የኢትዮጵያ ዋንጫ ለሦስት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ከተቋረጠ በኋላ በ2016 ዓ.ም ወደ ውድድር እንደተመለሰ ይታወሳል። ይህ አንጋፋ ውድድር ዘንድሮም ቀጥሎ እየተካሄደ ሁለተኛ ዙር ላይ ደርሷል። የሁለተኛ ዙር ጥሎ ማለፍ ጨዋታዎችም በቀጣዩ ወር መገባደጃ በተመረጡት ሜዳዎች የሚካሄዱ ይሆናል።
ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቀጥሎ በርካታ ክለቦችን የሚያሳትፈውና ትልቅ የውድድር መድረክ የሆነው የኢትዮጵያ ዋንጫ የሁለተኛ ዙር ጥሎ ማለፍ ጨዋታዎቹን በመጪው ታኅሣሥ ወር እንደሚደረጉም ታውቋል።
በመጀመሪያው ዙር የማጣሪያ ውድድር የአንደኛ ሊግና የከፍተኛ ሊግ ክለቦችን በማሳተፍ ወደ ሁለተኛ ዙር ያለፉ ክለቦች የተለዩ ሲሆን፤ በሁለተኛው ዙር ከሦስት የሊግ እርከን ተወክለው የሚሳተፉ ክለቦችን በማካተት ይከናወናል። ጨዋታዎቹ ታኅሣሥ 18 እና 19/2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይፋ በሚያደርጋቸው ሜዳዎች የሚካሄድ ይሆናል። ኅዳር 27/2017 ዓ.ም በተከናወነው የዕጣ ማውጣት ሥነሥርዓት 32 ክለቦች እርስ በርስ እንደሚጫወቱም ይፋ ሆኗል።
በዚህም 18 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች፣ 12 የከፍተኛ ሊግ ክለቦች እና 2 የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ክለቦች ሦስተኛውን ዙር ለመቀላቀል ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በተከናወነው የዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓትም 8 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች የቡድን አባላት ተደርገው ተጋጣሚዎቻቸውን ማወቅ ችለዋል።
በውድድሩ የሚሳተፉት ከሦስት የሊግ እርከኖች የተውጣጡ ክለቦች የሚያደርጉት ፉክክርም በጉጉት ይጠበቃል። ያለፈው ዓመት የዋንጫው አሸናፊ ኢትዮጵያ ቡና እና ሌሎች የሊጉ ክለቦች ወደ ሦስተኛው ዙር ለመቀላቀል ጠንካራ ጨዋታዎችን የሚያደርጉም ይሆናል።
በ32ቱ የሁለተኛ ዙር ተጋጣሚዎች መካከል በሚካሄዱት ጨዋታዎች 16 ሦስተኛ ዙርን የሚቀላቀሉት ክለቦች የሚለዩ ሲሆን የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦችም እርስ በእርስ የሚያደርጉት ጨዋታም አጓጊ ነው። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ሐዋሳ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ድሬዳዋ ከተማ ከአርባ ምንጭ እና ኢትዮጵያ መድን ከፋሲል ከነማ የሚያደርጉት ጨዋታዎች ከፍ ያለና ጠንካራ ፉክክር እንደሚያሳዩ ከሚጠበቁት የሁለተኛ ዙር ግጥሚያዎች ቀዳሚውን ግምት አግኝተዋል። ይህም አራት የሊጉ ክለቦች በሁለተኛው ዙር እንዲሰናበቱ የሚያደርግና ጠንካራ ፉክክር የሚጠበቅበት በመሆኑ ክለቦቹ ከወዲሁ ተፈትነው ወደ ሦስተኛው ዙር እንዲቀላቀሉ መንገድ የሚከፍትላቸው ይሆናል።
በአንጻራዊነት ቀለል ያሉ ተጋጣሚዎችን የሚያስተናግዱ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች እንዲሁ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ሲሆን የአምናው የውድድሩ አሸናፊ ኢትዮጵያ ቡና ከአራት ዓመት በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የተመለሰውን ስሑል ሽረን የሚያስተናግድ ይሆናል። በአምናው የፍጻሜ ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና በመረታቱ ዋንጫውን ያላሳካው ወላይታ ድቻ እንዲሁ ሦስተኛ ዙርን ለመቀላቀል በሚደረገው ፍልሚያ በተመሳሳይ ሁኔታ ከመቐለ 70 እንደርታ ይፋለማል። ሁለቱም ክለቦች በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ጦርነት ምክንያት ለሦስት ዓመታት ከውድድር ርቀው እንደመመለሳቸው የአምና የፍጻሜው ተፋላሚዎች ቀለል ያለ መርሐ ግብር የደረሳቸው ይመስላል።
የጣና ሞገዶቹ ባሕርዳር ከተማዎች ከስልጤ ወራቤ፣ አዳማ ከቦዲቲ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና ከሶሎዳ ዓድዋ፣ ሃድያ ሆሳዕና ከጋሞ ጬንቻ፣ መቻል ከአዲስ አበባ ከተማ የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ከሚያደርጉት ተጠባቂ ጨዋታዎች መካከል ይጠቀሳሉ። ደደቢት ከሀላባ ከተማ፣ ሸገር ከተማ ከቦሌ ክፍለ ከተማ፣ ደሴ ከተማ ከአርሲ ኔጌሌ፣ ሐረር ከተማ ከአምቦ ከተማ እንዲሁም ወልዋሎ አዲግራት ዪኒቨርሲቲ ከሱሉልታ ክፍለ ከተማ የሚደረጉ ሌሎች የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች ናቸው። በሁለተኛ ዙር የጥሎ ማለፍ ውድድር አሸናፊ የሚሆኑ ክለቦች ሦስተኛ ዙርን በመቀላቀል ለሩብ ፍጻሜ ይፋለማሉ።
በአንደኛው ዙር የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታቸውን አከናውነው ያለፉ ክለቦች ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ጋር የሚያካሄዱት የጥሎ ማለፍ ውድድር መሆኑም ተገልጿል። በዕጣ ማውጣት ሥነሥርዓቱ ላይ የቡድን አባት ሆነው ተጋጣሚዎቻቸውን ያወቁት አምና በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ባስመዘገቡት ነጥብ ነው።
የኢትዮጵያ ዋንጫ ከኢትዮጵያ ወንዶች ፕሪምየር ሊግ ቀጥሎ በኢትዮጵያ በእድሜ አንጋፋው የእግር ኳስ ውድድር ሲሆን እአአ በ1945 መካሄድ ጀምሯል። በየመሐሉ ለአስር ጊዜያት እየተቋረጠ ለ61 ጊዜ በተካሄደው ውድድር ዋንጫውን ብዙ ጊዜ ከፍ አድርጎ በማንሳት መቻል 14፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ 10፣ ኢትዮጵያ ቡና 6፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 4፣ እና ደደቢት 2 ጊዜ ማንሳት ችለዋል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም