ስፖርቱ በሕግና ሥርዓት እንዲመራ ለማድረግ

የኢትዮጵያ ስፖርት የዕድሜውን ያህል ላለማደጉና ላለመዘመኑ ከሚነሱ በርካታ ምክንያቶች መካከል አደረጃጀት ዋነኛው ጉዳይ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የስፖርት ውጤታማነት ጉዞ የኋልዮሽ በመሆኑ ምክንያትም፣ ጊዜውን በዋጀና ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ እንዲመራ ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ።

ይህንንም ተከትሎ የኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ‹‹ሀገራዊ የስፖርት ልማት ስብራቶችን በሳይንሳዊ ጥናት እንፍታ›› በሚል መሪ ሃሳብ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል። በዚህም መድረክ ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች በምሁራን የቀረቡ ሲሆን፤ በስፖርቱ እድገት ላይ ቁልፍ ሚና ያለው አደረጃጀትን የሚመለከተው ጥናት አንዱ ነው።

‹‹የኢትዮጵያ መንግሥታዊና ሕዝባዊ የስፖርት አደረጃጀትና አሠራር በፖሊሲ ተኮር ግቦች ላይ ያለው ተጽእኖ›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ይህ ጥናት፤ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ አስተባባሪነት እንዲሁም ከስድስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተወጣጡ የስፖርት ሳይንስ ተመራማሪዎችን ተሳትፈውበት የተከናወነ፤ የስፖርት አደረጃጀት፣ አስተዳደር፣ አመራርና የአሠራር ሥርዓት ላይ ያሉ ክፍተቶችን በመለየት ሊተገበሩ የሚችሉ የመፍትሔ ሃሳቦችን ማቅረብንም ዓላማው ያደረገ ነው።

በጥናቱ እንደተመላከተውም፣ ሕዝባዊና መንግሥታዊ መሠረት ያለው የኢትዮጵያ ስፖርት አደረጃጀት ተልዕኮውን ሊያስፈጽምና የዘርፉን ልማት ሊያረጋግጥ የሚችል፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተናባቢ እንዲሁም ወጥነት ያለው አደረጃጀትና መዋቅር አልነበረውም ለማለት በሚያስደፍርበት ሁኔታ ውስጥ ቆይቷል።

መንግሥታዊውን አካል በሚመለከትም፣ ከ1935 እስከ 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ 13 በሚሆኑ የአደረጃጀት ሂደቶች ውስጥ ማለፉን ነው ጥናቱ የጠቆመው። ይህም የተረጋጋ ተቋማዊ ጥንካሬና ተሰሚነት እንዳይኖር አድርጓል። አንድ አመራር ያስጀመረውን ሌላኛው በማስቀጠል (በቅብብሎሽ ከመሥራትና ከመምራት አኳያ) ረገድ የተፈጠሩ ክፍተቶችም በመደበኛ አሠራር ላይ ተግዳሮት ፈጥረዋል።

ክልል ላይ ያለው የስፖርት አደረጃጀትም፣ በተመሳሳይ ወጥነት ያለው ባለመሆኑ በተዋረድ እስከ ወረዳ የደረሰውን አደረጃጀት የሚያስተሳስር ሥርዓት እንዳይኖረውና ስፖርቱ ትኩረት እንዲያጣ አድርጎታል። በአጠቃላይ ሲታይ፣ በመንግሥታዊው ስፖርት አደረጃጀት ውስጥ የሚገኙ ተቋማት በአዋጅ የተሰጣቸውን ሥልጣንና ተግባር ሊያስፈጽሙ እንዳላስቻላቸው ጥናቱ አመላክቷል።

ሕዝባዊ አደረጃጀቱም ቢሆን እንደየስፖርት ማህበራቱ ከጠቅላላ ጉባኤው አንስቶ እስከ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ድረስ መስፈርትና ስብጥር የሌለው መሆኑ በስፖርቱ ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፉንም ነው በጥናቱ መለየት የተቻለው።

የጥናቱን ግኝት ማብራሪያ ተከትሎም፣ በመድረኩ የተገኙ የየክልሉ የስፖርት ቢሮ፣ የስፖርት ማህበራት እንዲሁም የስፖርቱ ተቋማት አመራሮች በሰጡት አስተያየት እንዳመለከቱት፤ በተለይ በኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር በኩል ሕግና ደንብን የማስፈጸም ውስንነት አለ። በዚህ ምክንያት ከዚህ ቀደም የተከናወኑ መሰል ጥናቶች ተግባራዊ ስላልተደረጉ በሕዝባዊ አደረጃጀት ላይም አምባገነንነት ተንሰራፍቷል፤ በመንግሥታዊው አካል ቁጥጥር ለማድረግም አዳጋች ሆኗል።

የተነሱትን ሃሳቦች ተከትሎ ምላሽ የሰጡት የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፤ ጥናቱ በምን መልክ ወደ መሬት ሊወርድ ይችላል በሚለው ላይ በአጥኚዎቹ የአተገባበር ስትራቴጂካዊ ዕቅድ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል። መቼ የትኛው አካል የትኛውን ጉዳይ ተግባር ላይ ያውላል የሚለውን በመነሻነት በመውሰድም በቀጣይ ወደ ሥራ የሚገባ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ስፖርት በሕግና በመመሪያ መመራት ስላለበት የአሠራር ሥርዓት፣ የስፖርት ፖሊሲ ማሻሻያ እንዲሁም ብሔራዊ የስፖርት ምክር ቤትን ለማስቀጠል እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ በተዘጋጀ የአሠራር ማሕቀፍ በሕግና በሥርዓት የሚመራ ስፖርት እንዲኖር ማድረግ ከሁሉም የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።

በኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ በበኩላቸው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የስፖርት አሠራር መረዳት እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት። ሕጎችና አሠራሮች ከዓለም አቀፍ ሕግና አሠራር ጋር ይጋጫል የሚሉ መደበቂያዎችና ሽኩቻዎች የሚመነጩት የስፖርት ፖለቲካና ስፖርትን ካለመረዳት መሆኑንም አብራርተዋል።

ይህንን ጥናቱ በሳይንሳዊ መንገድ አብራርቶ አሳይቷል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ስትራቴጂ በመቅረጽ ተግባራዊነቱ ላይ በቀጣይ የሚሠራው ብለዋል። በመሆኑም በየደረጃው ያሉ የስፖርት አደረጃጀቶች ለስፖርቱ እድገትና ስብራቶች መጠገን ተናበውና በቅንጅት በመሥራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። ሕግና ደንብን ከማስፈጸም አንጻርም መንግሥታዊና ሕዝባዊ አካሉ በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You