን እና የሕዝቦቻችውን የጋራ ተጠቃሚነት መሠረት ባደረገ መንገድ ማየት፤ ለችግሩ ሠላማዊ እና ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግ የሁሉም ኃላፊነት ነው።

ከትናንት በስቲያ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መንግሥታትም ሆነ ቀደም ባለው ጊዜ በኢትዮጵያ እና በሰማሌ ላንድ መካከል የተደረሰው ስምምነት ይህንን ሁኔታ በአግባቡ ከመገንዘብ የሚመነጭ፣ አካባቢያዊ ትብብርን በማስፋት፣ የቀጣናውን ሀገራት ሕዝቦች የማደግ እና የመበልፀግ መሻት እውን ለማድረግ የሚያስችል ትልቅ ርምጃ ነው።

ከዚሁ ተጨባጭ እውነታ በመነሳትም በቱር አንካራ በተደረገው ስምምነት ሀገራችን፤ የባሕር በር የማግኘት መብቷን፣ ከሶማሌ ላንድ ጋር የተፈራረመው የመግባቢያ ስምምነት እና በሶማሊያ ሠላም ያላትን የማይተካ ሚና እውቅና ማስቀጠል ችላለች፡፡ ይህ ደግሞ ለቀጣናው ዘላቂ ሠላም እና ልማት የሚኖረው ጠቀሜታ የላቀ፤ ለኢትዮጵያ እና ለሶማሊያ ሕዝብ ቀጣይ ሁለንተናዊ ትብብር ትልቅ ድል ነው!

 አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You