የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በሦስት ዙር ይካሄዳል

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ስፖርት ፕሪሚየር ሊግ መካሄድ ከጀመረ ዘንድሮ ዘጠናኛ ዓመቱን አስቆጥሯል:: በፕሪሚየር ሊጉ አስር ክለቦች በተመረጡ ከተሞች ውድድራቸውን የሚያከናውኑ ሲሆን፣ ክለቦች ካለባቸው የፋይናንስ እጥረት አኳያ እንዲሁም ለስፖርቱ እድገት ሲባል ክለቦቹ የሚኙበትና ስፖርቱ በስፋት በሚዘወተርበት አካባቢ መካሄድ እንደሚኖርበት ሃሳብ አቅርበዋል::

የ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ከታኅሳስ 6/2017 ዓ.ም ጀምሮ በሃዋሳ ከተማ በአስር ክለቦች መካከል ለማካሄድ የእጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት ኅዳር 28/2017 ዓ.ም የክለብ ኃላፊዎች፣ ተወካዮች እና አሰልጣኞች በተገኙበት ተከናውኗል:: ፌዴሬሽኑ የዓመቱን ውድድር ሃዋሳን ጨምሮ በሶስት ከተሞች (ሃዋሳ፣ ድሬዳዋና አዲስ አበባ) አካሂዶ ለማጠናቀቅ ሃሳብ ያቀረብ ቢሆንም፣ ለውድድሩ ከተመረጡት ከተሞች አኳያ ከክለቦች ቅሬታ ቀርቦበታል:: የውድድሩን ከተሞችን ስፖርት መሰረተ ልማትን፣ ጸጥታን፣ ትራንስፖርት ምቹነትንና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን መሰረት በማድረግ በሶስቱ ከተሞች የአንደኛና የሁለተኛ ዙር ግጥሚያዎችን ለማካሄድ ማቀዱን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል::

አዲስ አበባ ከተማ ላይ ሁለት ውድድሮችን ለማካሄድ የታቀደ ሲሆን የመጀመሪያ ዙር አንድ ውድድርና የመዝጊያ ውድድር እንደሆነም ተነግሯል:: ሃዋሳና ድሬዳዋ ከተሞች ውድድሩን ለማስተናገድ በሚደረገው ጥረት ከአመራሮች ጋር ውይይት መደረጉ የተገለጸ ሲሆን ቅድመ ዝግጅቶች እየተካሄዱም ይገኛሉ።

ፌዴሬሽኑ በቦርድና በስራ አስፈጻሚ ደረጃ ተወያይቶ ውድድሩ የሚካሄድበት ጊዜና የሚያስተናግዱ ከተሞችን ይፋ ቢያደርግም፣ ክለቦች ከእጣ- ማውጣትና የውድድር ከተሞችን ከማሳወቅ አስቀድሞ እነሱን ባሳተፈ መልኩ ውይይትና ግምገማ መደረግ ነበረበት በማለት ቅሬታቸውን አቅርበዋል:: የ2016 ዓ.ም ውድድር ሳይገመገም እና ጥፋት ያጡፉ ዳኞችም ሆኑ ክለቦች ተገቢውን ውሳኔ ሳያገኙ ወደ ውድድር መገባቱ ትክክል እንዳልሆነም ጠቁመዋል:: የክለብ ተወካዮችና አሰልጣኞች ከውድድሩ አካሄድ፣ ከዳኝነት ስርዓት፣ ከበጀት እና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ጥያቄዎችን አንስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል:: በዚህም መሰረት የውድድር ጊዜው ካለው የበጀት እጥረት እና የትራንስፖርት መወደድ አኳያ ወደ ሶስት ጊዜ እንዲያጥር የሚል አስተያየትም ተነስቷል::

በተለይ የፀጥታ ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች የአየር ትራንስፖርት ተጠቅመው የሚመጡ ክለቦች ትኩረት ካልተሰጣቸው በበጀት እጥረት ምክንያት የመፍረስ እጣ ፈንታ እንደተጋረጠባቸውም ተመላክቷል:: በተጨማሪም ውድድሩ በትላልቅ ከተሞች መካሄዱ ክለቦች ለቀን አበል የሚሰጣቸው ወጪና የሚያወጡት የማይመጣጠን እንደሆነም ገልጸዋል::

ውድድሩ ሁሌም ከዓመት ዓመት በተመሳሳይ ከተሞች እየተካሄደ ቢሆንም በስፖርቱና ክለቦች ላይ ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉ ክለቦች የሚገኙባቸውና ስፖርቱ በስፋት የሚዘወተርባቸው አካባቢዎች መካሄድ እንደሚኖርበትም ክለቦች አሳስበዋል። ውድድሩን የሚመሩት ዳኞች ቁጥር መቀነስና መደጋገም ከስፖርተኛው ጋር መላመድ መናናቅ እየፈጠረ በመሆኑ በትኩረት መሰራት እንደሚኖርበት ክለቦች አሳስበዋል:: የውድድር መረሃ ግብር መጣበብ ስፖርተኛውን ለጉዳት እንዳይዳርግና ፉክክሩ እንዳይቀንስም ስጋታቸውን ገልጸዋል::

የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰጠኝ አዲስ፣ ውድድሩ የእጅ ኳስ ክለቦች የማይገኙባቸው አካባቢዎች የሚካሄደው ከተሞቹ ክለብ እንዲይዙ ለማነቃቃትና ስፖርቱን ለማሳደግ መሆኑን ተናግረዋል:: ውድድሩን ከስህተትና ከዲሲፕሊን ግድፈት በጸዳ መልኩ ለማካሄድ ዝግጅት ተጠናቋል:: ከሃዋሳ ውጭ የውድድር ስፍራዎቹን ለመወሰን በውድድር ደንቡ መሰረት መታየት እንደሚኖርበትም አመላክተዋል::

የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ ተፈራ በበኩላቸው፣ ክለቦች የሚያነሷቸው ጉዳዮች የሚጠቅሙና መማሪያ በመሆናቸው ፌዴሬሽኑ በቀጣይ የግምገማና የውይይት መድረክ እንደሚያዘጋጅ ገልጸዋል:: በዚህም መሰረት ያለፈውን የውድድር ሂደት መገምገም ያልተቻለው በአህጉር አቀፍ ውድድሮች ምክንያት የጊዜ መጣበብ በመኖሩ መሆኑንና በቀጣይ የውይይትና ግምገማ መድረክ ለማዘጋጀት መታቀዱን እንዲሁም በዓለም አቀፍ ተሞክሮን መሰረት ሰነድ እየተዘጋጀ እንደሆነ ጠቁመዋል:: የዳኞችን ቁጥር መጨመርና ተገቢውን የሙያ ስልጠና ለመስጠት መታቀዱንም ጠቅሰዋል::

በውድድር መርዘም ምክንያት ወጪ እየበዛ ነው፣ የዳኝነት ችግር መኖር፣ የውድድር መቀነስ የስፖርተኛው አካል ብቃት ላይ ጫና ይፈጥራል የሚሉና የውድድር ከተሞች ተመሳሳይ መሆን ለስፖርቱ እድገት አልጠቀመም የሚሉ ነጥቦች በክለቦች ተነስቷ::

ውድድሩ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በሁለት ዙሮች ተከፍሎ በሶስቱ ከተሞች እንደሚካሄድ ፌዴሬሽኑ በሰጠው ማብራሪያ ተጠቁሟል:: በዚህም መሰረት የአንደኛ ዙር የፕሪሚየር ሊግ ውድድር አዲስ አበባ 25 እና ሃዋሳ ከተማ ላይ 20 በሁለቱ ከተሞች 45 ጨዋታዎችን አካሂዶ የመጀመሪያውን ዙር ውድድር ለማጠናቀቅ አቅዷል:: በሁለተኛ ዙር የሊጉ ውድድር እንዲሁ በድሬዳዋ ከተማ ላይ 25 ጨዋታዎችና አዲስ አበባ ከተማ ላይ 20 ጨዋታዎችን አካሂዶ ለማጠናቀቅ እንደ ተወሰነም ተጠቅሷል:: በሳምንት አምስት ጨዋታዎች የሚካሄዱ ሲሆን፤ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከታህሳስ 6 እስከ 15/2017 ዓ.ም እና የአንደኛ ዙር ከአምስተኛ እሰከ ዘጠነኛ ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ ከጥር 26 እስከ የካቲት 3/217 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል ተብሏል::

ባህር ዳር ከነማ፣ ፋሲል፣ መቐለ 70 እንደርታ፣ ኦሜድላ፣ ቂርቆስ፣ ኮልፌ፣ መቻል፣ ማረምያ፣ ሚዛን አማን እና ከምባታ ዱራሜ የሚሳተፉ ይሆናል::

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You